ከታኅሳስ 13 እስከ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በደሴ ከተማ በወሎ ዩኒቨርሲቲና በከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂክ ማዕከል በጋራ የተዘጋጀው ሁለተኛው አገር አቀፍ ምሥለ ፍርድ ቤት ውድድር በወሎ ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ውድድሩ የሰፋፊ እርሻዎች ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተስፋዎችንና ተግዳሮቶችን ዋነኛ ጭብጥ ያደረገ ሲሆን፣ የፍሬ ነገር ማብራሪያው በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል በካሩቱሪ ኩባንያ ከተከሰተው ውዝግብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
ምሥለ ፍርድ ቤት (Moot Court) ከሕግ ትምህርት ቤቶች የማስተማሪያ ቁልፍ ሥልቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ሥልት በእውነተኛው ፍርድ ቤት የሚከናወኑ ሥነ ሥርዓቶችን በማስመሰል በአንድ አከራካሪ የሕግ ጉዳይ ላይ የሕግ ተማሪዎች የከሳሽና የተከሳሽ ጠበቆች በመሆን ለግራ ቀኙ የጽሑፍ አቤቱታ አዘጋጅተው ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት የሚያቀርቡበት፣ በጽሑፍ ያቀረቡትን አቤቱታ በዚሁ ፍርድ ቤት ቀርበው የቃል ክርክር የሚያደርጉበትና የክርክር ክህሎታቸውን በጉዳዩ ላይ ለመከራከሪያነት መነሳት ባለባቸው ሕጎች ደጋፊነትና በፍሬ ነገር አመክንዮዎች የሚያዳብሩበት ሥርዓት ነው፡፡
በዘንድሮው ውድድር ተማሪዎች በአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ለማስፋፋት መንግሥት የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን የመሬት ይዞታ በመውሰድ ለኢንቨስተሮች በሚሰጥበት ወቅት፣ መንግሥት ከመሬቱ ለሚፈናቀሉ ዜጎች ስለሚሰጠው ካሳ፣ የካሳ ዓይነቶች፣ በኢንቨስትመንቱ በአካባቢ ሥነ ምኅዳር ላይ ስለሚደረግ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ፣ የኢንቨስትመንት ሥራው ከተጀመረ በኋላ ስለሚመጡ አሉታዊ ውጤቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ሕጎች በማጣቀሻነት በማንሳት እየተካሄዱ ባሉ ኢንቨስትመንቶች ሳቢያ ተጎዳን የሚሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በአመልካችነት በመወከል ኢንቨስትመንቱ ሊቆም ይገባል፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በሕግ አግባብ አልተከናወነም፣ ኢንቨስትመንቱ ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ በመሆኑ ኢንቨስተሩ የኢንቨስትመንት ፈቃዱ ሊሰረዝ ይገባል፣ ኢንቨስተሩ ለደረሰው ጉዳት ተገቢውን የጉዳትና የአካባቢ ማገገሚያ ካሳ ሊከፍል ይገባል የሚሉ ክርክሮች ቀርበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሰጠውን የመንግሥት አካልና ኢንቨስተሩን በተጠሪነት የወከሉ ተማሪዎች፣ ኢንቨስትመንቱ ተገቢውን የሕግ አግባብ ተከትሎ የተከናወነ መሆኑን፣ ተፈናቃዮች ተገቢው ካሳ የተከፈላቸው መሆኑንና ኢንቨስትመንቱ ያመጣቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች መጠነኛና የተገመቱ መሆናቸውን በማንሳት ተከራክረዋል፡፡ ተወዳዳሪ ዩኒቨርሲቲዎች በአመልካችነትና በመልስ ሰጪነት ክርክራቸውን ያደረጉ ሲሆን፣ ለፍፃሜው ባህር ዳርና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ደርሰዋል፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኤሊያስ ክብረትና በአዳም ደነቀው ሲወከል፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በምንሊክ ዓለማሁና በፍቅርተ ሽፈራው ተወክሏል፡፡
በአጠቃላይ በማጣሪያው 14 ዩኒቨርሲቲዎች የተወዳደሩ ሲሆን፣ የጽሑፍ ማጣሪያውን በማለፍ ለቃል ክርክር የቀረቡት ሰመራ፣ ድሬዳዋ፣ ሐሮማያ፣ አርባ ምንጭ፣ ባህር ዳር፣ ወሎ፣ ሚዛን-ቴፒና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ በቃል ክርክሩ ወደ ሁለተኛ ዙር ማለፍ የቻሉት ደግሞ ሐዋሳ፣ ሐሮማያ፣ ባህር ዳርና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ፡፡
በደሴ ከተማ ሩቅያ አዳራሽ በተካሄው የፍፃሜ ውድድር ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቃሬ ጨዊቻ የመሬት ሀብትን በዘላቂነት ለመጠቀምና በሕግጋቱ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር የአፈጻጸሙን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲዎች የጎላ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹በተለይ የሕግ ትምህርት የሚሰጡ ተቋማት ተማሪዎቻቸው በተግባር ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአካባቢ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ማስቻሉንና ሕዝባችንም ሒደቱን በመመርመር ግንዛቤውን እንዲያሳድግ ዕድል መፍጠሩን ሚኒስቴራችን የሚደግፈው ነው፤›› ብለዋል፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ሰለሞን በላይነህ ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በርካታ አካላትና ግለሰቦች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በውድድሩ በዳኝነት የሚሳተፉ የሕግ ባለሙያዎችን ለመመልመል ከፍተኛ ጥረት መደረጉንና በዚህም የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የዶ/ር አባተ ጌታሁን ሚና ከፍተኛ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በውድድሩ በዳኝነት የተሳተፉት የሕግ ባለሙያዎች የክልልና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ተመራማሪዎችና የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕግ አማካሪዎችና ኃላፊዎች፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ነበሩ፡፡
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ምሥለ ፍርድ ቤት ውድድሮችን የተለያዩ የትምህርት ተቋማት በማዘጋጀት የተወሳሰበውን የፍርድ ቤት ሥርዓት ቀለል ባለ መልኩ ለማስተማር ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ይሁንና ከባፈው ዓመት ጀምሮ ውድድሩ አገር አቀፍ መልክ ይዞ በቋሚነት መካሄድ ጀምሯል፡፡
ውድድሩ በቋሚነት መካሄድ የጀመረው የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ለማዘጋጀት በመወሰኑ ነው፡፡ በማዕከሉ የሕግ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪና ተመራማሪ አቶ ሰይድ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ከኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ (ኮንሶርትየም) የምሥለ ፍርድ ቤት ውድድር በቋሚነት እንዲካሄድ በቀረበው ሐሳብ ማዕከሉ በመስማማትና ድጋፍ በማድረግ ውድድሩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ መካሄድ ጀምሯል፡፡ ውድድሩ በገለልተኛ አካል እንዲመራ በቀረበው ሐሳብም ከአዘጋጅ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪ ሁለት ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፋሉ፡፡ በዚህም መሠረት በዘንድሮው ውድድር ከአዘጋጁ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ባህር ዳርና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ከማዕከሉ ጋር በአመራርነት ተሳትፈዋል፡፡ አባላቱ የሚመረጡት በሕግ ትምህርት ቤቶች ኮንሶርትየም እንደሆነ አቶ ሰይድ ገልጸዋል፡፡
አገር አቀፍ ምሥለ ፍርድ ቤት ውድድር ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄድ የጀመረው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከግንቦት 16 እስከ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በወልቂጤ ከተማ ሲካሄድ ነው፡፡ ከማዕከሉ ጋር በመተባበር በተካሄደው ይህ ውድድር ለፍፃሜ ወልቂጤና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ደርሰው በአዘጋጁ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በቃል ክርክሩ ዲላ፣ ድሬዳዋ፣ ሐሮማያ፣ ሐዋሳ፣ ደብረ ብርሃን፣ ባህር ዳር፣ ወልቂጤና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል፡፡ የውድድሩም ጭብጥ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሬት ማስለቀቅና የህዳጣን መብት ነበር፡፡