Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበአዳማ ከተማ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የ‹‹ጥልቅ ተሃድሶው›› ነፀብራቅ ቢሆን?

በአዳማ ከተማ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የ‹‹ጥልቅ ተሃድሶው›› ነፀብራቅ ቢሆን?

ቀን:

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ከአዳማ ከተማ ሕዝብ ጋር በገልማ አባ ገዳ አዳራሽ ተገኝተው ተወያይተው ነበር፡፡ ውይይቱን በከፈቱበት ወቅትም በርዕቱ አንደበታቸው ለከተማ ነዋሪው ተወካዮች ይፋ እንዳደረጉት፣ የአዳማ ከተማን ዘርፈ ብዙ ችግርና በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን አስተዳደራዊ በደል ለማስወገድ ቆርጠው መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም አዳማ በተለምዶ እንደምትባለው ‹የስምጥ ሸለቆ እንቁዋ ከተማ›› ሆና እንድትገኝ ለማድረግ ታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ወይም አብዮት እንደሚያስፈልግ አስገንዘበዋል፡፡ ለዚህም ስኬት ወይም አብዮቱን ለድል ለማብቃት፣ የክልሉ መንግሥት ለከተማው መስተዳድር ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ዋስትና ሰጥተዋል፡፡

ይኼንን ሕዝብ አሳታፊ ታላቅ የለውጥ አብዮት የሚመሩለት ብቃት ያላቸው የክልሉ ዜጎች እንዲሆኑ በማመን፣ በዕውቀትና በችሎታቸው ብቻ ሳይሆን በመልካም ሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸውን በጥንቃቄ መርጦ መሾሙን ለሕዝብ አሳውቋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የአዳማ ከተማን የአሁን ገጽታ ለመለወጥና አዳማን እውነተኛ ‹‹እንቁ ከተማ›› ለማስባል የሚያስችል አቅም አላቸው ብሎ ያመነባቸውን ከንቲባ፣ ምክትል ከንቲባ፣ ሥራ አስኪያጅ፣ የመሬት አስተዳደርና የድርጀት ጉዳይ ኃላፊዎች ሾሟል፡፡

የአዳማ ከተማ ሕዝብም ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የከተማ ከንቲባ የሆኑትን ሴትና እናት በታላቅ ደስታ በእልልታና በጭብጨባ ሹመታቸውን አፅድቆላቸዋል፡፡ በሙያቸው ዳኛ የሆኑትን ወ/ሮ አዳነች አቤቤን እንኳን መጡልን፣ የልማታችን አብዮት መሪ እንኳንም እርሰዎ ሆኑ፣ ስለሕግ ያውቃሉና በማለት ነው ከልቡ ደስታውን የገለጸው፡፡

ነዋሪው የአዳማን ሁለንተናዊ ወይም ‹‹ከ . . . እስከ›› የማይባለውን ችግር ጠንቅቆ ያውቃልና ሕግ አዋቂ መሪ ሲሆንለት መደሰቱ አይገርምም፡፡ በተዋረድ ያሉ ባለሥልጣናት ስለሕግ እንዲያውቁና አዳማን ‹እንቁ› ለማድረግ እንዲጥሩ ከንቲባዋ ያደርጓቸዋል ብሎ በማመኑ ደስታውን ቢገልጽም፣ ከቀድሞዎቹ ከንቲባዎችና ካቢኔዎቻቸው ያልተገባ አካሄድ በመነሳት ሥጋቱንም ገልጿል፡፡ እነዚህ አዳዲስ የሕዝብ አገልጋዮችም የክልሉ ፕሬዚዳንት እንዳሉት ‹‹ሐሺሽ በመቅመስ ከአብዮቱ መስመር ውጪ ቢነጉዱና አብዮቱን ቢቀለብሱትስ? . . . በአዳማ ከተማ ውስጥ ያለው የደላላና የአቀባባይ እንዲሁም በአቋራጭ ለመክበር ፈላጊ የአብዮቱ እንቅፋት ሊሆን አይችልም ወይ? . . . ›› በማለት ጥያቄ አንስቷል፡፡ ጸሐፊው ሐሳቡን ጠቅለል አድርጎ እንዳቀረበው፡፡

ባለ ፈርጀ ብዙ ችግር በዕድሜዋ ልክ እንዳትበለፅግ ያደረጋትን ይህቺን ለእንቁነት የታጨች ከተማ ዛሬ በቁመናዋ ላይ የሚታየውን አስከፊ ገጽታ (በመሀል ከተማዋ ያለው ቆሻሻ፣ በየአርጅኑ የተከማቸው ግሳንግስ፣ የከተማዋ ትልቅ አስከፊ ዕድፍ እንደሆነ ይታወቃል) እንዲሁም የነዋሪዎችዋን የመልካም አስተዳደና የፍትሕ ዕጦት (ፍትሕ በገንዘብና በሥልጣን ጉልበት ሳትሸራረፍና ሳታጋድል ለዜጎች በእኩልነት ታገለግል ዘንድ ከላይ ጀምሮ በተዋረድ በሰንሰለቱ ያሉ ባለሥልጣን መንግሥት የሾመው ለአገልጋይነት መሆኑን በቅጡ ተገንዝቦ፣ የተሰጠውን የማገልገል ኃላፊነት በወጉ እንዲጠቀምበትና እውነተኛ እንደሁም ታማኝ አገልጋይነቱን በተግባር እንዲያሳይ ‹‹የተጠያቂነት አሠራር›› መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የተጠያቂነትን አሠራር ለመተግበርም ራሱን የቻለ የክትትልና ምዘና ተቋም መመሥረት የሚያስፈልግ ይመስለኛል)፡፡ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጥብቅ የሆነ የበላይ ቁጥጥርና ድጋፍ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያዋ የሴት ከንቲባ በመባል ስማቸው በታሪክ ሊጻፍላቸው የቻለው ወ/ሮ አዳነች አቤቤም የሕግ ባለሙያ እንደመሆናቸው መጠን፣ በአዳማ ነዋሪዎች ላይ የተስተዋለውን አስተዳደራዊና ፍትሐዊ ችግር፣ እንዲሁም በከተማ ፅዳትና አረንጓዴ ልማት አሠራር ውስጥ በዕቅድ፣ በሕግና በመመሪያ ያልተደገፈውን አካሄድ ወደፊት ከካቢኔዎቻቸው ጋር በባለሙያ በመታገዝ ስለሚያወጡት ዕቅድ አካሄዳቸው በግልጽ አሳይቶናል፡፡ የነገ ሰው ይበለንና፡፡

ይሁንና ለወደፊት ሥራቸው በሚያወጡት ዕቅድ ላይ መካተት ይኖርባቸዋል የምለውን እኔም እንደ ከተማዋ ነዋሪነቴ መጠቆም እንደሚኖርብኝ በመገንዘብ፣ የአዳማ ቁልፍ ችግሮችን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ዋነኛዋ የአዳማ ከተማ ቁልፍ ችግር የሆነው ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ነው፡፡ በሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከቀበሌ ጀምሮ ወደ ላይ ባሉት አገልግሎት ሰጪዎች የሚስተዋለውና ለከተማዋ ዕድገት ማነቆ የሆነው ሙስናዊ አሠራር ወይም ኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ሳይሆን ‹‹ኪስን ለማስከበር›› መሯሯጥ ነው፡፡ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጎን ለጎን ተያይዘው የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦቶች በኃላኝነትና በሦስተኛነት ቁልፍ ችግር ናቸው፡፡  

በአራተኛነት የማስቀምጠው ይኼን ችግር ለመፍታት የፌዴራል መንግሥትንም እገዛ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የጎዳና ተዳዳሪነትና ለምኖ አዳሪነት የከተማዋን ገጽታ እያበላሸ ያለ ቁልፍ ችግር ነው፡፡ እርግጥ ነው የጎዳና ተዳዳሪዎችና የለምኖ አደሮች ችግር የመላው የአዳማ ነዋሪም ችግር ነው፡፡ የእኔም፣ የአንተም፣ የአንቺም፣ የሁላችንም ችግር ነው፡፡ ችግሩ ያገባናል፣ ይመለከተናል፣ በወጣን በገባን ቁጥር የምናስተውለው፣ በየቀኑ እያየንም ህሊናችንም የሚቆስልበት ሕመማችን ነው፡፡ ስለሆነም እኛ አያገባንም፣ አይመለከተንም ማለት አንችልም፡፡ ጎዳና ላይ ያሉት ዜጎች አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድምና እህቶቻችን ናቸው፡፡ ‹መወለድ ቋንቋ ነው› እንዲሉ፡፡

አምስተኛውና የመጨረሻ ያልኩት ቁልፍ ችግር ደግሞ ‹‹ሕገወጥ የጎዳናና የጥጋጥግ ንግድ ነው››፡፡ ይኼ ለዘመናት የቆየና በጎዳና ንግድና በየጥጋጥጉ ያላንዳች የንግድ ፈቃድ ተሠማርተው ያሉትን ዜጎች የሚመለከት ነውና በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል፡፡

ይኼንን ሕገወጥ ንግድ ሥርዓት ለማስያዝ ከተለፈገ ለእነዚህ በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች (በተለይም በቀበሌ 08) የሚገኝ ሥፍራ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ ለምን? ቢሉ ዜጎች ሕገወጥ ሥራን እንደ ሕጋዊነት ቆጥረው መተላለፊያ መንገዶችን ሞልተው ለዘመናት ሲነግዱ፣ እየነገዱም ቤተሰባቸውን ሲመግቡ፣ ሲያስተምሩና ለቁም ነገር ሲያበቁ ኖረዋልና ዛሬ ደርሰን ዞር በሉ ወደ ምትሄዱበት ሂዱ የማለት መብት የለንምና፡፡

ስለሆነም ይኼ ጉዳይ በጥልቀት ተመርምሮ የመገበያያ ሥፍራ ለእነዚህ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች ሊዘጋጅላቸውና ሕጋዊ ሆነው እንዲሠሩ በማድረግ፣ ራሳቸውንና አገርን ጠቃሚዎች ማድረግ ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡

በአዳማ ከተማ ተጨባጭ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ከላይ የዘረዘርኳቸውን፣ ለዘመናት የቆዩና እያደጉ የመጡ ቁልፍ ችግሮች መፍታት ያስፈልጋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት እንዳሉትም ‹‹አብዮት›› ያስፈለገው ለዚህ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የአዳማ ከተማ ሕዝብ በክልሉ ፕሬዚዳንት የተበሰረውን (የአዳማ ከተማን ቢያንስ ከሐዋሳና ከባህር ዳር ጋር አቻ ለማድረግ) አብዮታዊ እንቅስቃሴ በእልልታ ተቀብሏታል፡፡ አብዮታዊ እንቅስቀሴውን በእልልታ የተቀበለውም አብዮቱን የሚያካሂዱ አዳዲስ የካቢኔ አባላት ለከተማው በመሾማቸው የነገን በተስፋ በማየት ነው፡፡

ዛሬና በአሁኗ ሰዓት የሥልጣን ኳሱ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ እግር ሥር ናት፡፡ ይህቺን ኳስ ከካቢኔዎቻቸው ጋር በመሆን ሕዝቡን በማስተባበር ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉ ከሆነ፣ እልልታውና ጭብጨባው ይቀጥላል፡፡

እርግጥ ነው መሪ እንደ መሆናቸው መጠን ኳሷ በእግራቸው ሥር መገኘቷ ግድ ቢሆንም፣ እንዴት በኳሷ ተጫውቶ ግብ እንደሚያስቆጥር ለሕዝቡ የሚያስረዳ፣ የሚያስተምር፣ የሚያሠለጥን ሰፊ ዕቅድ፣ የአፈጻጸም ደንብና መመርያ በቅርቡ አዘጋጅተው ሕዝብን እንደሚያወያዩ አምናለሁ፡፡

ዛሬና አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የትኛውም ባለሥልጣን ሕዝብን ሳያሳትፍ ኳሷ በእግሬ ሥር ናት ብሎ እንዳሻው መጠለዝ እንደማይችል የተገነዘብንበት ወቅትና ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ መንግሥት ሥልጣን በእጄ ነው ብሎ እንዳሻው ለመሆን የሚሞክር ማንኛውንም ባለሥልጣን የሚታገስበት ልብ እንደሌለውና ጨከን ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡ ሕዝብም ኳሷ በእግሬ ሥር ናት ብሎ እንዳሻው የሚጠልዝ፣ በሕግ አግባብ ይጠየቅልኝ ማለቱን ዛሬም ሆነ ነገ እንደማያቆም አሳስቧል፡፡ የሁለቱም ወገን ማሳሰቢያዎች ለአገር ልማትና ብልፅግና እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡ በአዳማ ከተማ የተጀመረው ትልቅ ትኩረት የተደረገበት ወደ ልማትና ዕድገት የሚወስድ እንቅስቀሴም ፋይዳ ከዚህ አንፃር የሚታይ ነው፡፡ እንቅስቃሴውም ‹‹የጥልቅ ተሃድሶው ነፀብራቅ›› ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡     

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...