እስራኤል በዌስት ባንክና በምሥራቅ እየሩሳሌም የምታካሂደውን የሠፈራ ፕሮግራም ዓረቦች በተለይም ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሁም ፍልስጤማውያኑ ሲያወግዙትና ሲኮንኑት ከርመዋል፡፡ የእስራኤል የሠፈራ ፕሮግራም ከምዕራባውያኑም በአንዳንዶቹ በተለያየ ጊዜ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ሲነገር ከርሟል፡፡ ሆኖም አሜሪካ እስራኤልና ፍልስጤምን ለማስማማት በሚል በእስራኤል ጉዞ ሁሉ የቀኝ እጅ ሆና ትታወቃለች፡፡
በእስራኤል የሠፈራ ፕሮግራም በተለይም ፍልስጤም ዓለም ይፍረደኝ ስትልም እምብዛም የሰማት አልነበረም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዓመታዊ ጉባዔ በተካሄደ ቁጥር የዓረቦቹ አጀንዳ ቢሆንም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ከርሟል፡፡ ባለፈው ዓርብ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እስራኤል በዌስት ባንክና በምሥራቅ እየሩሳሌም የምታካሂደውን የሠፈራ ፕሮግራም በማውገዝ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ፣ አሜሪካ በድምፀ ተዓቅቦ ማለፏ እስራኤልን አስቆጥቷል፡፡
ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላት አሜሪካ እስራኤልን በተመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ ድምጿን እየተጠቀመች አጀንዳዎችን ስታስቀለብስ የእስራኤልን ፍላጎት ስታስጠብቅ የኖረች ቢሆንም፣ ይኼንን ጉዳይ አስመልክቶ በተካሄደው ጉባዔ፣ ድምፀ ተዓቅቦ በማድረጓ የውሳኔ ሐሳቡ በ14 ድምፅ ፀድቋል፡፡
የእስራኤል የሠፈራ ፕሮግራም ትክክል አለመሆኑን በማውገዝ የተላለፈውን የውሳኔ ሐሳብ ተከትሎም፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በውሳኔ ሐሳቡ ድምፃቸውን ከሰጡ የፀጥታ ምክር ቤት አባል አገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በገደብ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ከእስራኤል ጋር የንግድና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ካላቸውና በውሳኔ ሐሳቡ እስራኤልን ተቃውመው ድምፅ ከሰጡት እንግሊዝ ፈረንሣይ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ዩክሬን፣ አንጎላ፣ ግብፅ፣ ኡራጋይ፣ ስፔይን፣ ኒውዚላንድና ሴኔጋል ለጊዜው ከእስራኤል ጋር ያላቸው ግንኙነት በገደብ እንዲሆን ኔታንያሁ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
የእነዚህ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከኔታንያሁ ጋር ለጊዜው የማይገናኙ ሲሆን፣ ከአገሮቹ የተወከሉ አምባሳደሮችም በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት ወደ እነዚህ አገሮች የማይሄዱ ቢሆንም፣ በእነዚህ አገሮች የሚገኙ የእስራኤል አምባሳደሮች ከየአገሮቹ ባለሥልጣናት ጋር በሥራ መገናኘት ይችላሉ፡፡
ኔታንያሁ የወሰዱት ዕርምጃ ከብስጭታቸው የተነሳ እንደሆነ የዘገበው ሲኤንኤን፣ አያይዞም ውሳኔያቸው በእስራኤልም ሆነ በአገሮቹ የንግድ፣ የደኅንነትና ሌሎች ግንኙነቶችን እንደማያስተጓጉል አስፍሯል፡፡ እስራኤል ከአሜሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በውሳኔያቸው እንደማይሸረሸርም ተገልጿል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ በአጭር ጊዜ ምን ያስከትላል?
የውሳኔ ሐሳቡ በእስራኤል ላይ በእስራኤልና በፍልስጤም ግጭት ወይም በሰላም ስምምነት ሒደቱ ላይ በቅርቡ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ምክንቱም የውሳኔ ሐሳቡ አሳሪ አይደለም፡፡ ውሳኔው በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል በነበረው ግንኙነት ላይ ለውጥ የሚያመጣው፣ ውሳኔውን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚወሰዱ ተከታታይ አፈጻጸሞች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ እስራኤልም አሁን የሚያሳስባት ተከታታይ አፈጻጸሞች ቀጥለው እንደሚመጡ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ በተለይ ወሳኝ በሆኑ በድንበር ግጭት፣ እየሩሳሌምን የፍልስጤም ዋና ከተማ በማድረግና የፍልስጤም ስደተኞችን በተመለከተ የሚደረጉ ስምምነቶችና ለእነዚህ የሚቀመጡ የጊዜ ገደቦች ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ከ15 ቀናት በኋላ በፈረንሣይ ፓሪስ በሚደረገው ዓለም አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ፣ የአሜሪካው ተሰናባች ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከሥልጣን ሳይለቁ በምክር ቤቱ ውሳኔ ላይ ለመወያየት፣ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለውሳኔው ምንነት ለማብራራት ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ እስራኤል እንደማትሳተፍ ስታስታውቅ፣ ፍልስጤም ተሳታፊ እንደምትሆን ታውቋል፡፡
የውሳኔው የረዥም ጊዜ ውጤት ምን ይሆናል?
ውሳኔውና በዌስት ባንክና በምሥራቅ እየሩሳሌም ያለው የእስራኤል የሠፈራ ፕሮግራም ሕጋዊነት ላይ ድርድር እንደይማኖር አስቀምጧል፡፡ በውሳኔው ሐሳብም የእስራኤል የሠፈራ ፕሮግራም ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለውና ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ እንደሆነ ተካቷል፡፡ ድንበር ማካለልን በተመለከተ ውሳኔው ለድርድር ክፍት ያደረገው ሲሆን፣ አገሮችም በእስራኤልና በእስራኤል ተይዟል ስለሚባለው የፍልስጤም አካባቢን ለያይተው እንዲያዩ፣ ስለእስራኤል ተነገረ ማለት እስራኤል ሕጋዊ አገር አይደለችም ማለት እንዳልሆነና ውሳኔው ከሠፈራ ፕሮግራሙ ጋር መያያዙን አክሏል፡፡
የፍልስጤም ባለሥልጣናት እስራኤል ለውሳኔው እንድትገዛ፣ ይኼ ካልሆነ ደግሞ ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ እያሳወቁ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በፍልስጤም ድንበር አካባቢዎች ላይ ቀድሞ ምርመራ የጀመረ ሲሆን፣ እነዚህ ሲጠናቀቁ በእስራኤል ተጨማሪ ይዞታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡
እስራኤልና አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ?
አሜሪካ በእስራኤል ላይ የተላለፈውን ውሳኔ በድምፅ ተዓቅቦ ብታልፈውም፣ የደቡብ ካሮላይና ሴናተር ሊንዲሴይ ግርሃም፣ አሜሪካ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምታደርገውን ፈሰስ ትቀንሳለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ ከድርጅቱ በጀት 22 በመቶ ያህሉን የምትሸፍን ሲሆን፣ ከዚህ በጀት ከቀነሰች በእስራኤል ላይ ሌላ ጉዳት ያስከትላል፡፡ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2011 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በእስራኤል ላይ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን አላጠራም በማለት የበጀት ድጎማ በመቀነሷ፣ ዩኔስኮ አሜሪካን በዩኔስኮ የባህል ክንፍ ውስጥ ያላትን ድምፅ የመስጠት መብት አግዷል፡፡ አሜሪካም በወቅቱ ለዩኔስኮ በዓመት 80 ሚሊዮን ዶላር ትሰጥ ነበር፡፡ አሜሪካ የአሁኑን ውሳኔ ተከትሎ በድርጅቱ ላይ የምትወስደው ዕርምጃ እስራኤልን በተቃራኒው ሊጎዳት ይችላል፡፡ ሆኖም ከወደ አሜሪካ የተሰማው የበጀት ድጎማው እንደሚቀነስ ነው፡፡
እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ለሆኑ አምስት ድርጅቶች የምትሰጠውን ስምንት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መቀነሷን አሳውቃለች፡፡ ኔንያሁም በእስራኤል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መልሰው እንደሚገመግሙ አስታውቀዋል፡፡
የሠፈራ ፕሮግራምን በተመለከተ ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ ሆኖም ከዌስት ባንክና ከምሥራቅ እየሩሳሌም ጋር ተያይዞ የእስራኤል የሠፈራ ፕሮግራም ላይ ውሳኔ ሲተላለፍ እ.ኤ.አ. ከ1980 ወዲህ ይኼ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እስራኤል በፍልስጤምና በሌሎች የዓረብ ግዛቶች የነበራት መስፋፋት የተወገዘ ሲሆን፣ የእስራኤል ፍልስጤም ግጭትም ትክክል አለመሆኑ ተነግሯል፡፡ ሆኖም ከሠፈራ ፕሮግራም ጋር ተያይዞ የተላለፈ የመጀመሪያ ውሳኔ ነው፡፡
አሜሪካ የእስራኤል ደጋፊ ብትሆንም እንደ ኦባማ ሁሉ ከሥልጣን በመሰናበታቸው ዋዜማ በእስራኤል ጉዳይ ጣልቃ የገቡ ፕሬዚዳንቶች ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1988 ሮናልድ ሬገን የሁለተኛ ዘመን ሥልጣናቸውን ከማስረከባቸው አስቀድሞ ከፒኤልኦ ጋር ውይይት ጀምረው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 ደግሞ ቢል ክሊንተን ‹‹የክሊንተን ፓራሜትር›› የሚባለውን የሰላም ራዕይ ሲያስቀምጡ እ.ኤ.አ. 2008 የጆርጅ ደብለው ቡሽ ተወካይ የፀጥታው ምክር ቤት የ1850ኛ የሰላም ስምምነት ለማሻሻል የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ደግፈዋል፡፡ ሆኖም በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ያለውን አለመግባባት ለማረቅ በፀጥታው ምክር ቤት የቀረበን ሐሳብ፣ ድምፅን በመሻር ተጠቅሞ የእስራኤልን ፍላጎት ያላስጠበቀ ውሳኔ የተላለፈው በኦባማ የሥልጣን ማብቂያ ዘመን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ባራክ ኦባማ አስተዳደራቸው በእስራኤላውያን እየተብጠለጠለ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ድርጊት ‹‹አሳፋሪ›› ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በንዴት ተናግረዋል፡፡ .