ሰሞኑን የአልጄዚራ ድረ ገጽ ላይ አንድ አስደንጋጭ ዜና አየሁ፡፡ የዜናው ርዕስ ‹‹የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ሙሰኛ ባለሥልጣናትን ከሔሊኮፕተር ላይ እወረውራለሁ›› ይላል፡፡ በመጀመሪያ ብደነግጥም ሰውየው እየቀለዱ ይሆን እንዴ በማለት ዜናውን ማንበብ ቀጠልኩ፡፡ ሰውየው በፍጹም እየቀለዱ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ድርጊት መፈጸማቸውን በግልጽ እየተናገሩ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርት በቅርቡ በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ላይ የወጡ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ዓቃቤ ሕግና የከተማ ከንቲባ ነበሩ፡፡ እሳቸው ግን ሙሰኛም ሆነ የዕፅ አዘዋዋሪ ‹‹ወንጀለኛ›› ስለሆነ በሕግ ሳይሆን አስፈላጊው ዕርምጃ ይወሰድበታል ነው የሚሉት፡፡
ከዚህ ቀደም በአስገድዶ ደፋሪዎች፣ በአጋቾችና በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ራሳቸው ግድያ መፈጸማቸውን፣ አሁን ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሙስና ሲፈጽሙ ካገኙ በመብረር ላይ ካለ ሔሊኮፕተር ላይ ወደ መሬት እንደሚወረውሩ ዝተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት በአስገድዶ መድፈርና በግድያ የተጠረጠረ ቻይናዊ ከሔሊኮፕተር ላይ ወርውሬያለሁ፡፡ አሁንም እንዲህ ዓይነቱን ዕርምጃ ከመውሰድ የሚገታኝ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ወንጀልን መከላከልና የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚቻለው እሳቸው ‹‹ወንጀለኛ›› በሚሏቸው ሰዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ብቻ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ዱቴርት ሥልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ በወሰዱት ወታደራዊ ዕርምጃ 6,000 ያህል ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በዚህ የተነሳ የአገር ውስጥም ሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ከሕግ ውጪ በሚወሰድ ዕርምጃ ንፁኃን እየተገደሉ መሆኑን፣ ይህም በፊሊፒንስ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ፍራቻ መፍጠሩን ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ እሳቸው ግን ዳቫኦ የምትባለው ከተማ ከንቲባ በመሆን ለ22 ዓመታት ሲሠሩ፣ ሞተር ብስክሌት በመጠቀም ጭምር ‹‹ወንጀለኞች››ን ይገድሉ እንደነበሩ በይፋ መናገራቸው ከማስገረሙም በላይ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡
እኝህ ሰውዬ ጤነኛ አይመስሉም፡፡ በተገኙበት ቦታ የሚገድሏቸው ሰዎች በሕጋዊው የፖሊስ ኦፕሬሽን መሠረት የሚገደሉ ናቸው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን እሳቸው ከከተማ ውጪ በነበሩበት ጊዜ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ስድስት ግለሰቦች ‹‹ዕድለኛ ናቸው›› ይላሉ፡፡ ግለሰቦቹ የተያዙት ከግማሽ ቶን በላይ ዕፅ ተገኝቶባቸዋል ነው ተብለው ሲሆን፣ እሳቸው ከከተማ ውጪ መሆናቸው በጀ እንጂ ‹‹ይገደሉ ነበር›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኔ በዋና ከተማዋ ማኒላ አለመኖሬ ዕድለኞች ናቸው፡፡ እኔ እዚያ ብኖርና ከእነ ዕፃቸው ባገኛቸው ዕጣ ፈንታቸው ተረሽኖ መሞት ነበር፤›› በማለት አስደንጋጭ ንግግር አድርገዋል፡፡ ‹‹ፈፅሞ ድራማ ለመሥራት አንሞክር፡፡ እኔ ራሴ ነበርኩ የምረሽናቸው፤›› የሚለው ንግግር የዓለም መነጋገሪያ እንደሆነ በተለያዩ ዘገባዎች መውጣቱን አይቻለሁ፡፡
እንግዲህ ወገኖቼ ልብ በሉ፡፡ ሕግና ሥርዓት በማስከበር ስም እንዲህ ውንብድና መፈጸም ምን ይሉታል? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፕሬዚዳንቱ በግልጽ ፈጽሜዋለሁ የሚሉትን አደገኛ ወንጀል በፍጥነት ተመርምሮ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ቢልም፣ የኮሚሽኑን መልዕክተኛ ‹‹ደደብ›› ከማለታቸው በተጨማሪ ፀያፍ ስድብ አክለውባቸዋል፡፡ የሕግ የበላይነት ማለት ንፀኃንን ከጥቃት መከላከል፣ አጥፊዎችን ደግሞ ፍትሕ ፊት ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለ ድርጊት ግን ወረበላነት ነው፡፡ እኔ ይህንን መነሻ በማድረግ የማነሳው ሐሳብ አለኝ፡፡
አንድ ጊዜ መገናኛ አካባቢ ለሥራ ጉዳይ እሄዳለሁ፡፡ ንብረትነቱ የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከሆነው ማራቶን ሞተር የሚገኝበት ሕንፃ አለፍ ብዬ ወደ መገናኛ ታክሲ መናኸሪያ ሳዘቀዝቅ፣ ሁለት ፖሊሶች አንድ ሰው ይዘው እየደበደቡ ወደ ላይ ይወጣሉ፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች በያዙት አጭር ጥቁር ቆመጥ እየቀጠቀጡት አጠገቤ ሲደርሱ ሰውየው ከአፉና ከአፍንጫው ደም ቡልቅ ይላል፡፡ በቀጥታ ወደ እነሱ በመሄድ፣ ‹‹በሕግ አምላክ!›› ስላቸው ቆሙ፡፡ አንዱ ወዲያው ዘሎ ላዬ ላይ ለመከመር ሲንደረደር ዞር አልኩበት፡፡ ተንገዳግዶ በሁለቱ እጆቹ መሬት ከነካ በኋላ ተፈናጥሮ በመነሳት ቆመጡን ማወናጨፍ ሲጀምር አሁንም፣ ‹‹በሕግ አምላክ!›› በማለት ስጮህ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች መሀላችን ገቡ፡፡ አካባቢው በአንዴ በሰዎች ተወረረ፡፡ ብዙ ንትርክ ተፈጥሮ በስንት ገላጋይ ተለያየን፡፡
ሌላውን ሀተታ ልተወውና ፖሊስ ያልተፈረደበትን ተጠርጣሪ አይደለም እጅ ከፍንጅ የተያዘን ቀማኛ ሕግ ፊት ማቅረብ እንጂ መማታት የለበትም፡፡ ሕጉ፣ ‹‹ማንም ተጠርጣሪ እስክፈረድበት ድረስ ንፁህ ነው ተብሎ ይታሰባል›› ይላል፡፡ ብዙ ቦታ ግን ፖሊሶቻችን የያዙትን ሰው ለምን ይደበድባሉ? አስቸጋሪ ሰው ቢያጋጥማቸው እንኳ አረጋግተው ወደ ሕግ ማቅረብ ለምን ይቸግራቸዋል? የሚለው በጣም ያሳስበኛል፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ሁሉ አንድ መላ ቢፈልጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ የእኔ ቢጤው ዜጋ ድረስ ለሕግ የበላይነት ክብደት አለመስጠት በአገር ላይ የሚያመጣውን ትልቅ ችግር መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ ሁላችንም ብንሆን ጊዜ ሲያጋድልብን ወይም ባላሰብነው ጊዜ ችግር ሲገጥመን ከሕግ በላይ ምንም መተማመኛ ሊኖረን አይገባም፡፡ ፍትሕ ያጡ ሰዎች ይህንን ይረዱታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሕግ ባለበት አገር ሕገወጦች ንፁኃንን ሲያስለቅሱ ከማየት የበለጠ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ‹‹ነግ በእኔ›› ማለት ካልተቻለ ሁላችንም የሕገወጦች ሰለባ እንሆናለን፡፡ እስኪደርስብን ድረስ ግን ላይሰማን ይችላል፡፡ ሕመሙ ከባድ ነው፡፡ ከሕግ በላይ መሆን ለጊዜው ቢቻልም፣ ከተጠያቂነት ማምለጥ ፈፅሞ እንደማይቻል ባንረሳስ? ምን ይመስላችኋል? (ተሾመ ተፈራ፣ ከአራት ኪሎ)