Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹በጎነት ይከፍላል!››

‹‹በጎነት ይከፍላል!››

ቀን:

በኢትዮጵያ 12 ሚሊዮን ያህል ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከአራት ሚሊዮን በላይ ወላጅ ያጡ እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ሕፃናት በድርቁ ምክንያት ለጤና እና ለከፋ የሥነ ምግብ ዕጥረት እንደሚዳረጉ አስፍሮ ነበር፡፡ የሕፃናትና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ለችግር የተጋለጡት አገሪቱ ሕፃናት ቁጥር ሦስት ሚሊዮን እንደሆኑ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡

ሕፃናት ‹‹ፈልገው . . . ይሁነኝ ብለው . . .›› ወደዚህ ምድር ባይመጡም ወላጆቻቸው በመሞታቸው ምክንያት፣ አሊያም በተለያየ የኑሮ ችግርና ውጣ ውረድ መንገድ ላይ የሚጣሉት ሕፃናት ቁጥራቸው ከፍተኛ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ ያለው ሌላው ችግር ደግሞ ያለዕድሜያቸው፣ ሳያስቡና ሳይፈልጉ በማርገዛቸው፣ ተደፍረውና በሌላም ማኅበራዊ ቀውስ ሳቢያ ወልደው የሚጥሉ ልጃገረዶች ቁጥር እየተስፋፋ መምጣት ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ እስከ አንደኛ ደረጃ ባለው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ልጃገረዶች ላልተፈለገ ወሲባዊ ግንኙነት ተጋላጭ እየሆኑ በመምጣታቸው ምክንያት የማርገዝ ዕድላቸውም በዚያው መጠን ሰፊ እየሆነ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡  

ይሁንና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሰለባ እየሆኑ ያሉትን እነዚህን ለመታደግ የሚጣጣሩ የተወሰኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ቢኖሩም፣ በየጊዜው እየተበራከተ የመጣው ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት ቁጥር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን ብቻም ሳይሆን ኅብረተሰባዊ ተረባርቦሽ እንደሚጠይቅ ዕሙን ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በአገሪቱ ውስጥ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተዳረጉ ሕፃናትን በመንከባከብ ሥራ ላይ ለመሠማራት ፈቃድ የተሰጣቸው 46  ተቋማት እንዳሉ ነው፡፡ በጥንትም ቢሆን በጉዲፈቻ ሕፃናትን የማሳደግ ልማድ በኢትዮጵያ ቢኖርም፣ በበጎ ፈቃደኛነት መርዳትና ድጋፍ መስጠት ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የተዳከመ ሆኖ ይታያል፡፡ ከኅብረተሰቡ የሚያገኙት ደካማ ድጋፍ፣ የራሳቸው የአሠራር ችግርም ታክሎበት በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በመዘጋት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአብዛኞቹ ችግር በተለይ ለሚንቀሳቀሱበት የበጎ አድራጎት ሥራ የገንዘብም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ማግኘት ማነቆ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይሁንና ከ70 እስከ 80 ከመቶ የፋይናንስና መሰል ድጋፎችን ከውጭ የሚያገኙ እነዚህ ድርጅቶች ከውጭ ይልቅ በአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች፣ በበጎ አድራጊዎች ድጋፍና በድርጅቶች ልገሳ ለመተዳደር ፈተና እንደሆነባቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወላጆች የሌሏቸውን ጨምሮ ለተለያየ ችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ከሚያሳድጉ ድርጅቶች አንዱ ‹‹ስለ እናት ማኅበር›› የተባለው ተቋም ነው፡፡

ይኼ ተቋም ከተመሠረተ 14 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በጊዜያዊ ማቆያ እየተንከባከበ ከሚያሳድጋቸው ለችግር የተጋለጡ 70 ሕፃናት ባሻገር፣ በየቤታቸው ሆነው ድጋፍና ክትትል የሚያደርግላቸው፣ ከወላጆቻቸው ጋር የሚኖሩ 202 ችግረኛ ሕፃናትም በማኅበሩ ጥላ ውስጥ እንደሚገኙ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡ 

ስለማኅበሩ ለመናገር ሰበብ የሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈሊጥ እየሆነ የመጣ ቁም ነገር በአንዳንድ ኩባንያዎች ሲተገበር መታየቱ ነው፡፡ ይኸውም አንከር የተባለውን የወተት ምርት በኢትዮጵያ የሚያሠራጨው ኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ ኢትዮጵያ የተባለው ኩባንያ ስለ እናት ማኅበር ለሚያሳድጋቸው 70 ሕፃናት ለየቀኑ ፍጆታቸው የሚውል የአንድ ዓመት የወተት ድጋፍ የሰጠበት አጋጣሚ ነው፡፡ ኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ ኢትዮጵያ፣ በአገሪቱ እንቅስቃሴ የጀመረበትን አንደኛ ዓመት፣ በመላው ዓለም ሲንቀሳቀስ 130 ዓመታት የቆየበትን ጊዜ አስታውሶ፣ በስለ እናት ማኅበር ጥላ ሥር የሚገኙ ሕፃናት በልዩ ልዩ አልሚ ንጥረ ነገሮች የበለፀገውን ወተት ለሕፃናቱ በልግስና ማቅረቡ ኩባንያው የድርሻውን ለመወጣት በማሰብ ያደረገው እንደሆነ የገለጹት የኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዜኮ ቃሲም ናቸው፡፡ የዚህ ኩባንያ ሌላኛው ሸሪክ ፋፋ ምግብ ማቀነባበሪያም ለሕፃናቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የፋፋና የሴሪፋም ምግብ ዕርዳታ ለግሷል፡፡

እንዲህ ያሉ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ድጋፎች ግን በዘላቂነት ስለማይቀርቡ በጎ አድራጎት ማኅበራቱንና ድርጅቶቹን ለውጭ ዕርዳታ እንዲዳረጉ ያስገድዳቸዋል ያሉት፣ የስለ እናት ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ኢተፋ ናቸው፡፡

እነኚህ ሕፃናት ተገቢውን ክብካቤ አግኝው እንዲያድጉ ለማድረግ ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች በሚሰጡት ድጋፍ ላይ ማኅበሩ እንደሚንተራስ የገለጹት አቶ ዘላለም፣ ከገንዘብና ከቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር ሕፃናቱን በመጎብኘት፣ አብረዋቸው ጊዜ የሚያሳልፉ በጎ ፈቃደኞች እንደልብ ማግኘትም ትልቅ ዕርዳታ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ‹‹አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት ለአንድ ጊዜ ከሚሰጠው አንድ ሚሊዮን ብር ይልቅ በርካቶች ተሰባስበውና አዋጥተው አንድ ሚሊዮን ብር ቢሰጡ ትልቅ ፋይዳ አለው፤›› ብለዋል፡፡

በተናጠል የሚሰጠው ድጋፍና ልገሳ እንዳለ ሆኖ ማኅበረሰቡ በያለበት የሥራ መስክ፣ ከሚሠራበት አካባቢ በቋሚነት ድጋፍ ለማድረግ የሚችልባቸው የበጎ ሥራ ድርሻዎች ቢፈጠሩ እንደ ተራራ የከበዱ ችግሮችን ቀስ በቀስ ማቃለል እንደሚቻል ይታመናል፡፡

አቶ ዘላለም እንደሚያብራሩትም ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት በአብዛኛው በአምስት ዋና ዋና መንገዶች ድጋፍ ቢያገኙም፣ በአገሪቱ ካለው የተንሰራፋ ችግር አኳያ አብዛኞቹ ሕፃናት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች የሚያጡት ድጋፍ እጅጉን አነስተኛውን ቁጥር የሚሸፍን እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ አንደኛው መንገድ ሕፃናቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዳሉ ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው (በአብዛኛው በእናቶቻቸው የሚያድጉት) ድጋፍ እንዲያገኙ የሚደረግበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በጊዜያዊ ማሳደጊያዎች የቆዩና ዕድሜያቸው እየጨመረ ያሉ ሕፃናት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል በቡድን እየሆኑ መኖር እንዲችሉ (ፎስተር ኬር) የሚደረግበት አሠራር ሁለተኛው  ነው፡፡ ለሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑና ለጎዳና የተጋለጡ ሕፃናትን መልሶ ወደ ወላጆችና አሳዳጊዎቻቸው እንዲቀላቀሉ ማድረግም ሌላው ተጠቃሽ ሥራ ነው፡፡ በጉዲፈቻ ለአገር ውስጥና ለውጭ አሳዳጊ ወላጆች መስጠትም ሌላኛው ሲሆን፣ በማሳደጊያ ማቆየት ደግሞ በመጨረሻ አማራጭነት ለሕፃናት ድጋፍ የሚሰጥበት አሠራር መሆኑን አቶ ዘላለም አብራርተዋል፡፡

ከመሠረቱ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነ ሕፃናትን የመንከባከብና የመርዳት ሥርዓት መኖሩ ዋናው ችግር እንደሆነ የሚያብራሩት አቶ ዘላለም፣ ከአገር ውስጥ ምንጮች የሚገኘው ድጋፍ በተለይ ከፋይናንስ ረገድ ከባድ እየሆነ ከመጣባቸው ምክንያቶች መካከል በሕዝቡ ዘንድ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ያለው አመለካከት አንዱ ነው፡፡ በአብዛኛው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ‹‹እንደ ሌባ›› መታየታቸው ጥሩ የሚሠሩት ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለውጦች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ስለ እናት ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለ23 ሕፃናት በአገር ውስጥ የጉዲፈቻ አሳዳጊዎችን ማግኘት መቻሉ የለውጡ መገለጫ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

‹‹ኅብረተሰብ አቀፍ እንቅስቃሴ መኖር አለበት፡፡ ከገንዘብ ባሻገር ልጆቹን በየጊዜው መጎብኘት፣ በአብሮነት ጊዜ ማሳለፍ ለልጆቹ ትልቅ ሰብዕና መገንባት ይረዳል፤›› ያሉት አቶ ዘላለም፣ በማሳደጊያ የቆዩ ሕፃናት ወጥተው ትልቅ ቦታ ላይ እንዲደርሱ ያግዛል ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ለችግር የሚዳረጉ ሕፃናትን ለመታደግ፣ በየጊዜው የሚጨምረውንም የተጎጂዎች ቁጥር ለመቀነስ በአገር ደረጃ ቢሠራበት መፍትሔ ነው የሚሉት በቤተሰብ ዕቅድ ላይ ቢሠራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቤተሰብ ዕቅድና ምጣኔ ላይ ብዙ መሥራት አለበት የሚሉት አቶ ዘላለም፣ ከዩኒቨርሲቲ እስከታች ትምህርት ቤቶች ያሉ ወጣቶች ሳይፈልጉ ከማርገዝና ወልደው ከመጣል እንዲቆጠቡ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችንም በመፍትሔነት ጠቁመዋል፡፡

ድርጅታቸው ከኅብረተሰቡና ከበጎ ፈቃደኞች ከሚያገኘው ድጋፍ በተጓዳኝ ሕፃናቱን በዘላቂነት ለመደጎም ሁለት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ለመተግበር ወዲያ ወዲህ እያለ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲን በማስፈቀድ ለመተግበር ካሰባቸው ፕሮጀክቶች አንደኛው፣ አሥር የወተት ላሞችን ገዝቶ በማርባት ከስድስት ወራት በላይ የሆናቸውን ሕፃናት ማጠጣት ሲሆን፣ ከፍጆታቸው የተረፈውን ለገበያ በማቅረብ ከሽያጩ ለሕፃናቱ አስፈላጊውን ለማሟላት መቻል ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር በቅርቡ ሳር ቤት አካባቢ፣ ቫቲካን ኤምባሲ ፊት ለፊት በተሰጠው የሕፃናት ማቆያ ግቢ ውስጥ ባለአራት ፎቅ ሕንፃ በመገንባት ለ400 እናቶች (በስፖንሰር ድጋፍ ለሚሰጣቸው) የተለያዩ ሥልጠናዎችና መሰል ድጋፎች የሚሰጥባቸውን ክፍሎች ጨምሮ ለልዩ ልዩ ተቋማት በኪራይ ገቢ የሚያስገኙ ክፍሎችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ደጓሚ ሥራዎችንም ለመሥራት የኅብረተሰቡ ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው ዘርፈ ብዙ ሕፃናትን ብቻም ሳይሆን አረጋውያንና ሴቶችን ሌሎችም በኑሮ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ክፍሎችን እጅጉን የሚፈታተን ሆኖ ይታያል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ስፍር አልባ ማኅበራዊ ቀውሶችን ለመቋቋም በብዙ አገሮች የተለያዩ ተሞክሮዎች ይታያሉ፡፡ ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል የማኅበራዊ ዋስትና ሥራዎች ናቸው፡፡ መንግሥት በዚህ መስክ በገጠር ከሚሠራው ባሻገር በከተማ የሚተገበር የሴፍቲኔት ፕሮግራም ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ኩባንያዎች በራሳቸው ተነሳሽነትና በጎነት ለሚያከናውኗቸው የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራት መስፋፋት የታክስ ዕፎይታ፣ የታክስ ተመላሽ ወይም ከሚከፍሉት ታክስ ላይ ታሳቢ የሚደረግ አሠራር ቢተገበር ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉንም ርብርቦሽና ባለድርሻነት ለማምጣት እንደሚያስችል የሚጠቁሙ ልምዶችም መታሰብ እንዳለባቸው ይመከራል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...