Sunday, February 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢኮኖሚስቶች ስለሥራ አጥነት ምን ይላሉ? በሳይንሳዊ ዓለም ውስጥ ልማዳዊ አስተሳሰብ

በጌታቸው አስፋው

‹‹የእኔን ወሬ ለአንቺ የአንቺን ወሬ ለእኔ የሚያመላልሰው የት አለ ደመወዙ ልብሱን የለበሰው፤›› ማን እንደ ገጠመውና መቼ እንደ ገጠመው አላውቅም፡፡ የዘፈን ግጥም እንደሆነ ግን አውቃለሁ፡፡ በኢኮኖሚክስ ሲተነተን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በመጀመሪያ ደመወዝ የሥራ ዋጋ መሆኑን ይነግረናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ወሬም ሥራ ሆኖ ደመወዝ የሚያስገኝ መሆኑን ይነግረናል፡፡

አፍ ያወራውን እጅ የሚሠራበት እጅ የሠራውን አፍ የሚያወራበት ጊዜዎች ቢኖሩም፣ አፍ አውርቶ እጅ የማይሠራበትና እጅ ሠርቶ አፍ የማያወራበት ጊዜያትም አሉ፡፡ ትልቁ ቁም ነገር የቱ ያመዝናል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅ ሳይሠራ አፍ የሚያወራበት ጊዜ አመዝኗል፡፡ ወሬ አመላላሾች ልብስ መልበስ ብቻ ሳይሆን፣ በወርቅና በአልማዝ ጌጣጌጥ ተንቆጥቅጠውም አይተናል፡፡ የወሬ ሙስናው ከገንዘብ ሙስናው ስለሚበልጥና በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ ስለሆነ፣ ለአፍ ልጓም የወሬ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋምም ሊያስፈልግም ይችላል፡፡ ስለዚህም ሥራ በአፍም ይሠራል፣ በእጅም ይሠራል፡፡ ማን በአፍ ይሠራል? ማን በእጅ ይሠራል? የሚለውም ተለይቶ ይታወቃል፡፡ በእጅ የሚሠራው ሰው ደመወዝ ይበልጣል? ወይስ በአፉ የሚሠራው ሰው ደመወዝ ይበልጣል? የሚለውም ይታወቃል፡፡ ለማጥናት የፈለገ አጥንቶ ያውቃል፡፡ ጥናቱን ለአጥኚው ትቼ እኔ ስለተነሳሁበት ዓላማ ስለሥራ አጥነት ልቀጥል፡፡

 

ስለሥራ አጥነትም ሆነ ስለሥራ ፈጠራ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ተብሏል፡፡ አዲሱን ትውልድ በቀድሞ ታታሪ ሰዎች ተሞክሮ ለማነቃቃት እነ አቶ በቀለ ሞላ፣ አቶ ተካ ኤጋኖ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገርም ከባዶ ተነስተው ስለከበሩ ሰዎች ምሳሌ እየተጠቀሰ ተወርቷል፡፡ ስለሥራ ፈጠራ መጻሕፍትም ተጽፈዋል፡፡ የሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችም ብዙ የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ኮርሶች ተካትተዋል፡፡ የሥራ ፈጠራ ጥሪት (Fund) በመንግሥት ተይዟል፡፡ ባንኮች ለወጣቱ የሥራ ፈጠራ ብድር እንዲያመቻቹ ታዘዋል፡፡ የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ፕሮግራም ፓኬጅ ተነድፎ በአንደኛውና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመናት፣ በጥቃቅንና በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አማካይነት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ተደርጓል፣ እየተደረገም ነው፡፡

 የብዙ አገሮች ልምድ ተዳሰሰ፣ ቢዝነስ ፕላን ተዘጋጅቶ ተሰጠ፣ ብድር ተመቻቸ፣ የገበያ ትስስር ተፈጠረ፣  የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ ተሰጠ፣ ስለሥራ ፈጠራ ያወሩም ደመወዛቸውን ወሰዱ፡፡ በመጀመርያዎቹ ዓመታት ውጤቱ በከፊል ታይቶ ይሆናል፡፡ የኋላ ኋላ ግን እንደ ጀግንነት የጉድ ያህል ተወርቶ ወረት ሆኖ እንደቀረው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የኮብልስቶን አንጣፊ መሆን ጋር የሥራ ፈጠራ ወሬውም ቀዝቅዞ ነበር፣ ባለፈው ሰሞን ከተቀሰቀሰው አመፅ ጋር ተያይዞ እንደገና አገረሸ እንጂ፡፡ ከሕዝብ መጨመር ጋርና ለሥራ ዕድሜያቸው ከደረሰ ወጣቶች ጋር ሲነፃፀር የሥራ ፈጠራ ወሬውና የሥራ ፈጠራው ውጤት ዜሮ ድምር ሆኖ ጥረቶቹ ሁሉ መና ቀርተው እዚያው በዚያው ተሽከረከሩ፡፡

አንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበትና በዓመት ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ በሚጨመርበት አገር፣ ሁለትና ሦስት የውጭ ኢንቨስተሮች መጡ፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ሺሕ፣ ሦስት ሺሕ፣ አምስት ሺሕ ሰዎች ይቀጥራሉ ተብሎም እንደ ታላቅ የሥራ አጥነት ቅነሳ ገድል በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ ዘገባ ለሕዝብ ቀረበ፡፡ ስለሥራ ቅጥርና ሥራ አጥነት ያልተነገረውና ለሕዝብ ያልተገለጹ ነገሮች ቢኖሩ የሥራ ቅጥርም ሆነ ሥራ አጥነት የኢኮኖሚክስ ሙያ ማዕከላዊ ነጥብ መሆናቸውና ስለሥራ ቅጥርና ደመወዝ መጣኝ ግንኙነትና ተዛምዶ፣ ምርምር ያደረጉ ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች ያደረጓቸው የምርምር ውጤቶች ምን እንደሚሉ ነው፡፡

ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች እንደ ሌሎቹ የኢኮኖሚ ሁኔታ ትንታኔዎቻቸው የሥራ አጥነትንና የሥራ ቅጥርን ሁኔታ የሚያዩት እንደ የግል ኢኮኖሚ ጉዳይ (Microeconomic Phenomena) ሆኖ፣ በሠራተኛ ገበያ ውስጥ በሠራተኛ ፍላጎትና በሠራተኛ አቅርቦት መስተጋብር በሚወሰን የደመወዝ መጣኝ ሁለቱ እኩል እንደሚሆኑ ቢሆንም፣ ከኬንስ ኢኮኖሚክስ ወዲህ ግን የሥራ አጥነትና የሥራ ቅጥር ሁኔታ የጠቅላላ ብሔራዊ ምርት መጠንና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ጉዳይ (Macroeconomic Phenomena) ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርትን ዕድገትና ይህም ከዋጋ ንረት፣ ከሥራ አጥነትና ከውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠና ነው፡፡ ስለዚህም የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን፣ የብሔራዊ ኢኮኖሚ የጥናት መስኮች ናቸው፡፡

አንድ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ባለሙያም የብሔራዊ ኢኮኖሚውን ዕድገትና መመጣጠን የሚለካው በእነኚህ መሥፈርቶች አማካይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያም በየዓመቱ አሥራ አንድ በመቶ እያደገች ነው ከሚለው ማረጋገጫ የሌለው ሪፖርት በቀር፣ የብሔራዊ ኢኮኖሚው ሁኔታ መገለጫ በሆኑት በሥራ አጥነት፣ በዋጋ ንረትና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ክፉ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ለማንም የተደበቀ ሚስጥር አይደለም፡፡ ገበያ ውስጥ የሚታይ ነገር ስለሆነ ሊደበቅም አይችልም፡፡ የካዱም እያመኑ ናቸው፡፡

በሳይንሳዊ ዓለም የሥራና የደመወዝ ጽንሰ ሐሳቦች

 

ሥራ አጥነትንና የደመወዝ መጣኝን አስመልክቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉና እየዳበሩ የመጡ በርካታ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች ተተንትነዋል፡፡ ብዙ አገሮችም የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው ማዕከላዊ ነጥብ አድርገዋቸዋል፡፡ በአጭር ጽሑፍ ውስጥ ሁሉንም ማቅረብ ባይቻልም፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከሚገልጹት ውስጥ ጥቂቶቹ ለግንዛቤ ያህል እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡  

የዴቪድ ሪካርዶ ጽንሰ ሐሳብ

የመጀመሪው ዘመናዊ የሥራና የደመወዝ ወጥ ጽንሰ ሐሳብ የተተነተነው በእንግሊዛዊ ኢኮኖሚስት ዴቪድ ሪካርዶ ሲሆን፣ የሥራ ዋጋ ደመወዝ መጠን በገበያ ውስጥ የሚወሰነው ሠራተኛው ራሱንና ቤተሰቡን በሕይወት አቆይቶ ዘር ወይም ትውልድ ለመተካት የሚያስችለውን ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ ብቻ በሚያገኝበት የደመወዝ መጠን ነው ይላል ሪካርዶ፡፡ ደመወዙ ኑሮ ዘር ለመተካት ከሚያስችል ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ በታች ከሆነ ሠራተኛው ትውልድ ስለማይተካ፣ የሕዝብ ቁጥር በመቀነስ የሠራተኛ አቅርቦት አንሶ ከፍላጎት በታች ስለሚሆን ደመወዝ ወደ ላይ ይወጣል፡፡ ደመወዝ ኑሮ ዘር ለመተካት ከሚያስችል ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ መጠን በላይ ከሆነ ግን፣ ሠራተኛው ብዙ ሠራተኛ ልጆችን ስለሚወልድ የሕዝብ ቁጥር በመጨመር የሠራተኛ አቅርቦት በዝቶ ከፍላጎት በላይ ስለሚሆን የደመወዝ መጠን ወደ ታች ይወርዳል፡፡ ይህ የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት ውጣ ውረድ ደመወዝ አወሳሰን ሥራ አጥነትን ያስወግዳል፡፡

ይህ ዘር መተኪያ ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ መጠን ደመወዝ የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት እኩልነት አወሳሰን ጽንሰ ሐሳብ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመናት የምግብ ምርትና ምርታማነት ከሕዝብ ቁጥር በላይ በፍጥነት ማደግ ምክንያት ውድቅ ሆነ፡፡

የጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች ጽንሰ ሐሳብ

የሪካርዶ የሥራና የደመወዝ መጠን ጽንሰ ሐሳብ ከጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች አስተሳሰብ አንዱ ይሁን እንጂ፣ በአጠቃላይ የጥንታውን ኢኮኖሚስቶች የሥራ አጥነትና የደመወዝ መጣኝ ጽንሰ ሐሳብ ትንታኔ የሚያተኩረው በግል ኢኮኖሚው የሠራተኛ ገበያ ውስጥ ነው፡፡ ይህም የደመወዝ መጣኝን የሚወስነው በሠራተኛ ገበያ ውስጥ የሚታየው የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ሲሆን፣ በሁለቱ መስተጋብር በሚወሰነው የደመወዝ መጣኝም ሥራ አጥነት አይኖርም፡፡ በሠራተኛ ገበያው ሥራ አጥነት የሚከሰተው የነፃ ገበያው ኢኮኖሚ ሕግጋት በመንግሥትና በሠራተኛ ማኅበራት ጣልቃ ገብነት ሲጣሱ፣ ወይም ሠራተኛውና አሠሪው የረጅም ጊዜ ቅጥር ስምምነት ውል ስለሚዋዋሉ በሠራተኛ ገበያዎች አለመጥራት (Labor Markete Imperfections) ነው፡፡

ስለዚህም ገበያውን በማጥራትና የመንግሥትና የማኅበራትን ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት በማስወገድ፣ በገበያ የሚወሰን የደመወዝ መጣኝ ፍላጎትና አቅርቦትን አጣጥሞ ሥራ አጥነትን ያስወግዳል፡፡ ሥራ አጥነት የሚከሰተው ሥራ ያልተቀጠሩ ሥራ ፈላጊዎች ከተቀጠሩት በዝቅተኛ ደመወዝ ሊሠሩ ቢፈልጉም እንኳ፣ ከላይ በተገለጹት ምክንያቶችና በሌሎች እንደ ሞራልና ሰብዓዊ ስሜት አመለካከቶች በመሳሰሉ ምክንያቶች አሠሪዎች የቀድሞ ሠራተኞቻቸውን አስወጥተው አዲሶቹን በዝቅተኛ ደመወዝ ሊቀጥሩ ስለማይችሉ፣ ወይም ስለማይፈልጉ የሠራተኛ ገበያው የገበያ ኃይሎች በሆኑት በፍላጎትና በአቅርቦት ስለማይመራ ነው፡፡

ካርል ማርክስ

የካርል ማርክስ የደመወዝ ጽንሰ ሐሳብ የሪካርዶን ለሥራ ከእጅ ወደ አፍ ለቀለብ የሚበቃ የደመወዝ መጠንን የመሰለ ሲሆን፣ በካፒታሊዝም ሥርዓት ሠራተኛው ምርት በማምረት ሒደት ውስጥ ለመኖር ከሚበቃው በላይ ያመረተውን ተጨማሪ እሴት፣ በትርፍ መልክ ካፒታሊስቱ ከሠራተኛው የሚበዘብዘው እንደሆነ ነው፡፡ ካፒታል በምርት ሒደት ውስጥ ምንም አስተዋጽኦ የለውም፡፡ ካፒታል ራሱ ተጠራቅሞ ወደ ቴክኖሎጂነት የተቀየረ በምርት ላይ የፈሰሰ የሰው ጉልበት ነው፡፡ ስለሆነም በሶሻሊስት አብዮት ወዛደሩ በካፒታሊስቱ የተነጠቀውንና በዘመናት የሥራ ሒደት ወደ ካፒታልነት የተቀየረውን የተጠራቀመ የሰው ጉልበት ወርሶ፣ ወደ እውነተኛው ባለቤት ወደ ራሱ ማስመለስና ከእንግዲህም ጉልበቱን እንዳይበዘበዝ የካፒታሊዝም የግል ሀብት ይዞታን ያፈርሳል፡፡ በምትኩም በወዛደሩ የሚመራ ማኅበራዊ የሀብት ይዞታን የሶሻሊዝም ሥርዓትና ይህን ሥርዓት የሚመራ መንግሥት  መቋቋም አለበት ይላል፡፡

ይህ የማርክስ የሶሻሊስት አብዮት ጽንሰ ሐሳብም በካፒታሊዝም ሥርዓት ውስጥ በቴክኖሎጂ ዕድገት በፍጥነት መገስገስ፣ ለሠራተኛው ከእጅ ወደ አፍ ለቀለብ ከሚበቃ  በላይ የሚከፍል የበለፀገ የካፒታሊዝም ማኅበረሰብ ከመፈጠር ጋር ማኅበራዊ የሀብት ይዞታና የሶሻሊዝም ሥርዓት ከካፒታሊዝም እኩል ፈጥኖ አለማደግ፣ የሕዝቡንም መሠረታዊ ቁሳዊ ፍላጎቶች ማርካት አለመቻል ይሻላል የተባለው ብሶ በመገኘቱ ምክንያት ከሸፈ፡፡ የሶሻሊዝም ሥርዓተ ኢኮኖሚ ፈራረሰ፡፡ የካፒታሊዝም ሥርዓተ ኢኮኖሚ ያለተቀናቃኝ ብዝበዛውን ቀጠለ፡፡

ኬንስ

ኬንስ ትኩረቱን ከግል ኢኮኖሚ አንስቶ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር፣ የሠራተኛ ገበያዎች ቢፈጠሩምና በግል ኢኮኖሚ ደረጃ የሠራተኛ ፍላጎትንና የሠራተኛ አቅርቦትን የደመወዝ መጣኝ እኩል ቢያደርጉም እንኳ፣ በቁጠባ ከመዋዕለ ንዋይ በላይ መሆን ምክንያት የጠቅላላ አገራዊ ምርት ፍላጎት (የግል ፍጆታ፣ የመዋዕለ ንዋይ፣ የመንግሥት ፍጆታ፣ ኢምፖርት) አገሪቱ ከሚኖራት የሰው ኃይልና የካፒታል ማምረቻ ኃይሎች ምርት የማምረት አቅም (Potential Output Level) በታች ቢሆንም፣ ሥራ አጥነት ይፈጠራል በማለት የሥራ አጥነትን ምክንያት ከሠራተኛ ገበያ ጉድለት አውጥቶ ወደ ምርት ገበያ ጉድለት አመጣው፡፡ ስለዚህም በኬንስ ኢኮኖሚክስ ሥራ አጥነት የሚከሰተው በሠራተኛው ገበያ ውስጥ በደመወዝ ውጣ ውረድ የሠራተኛ ፍላጎትና የሠራተኛ አቅርቦት አለመጣጣም ምክንያት ሳይሆን፣ በምርት ገበያ ውስጥ የምርት ፍላጎት ከማምረት አቅም ወይም ከምርት አቅርቦት በታች ሲሆን ነው፡፡ በተለይም ቁጠባ ከመዋዕለ ንዋይ ሲበልጥ የምርት ፍላጎት ከምርት አቅርቦት ያንሳል፡፡ ምንም እንኳ ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች በግል ኢኮኖሚው ውስጥ የአንድ ማንኛውም ዓይነት ሸቀጥ ዋጋ ፍላጎትና አቅርቦትን እንደሚያመጣጥን ሁሉ፣ በብሔራዊ ኢኮኖሚውም የወለድ መጣኝ በጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት አማካይነት ብሔራዊ ቁጠባና ብሔራዊ መዋዕለ ንዋይን ያመጣጥናሉ ቢሉም፣ ኬንስ ግን በብሔራዊ ኢኮኖሚው ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ የሚጣጣሙት በገቢና በምርት መካከል መመጣጠን ሲኖር ነው፡፡ ገቢ የምርት ፍላጎት ምንጭ ሲሆንም የማምረት አቅምም (የሰው ኃይልና ካፒታል) የምርት አቅርቦት ምንጭ ነው ይላል፡፡

ኬንስ በምርት ፍላጎት ማነስ ምክንያት ኢኮኖሚው ለማምረት ከሚችለው በታች ማምረት ዋናው መንስዔ የሕዝቡ ገቢ ማነስ ስለሆነ፣ መንግሥት የበጀት ጉድለት ውስጥም ቢሆን ገብቶ መሠረተ ልማትን በመገንባት የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ ለሕዝቡ ፈጥሮ ኢኮኖሚውን ማስፋፋት አለበት ይላል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ከ1930ዎቹ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስና የሥራ አጥነት ችግር ምዕራባውያን የወጡት በዚህ የኬንስ ኢኮኖሚክስ ፍልስፍና ነበር፡፡ በዚህም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰንና ዋና አማካሪያቸው ታዋቂው የጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚስት ሚልተን ፍሬድማን ሳይቀሩ፣ ‹‹አሁን ሁላችንም ኬንሳውያን ወይም የኬንስ ኢኮኖሚክስ ተከታይ ነን›› ብለው ነበር፡፡ ሆኖም ቴክኖሎጂ ሲያድግና የምዕራቡ ዓለም ሲዘምን በድርጅቶች ላይ በተፈጠረው ጫና በቅጥር ላይ ያሉት ሠራተኞች ደመወዝ በመጨመሩ ምክንያት፣ ለሠራተኞቻቸው ከምርታማነታቸው ዕድገት በላይ የፈጠነ የደመወዝ ዕድገት መክፈል በመገደዳቸው ለማካካስ የምርታቸውን ዋጋ ሲጨምሩ የዋጋ ንረት ተከሰተ፡፡ በሥራ ላይ ያሉ ሠራተኞች ከምርታማነታቸው በላይ የደመወዝ ዕድገት አገኙ፡፡ ሥራ ፈላጊ ሠራተኞችና ሥራ አጦች በበጎ አድራጎት ድጋፎች መረዳት እስከሚያስፈልጋቸው ድረስ በዋጋ ጭማሪው ምክንያት ኑሮም ተወደደባቸው፡፡

ስታግፍሌሽን

በ1970ዎቹ ሥራ አጥነትና የዋጋ ንረት ጎን ለጎን በመከሰታቸው ምክንያት ቀድሞ ይታመን የነበረውን በሥራ አጥነትና በዋጋ ንረት መጣኞች መካከል አንዱ ሲቀንስ ሌላው የመጨመር በተቃራኒ አቅጣጫ መጓዝ ሥርዓታዊ ተዛምዶ (Systematic Relationship) አለ የሚለው ተዛምዶውን በተነተነው ኢኮኖሚስት ስም ከግራ ወደ ቀኝ የሚወርድ የፊሊፕስ ደጋን መስመር (Phillips Curve) ተብሎ የሚታወቀው በግራፍ የሚመለከት አቅጣጫ አመልካች የሒሳብ ስሌት ኢኮኖሚ ትንታኔ ተፋለሰ፡፡ ከዚህም ጋር አብሮ በኬንስ ኢኮኖሚክስና በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ያለው እምነት በብዙዎች ዘንድ ቀነሰ፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ ሥራ አጥነትንና የዋጋ ንረትን ማመጣጠን መቻሉም ጥርጣሬ ላይ ወደቀ፡፡

ይህ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤት ላይ የተፈጠረ ጥርጣሬ ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተሟጋች ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች እንደገና ማንሰራራት ዕድል ሰጠ፡፡ ኬንስ ራሱ ያቋቋማቸው የዓለም ባንክና ዓለም አቀፍ የጥሬ ገንዘብ ድርጅት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ (Neo-liberalism) ተሟጋች ሆኑ፡፡ ታላላቅ ኢኮኖሚስቶችም በሁለቱ ጎራዎች ተከፍለው የየራሳቸውን ኢኮኖሚክስ እየተነተኑ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱን አጣምረው የግል ኢኮኖሚና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ቅንጅት ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ የሚሰጡም አሉ፡፡

ቅጥ ያጣ የደመወዝ ውሳኔና የሥራ አጥነት ችግር

ምንም እንኳ የኢኮኖሚ ባለሟሎቹ የመንግሥት ፖሊሲንና የሥራ አጥነት ተዛምዶን በመጣኝ መለኪያዎች ለክተው ለማስረዳት አቅም ቢያጡም፣ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ትኩረት በኬንስ ትንታኔ መንገድ ገቢን በማሳደግ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን የማስፋፋት ሥልት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ያልተለካው የፖሊሲ ዕርምጃ ለጊዜው ውጤት ያሳየ ቢመስልም፣ በረጅም ጊዜ ውጤቱ  ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ አብዛኛው ከተሜ ሠራተኛ የሚያገኘው ደመወዝ መጠን ሥራ ለመኖር ብቻ የሚያበቃ ከእጅ ወደ አፍ ያህል ነው፡፡ የሪካርዶና የማርክስ ጽንሰ ሐሳቦች ከዚያ ወዲህ ከፈለቁት የጥንታውያንና የኬንስ ጽንሰ ሐሳቦች በይበልጥ የኢትዮጵያን የሠራተኛ ገበያ ይገልጻሉ፡፡ የምርት ሸቀጦች ዋጋ ዕድገት ከዝቅተኛ ሠራተኞች ደመወዝ ዕድገት ይልቅ በጣም ፈጣን ነው፡፡ በሌላ በኩል በጣም ጥቂት የሆኑ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ያሉ ሠራተኞች፣ በደርግ ዘመን ያገኙት ከነበረው አንድ ሺሕ ብር በመቶ እጥፍ አድገው በወር እስከ መቶ ሺሕ ብር ደመወዝ ውስጥ ገብተዋል፡፡

ምርታማነታቸው ቢለካ የደመወዛቸውን ሩብ ያህል እንኳ እንደማይሆን ይታወቃል፡፡ ለንግዱ ማኅበረሰብ የረባ አገልግሎት ሳይሰጡ በዓመት ሁለት ሳምንት ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት በየወሩ ሰላሳ፣ አርባና ሃምሳ ሺሕ ብር ቆጥረው የሚቀበሉትን ሰሞኑን ተጠያቂነት የጎደላቸው ተብለው በመገናኛ ብዙኃን የተብጠለጠሉትና የቃላት ዱላ ያረፈባቸውን የንግድ ምክር ቤቶቻችንን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይበቃል፡፡ የሌሎች አገሮችን የደመወዝ ዕድገት ታሪክ ከእኛው ሁኔታ ጋር ብናነፃፀር ከ1950ዎቹ በኋላ በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ በቴክኖሎጂ ዕድገት ምክንያት ምርታማነት ስለጨመረ፣ የደመወዝ መጠን ከምርት ሸቀጦች ዋጋ በላይ በፍጥነት አደገ፡፡ በመንግሥት ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል መወሰን ተጀመረ፡፡ የሠራተኛ ማኅበራትም ለደመወዝና ለልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች መሟገት ጀመሩ፡፡ በብዙ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ አገሮች ከብሔራዊ ገቢው ውስጥ የደመወዝ ድርሻ እስከ ሦስት አራተኛ ደርሷል፡፡ ለጡረተኞችና ለሥራ አጦች በደመወዝ የሚለካ እንክብካቤ ይደረጋል፡፡ ተረዳድቶና ተካፍሎ መብላት ልማዳዊ ወግ በሆነበት በእኛ ኅብረተሰብ ውስጥ የገቢ ምንጭ ፖሊሲን ለወጣቱ፣ ለአረጋዊው ብሎ መከፋፈል ከንቱ ውዳሴ ነው፡፡ አባት ልጁን ይጦራል፣ ልጅም አባቱን ይጦራል፡፡ ሕልውናችን የተመሠረተው በመረዳዳት ነው፡፡ አባት ያገኘው ልጅ አገኘው፣ ልጅ ያገኘውም አባት አገኘው ነው፡፡ ብዙ አገሮች በየጊዜው የጡረታ ክፍያን ከዋጋ ንረት ጋር የሚያስተካክሉ ሲሆን፣ ዛምቢያን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች እንኳ የመንግሥት ተቀጣሪዎች በሚያስቀምጡት የጡረታ መዋጮ ቦንድ ገዝተውላቸው፣ በሚገኘው ወለድ በጡረታቸው ጊዜ መዋያና መዝናኛ ቦታ ይሠሩላቸዋል፡፡

የወጣቱም የአረጋዊውም ሥራ ማጣት የዚህች አገር ከፍተኛ ችግር መሆኑ ከተስተዋለ ውሎ አድሯል፡፡ የኅብረተሰቡ ግማሽ የሚሆነው ዕድሜው ከአሥራ አምስት እስከ ሰላሳ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለው መሆኑ ደግሞ ችግሩ ለወደፊትም እንደሚቀጥል ጠቋሚ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 የኢትዮጵያንም ጨምሮ የአፍሪካዊ አማካይ ዕድሜ ከ25 እስከ 27 ዓመት ሆኖ ወጣት የበዛበት ትውልድ እንደሚሆን አዋቂዎች ይገምታሉ፡፡ ዕድሜ ቆጥሮ ማረፍ እንኳ በማይቻልባት ኢትዮጵያ ጡረተኞች ዛሬ በጥበቃ፣ በተላላኪነት፣ በጉዳይ አስፈጻሚነትና በደላላነት ከመሰማራታቸውም በላይ ሥራ ያጡም ሥራ ፍለጋ እየተንከራተቱ ነው፡፡

የዛሬ አርባ ዓመት የሆቴል የፆም በየዓይነቱ በአሥራ አምስት ሳንቲም ይበላ በነበረበት ጊዜ ለጡረታ ብለው መንግሥት ዘንድ ያስቀመጧት አንድ ብር፣ በያኔው ዋጋ ሰባት የሆቴል የፆም በየዓይነቱ ትገዛላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ያችን ምሳ ለመብላት ሰላሳ ብር መክፈል ሲያስፈልጋቸው፣ በጡረታ መልክ ያስቀመጧትን ያችኑ  አንድ ብር እያገኙ ኑሮው ግን በምሳዋ የቀድሞ ዋጋ ሒሳብ ሁለት መቶ አሥር እጥፍ ተወዶባቸዋል፡፡ አባትና ልጅ ተረዳድተው በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ደግሞ ይህ ሁለቱንም በድህነት አዙሪት ውስጥ የሚያሽከረክር ነው፡፡ የእነርሱን መንደላቀቅ የአገር ዕድገት አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች፣ ሕዝቡ የኢኮኖሚ ቀውስ አደጋ ላይ እንደሆነ ምን ዓይነት ማስረጃ ተቆጥሮ እንደምን ተደርጎ ቢነገራቸው ይሆን የሚያምኑትና እየተጎዳ ላለውና ወደፊት ለሚጎዳው ሕዝብ የሰብዓዊ ፍጡር መተዛዘን ስሜት የሚሰማቸው፡፡ የራሳቸውን መንደላቀቅ በሁለት ዓይናቸው ሲያዩ ለተጎዳው ሕዝብ በአንድ ዓይናቸው እንኳ ማየት የሚጀምሩት መቼ ይሆን? ዘለዓለም ይኖሩ ይመስል ለምን የእናቶች፣ የሕፃናትና የአረጋውያን ስቃይ አይታያቸውም? ለምንስ ቀጣዩን ትውልድ መከራ ትተውለት ያልፋሉ?

ʻእንደምን አለህ?ʼ ተብሎ የእግዜር ሰላምታ ሲሰጥ፣ ʻዛሬ ከነገ ይሻላልʼ ተብሎ ነገ የሚናፈቅ ሳይሆን የሚፈራ እንደሆነ የሚገምተውን ሕዝብ ቢያስቡት ምን አለበት? እናት ልጇን ተሰደድና ይለፍልህ ብላ ከአጠገቧ ልታርቀው የጨከነችበትን ጊዜ፣ አባት ዕድሜ ልኩን ያጠራቀመውን ጥሪት ለበረሃና ለባህር አሻጋሪዎች ከፍሎ ልጁን አልቅሶ የሚሸኝበትን ጊዜ፣ ከከተማ ወጣቶች ግማሽ ያህሉ በየመንገድ ዳሩ እየጮሁ ሳልባጅ ጨርቅና ቅራቅንቦ ነጋዴ የሆኑበትን፣ ለእያንዳንዱ ሕጋዊ ጉልት ቸርቻሪ ሕጋዊ ካልሆኑ አሥር እጥፍ ተቀናቃኝ ጉልት ቻርቻሪ ነጋዴዎች ለመከላከል ደንብ አስከባሪ መድቦ ዘብ ማቆም ያስፈለገበትን፣ ሰው ከሰው ለቁራሽ እንጀራ የሚናቆርበትና የሚደባደብበትን፣ የየመንደሩ ጎረምሶች እርስ በርሳቸው ተሿሹመው የመኪና ተራ አስከባሪና ዋጋ አስከፋይ የሆኑበትን ጊዜ እንደምን አያዩም?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles