የሪፖርተር ጋዜጣ ታኅሳስ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ዕትሙ፣ ከድርጅቱ ሠራተኞች የተሰጠ አስተያየትን አትሟል፡፡
አስተያየት፡- የድርጅቱ ሒሳብ ሳይዘጋና በውጭ ኦዲተሮች ሳይመረመር ለብዙ ጊዜያት ስለቀረ ለሙስናና ለብክነት መጋለጡን ተገልጿል፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ የተወሰደው ከአሁን በፊት ችግር አለበት ተብሎ በግምገማ ከድርጅቱ የተሰናበቱ ግለሰቦችን እንደገና ለመቅጠር መሞከር ነው፡፡ ይህ በድርጅቱ ሀብትና ንብረት ላይ መቀለድ እንደሆነ ይሰማናል፡፡ ስለሆነም ይህ አማራጭ ለምን እንደተፈለገና የድርጅቱን ሒሳብ ለመዝጋት ያልተቻለበት ምን እንደሆነ በዝርዝር እንዲፈተሽና እንዲመረመር እንጠይቃለን፡፡
የድርጅቱ ምላሽ፡- ላለፉት ዓመታት እንዲሁም እስከያዝነው በጀት ዓመት ድረስ የድርጅቱ ሒሳብ በድርጅቱ የውስጥ ኦዲት የተመረመረ ሲሆን፣ ይህም ከላይ እንደተባለው ለብዙ ጊዜያት ሳይመረመር ለሙስናና ለብክነት እንዳልተጋለጠ ማረጋገጫ ነው፡፡ የድርጅቱን ሒሳብ በውጭ ኦዲተር የማስመርመርም ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በውህደት ወቅት ማንኛውም ድርጅት እንደሚያጋጥመው ሁሉ ሒሳቡን ወቅታዊ ከማድረግ ጋር ተያይዞና ኦፕሬሽናል ሥራው በፈጠረው ጫና ምክንያት የበጀት ዓመቱን ሒሳብ በወቅቱ ለመዝጋት ባለመቻሉ የተፈጠረ የውዝፍ ሥራ አለ፡፡ ሆኖም ግን ወዲያው የማካካሻ ዕቅድ ወጥቶ የየበጀት ዓመቱ ሒሳብ በውጭ ኦዲት እንዲመረመር ተደርጎ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፡፡ በሒደት ላይ ያሉትም በያዝነው ዓመት የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡
በኮንትራት እንዲቀጠሩ የተደረጉት ባለሙያዎች በድርጅቱ የፋይናንስ ሥራ ውስጥ የካበተ ልምድ ያላቸውና የድርጅቱን የፋይናንስ ገጽታ ለመገንባት ብቃት እንዳላቸው ታምኖባቸው በማኔጅመንት ተወስኖ የተመደቡ ናቸው፡፡ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድም እንዲያውቁት ተደርጎ የተፈጸመ ነው፡፡ ማንኛውም ሠራተኛ የሚያስጠይቀው ጉዳይ ካለ ቀርቦ በሕግም ጭምር ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ሆኖም ግለሰቡን ሳይሆን የተቋምን ሥራ ለመቀየር ታስቦ የተፈጸመ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
(የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት)