Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገሪቱን ከአሳፋሪው ዶፒንግ ማፅዳት የሚቻለው በምሕረት የለሽ ዕርምጃ ብቻ ነው!

አንገት የሚያስደፋው አበረታች ንጥረ ነገር (ዶፒንግ) ኢትዮጵያ አገራችንን መበከሉ እጅግ በጣም ያሳፍራል፣ ያሳዝናል፡፡ የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (WADA) ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት አገሮች በዶፒንግ ምክንያት አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ካስታወቀ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይ በመካለኛና በረዥም የአትሌቲክስ ርቀቶች በዓለም ዝነኛ በሆኑት ኢትዮጵያና ኬንያ የዶፒንግ ተዘውታሪነትና ሥርጭት ከፍተኛ አደጋ መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ፀረ ስፖርት አሳፋሪ ድርጊት አገራችን ኢትዮጵያ ስሟ ሲነሳ በጣም ያስቆጫል፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በአትሌቲክስ ስፖርት በዓለም አደባባይ ስሟ በመልካም የሚነሳው የጀግኖች አትሌቶች አገር፣ በአሳፋሪ ተግባር ስሟ ሲብጠለጠል እየተሰማ ነው፡፡ ይህንን ፀያፍ ድርጊት በአስቸኳይ ለማስቆም ምሕረት የለሽ ዕርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ዶፒንግን ከሥር መሠረቱ መንቀል የሚቻለው በምሕረት የለሽ ዕርምጃ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (IAAF) የተሰጣት ከፍተኛ ማሳሰቢያ አለ፡፡ ይህም ዶፒንግን በተመለከተ ጠበቅ ያሉ ተከታታይ ሥራዎችን ማከናወንና በፍጥነት ራሷን እንድታፀዳ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ በመላ አገሪቱ የስፖርቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ጨብጠው የጋራ መግባባት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የግብር ይውጣ ወይም በዘፈቀደ የሚከናወኑ ሳይሆኑ፣ አገሪቱ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ መንጭቆ ለማውጣት የሚያገለግሉ መሠረታዊ መፍትሔ መሆን አለባቸው፡፡ በለብለብ ሥልጠናና በበራሪ ወረቀቶች ላይ ብቻ በመንጠልጠል ይህንን ሠርተናል ማለት ዋጋ የለውም፡፡ የችግሩን ምንጭ ማድረቅ የሚቻለውና ሥር ነቀል ለውጥ የሚመጣው ባለድርሻ አካላት በሙሉ በሚኖራቸው ነፃና ግልጽ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ አበረታች ንጥረ ነገርን ተጠቅሞ ውጤት ለማግኘት የሚደረግ አሳፋሪ ተግባር ፀረ ስፖርት ነው፡፡ መወገዝ አለበት፡፡ በምሕረት የለሽ ዕርምጃ መገታት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ፣ ዶፒንግን በተመለከተ ምንም ዓይነት ድርድር አይኖርም ብሏል፡፡ ለእውነተኛና ለንፁህ አትሌቶች መብት መከበር በማንኛውም ሁኔታ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደሚሟገት፣ መግለጫው ከተሰጠበት ጊዜ አንስቶ ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር ከተጠረጠሩ አትሌቶች፣ ማኔጀሮችና አሠልጣኞች ጋር አብሮ ለመሥራት እንደማይገደድ፣ አዲሱን ፀረ አበረታች እንቅስቃሴ በምርመራ ላይ በማተኮር በናሙናዎች ላይ ምርምራ ለማድረግ ማቀዱን፣ ከራሱ ከፌዴሬሽኑና ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን የዕገዳ ቅጣት በተጨማሪ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሠረት ዶፒንግ በሚጠቀሙ አትሌቶች ላይ ሕጉ ተግባራዊ መደረጉን በማረጋገጥ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ፣ ወዘተ አስታውቋል፡፡ መግለጫው ከተሰጠበት ቀን አንስቶም ከዶፒንግ ጋር ተያይዞ ዕገዳ የተጣለበትን አትሌት እስከ መጨረሻው አግዳለሁ ብሏል፡፡ በዚህ መንፈስ ተነሳስቶ ለዕርምጃ መዘጋጀት ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዕርምጃ የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት፡፡ አሳማኝና የማያዳግም መሆን ስላለበት፡፡ በተለያዩ አቅጣጫ ያሰፈሰፉ አጭበርባሪዎችን ፋታ በማይሰጥ ዕርምጃ ማስወገድ የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ያለንበት ዘመን በስፖርቱ ዓለምም ሆነ በሌላው ከፍተኛ የሆነ ፉክክር የሚደረግበት ነው፡፡ ከሌሎች በልጦ ለመገኘት ሲባል ትክክለኛውን መንገድ የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ፣ የተለያዩ አቋራጮችን በመጠቀም የውንብድና ተግባር የሚፈጽሙ ብዙ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ እየተባለበት ያለው የዶፒንግ ጉዳይ ወደ አገራችን ጓዙን ጠቅልሎ ሲገባ፣ አፍጥጠው የሚታዩ እውነታዎችን መመርመር ተገቢ ነው፡፡ አንድ አትሌት ከፍተኛ ጥቅምና ዝና የሚያስገኝለትን የአትሌቲክስ ስፖርት የዘለቄታዊ ሕይወት አካል አድርጎ ከቆጠረው፣ ተፈጥሮ በለገሰችው ብርታትና በግል ጥረቱ በንፅህና ይወዳደራል፡፡ ውጤቱም አሳማኝ ይሆናል፡፡ በአቋራጭ ብልፅግና ለማግኘት የሚፈልገው ደግሞ አበረታች ንጥረ ነገር በመውሰድ ጊዜያዊ ፍላጎቱን ለማርካት ወደ ውድድር ይገባል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ቤተሰብ፣ ጓደኞቹ፣ የሚወዳደርለት ክለብ፣ አሠልጣኝ፣ ማኔጀር፣ ወዘተ የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እነዚህን አካላት ጠበቅ አድርጎ መያዝ ካልቻለ፣ በአቋራጭ ጥቅምና ዝና ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ አይቆምም፡፡ አንድን ግለሰብ ዶፒንግ ለመጠቀም የሚያነሳሳው ምክንያት ያላግባብ በአቋራጭ የመበልፀግ ፍላጎት ሲሆን፣ በግለሰቡ ዙሪያ ያሉ ገፊ አካላት ደግሞ የፍላጎቱን ግለት ያባብሳሉ፡፡ የኢትዮጵያን ንፁህና ተፈጥሯዊ የአትሌቲክስ አሸብራቂ ድሎችን ገድል ከማበላሸቱም በላይ፣ አሁን ያለንበት አስከፊ ሁኔታ ለወደፊቱ ጭምር ጠባሳ የሚፈጥር መሆኑን መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ዶፒንግ አደገኛ የሙስና መገለጫ ሲሆን፣ ከግለሰቡ አልፎ ሌሎች አካላት የሚነካኩበት እኩይ ድርጊት ነው፡፡ የአገርን የዓመታት ልፋትና ጥረት ገደል የሚከት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በስፖርት ዘርፍ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ንፁኃንን ጭምር የሚያሸማቅቅ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ይህንን አፀያፊ ድርጊት ከኢትዮጵያ ጠራርጎ ማስወጣት የሚቻለው ደግሞ በጊዜያዊ ግርግርና ሁካታ ሳይሆን፣ እጅግ በተጠና ሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸውም ባለድርሻ አካላትና የመላው ሕዝብ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ አትሌቲክሳችንንም ሆነ ሌሎች ስፖርቶችን ከአጭበርባሪዎች መጠበቅ የግድ ይላል፡፡ በአገራችን ውስጥ እየታየ ያለው በአቋራጭ የመክበር ጤነኛ ያልሆነ ድርጊት ስፖርቱ ውስጥም በስፋት ገብቷል፡፡ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለመክበርና ዝነኛ ለመሆን የሚደረገው አሳፋሪ ተግባር እየገነነ የመጣው ሕገወጥነት በስፋት ስለሚታይ ብቻ ነው፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት፣ የሕገወጥነት መበራከት፣ ቸልተኝነት፣ ብቃት አልባነት፣ ለአገርና ለሕዝብ የጋራ ጥቅም አለመቆርቆር፣ ጥልቅ የሆነ ራስ ወዳድነት መንሰራፋትና የመሳሰሉት የአገር አደጋ ሆነዋል፡፡ አሁን ጥያቄው ሕግ ማስከበር ነው፡፡ በዚህም አገሪቱን ለውርደት የዳረገ አሳፋሪ ድርጊት ማስቆም ነው፡፡ ንፁህና ተፈጥሯዊ ችሎታቸውን ጠብቀው የሚወዳሩ ስፖርተኞችን መታደግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ሌሎች በስፖርቱ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት ራሳቸውን ከነውረኛ ድርጊቶች በማራቅ፣ ስፖርቱን መታደግ ካልቻሉ ሌላው ቢቀር በታሪክ ይጠየቃሉ፡፡ ዶፒንግን ከማውገዝ በላይ ምሕረት የለሽ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያን ከአሳፋሪው ዶፒንግ ማፅዳት የሚቻለው በምሕረት የለሽ ዕርምጃ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...