Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲፈጸም ማሳሰቢያ ተሰጠ

የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲፈጸም ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያስቀመጠችው ስትራቴጂ ትርጉም ባለው ደረጃ ለመፈጸም፣ በትኩረት መሥራትና የተሠራውንም በማስረጃ ጭምር እያሳዩ፣ የመሪነት ጉዞዋን እያሳደገች እንድትሄድ ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

በ2017 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ2025) መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ራዕይ ሰንቃ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያ፣ በተለይ አረንጓዴ ልማት ለሕዝቧ የህልውናና የኑሮ መሠረት በመሆኑ፣ እየተሠራ ያለው ሥራ ዓለም ጭምር በሞዴልነት እየወሰደና እየሠራበት እንደሚገኝ፣ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶ/ር ገመዶ ዳሌ ተናግረዋል፡፡

በፍጥነት ለማደግ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ፣ የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች ሳይዛነፉ የተሻለ ጥቅም እንዲሰጡ አድርጎ፣ ቀጣይነት ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀምን ዕውን ማድረግ ትልቅ ፈተና መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ታኅሣሥ 10 እና 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዳማ ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ ዶ/ር ገመዶ እንደተናገሩት፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች እንዳይዛነፉ ለማድረግና የተሻሉ ጥቅሞችን እንዲሰጡ፣ አመጣጥኖና ጠብቆ ለመሄድ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው፡፡

ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ከውጭ በማስገባት፣ በማለማመድና ጥቅም ላይ በማዋል፣ የአገር ውስጥ አቅምን ገንብቶ ቴክኖሎጂን በአገር ደረጃ የማፍለቅ አቅም ግንባታ ሥራ ለመሥራት፣ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ክፍተቶችን የመለየት መርሐ ግብር አውጥቶ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ገመዶ አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ ያሉትን ቴክኖሎጂዎች በማሰራጨት በኩል ተመራማሪዎች የሚያነሱት ነጥብ መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በምርምር የተገኙ ቴክኖሎጂዎች በጥቅም ላይ ሳይውሉ ወይም ለተጠቃሚው ሳይደርስ በመደርደሪያ ላይ እንደሚቀሩ ጠቁመዋል፡፡

የውይይት መድረኩ በዋናነት የተዘጋጀው ተመራማሪዎች በምርምር ያገኙት ቴክኖሎጂ በመደርደሪያ ላይ ለምን እንደሚቀር፣ ችግሩ ከተመራማሪው ነው ወይስ ከተጠቃሚው? የሚለውን ተወያይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ሊሆን የሚችለው ተመራማሪው ቴክኖሎጂውን ለተጠቃሚው በሚገባው ሁኔታና ደረጃ እያመረተ ስለመሆኑና ተጠቃሚውም ቴክኖሎጂውን መውሰድ ያቃተው በምን ምክንያት እንደሆነ አለመታወቁ እንደሚሆንም ግምታቸውን አክለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ሌላው ትኩረት የሚደረግበት ‹‹ቴክኖሎጂው እየመነጨ ያለው ለተጠቃሚው መልስ በሚሰጥ ሁኔታ ነው?›› የሚለው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የቴክኖሎጂ ስርጭት፣ አጠቃቀምና ክፍተቶችን በሚሞላ አኳኋን የተከተለ አሠራርና ግብ ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ተመራማሪዎች ችግሮችን ሲለዩ፣ ችግሩ የማንን ፍላጎት መሙላት እንዳለበት አውቀው መሥራት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የምርምር ተቋማት የሚተዳደሩት በመንግሥት በጀት ከመሆኑ አንፃር፣ የምርምር አሠራሮች በሚቀርቡበት ጊዜ፣ አሠራሩ ተገምግሞ ‹‹ማለፍ አለበት ወይስ የለበትም? የሚለው ከጥራት ደረጃውና ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር መመዘን እንዳለበት ዶ/ር ገመዶ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ተመራማሪዎች በየጊዜው ቴክኖሎጂዎች ሠርተው ሲያቀርቡ፣ ደረጃቸውን በጠበቁና ከወረቀት ላይ ከማስቀመጥ ባሻገር፣ አጠር ባለና በቀላሉ አገላለጽ የተቀመጠ ምክረ ሐሳብ ለተጠቃሚዎች በሚመጥንና እነሱን ማዕከል ባደረገ አግባብ እንዲያቀርቡ የሚያበረታታ መሆኑንም ሚኒስትሩ አሳውቀዋል፡፡ ተመራማሪው በየምርምር ተቋማቱ የተሠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወስዶና አደራጅቶ፣ የቀረውን በመለየት የመመራመር ሥራ መሥራት እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ክፍተቶች እንዳይደገሙና ለተጠቃሚው በቀጥታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ የምርምር ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

የአገር ውስጥ ተመራማሪዎች በሠሯቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተመረቱ ምርቶች እያሉ፣ ከውጭ አገር ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ፣ ተመራማሪው ለተሻለ ምርምር እንዳይነሳ እንቅፋት እንደሆኑበት ከተመራማሪዎቹ አስተያየት ተሰጥቶ፣ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በምርምር የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተመረተ ምርት አገር ውስጥ እያለ ከውጭ የሚገባው ምርት ያን ያህል ሰፊ ነው ብሎ መውሰድ ያስቸግራል›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ አገር ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር ‹‹እየሠራን ነው?›› የሚለው በጥናት መረጋገጥ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት የሚቻል ከሆነና የሕዝቡን ፍላጎት ሊመልስ የሚችል ምርት በአገሪቱ ካለ በትክክል ተረጋግጦ ማስተካከል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ በአገር ውስጥ ምርት ራስን መቻል የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረቱም በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ከመደገፍና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ከማድረግ አንፃር፣ ከሚመለከታቸው አካላት በመነጋገር በቀጣይ የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ተቋማት አንዱ የሆነው የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ውባለም ታደሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በምርምር የተገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ መሆናቸውንና ለኅብረተሰቡም በሚገባ መተዋወቃቸውን መፈተሽና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የእንጨት ኢንዱስትሪ ከውጭ በማስገባት በተደረገው ምርምር ብዙ ውጤት መገኘቱን የገለጹት ዶ/ር ውባለም፣ ከ60 በላይ አገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን አጥንተው ወደ እንጨት ኢንዱስትሪው እንዲገባ መደረጉን አክለዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የሶሺዎ ኢኮኖሚክስ፣ የፖሊሲና የኤክስቴንሽን የሥርዓተ ፆታ ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ዓለማየሁ ነጋሳ እንዳብራሩት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ፣ በደን ልማት፣ አየር ንብረት ለውጥና ከባቢ አየር ላይ ያተኮሩ መርሐ ግብሮች ውጤታማ ናቸው፡፡ አገሪቱ በቀጣዩ ዓመታት ለማሳካት ያስቀመጠችውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ለመገንባት በዘርፉ ራሱን የቻለ የልማት ሠራተኛ ኤክስቴንሽን ኤጀንት፣ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ማሰማራት ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...