Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ሺዎች የታደሙት ልደት

ትኩስ ፅሁፎች

ድግስ ሲደገስ ከግምት ከሚገቡ ነገሮች አንዱ ለድግሱ የሚጠሩት ሰዎች ቁጥር ነው፡፡ ብዙዎች ከአቅማቸው ጋር የተመጣጠነ ተጋባዥ መጥራትንም ይመርጣሉ፡፡ ከወደ ሜክሲኮ የተሰማው ዜና ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በማዕከላዊ ሜክሲኮ የሚኖሩ አባት ለልጃቸው 15ኛ ዓመት ልደት እንግዶችን የጋበዙት በማኅበረሰብ ድረ ገጽ ነበር፡፡ በሜክሲኮ ኩዊንሴኔራ በመባል የሚታወቀው 15ኛው ዓመት ልደት በዓል ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ አባትም ለልጃቸው ልደት ሁሉም ሰው እንደተጋበዘ የሚገልጽ ቪዲዮ ለቀቁ፡፡ ቪዲዮውን ከ800 ሺሕ በላይ ተመልካች ያገኝና ወደ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ሰዎች ልደቱን ለመታደም ቃል ይገባሉ፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ቃል ከገቡት መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት የታዳጊዋን ልደት ለማክበር ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ሲሄዱ፣ አባትየው ግር ቢሰኙም ከማስተናገድ ወደኋላ አላሉም፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው ተጋብዟል ያልኩት በአካባቢያችን የሚኖሩ ሰዎችን በአጠቃላይ ለማለት ነበር፤›› ሲሉ አባትየው ቤታቸው አካባቢ ለተገኙት ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ የሰዎቹ መስተንግዶ ዳስ ተጥሎ ምግብና መጠጥም ቀርቧል፡፡ ሦስት የሜክሲኮ ባንዶች ልደቱን በሙዚቃ አድምቀውታል፡፡ ባለልደቷ ሩቢ ሊቤራም እንግዶቿን ሳትሰለች ተቀብላለች፡፡

* * *

የቃል ቅሌት

ከሚሊዮናት ውስጥ

የቅርብ ዘመድ ጠፍቶ

አንድ ረዳት አጥቶ

ጠባብ ኩሽና ውስጥ

ቢገኝ አንድ አዛውንት

ደርቆ ተኮራምቶ

ከዚህ ዓለም ጣጣ

በሞት ተለያይቶ

በሰላም ‹‹አረፈ››

‹‹ተገላገለ›› እንጂ

እንዴት ‹‹ሞተ›› ይባላል?!?

‹‹ቃል››ም እንደሰው ልጅ

ለካ እንዲህ ይቀላል!!

ፋሲል ተካልኝ ‹‹ጡዘት›› (2008)

* * *

 

‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . . ›› ቅዳሜ ለውይይት ይቀርባል

  • የስድስት ቀናት የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ተዘጋጀ

በፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በተዘጋጀው ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . . ›› መጽሐፍ ዙሪያ ቅዳሜ ታኅሣሥ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት በትራኮን ሕንፃ (ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት) ውይይት ይካሄዳል፡፡

‹‹ሐሳብን በሐሳብ፤ ዕውቀትን በመረጃ›› መፈተንን ዓላማ አድርጎ ‹‹መጻሕፍት እንደመሠረታዊ ፍላጎት›› በሚል መሪ ቃል በሚዘጋጀው ወርኃዊ መድረክ ላይ፣ በ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . . ›› ላይ የመወያያ ሐሳብ የሚያቀርቡት ከሥነ ምግባርና ሞራል አንፃር ዶ/ር ዘካርያስ ዐምደ ብርሃን፣ ከምርታማነትና ውጤታማነት አንፃር አቶ ሮበን ነዳሳ መሆናቸውን የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ገልጸዋል፡፡ 

በሌላ በኩልም ከታኅሣሥ 22 ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን ድረስ የሚቆይ የመጻሕፍት ዐውደ ራዕይ በትራኮን ሕንፃ ላይ ተዘጋጅቷል፡፡ አስተባባሪው እንደገለጹት፣ ከ20 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖር፣ በዐውደ ርዕዩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጎ አድራጎት ማኅበር ለቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቤተ መጻሕፍት ማደራጃ እንዲሆን ለሚያሰባስቡት መጻሕፍት ልገሳም ይደረጋል፡፡

* * *

 

ደቡብ ኮርያ የውሻ እርድን ልታስቆም ነው

ደቡብ ኮርያ የውሻ እርድና የውሻ ሥጋ ሽያጭን ልታስቆም መሆኑን አስታውቃለች፡፡ ዘ ኮርያ ሄራልድን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ በደቡብ ኮርያ ሴዎንጋም ከሚገኘው ትልቁ የውሻ ሥጋ ገበያ (ሞራን ገበያ) ሻጮች የገንዘብ ካሳ ተሰጥቷቸው ወደ ሌላ ንግድ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል፡፡ የአገሪቱ አመራሮች እንደተናገሩት፣ የውሻ ሥጋ ለገበያ ማቅረብ የአገሪቱን በጎ ገጽታ ሊያጎድፍ ይችላል፡፡ የሴዋንጋም ከንቲገ ሊ ጄሜየንግ ‹‹የአገሪቱ ታላቅነት ለእንስሳት ባለን አመለካከት ጥላሸት ሊቀባ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ የአገሪቱ የእንስሳት ጥቃትን የሚከለክሉ ማኅበሮች ውሳኔውን ደግፈዋል፡፡ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚሆን የገለጹም አሉ፡፡ በሞራን ገበያ የውሻ ሥጋ የሚሸጡ 22 ነጋዴዎች ያሉ ሲሆን፣ በሴንጋም ከተማ ሚሊዮኖች ደንበኞቻቸው ናቸወ፡፡ ከደቡብ ኮርያ የውሻ ሥጋ ንግድ አንድ ሦስተኛውን የሚሸፍኑትም እነሱ ናቸው፡፡ 

* * *

የህንድ ጋዜጣ ወንድ መውለድ ከፈለጋችሁ በሚል ያልሆነ ምክር ሰጠ

      አንድ የህንድ ጋዜጣ ባሳተመው አንድ ጽሑፍ ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው ምክር መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ጋዜጣው እናቶች በሴት ፈንታ ወንድ እንዲፀንሱ ብዙ እንዲበሉና ወደ ምዕራብ ዞረው እንዲተኙ መክሯል፡፡ ሳይንስ እንደሚለው የፅንስ ፆታ ከወንድ ኩሊት (ስፐርም) ክሮሞዞም እንደሚወሰን በመግለጽ ፈንታ የማይሆን ምክር ሰጠ የተባለው ጋዜጣ፣ ማንገለም የተሰኘና በደቡባዊ ህንድ የሚታተም ነው፡፡ በለንደን ፖርትላንድ ሆስፒታል የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ሻዚያ ማሊክ፣ ወንድ ወይም ሴት የመፀነስ ዕድል እንዲሁ የሚሆን (Random) በመሆኑ ይኼን እውነት መቀየር የሚያስችል እስከ አሁን በሳይንስ የተደገፈ ምንም ዓይነት መንገድ እንደ ሌላ ያስረግጣሉ፡፡

* * *

የሙሴቬኒና የኤልሲሲ ጋርዶች ተደባደቡ

ነገሩ ባለፈው ሳምንት በዑጋንዳ ኢንቴቤ የሆነ ነው፡፡ ኢንቴቤ በሚገኘው የፕሬዚዳንቱ መኖርያ፣ አራቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት ጠባቂዎች ከተለመደውና ከተፈቀደው ውጪ መሣሪያ እንደታጠቁ ወደ ውስጥ ካልገባን በማለታቸው ግጭቱ መቀስቀሱን የዑጋንዳ ጋዜጣዎች ዘግበዋል፡፡ የሙሴቬኒና የቤተሰባቸው ጠባቂዎች ደግሞ ይኼን ፈጽሞ አሻፈረን በማለታቸው ግብግቡ ሊጧጧፍ ችሏል፡፡ በዑጋንዳው ፕሬዚዳንት መኖሪያ የካቢኔ ሚኒስትሮች ጠባቂዎች እንኳን መሣሪያቸውን ከደጅ አኑረው ነው የሚገቡት፡፡ 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች