የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በከፊል በቀድሞ አትሌቶች መመራት ከጀመረ በኋላ የመጀመሪያውን የብሔራዊ አሠልጣኞች ምርጫ ይፋ አደረገ፡፡ የቀድሞ የረዥም ርቀት ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ የረዥም ርቀት የዋና አሠልጣኝ ኃላፊነት አግኝተዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በምርጫው ቅሬታ ያላቸው ካሉ የቅሬታ ማቅረቢያ ጊዜም አስቀምጧል፡፡
በዚሁ መሠረት በቀድሞ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አካላት የወጣት ብሔራዊ ቡድኑ የረዥም ርቀት ዋና አሠልጣኝ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ሳይቀበሉ የቀሩት ዶ/ር ይልማ በርታ፣ በአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ የፕሮጀክቶች፣ የማዕከላት፣ የክለቦች እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኖችና የማናጀሮች ሥልጠና ዋና አስተባባሪ አድርጎ መርጧቸዋል፡፡ የቀድሞ ማራቶን አሠልጣኝ አቶ መላኩ ደረሰ ደግሞ የማዕከላት፣ ፕሮጀክቶችና አካዴሚ ሥልጠና ክትትል ኃላፊ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ከብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ምርጫና ምደባ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት ሲፈጠርበት የሚደመጠው የረዥም ርቀት ዋና አሠልጣኝ ቦታ ነው፡፡ በሻለቃ ኃይሌ የሚመራው አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዚሁ ውዝግብ ምክንያት ከፌዴሬሽኑ የብሔራዊ አሠልጣኝነት ርቀው የቆዩት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ የርቀቱ ዋና አሠልጣኝ እንዲሆኑ መርጧቸዋል፡፡ በርቀቱ የቀድሞ ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ሱፐርኢንቴንደት ሁሴን ሽቦ የምክትል ዋና አሠልጣኝነቱ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአሠልጣኝነት ደግሞ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ፣ አቶ ባሕሩ ሚኮ፣ ወ/ት ሰናይት ኃይሌ፣ አቶ በሪሁን ተስፋዬና ኮማንደር አበበ መኰንን ተመድበዋል፡፡
በዚሁ ርቀት የታዳጊ ወጣት ብሔራዊ ቡድን የዋና አሠልጣኝነቱ ኃላፊነት ለአቶ ንጋቱ ወርቁ ሲሰጥ፣ አቶ ካሱ ዓለማየሁ ምክትል ዋና አሠልጣኝ ሆነዋል፡፡ በአሠልጣኝነት ኢ/ር ግርማ ፈዬ፣ አቶ ይበልጣል መርሻ፣ አቶ ብርሃኑ መኰንንና ወ/ሮ ንጋቷ ወልዴ ሆነዋል፡፡
በ3,000 ሜትር መሰናልክ አቶ ተሾመ ከበደ ዋና አሠልጣኝ ሲሆኑ፣ አቶ ብዙነህ ያኢ፣ አቶ ብዙአየሁ ታረቀኝ፣ ሻምበል ዮሐንስ መሐመድና ሻምበል እሸቱ ቱራ በአሠልጣኝነት ተመርጠዋል፡፡
ዕርምጃ በዋና አሠልጣኝነት ሻለቃ ባዩ አሰፋ ሲመረጡ፣ ወ/ት አምሳል ያዕቆብ በምክትልነት ተመርጠዋል፡፡ ለአጭር ርቀት ደግሞ አቶ አብዱልአዚዝ ሁሴን ዋና አሠልጣኝ ሲሆኑ፣ ሻምበል ሙሉጌታ መለሰ፣ አቶ ጌታቸው ሙሉጌታ፣ ወ/ት ንፁህ ወንድሜነህ፣ ወ/ት ብርቱካን ቀፀላና አቶ ገነት ባዲ በአሠልጣኝነት ተመርጠዋል፡፡
ለመካከለኛ ርቀት ዋናው ቡድን አቶ ንጉሤ ጌቻሞ ዋና፣ አቶ ዳዊት ጥሩነህ ለምክልት ዋና አሠልጣኝ ሲመረጡ፣ በአሠልጣኝነት ወ/ት ዘውዴ ኃይለ ማርያምና አቶ ሀብታሙ ግርማ ሆነዋል፡፡ ለወጣቱ ቡድን አቶ ስንታየሁ ካሳሁን ዋና፣ አቶ አብርሃ ኃይለ ማርያም ምክትል ዋና አሠልጣኝ ሲሆኑ፣ አቶ ፈጠነ ታደሰና አቶ ንጉሤ ደምሴ አሠልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ለውርወራ አቶ ቤተሳይዳ ተሾመ ዋና ሲሆኑ ወ/ት ዝናሽ ታከለ በምክትል አሠልጣኝነት ተመርጠዋል፡፡ ለዝላይ አቶ ለማ ደበሌ ዋና ሲሆኑ፣ አቶ ጋሻው በዛለማ በምክትል አሠልጣኝነት ተመድበዋል፡፡