Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መዘመን ሥራ ፈጠራም ነው

እርድ የሚፈጸምባቸው እንደ ገና ያሉ በዓላት በመጡ ቁጥር ከሚታወሱኝና ፈጽሞ እርምት ሊደረግበት ያልቻለ አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ የቀንድ ከብት ግብይትና ከብቶቹ ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ የሚንቀሳቀሱበት መንገድ ነው፡፡

በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ከቀንድ ከብት ግብይት ጋር ተያይዞ የምናየው እንቅስቃሴ ፈጽሞ የሚመች ካለመሆኑም በላይ፣ ሁሌም የአደጋ ሥጋት ሆኖ እስከ መቼ እንደሚቀጥል ግራ ያጋባል፡፡ የአፍሪካ መዲናነትዋን እየጠቀስን ጠዋት ማታ በምንወተውትላት አዲስ አበባ ብዙ ያልዘመኑ አገልግሎቶች የሚስተዋሉ ቢሆኑም፣ በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ነገሮች ሳይቀሩ ችላ በመባላቸው የከተማዋን ስም በአሉታ ሲያስነሱ ማበሳጨቱ አይቀርም፡፡ አዲስ አበባ የተሰጣትን ክብር ያህል እየተለፋባት ላለመሆኑ አንዱ ማሳያ ደግሞ፣ የቀንድ ከብት ግብይት ሥርዓቷና ጎዳናዎችዋ ከተሽከርካሪዎችና ከእግረኞች ውጪ የቀንድ ከብቶች መንጎማለያ ሆነው መቀጠላቸው ነው፡፡

ከዘመኑ ጋር ያልተራመደው የከብት ግብይትና እንቅስቃሴ ከቀደመው ጊዜ የተለየ ሥርዓት ያልተበጀለት ሆኖ መዝለቁ ደግሞ፣ የከተማዋን ከፍታ ዝቅ ሊያደርገው ችሏል ማለት ይቻላል፡፡

የቀንድ ከብት ግብይቱ በልምድ እንደ ገበያ ሥፍራ በሚቆጠሩ ቦታዎች የሚካሄድ መሆኑ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ ግብይቱ ከተፈጸመ በኋላ የቀንድ ከብቶቹ የሚጓጓዙበት መንገድ ከአንድ ትልቅ ከተማ የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ከብቶች ወደሚሸጡበት የገበያ ሥፍራ የሚመጡት መንገድም ሆነ ከገበያው ወደየመንደሩ የሚወሰዱበት መንገድ ሳይቀየር ያለ ለውጥ ለዘመናት የተጓዘ ነው፡፡ በተለይ ገናን በመሰሉ በዓላት ወቅት አዲስ አበባ ጭንቅ ጥብብ ከምትልባቸው ነገሮች መካከል የቀንድ ከብቶችን በየጎዳናው ማሯሯጡና ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀሱ ሒደት የሚፈጥረው ትርምስ ነው፡፡

እንኳን የቀንድ ከብቶች ምልልስ ታክሎበት ለተሽከርካሪዎችም እንቅስቃሴ ፈተና በሆነበት ጎዳና ላይ፣ ደንባራ ከብቶች ሲሯሯጡበት የሚፈጠረውን ውጥረት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠንቅቀን የምናውቀው ግን ሊሻሻል ያልቻለ ተግባር ነው፡፡

ያልተገሩ ወይም በቀላሉ የሚደነብሩት እነዚህ ከብቶች አገር ሰላም ብለው የሚንቀሳቀሱ መንገደኞችን ለአደጋ ሲያጋልጡም እንመለከታለን፡፡ በተለይ በዓውደ ዓመት ሰሞን የአዲስ ጎዳናዎች በተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን በቀንድ ከብቶች ትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልባቸው በመሆኑ፣ በከብቶቹ እንቅስቃሴ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ቤት ይቁጠረው፡፡ የቀንድ ከብቶች እንቅስቃሴ በሚበዛበት የዓውድ ዓመት ሰሞኖችም በደነበሩ ከብቶች ተወግተው ሕይወታቸው ስለመጥፋቱም ተሰምቷል፡፡ ለአካል ጉዳት የተጋለጡ እንዳሉስ የሚያውቅ አለ? የደነበረ ከብት ለመሸሽ የሚፈጥረውም ድንጋጤ በራሱ ቀላል ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ይህንን ጉዳይ ከተለያዩ ማዕዘናት እንመልከተው ከተባለም የእነዚህ ከብቶች እንቅስቃሴ በአደጋ አጋላጭነታቸው ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ለከተማዋ ፅዳት ጉድለት ተጨማሪ ጦስ ስለመሆናቸው ከማን ይሸሸጋል?

ጥንቃቄ ያልታከለበት እንቅስቃሴ ከተሽከርካሪዎች ጋር መጋጨትን ይፈጥራልና ለደስታ ተብሎ በግልና በማኅበር የተገዛ ከብት መንገድ ላይ ቀርቶ ባዶ እጅ መመለስም ሊኖር መቻሉ በራሱ ሌላው ችግር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይህ ከታወቀ የቀንድ ከብቶች ግብይትና የማዘዋወሪያ ዘዴ መዲናችን ከተጎናፀፈችው ስም ጋር የተስተካከለ ለማድረግ ለምን አልተቻለም? ቢያንስ ለሁላችንም ደኅንነትና ለከተማችንም ስም ሲባል የቀንድ ከብቶች እንቅስቃሴ በተሽከርካሪዎች ማድረግ ይህንን ያህል ከባድ ለምን እንደሚሆን ግራ ይገባል፡፡ በነገራችን ላይ በከተማ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በመቶ ኪሎ ሜትሮች እየተነዱ የሚመጡ የቀንድ ከብቶች አዲስ አበባ የሚደርሱት ሰውነታቸው ዝሎ፣ ቀንሶና ተጎድቶ መሆንስ ይገባዋል? በረዥሙ ጉዟቸው ጀርባቸው ላይ የሚያርፈውን አለንጋ ችለው ጭምር የሚመጡት የቀንድ ከብቶች፣ ከእርድ በኋላም የምንቆጭበትን ስሜት ስለመፍጠራቸው ይታሰባል? አለንጋ እያረፈበት የተጎዳ ቆዳ ይዞ ለገበያ ማቅረቡ ለብዙ ጉዳይ የሚፈለገውን ቆዳ ለቁም ነገር እንዳይበቃ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት ያልዘመነው የቀንድ ከብቶች እንቅስቃሴ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የቀንድ ከብቶችን አጠቃላይ የግብይት ሥርዓትና የሚንቀሳቀሱበት መንገድ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ያለው ስለመሆኑ ከዚህም በላይ በርካታ ምሳሌዎች ሊቀርቡ ይችላል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትሮች ከብቶቹን እየነዱ መምጣት ለነጋዴውስ ምን ያህል አዋጭ ነው? አንዳንዴ እንደምናየው በአይሱዙ ተጭኖ መምጣት እየተቻለ ከብቶችን እያጉላሉ ማምጣት አደጋ እንዳለው ማስተማርና ከዚያም በሕግ እንዲከለከል ማድረግ ምን ያዳግታል?

ስለዚህ የከብቶች እንቅስቃሴዎች ጉዳት ብዙ ስለሚሆን ከመነሻው እስከ መድረሻው ድረስ ያለው የግብይት ሥርዓትም ሆነ ዝውውር እንዲዘምን ማድረግ ይገባል፡፡

በመሃል አዲስ አበባ የጋማ ከብቶች ሳይቀሩ እንዲዘዋወሩ መፈቀዱ እውን የዘመናዊነት መገለጫ ነውን? አዲስ አበባንስ ይገልጻል?

እንዲህ ያለውን ጉዳይ መስመር ለማስያዝ ሕግ ማስቀመጥ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው በዘመናዊ መንገድ ከብቶችን በተሽከርካሪዎች እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ራሱን የቻለ ቢዝነስ መሆኑን በመረዳት፣ ቢያንስ ወጣቶችን በማደራጀች ቢዝነሱን እንዲጀምሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያለውን ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ዛሬ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በብድር ለወጣቶች ይሰጣል ከተባለ ይህ አገልግሎትም ይታሰብ፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት