ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ለማስመዝገብ ያቀደቻቸውን ሁሉን አቀፍ ዕድገት በአጭር ጊዜ ለማሳካት ከተደቀኑባት ተግዳሮቶች መካከል የበቁ ባለሙያዎች እጥረት አንዱ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም የዓለም ባንክ ያወጧቸው ሰሞነኛ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የበቁና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ማሳተፍ የሚያስችላትን የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ ነድፋ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት ቁልፍ ተግባራት መካከል የአገሪቱ የስፖርት ልማት አጀንዳ አንዱ ነው፡፡ ይህ በስፖርት ዘርፍ በአገሪቱ የሚታየውን የክህሎትና የዕውቀት እንዲሁም የሙያ ክፍተት ለመሙላት አስተዋጽኦ ታሳቢ በማድረግ የተዘረጋ የዕቅድ ሰንሰለት መሆኑም ታሳቢ ሊደረግ እንደሚገባ የሚናገሩ አሉ፡፡
የስፖርት ልማት በተለይ እግር ኳስና አትሌቲክስ ከፍተኛ አገራዊ መግባባትን በመፍጠርና ገጽታን በማስተዋወቅ እንዲሁም ገቢ በማስገኘት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለስኬቱም በሙያው ከፍተኛ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ከፍተኛ ንቅናቄ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን የተለያዩ የስፖርት ጥናቶች በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ይህን አገራዊ የተሳትፎና የዕድገት መሠረታዊ እሳቤ ወደ ጎን በመተው የተለያዩ የስፖርት አደረጃጀቶች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ገሸሽ የሚያደርጉ ወይም የሚገድቡ ውስጠ ደንቦችን በማውጣት ለስፖርቱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊደረግ የሚችልበትን ዕድል በመንፈግ ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጠ ደንቦች አንዳንዶቹን ለዚህ በማሳያነት በመጥቀስ የሚተቹ አሉ፡፡ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አቶ ዮሐንስ ሳሕሌ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት በአዋጅ ቁጥር 1/1987 ዓ.ም. በወጣው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ሥራ ላይ የሚውሉ ማንኛውም ሕጎችም ሆነ ደንቦች ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጋጨት ወይም መቃረን የሌለባቸው እንደሆነ የደነገገውን በመጥቀስ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚጠቀምባቸው አንዳንዶቹ ውስጠ ደንቦች ከአገሪቱ ሕግ ጋር ተጣጥመው እንዲወጡና ሥራ ላይ እንዲውሉ ከሚጠይቁት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
እንደ አቶ ዮሐንስ ከሆነ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ ላይ በዋለው መተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ 30 በሰፈረው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመምረጫ መመዘኛዎች ውስጥ ከተዘረዘሩት አንዱ፣ ከአገሪቱ መደበኛ ሕጎች ጋር የሚጋጭ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ይኼውም የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆነ በሚል የተቀመጠው ይህ አንቀጽ ለአገሪቱ ስፖርት ዕድገት ሊጠቅሙ የሚችሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ አያካትትም ይላሉ፡፡
በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሥራ ላይ በዋለው አዋጅ ቁጥር 270/1994 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ተወላጅ ሆነው የውጭ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣ ከመሆኑ ጎን ለጎን የተወላጅነት መታወቂያ ካርድ የያዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማንኛውም የስፖርት ዓይነት በሥራ አስፈጻሚ አመራርም ሆነ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ እንዳይሳተፉ እንደማይከለክል በመጥቀስ አቶ ዮሐንስ ያምናሉ፡፡
በዚህ የኢትዮጵያ ተወላጆች በሚለው አዋጅ ውስጥ በአንቀጽ 6 በተገለጸው ማለትም በማናቸውም በመንግሥት ደረጃ በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንደሌላቸው፣ በማንኛውም የአገር መከላከያ፣ የአገር ደኅንነት ወይም በውጭ ጉዳይ መሰል የፖለቲካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመደበኛነት መሥራት የማይችሉ መሆኑ መደንገጉን ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ግን ይህንን አዋጅ በሚቃረን መልኩ ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት በሚደረግ ምርጫ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መገደቡን በመጥቀስ ማስተካከያ እንዲደረግ የጠየቁት አቶ ዮሐንስ፣ በዚህ ረገድ በሌሎችም ፌደሬሽኖች በቅርቡ በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ለመወዳደር በዕጩነት በቀረቡት አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የውጭ አገር ዜጋ ናቸው በሚል ክርክር መፍጠሩን ጭምር ያስታውሳሉ፡፡ ለእነዚህ ችግሮች የስፖርት መተዳደሪያ ደንቦች ከአገሪቱ መደበኛ ሕጎችና አዋጆች ጋር ተጣጥመው አለመቀረፃቸው መሆኑን ጭምር ለፌዴሬሽኑ ባስገቡት የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ አካተዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ከዚህም በተጨማሪ በአንቀጽ 58 መሠረት ተዘጋጅቶ የወጣው ደንብና መመርያ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) እና በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ደንቦችና መመሪያዎች ያልተጠቀሱ ቢኖሩና ከአገሪቱ መደበኛ ሕጎች ጋር የሚቃረኑ ልዩ ድንጋጌዎች እንኳ ቢያጋጥሙ፣ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጉዳዩን አጣርቶ ስህተቱን በማስተካከል ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን እንደሚደነግግ የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ይህንኑ በግልባጭ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለዳያስፖራ ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት፣ ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳውቀዋል፡፡