Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአንድ ሚሊዮን ዶላር የሚቋቋሙት የእርሻ አገልግሎት ማዕከላት

በአንድ ሚሊዮን ዶላር የሚቋቋሙት የእርሻ አገልግሎት ማዕከላት

ቀን:

በግብርናው ዘርፍ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችሉ ስልቶችን ከሚነድፉ ተቋማት አንዱ የሆነው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች በተለያዩ ግብአቶች እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ፕሮጀክቶች ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

የአርሶ አደሮችን ምርታማነት በማሳደግ ገቢን ለማሻሻልና በግሉ ዘርፍና በመንግሥታዊ ተቋማት የጋራ ትብብር አማካይነት ለማከናወን የሚረዱ የእርሻ አገልግሎት ማዕከላትን ለማቋቋም አዲስ ፕሮጀክት ዘርግቷል፡፡

ለዚህም ኤጀንሲው በአራት ክልሎች ከሚገኙ ሃያ የግብርና ማኅበራትና ኢንተርፕራይዞች ጋር የእርሻ አገልግሎት ማዕከላትን ለማቋቋም የሚያስችላቸውን የአንድ ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነትን ታኅሣሥ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡

በተደረገው ስምምነት መሠረት፣ የግል ድርጅቶቹና የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖች፣ በኦሮሚያ ሰባት፣ በአማራ ስድስት፣ በትግራይ አራት፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሦስት ወረዳዎች ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዕከላትን ይገነባሉ፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን እያንዳንዳቸው 50 ሺሕ ዶላር ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ድጋፉን ከሚያገኙት መካከል አሥሩ የግል ድርጅቶች ሲሆኑ፣ የቀሩት ደግሞ ዩኒየኖች ናቸው፡፡

ድጋፉን የሚያደርገው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ደግሞ ለማዕከላቱ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

የሚቋቋሙት ማዕከላት የሥራ ድርሻ በአቅራቢያቸው ለሚገኙ አነስተኛ አቅም ላላቸው አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ዝርያዎች፣ ኬሚካሎች፣ የእርሻ መሣሪያዎች፣ የእንስሳት መድኃኒቶችና ልዩ ልዩ የእርሻ መገልገያዎችን የአርሶ አደሩን አቅም ባገናዘበ መልኩ በሽያጭ ያቀርባሉ፣ የምክርና የሥልጠና አገልግሎትም ይሰጣሉ፡፡

ድርጅቶቹና ዩኒየኖቹ ይህን ዕድል ያገኙት ፊድ ዘ ፊውቸር ኮመርሻል ፋርም ሰርቪስ ፕሮጀክት ያወጣውን መመዘኛ ከሌሎች 266 መሰል ተቋማት ጋር ተወዳድረው በማለፋቸው ነው፡፡

በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የፊድ ዘ ፊውቸር ኮመርሻል ፋርም ሰርቪስ ፕሮጀክት ቡድን መሪ አቶ ግዛቸው ሲሳይ ባደረጉት ገለፃ፣ የፕሮጀክቱ የቆይታ ጊዜ ከ2007 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ሲሆን፣ ጠቅላላ በጀቱም ሰባት ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ አራት ሚሊዮን ዶላር የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ሲሆን፣ የቀረው ሦስት ሚሊዮን ዶላር የሚሸፈነው ደግሞ በዩኤስኤይድ ካልቲቬቲንግ ኒው ፎርንቲርስ ኢን አግሪካልቸር (ሲኤንኤፍኤ) የተባለው ተቋም ነው፡፡

በሲኤንኤፍኤ የፕሮጀክቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዋቅቶላ ዋቅጅራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተጠቀሱት ማዕከላት አማካይነት ወደ 100 ሺሕ የሚጠጉ አባወራዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ፕሮጀክቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ስድስት ማዕከላትን በሙከራ ደረጃ አቋቁሞ ጥሩ ውጤቶችን እንዳገኘ ተናግረዋል፡፡ ከ30 ሺሕ በላይ የሚሆኑ አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግና 50 አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ከውጤቶቹ ይጠቀሳሉ፡፡

የዚህን ስኬት በማየት በተጠቀሱት አራት ክልሎች ተመሳሳይ ማዕከላትን ለማቋቋም እንደተቻለና በዚህም ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ያሉት የእርሻ ማዕከላት ወደ 26 ከፍ ማለታቸውን ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቀደም ሲል ከተቋቋሙት ስድስት ማዕከላት መካከል አራቱ ‹‹ኤጋ›› በሚል መጠሪያ አግሪካልቸራል ኢምፑት ሰፕላይስ ፒኤልሲ የሚል ኩባንያ አዲስ አበባ ላይ አቋቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በክልሎቹ ንግድ ተኮር የሆኑ 20 የእርሻ አገልግሎት ማዕከላትን ማቋቋምና የኤጋ አግሪካልቸር ሰፕላይ ፒኤልሲን ዘላቂ፣ ትርፋማና ገበያ ተኮር ማድረግ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...