Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየስዊፍት ሚዲያ መስኮት

የስዊፍት ሚዲያ መስኮት

ቀን:

22 የሚገኘው ጎላጉል መገበበያ ሕንፃ በሸማቾችና ሻጮች ፈጣን እንቅስቃሴ ተሞልቷል፡፡ ወደ ሕንፃው ከሚገቡ ሰዎች አንዳንዶቹ ፍጥነታቸውን ገታ እያደረጉ በሩ ጋር ያለውን ረዘም ያለ ሳጥን የሚሆኑ መሰል የኤሌክትሮኒክስ ቁስ ይመለከታሉ፡፡ የኤሌክትሮኒክሱ የላይኛው ክፍል ላይ ባለው ስክሪን የፊልም ትሪለር (እንደ ማስታወቂያ የሚሆን የፊልም ቅንጭብጫቢ) ይታያል፡፡ አጠገቡ አንድ ወጣት ቆሞ ስለ ኤሌክትሮኒክሱ አጠቃቀም መረጃ ይሰጣል፡፡

ስዊፍት ሚዲያ ይባላል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ፊልሞችን፣ መጻሕፍትንና ሙዚቃ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርብ ዲጂታል ኪዮስክ ነው፡፡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከሦስት ወራት በፊት ሲሆን፣ ከጎላጉል ሕንፃ በተጨማሪ ቦሌ አካባቢ በብርሃኔ አደሬ ሕንፃ፣ መገናኛ አካባቢ በመተባበር ሕንፃ፣ ገርጂ አካባቢ በኦልማርት ሱፐርማርኬትና አቢሲኒያ ሕንፃ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያ ተጠቃሚዎች የ25፣ የ50 ወይም የ100 ብር ካርድ ይገዛሉ፡፡ ከዚያም መለያ ቁጥር ይሰጣቸውና ካርዳቸው እስኪያልቅ የሚፈልጉትን ፊልም፣ መጽሐፍ ወይም ሙዚቃ ከማሽኑ ገዝተው በሐርድ ዲስክ፣ በፍላሽ ወይም በሜሞሪ ካርድ ይወስዳሉ፡፡

በፊልሙ ዘርፍ ተከታታይ፣ ዘጋቢ እንዲሁም ፊቸር ፊልሞች ማግኘት ይቻላል፡፡ ፊቸርና ዘጋቢ ፊልም በሦስት ብር ይሸጣል፡፡ ተከታታይ ፊልሞች ደግሞ አንድ ኤፒሶድ (ክፍል) በአንድ ብር ይሸጣል፡፡ ፊልሞቹ እ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ እስከ 2016 ለዕይታ የበቁ ናቸው፡፡ አንድ ሙዚቃ በ50 ሳንቲምና የሙዚቃ ቪዲዮ በአንድ ብር መግዛት ይቻላል፡፡

በጎላጉል ሕንፃ ስለ ኪዮስኩ እያስረዳና መገልገል ለሚፈልጉ ሰዎች እገዛ እያደረገ ያገኘነው አብዱልራህማን ሬድዋን ይባላል፡፡ ዘወትር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ኪዮስኩ እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ ‹‹ሰዎች ካርድ  ገዝተው እስከሚያልቅ የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ ብዙዎች ተከታታይ ፊልሞችና ሙዚቃ ይገዛሉ፤›› ይላል፡፡

እንደ ‹‹ኢምፓየር›› እና ‹‹ጌም ኦፍ ትሮንስ›› ያሉ ተከታታይ ፊልሞች በርካታ ተመልካች አላቸው፡፡ በኪዮስኩ ቀደም ካሉት ‹‹ዘ ፍሬሽ ፕሪንስ ኦፍ ቤል ኤር›› ፊልም እስከ ቅርብ ጊዜዎቹ ‹‹ዘ ቢግ ባንግ ቲዮሪ›› እና ‹‹ናርኮስ››ን ማግኘት ይቻላል፡፡ ፊልሞችን በርዕስ፣ በተዋንያንና በአዘጋጆች ስም መፈለግ ይቻላል፡፡ በአስቂኝ፣ የፍቅር፣ እውነተኛ ታሪክና ሌሎችም የፊልም ዓይነቶች ዝርዝር ውስጥም ፊልሞች ይገኛሉ፡፡

በኪዮስኩ ልብ ወለድና ኢልብወለድ መጻሕፍትም ይገኛሉ፡፡ በኢልብወለድ ዘርፍ የሥነ ልቦና፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖትና በሌሎችም ዘውጎች መጻሕፍት አሉ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጸሐፍት የተዘጋጁ የታሪክ መጻሕፍትም መግዛት ይቻላል፡፡  ሂፕ ሃፕ፣ አር ኤንድ ቢ፣ ሮክ ኤንድ ሮልና ሌሎችም የሙዚቃ ዓይነቶች ቀርበዋል፡፡ በቢልቦርድ ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ሙዚቃዎች ስብስብም አለ፡፡ የአዴል፣ ቢዮንሴ፣ ኬንድሪክ ለማር፣ ፒ ስኩዌር እንዲሁም የሌሎችም አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን አልበም በኦዲዮና ቪዲዮ ይሸጣል፡፡ በሙዚቃው ዘርፍ፣ ብዙዎች የተለያዩ አፍሪካ አገሮችን ሙዚቃዎች አዘውትረው እንደሚገዙ አብዱልራህማን ይናገራል፡፡ ከሥራ ሰዓት በኋላ ፊልም፣ ሙዚቃና መጻሕፍት የሚገዙ ሰዎች እንደሚበራከቱም ያክላል፡፡

ኩሩቤል ጌታቸው የስዊፍት ሚዲያን ሶፍትዌር ከሠሩ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ሶፍትዌሩን መሥራት የጀመሩት ከአምስት ወር በፊት እንደነበር ይናገራል፡፡ ዲጂታል ኪዮስኩን ከውጪ አስመጥተው በመገበያያ ሕንፃዎች ቦታ ተከራይተው ለመሥራት ፍቃድ አወጡና ሥራ ጀመሩ፡፡ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ ያለባቸው አምስት መገበያያ ሕንፃዎችን እንደመረጡ ይገልጻል፡፡ በቀጣይም በርካታ ሰዎች በሚገለገሉባቸው ሕንፃዎች ቅርንጫፍ የመክፈት ዕቅድ አላቸው፡፡

ኪሩቤል እንደሚናገረው፣ ሶፍትዌሩን ያዘጋጁት ባለሙያዎች ዓላማቸው ሰዎች የሚፈልጉትን ፊልምም ይሁን ሙዚቃ በቀላሉና ከብዙ አማራጭ ጋር የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ ተከታታይ ፊልሞች ለማግኘት ቪዲዮ ቤቶች ድረስ ከመሄድ፣ ከሥራ በኋላ ከመገበያያ ሕንፃዎች መግዛት ይቻላል፡፡ አሁን ከቀረቡት አማራጮች በተጨማሪ በቅርቡ ሶፍትዌሮች፣ የልጆች መዝናኛ መርሐ ግብሮች፣ ጌሞች፣ ኦዲዮ ቡክስ (በድምፅ የተቀዱ መጻሕፍት) እና አፕልኬሽኖችንም መሸጥ ይጀምራሉ፡፡

ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ የተገልጋዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይናገራል፡፡ በቀን በአማካይ 40 ሰዎች ከአምስቱ ኪዮስኮች በአንዱ የሚሸምቱ ሲሆን፣ የበለጠ ሲለመድ ደግሞ የተጠቃሚዎች ቁጥር እንደሚበራከት ያምናል፡፡ ብዙ ሰው ስለ አገልግሎቱ እስኪገነዘብ ድረስም በየመገበያያ ሕንፃው አጠቃቀሙን የሚያብራሩ ባለሙያዎች ይኖራሉ፡፡

አሠራሩን በማሻሻል ሰዎች ያለ ባለሙያ ዕርዳታ በማሽኑ እንዲጠቀሙ የማስቻል ሐሳብ እንዳላቸውም ይገልጻል፡፡ ‹‹ሰዎች ካርዱን ከሻጮች ከሚገዙ፣ በቀጥታ ገንዘቡን ወደ ማሽኑ አስገብተው የካርድ ቁጥራቸው ከማሽኑ ወደ ሞባይላቸው ተልኮላቸው የሚጠቀሙበት አሠራር የመዘርጋት ሐሳብ አለን፤›› ይላል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጪ የሚሠሩ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችንና መጻሕፍትን የአገር ውስጥ  ሥርጭት የሚመራ ደንብ ባለመኖሩ ዳውንሎድ ማድረግ የሚችሉትን መረጃ ባጠቃላይ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ኪሩቤል እንደሚለው፣ የአገር ውስጥ ፊልሞች፣ ሙዚቃና መጻሕፍትም የመሸጥ ሐሳብ ያላቸው ሲሆን፣ በቅድሚያ ከሥራዎቹ ባለቤቶች ጋር መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

ኪዮስኮቹን የሚጠቀሙ ሰዎች ቆመው መጠበቅን የመሰሉ ምቾት የሚነሱ ችግሮች ቢኖሩም፣ የፊልም ትሪለርና የመጻሕፍት ሲኖፕሲስ (አጠር ያለ የመጽሐፍ ይዘት ማብራሪያ) በማቅረብ ሰዎች የሚፈልጉትን እንዲመርጡ ማስቻላቸው ለተጠቃሚዎች መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ይላል፡፡ የኦዲዮ መጻሕፍት በተለይ  ለዓይነ ሥውራንና በጉዞ ላይ ሆነው መጻሕፍት ለሚያዳምጡ ሰዎች ይሆናሉ፡፡

አሁን በመገበያያ ሕንፃዎች ብቻ የተገደቡት በሌሎች የንግድ ተቋሞች ኪዮስኮችን አስገብቶ ለመነገድ ሕጉ ስለማይፈቅድ እንደሆነ ገልጾ፣ ሰዎች በምግብ ቤት ወይም በማንኛውም ቦታ ሆነው ማሽኑ ካለበት ቦታ በኔትወርክ አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመተግበር ማሰባቸውን ይናገራል፡፡

በሌሎች አገሮች ካለው ተሞክሮ የሬድቦክስ ኪዮስክ ይጠቀሳል፡፡ ሬድቦክስ እስከ 2012 ድረስ በምግብ ቤቶች፣ በመጠጥ ቤቶችና በሌሎችም መገበያያ ቦታዎች ከ42,000 በላይ ኪዮስኮች ነበሩት፡፡ ከጊዜ በኋላ በየሰዎች ቤት ባለው የኢንተርኔት አገልግሎት በቀጥታ ስትሪም የሚያደርገው ኔትፍሌክስ፣ የሬድቦክስን ገበያ መቀናቀን ጀመረ፡፡ በኢትዮጵያ ባለው ውስን የኢንተርኔት ዝርጋታ ተመሳሳይ የስትሪሚንግ አገልግሎት ባለመኖሩ ስዊፍት ሚዲያ ጥሩ አማራጭ እንደሚሆን ኪሩቤል ያምናል፡፡

ኃይለልዑል አባተ በስዊፍት ሚዲያ የተጠቀመው ከ15 ቀን በፊት ነበር፡፡ ከአንድ ወር በፊት ኪዮስኩን በብርሃኔ አደሬ ሕንፃ ሲያየው ምን እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ጎላጉል ሕንፃ ውስጥ በድጋሚ ሲያየው ምን እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ተከታታይ ፊልሞች የሚወደው ኃይለልዑል፣ ለሙከራ ብሎ በገዛው የ25 ብር ካርድ ፊልም መግዛቱን ይናገራል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ፒያሳ፣ 22 እና ቦሌ አካባቢ አንድ ኤፒሶድ በአንድ ብርና ፊቸር ፊልም በሦስት ብር የሚሸጡ ደንበኞች ነበሩኝ፡፡ ይህኛውም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል፤›› ይላል፡፡

በፊልም አቅርቦት ረገድ ከቪዲዮ ቤቶች ተጨማሪ አማራጭ መምጣቱ ጥሩ ነው ይላል፡፡ ቢሆንም ፊልሞችና ሙዚቃ ለማግኘት ቀላል እንደሆነና እሱ የበለጠ መጠቀም የሚፈልገው በመጻሕፍት አቅርቦቱ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በፊልምና ሙዚቃ ጥሩ ስብስብ ቢኖራቸውም የመጻሕፍት ክምችታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም ያክላል፡፡

በየሠፈሩ ፊልሞችና ሙዚቃ የሚሸጡ ቪዲዮ ቤቶች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡ መጻሕፍት፣ አፕልኬሽን፣ ሶፍትዌር፣ ጌምና የልጆች መርሐ ግብሮችን አጣምሮ በመያዝ ስዊፍት ሚዲያ አማራጭ አቅርቧል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...