ሰላም! ሰላም! ተስፋን በውስጣችን የመለኮስ ባለሙሉ ሥልጣን ባለቤት ነንና እነሆ ዛሬን በደስ ደስ እንጀምረው። ምን አባቱ። ስንት ዓመት ይኖራል? ስላችሁ ʻተኑሮ ተሞቷልʼ እንዳትሉኝና እንዳይብሰኝ አደራ። ጉድ እኮ ነው፡፡ ይልቅ የደስ ደሱ ምክንያት ከብዙ ዓመታት በፊት የተለየኝን የቀድሞ ወዳጄን ማግኘቴ ነው። አንድም አንገናኝ ብለን መሰለኝ ዛቻ የበዛው። መቼም ʻሰው ካልሞተ በስተቀር መገናኘቱ የማይቀር ነውʼ የሚባለው አባበል በሕይወቴ ብዙ ጊዜ ሠርቷል። ያከራየኋቸውን ሰዎች ሳስለቅቅ፣ መልሼ ሳከራይ፣ የአሻሻጥኩትን መልሼ ሳሻሽጥ ከስንት ሰዎችና ነገሮች ጋር በተደጋጋሚ እገናኛለሁ መሰላችሁ?እኛ ክፉ እየሆንን እንጂ መኖር ደግ ነው፡፡ ‹‹እንደ መሰንበት ያለ ሸጋ ነገር የለም፤›› ይላሉ ባሻዬ፡፡ ታዲያ ሰሞኑን ከዓመታት መለያየት በኋላ ከአንድ አብሮ አደግ ወዳጄ ጋር ተገናኘን። ‹‹ሁሉንም ያገኛል ሰው በሕይወት ካለ፣ የሞተ ተጎዳ መቃብር ውስጥ ያለ›› ተብሏል አሉ። ኧረ ምፅዓት ናፋቂ በዛ ጎበዝ!
እናላችሁ ይህ የቀድሞው ወዳጄ እንደኔው ደላላ ነው። ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደመገናኘታችን መጠን አንዳችን ስለአንዳችን የማወቅ ጉጉታችን ጨምሮ ኑሮ፣ በአንዴ ጊዜ ለመናገር ስንደነቃቀፍ ቆየን፡፡ ስለሥራ ስለቤተሰብ በአጠቃላይ ስለሕይወት ማውጋት ጀመርን። ‹‹ምን እባክህ የዘንድሮን ነገር ለመርሳት መሞከር፣ ከማሰብ የከበደ ቢሆንም የተቻለንን ያህል ብንጥር ነው የሚሻለን። ከኑሮ መክፋትና እንደ እቶን መንደድ አኳያ ቤተሰብ መምራት የማልችልበት ደረጃ ደርሻለሁ። መቼም አንድ አንተ ለራስህ አታንስም። ምናልባት ግን ለአንድ ለራስህ የምታንስበት ቀን ሊመጣም ይችል ይሆናል፡፡ ደግ ደጉን ካልተመኘህ። ለብዙ ስትሆን ግን አቅልህን ትስታለህ። ይኼውልህ እሱን ብለን እኔና ባለቤቴ ተማክረን ተለያየን። ቤተሰብ ከማስተዳደር ራስ በረንዳ ማደር የሚል መፈክር አንግበን ተለያየን። ሳንለያይ ተለያየን፤›› አለኝ፡፡ በጣም ተገርሜ በአንድ በኩል ስለሰላማዊ ፍቺ የሰማሁበትን ቀን ለመዘከር እያውጠነጠንኩ፣ በሌላ በኩል ʻችግር ብልኃትን ይወልዳልʼ እንዲሉ የሰው ልጅ ለመኖር የሚፈነቅላቸው ደንቃራ ድንጋዮች በምናቤ ለመሳል ተጣጣርኩ። ለካ ተማክሮም ፍቺ አለ እናንተ!
እንዲህ ያንንም ያንንም ስናነሳ ስንጥል ቆየን። በመካከላችን ሰፊ ርቀት ፈጥረው ያለያዩንን እልፍ የትውስታ ዘመናት ቆጠርን። ብዙ ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ የሚጠቡ ይመስል በብዙ የሐሳብ እንሽርሽር ʻትዝ ይልሃል ትዝ ይልሃልʼ እየተባባልን በትዝታ ደከምን። ‹‹እንዲያው ይህን ያህል ጊዜ ስንለያይ ትዝ ብየህ አውቃለሁ?›› ብዬ ትዝብትን ሳላጠምድ ጠየቅኩት። ‹‹አይ አንተ ሰው ከራሱ ጋር ተረሳስቷል እንኳን ከቀድሞ ወዳጁ፡፡ ትዝ ብትለኝም አፍታ ከውስጤ ሳትቆይ በኑሮ ኮተተ ሐሳቦች ተጠርገህ ትጠፋለህ። የሆነው ሆኖ ፍቅርንና መተሳሰብን የሚያቀዘቅዝ ዘመን በአፍንጫችን ይውጣ . . . ለነገሩ እኛ ነን ፊት የሰጠነው መሸ ነጋ ሆድ። ስለሆድ አስበን ስለሆድ ተጨንቀን ስለምግብ አውርተን አናታችን ላይ ወጣ። አኅጉር ከአገር እደምትሰፋው ፍቅርና መተሳሰብም ከሆድ ብለህ ብትል ዛሬ ቅጥያህ ብዙ ነው፤›› ብሎኝ በረጂሙ አሰበ። እኔም ግር ብሎኛል፡፡ ወይ ዘመን!
አንዳንዱን መኖር ሲያቅተው እንዴት ፈላስፋ እንደሚያደርገው ታያላችሁ? ወዳጄ ቀጠለ። ‹‹ይህ አልገባን ብሎ ነው መሰለኝ የዳዴአችን ዙሩ በዛ። ለምሳሌ ወታደርን ተመልከት፣ ውትድርናን ሲያስብ አብሮ ፈንጂ መርገጥን ጦር ሜዳ መውደቅን ያስባል፡፡ እኛም ስለኑሮ አስፍተን ልናስብ የሚገቡን ብዙ ጉዳዮች አሉን እኮ፡፡ ለእነሱ ካልተዘጋጀን ትርፋችን ከራስ ጋር ፀብ ይሆንና ያርፋል አየህ? ገባህ አይደል? ግን ምናባቱ አዕዋፋትን የሚመግብ አምላክ ለእኛ ደግሞ የዕለታችንን ያሳጣናል ብለህ ነው?›› ሲለኝ እኔ የለሁም። በልጅነት ጓዴ አናት ላይ የተዘራውን ሽበት፣ ከግንባሩ ወደ መሀል አናቱ የሸሸ ፀጉሩን እያየሁ፣ ደግሞ ከሁሉ ያ የማውቀው ቀዥቃዣ ስቆ የሚያስቅ ወዳጄ እንዲህ በነገር ቆርቦ እያየሁ ጭልጥ ብያለሁ። ወይ ዕድሜ!
ለማንኛውም ከትውስታ ወደ እውነታ ስንመለስ ዕድልና ትግል በሁለት ተቃራኒ የዕጣ ፈንታ መስመር ዕጣ ሲጣጣሉብን እንደርሳለን። ምን ሆነ መሰላችሁ? ማንጠግቦሽ ለውድ ባለቤቷ አምበርብር ምንተስኖት ምሳ ለማቅረብ ጓዳዋ ውስጥ ትንጎዳጉዳለች። አልፎ አልፎ በብስጭት ቃና፣ ‹‹ኤድያ ዘንድሮስ. . .›› ስትል እሰማታለሁ። አሳዝናኝ፣ ‹‹አይዞሽ እናቴ እኛ ጤና፣ ጤና እኮ ይበልጣል፤›› ስላት፣ ‹‹ምን አባቱንስ ጥንቅር ይላል እንጂ ጤናንማ አናጣም፤›› ስትለኝ ደስታ የውስጤን ጉብጠት ያቃናዋል። ይብላኝ ላላገባ እንጂ ሚስት ያለውማ ይኼው እንደዚህ ʻአይዞህʼ ሲባል በአንዴ ሌላ ሰው ይሆናል። ድሮ የሚባለው ʻሴት የላከው ሞት አይፈራምʼ አይደል? አሁን ደግሞ ʻሴት ያፀናው ኪሳራ አይፈራም፣ ቫት አይፈራም፣ ብድር አይፈራምʼ ይባላል አሉ። ጉድ እኮ ነው።
እና ምንድን ነበር የምናወራው? አዎ መታደልና ትግል ስላችሁ ነበር። ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ይልቅ እስካሁን ሳልነግርህ?›› ብላ ወሬ ጀመረች። ‹‹ምኑን ማንጠግቦሽዬ?›› ስላት፣ ‹‹እስኪ እንደገና በለኝ?›› ስትለኝ፣ ‹‹ምንድን ነው የምልሽ?›› ማለት፡፡ ‹‹አሁን ያልከኝን?›› አለች እንደገና፡፡ ‹‹ምን ማንጠግቦሽዬ?›› ብላት፣ ‹‹አዎ እሱን፤›› ስትል፣ ‹‹ማንጠግቦሽዬን?››፣ ‹‹ወይዬ? ለምንድን ነው ግን እንዲህ ለረጅም ጊዜ የተውከው?›› ብላ ከንፈሬን ስትነክሰው የጎረቤታችን ሚስት ሠፈሩን በጩኸት ቀውጢ ስታደርገው አንዴ ሆነ። ተሯሩጠን ስንወጣ ከቅንድቧ አካባቢ ቡልቅ እያለ ደም ይፈሳል። የታደለው ከንፈር ሲነካከስ ትዳር ትግል የሆነበት ደግሞ ዘንድሮም በዚህ በሠለጠነ ጊዜ ይቧቀሳል። እኛ ደግሞ ጥሎብን የሚቀናን የጨበጣ ውጊያ፣ በድንጋይ የታጀበ ሠልፍና የተመናቀረ ፍቅር ነው። ምን እንደሚሻለን ብቻ እንጃ!
ካነሳሁት አይቀር ታዲያ ሰሞኑን ከገጠመኝ ጋር አስማምቼ ይኼን የፍቅር ነገር ልፍተለው። በመጀመሪያ እንደ ነገርኳችሁ የዘንድሮ ሰው ትዳር በሁለት የተከፈለ ነው ብያችኋለሁ? ምንና ምን? በጣም ጥሩ! ምን ሆነ መሰላችሁ? ሁለት አዲስ ሙሽሮች መሆናቸው ነው። ከተጋቡ ገና አንድ ዓመታቸው ነው። በተጋቡ በስድስት ወራቸው ኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ወጥቶላቸዋል። በዚህ አያያዛቸው ገና ለእኛ ይተርፋሉ ሲል ቤተ ዘመድ እንዳልኳችሁ ʻአንቨርሰሪʼ ደረሰ። በአማርኛ ፍቅራቸው የተጀመረበት ቀን ዓውደ ዓመት ማለት ነው። ያዛችሁኝ? ከዚያስ? ʻእንኳን አደረሳችሁʼ ልትል የሚስት ጓደኛ ከተፍ። በሉ፣ ጠጡ፣ ሳቁ፣ ዘፈኑ፣ ዘፈኑ… ጠጡ፣ ጠጡ… ‹‹ለምን እኛ ዘንድ አታድሪም ዛሬ?›› በማለት ሚስት ወዳጇን ጠየቀች። ያቺም እሺ አለች። መስማማት። ማደር። ባል ሌሊት የሚስቱ ጓደኛ የተኛችበት ክፍል ዘው ማለት። ውሎ አድሮ የሚስት አብሮ አደግ ሆድ መግፋት።
ነገሩ ፍርጥርጡ ሲወጣ ያቺ ኮንዶሚኒየም ቤት ለሽያጭ ቀረበች። ደላላው አንበርብር የተጠራውና ነገረ ታሪኩን ያጠናው ይኼ ነው። አይገርምም ግን? የባሻዬ ልጅ ይኼን ታሪክ ሰምቶ፣ ‹‹ምን እባክህ የዘንድሮ ትዳር ራዳር የሌለው የአየር ክልል ሆኗል፤›› አለኝ። ሳቅ ብዬ፣ ‹‹ምን ማለት ነው?›› ስለው፣ ‹‹በቃ በአየር ክልሉ ውስጥ የሚበሩ ብዙ ነፍሶች አሉ። በያኝ፣ ገዥ፣ ቆንጣጭ እሴቶች እያደር ተረስተው ተረስተው በየጓዳው በየቤቱ የማትሰማው የማታየው ጉድ የለም እኮ፤›› ብሎኝ ብክንክን አለ። ‘ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፡፡ ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም’ ያለው ለካ ጥላሁን ገሰሰ ወዶ አይደለም። ግን እንዲያው እንዲህ የትዳርና የአገር ጉዳይ ቅልል ያለብን ለምን ይሆን?
በሉ እንሰነባበት። የዘንድሮ ጉድና ጓደኛ ማለቂያ የለውም። ሁሉም በየፊናው በሚወጥረው ተወጥሯል። ባሻዬም ፆማቸውን ከረር አድርገው ይዘው ብዙም አይታዩም። ልጃቸውም አንድ የግል ኩባንያ አቋቁማለሁ እያለ ጠዋት ወጥቶ ማታ ይገባል። ማንጠግቦሽ ከሥራ የተረፋትን ጊዜ ʻቃናʼ ላይ ወስዳ ትዘፈዝፈውና ቢጠሯት አትሰማም። እኔ ደግሞ እንዲህ ትኩረት የተነፈግኩ ሰሞን ወጣ ወጣ በማለት እጠመዳለሁ። ስለዚህ እንደተለመደው ወደ ግሮሰሪያችን ጎራ ብዬ ቢራዬን ይዣለሁ። አጠገቤ አንድ ፀጉረ ልውጥ ተቀምጧል። ብቻ ለብቻማ አንዛለቅም። ‹‹ቺርስ!›› አልኩት። ስቆ ‹‹ቺርስ!›› አለኝ።
ሲያጫውተኝ ለሰላሳ ዓመት አገሩን አላየም። አሁንም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ይኖራል። ‹‹እንግዳ ሆኖብሃላ?›› ስለው፣ ‹‹ወይ አዲስ አበባ›› ብሎ አፉን ያዘ። ‹‹ከዓለም አቀፍ ከተሞችና የከተማ ልማት ጽንሰ ሐሳብ አኳያ አዲስ አበባን እንዴት አገኘሃት?›› አልኩት። ‹‹የሚገርምህ ከመጣሁ ሁለት ሳምንቴ ነው። የወጣሁት ትናንትና ነው። ለምን? የመጣሁ ቀን የሆነ ቱቦ ሸተተኝ። ታመምኩ፣ ተኛሁ፣ ተኛሁ። በዚያ ላይ የመኪናው ጪስ፣ በዚያ ላይ ማስታገሻ ማስተንፈሻ አለመኖሩ…›› ሲለኝ ይኼ ሰውዬ ነገረኛ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ሸሸሁት። ነው ራሴን በራሴ ስቃመው ይሆን? ዓይን ራሱን አያይም አሉ። አንዳንዴ ግን አኳኋናችን አላምር ሲለኝ ብቻዬን መሆን ያምረኛል፡፡ እና አንድ ቀን ቁጭ ብዬ ስተክዝ አንዱ ደወለልኝ፡፡ ‹‹ሃሎ!›› ስል ይስቃል፡፡ ‹‹ምን ሆነሃል?›› ስለው፣ ‹‹የሆነ ጥቅስ አንብቤ ነው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እስቲ እኔም ልሳቅ ንገረኝ፤›› ከማለቴ አንበለበለው፡፡ ʻልብ እየጠበበ ሳንባ እየሰፋ፣ ታዋቂ ሰው በዝቶ አዋቂ ሰው ጠፋ…ʼ ሲለኝ ከእሱ በላይ ሳቅኩ፡፡ ወይ ጊዜ! መልካም ሰንበት!