Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኤርትራና የዓረብ አገሮች ቁርኝት

ኤርትራና የዓረብ አገሮች ቁርኝት

ቀን:

አፄ ምኒልክ የጣሊያንን ወታደሮች መረብ ምላሽ አድርሰው ወደ መናገሻ ከተማቸው  ሲመለሱ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የቀረች አገር እየተባለች በታሪክ የሚነገርላት ኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ዓይንና ናጫ ሆና ዓመታትን ተሻግራለች፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (Eritrean People Liberation Front) ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ግንባር (Tigray People Liberation Front) ጋር በመሆን የአምባገነኑንና በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኃይል እየተባለ ይጠራ የነበረውን የደርግ መንግሥት ካስወገዱ በኋላ ሁለቱም አገሮች የየራሳቸውን የአስተዳደር ሥርዓትና የድንበር ወሰን በአግባቡ ሳያበጁ መኖር ቢጀምሩም፣ ወደ ጦርነት ሲገቡ ግን ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል በተፈጠረው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከሁለቱም ወገኖች በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሰው ከመሞቱ በላይ፣ በብዙ ዓመት ሊተካ የማይችል ኢኮኖሚም ወድሟል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት (No war No Peace) ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በዚህም የተነሳ የሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ሰፊ ልዩነት እየታየበት መምጣቱን አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በዛሬዎቹ ሊቢያና ቻይና ይወክሏቸዋል፡፡ ኤርትራ የሊቢያን ውክልና ስትወስድ ኢትዮጵያ ደግሞ የሩቅ ምሥራቋን ቻይና ትወስዳለች፡፡ በሌላ አገላለጽ ሲገልጿቸው ደግሞ በአይብና በጠመኔ (ቾክ) ሲወክሏቸው ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ የአይብን ኤርትራ ደግሞ የጠመኔን ውክልና ይወስዳሉ፡፡ ይህንንም ባለሙያዎች ሲያስቀምጡት ኤርትራ የተስፋ ዳቦ ከመብላት ባሻገር፣ ጠብ የሚል ተጨባጭ ለውጥ የማይታይባት አገር መሆኗን በማብራራት፡፡

የዛሬዋ የኤርትራ ዜጐች የበረሃና የውቅያኖስ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ የቀደመ ታሪኳ እንደሚዘክረው በእነ ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ ትከሻ ላይ ተንጠልጥላ ዛሬ ላይ የደረሰችው ኤርትራ፣ በደቡብ ምሥራቅ በኩል በቀይ ባህር የምትዋሰን ትንሽ አገር ነች፡፡ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት ኤርትራ አጠቃላይ የሕዝቧ ቁጥር 5,390,379 ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 49.3 በመቶ የሚሆነው ወንድ፣ 50.3 በመቶ ደግሞ ሴት ነው፡፡ ይህ አኃዛዊ መረጃ ከዓለም አቀፍ የፆታ ንጽጽር ጋር ሲወዳደር ከደረጃ በታች መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዓለም አቀፉ የፆታ ንፅፅር 1,016 ወንዶች ለ1,000 ሴቶች ነው የሚለውና፡፡ በመሆኑም የኤርትራ ዜጐች የፆታ ንፅፅር ከዓለም አቀፉ የፆታ ንፅፅር ጋር ሲወዳደር ከደረጃ በታች የሆነበትን ምክንያት አንዳንድ ባለሙያዎች ሲገልጹ፣ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ለስደትና ለጦርነት ተጋላጭ በመሆናቸው እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱ የቆዳ ስፋትም 117.6 ቢሊዮን ስኩየር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ኤርትራ በአሁኑ ወቅት በስድስት ክልሎች ተከፋፍላ ትገኛለች፡፡

በአሜሪካ የኮንግረስ አባል፣ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ምክትል ጸሐፊና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ክርስቶፎር ኤች ስሚዝ (ከኒውጀርሲ የሪፐብሊካን አባል) ‹‹ኤርትራ የተገለለችው የሰሜን ምሥራቋ አፍሪካዊት አገር›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. መስከረም 2016 ‹‹አትላንቲክ ካውንስል›› ለተሰኘው ድርጅት ባቀረቡት ሪፖርት፣ ‹‹የኤርትራ ሕዝብ እ.ኤ.አ. በ1991 ነፃነቱን ሲያውጅ ተስፋ የሰነቀና ለአገሪቱ ብርሃን የናፈቀ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ሆኖ አገሪቱን በአሁኑ ወቅት የኋሊት እያስኬዳት ቢሆንም ቅሉ. . .›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ ኤርትራውያን በአሁኑ ወቅት አካላቸው ከቀይ ባህር ማዶ ልባቸው ደግሞ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ተሰዶ ያለ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆን በየወሩ ከ5,000 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች በቀይ ባህር፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ አድርገው ከአገራቸው የሚሰደዱ መሆናቸውን በማብራራት፡፡

በዓለም አቀፍ የስደተኛ ጉዳዮች ተጠሪ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ጃይ ጀሪማን በሌላ በኩል፣ በየዓመቱ ታኅሳስ 18 ቀን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ከአልጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እ.ኤ.አ. 2016 በዓለም ታሪክ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የስደተኞች ቁጥር የተመዘገበበትና ዜጐችም ለከፉ ጉዳት የተዳረጉበት ወቅት እንደነበር አብራርተዋል፡፡ ኤርትራውያን ስደተኞችን ከሶሪያ፣ ከሊቢያ፣ ከየመንና ከአፍጋኒስታን ስደተኞች ጋር በማነፃፀር፡፡

ኤርትራ በአሁኑ ወቅት የዓለም ዓይንና ጆሮ ሆናለች፡፡ በአንድ በኩል መቆሚያ የሌለው የዜጎች ስደት፣ በሌላ በኩል አገሪቱን በአሁኑ ወቅት እያስተዳደራት ያለው የመንግሥት ሥርዓት አምባገነንነትና ከአውሮፓ ብሎም ከአሜሪካ ጋር ያለው ግንኙነት እዚህ ግባ የሚባል ካለመሆኑ ባሻገር በተቃራኒው ከዓረብ አገሮች  ጋር ያላትን ወዳጅነት በመጥቀስ፡፡

የዛሬዋ አስመራ አልሸባብን ከመደገፍ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ እንደ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ ግንቦት ሰባትና ሌሎች ቡድኖችን ከመደገፍና ከማስታጠቅ ባሻገር የአሸባሪ ቡድኖች መናኸሪያ ሆናለች ሲሉ አንዳንድ ባለሙያዎችና ሚዲያዎች ይናገራሉ፡፡ በግብፅና በሳዑዲ ዓረቢያ ድጋፍ አንገቷን ቀና አድርጋ የምትሄደው የዛሬዋ የኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራ በዓለም ፊት ውግዘትንና መገለልን እያስተናገደች ነው፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማዕቀብ ሰለባ ሆናለች፡፡

ኤርትራ ዛሬ አፏን ሞልታና ደረቷን ነፍታ እንደ አገር መቀጠል የቻለችው በዓረብ አገሮች የገንዘብና የወታደራዊ ሎጅስቲክስ ድጋፍ ነው፡፡ በተለይ ከዓረብ አገሮች ጋር ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስቻላት ጉዳይም የባህር በሯ ነው፡፡ ከስዊዝ ቦይ ጋር የሚገናኘው ይህ የቀይ ባህር ዳርቻ ኤርትራን የዓረብ አገሮች ምርጫ አድርጓታል፡፡ ይህ ታሪክ የሚወድቀው ደግሞ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መነሻ በመሆኗና ይኼንን ወንዝም እገድባለሁ የምትል ከሆነ የታችኛው የተፋሰስ አገሮችን በዋናነት ግብፅን ስለሚነካ፣ በዓባይ ወንዝ ላይ መተማመኛ ድምፅ ለማግኘት ብሎም ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ስለሚፈልጉ ኤርትራን ወዳጅ አድርገው መርጠዋታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ እንደሚደመጠው፣ ኤርትራ ከግብፅና ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያላትን ቀጣናዊና አኅጉራዊ ሚና ለማዳከም ብሎም በዓለም ፊት ደካማ የሆነ አቅም እንዲኖራት ለማስቻል ነው ይላሉ፡፡ ከሳምንታት በፊት የየመኑ ‹‹አልሃዳዝ›› የተሰኘው የዜና አገልግሎት ባሰራጨው መረጃ ‹‹ግብፅና ኤርትራ ኢትዮጵያን ለመውጋት በቀይ ባህር በኩል ተጠባባቂ ኃይል ለማሰማራት ተስማሙ›› የሚል ዜና አስነብቧል፡፡ይህ ዜና የተፈበረከ የሐሰት ኘሮፓጋንዳ ነው እያሉ ብዙ ሚዲያዎች ቢያጣጥሉትም፣ ኢትዮጵያ ግን ይህንን ጉዳዩ በአጽንኦት መከታተል እንዳለባት የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡  

ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በየመን ሁቲ አማፂያን ላይ በሚያደርጉት ዘመቻ ኤርትራ ከ2,000 በላይ ወታደሮችን ወደ ግንባሩ ልካለች በማለት የተለያዩ ድርጅቶች ያስረዳሉ፡፡ ኤርትራ ወታደሮቿን ወደ የመን ከመላኳ ባሻገር ለአገሪቱ የአየርና የባህር ክልሏን ፈቅዳለች ሲሉም ያክላሉ፡፡ እዚህ ላይ ኤርትራ በየመን በፀረ ሁቲ አማፂያን ዘመቻ ላይ ‹‹የዓረብ ኅብረት›› (Arab Coalition) እየተባለ የሚጠራውን ጥምረት በመደገፍ ለምን ተሳታፊ ሆነች? የአየርና የባህር ክልሏንስ ለምን ፈቀደች? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ ሊሆን የሚችለው ኤርትራ በተደጋጋሚ ጊዜ ከአውሮፓም ሆነ ከአሜሪካ ጋር ይህ ነው የሚባል የንግድም ሆነ የኢንቨስትመንት ግንኙነት ስለሌላት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ማካካስና ወታደራዊም ሆነ ሌሎች ድጋፎችን ማግኘት የምትችለው ከእነዚህ አገሮች እንደሆነ በመገንዘብ ነው (ታሪካዊ ግንኙነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ታሪካዊ ጠላቴ ነች ብላ ከምትፈርጃት ኢትዮጵያ በሁሉም ነገር ልቆ ለመገኘት እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ Anchorአገሮች ጋር ባላት ጥብቅ ግንኙነት የወታደራዊ ሎጅስቲክስ አቅርቦት፣ ሥልጠናና ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን ስታገኝ ኖራለች (አሁንም እያገኘች ነው)፡፡ ይህንን ድጋፍ በማግኘት የተጠናከረ መከላከያ ኃይል በመገንባት አካባቢያዊና ቀጣናዊ አቅሟን ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡

‹‹አናዱሉ›› የተሰኘው የዜና አገልግሎት ከኤርትራ ታማኝ ዲፕሎማቶች አገኘሁት ብሎ ባሰራጨው መረጃ መሠረት፣ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በማቅናት ከንጉሥ ሳልማን ጋር መክረዋል፡፡

‹‹አህራም›› ኦንላይን የተሰኘው የግብፅ የመረጃ መረብ ደግሞ ከሦስት ሳምንታት በፊት ባሰፈረው መረጃ፣ ‹‹የኤርትራ ፕሬዚዳንት ካይሮ ገቡ›› ሲል አስነብቧል፡፡ መረጃው አክሎም ፕሬዝዳንቱ ካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሸሪፍ እስሜል ተቀብለዋቸዋል፡፡ በቆይታቸውም ከግብፅ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የሚመክሩ ሲሆን፣ በዋናነት በሁለቱ አገሮች መካከል ስለሚኖረው ትብብር በተለይም በእርሻና በዓሳ ሀብት ልማት ዙሪያ ተባብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ይጠበቃል ሲል ዘግቧል፡፡ 

ይህንን የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግብፅ ጉብኝት ዓላማ በተመለከተ  የተለያዩ ሚዲዎች የዘገቡት ሲሆን፣ በዘገባቸውም የተለያየ ፈር ሲያስይዙት ተስተውሏል፡፡ የተወሰኑት ሚዲያዎች የፕሬዚዳንቱ የካይሮ ጉብኝት ዋና ዓላማ ሁለቱ አገሮች በቀይ ባህር በኩል ስለሚያቋቁሙት ኮማንድ ፖስት ለመምከር ነው ሲሉ፣ የተወሰኑት ደግሞ በሶሪያ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ያካሄዱት ግንኙነት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ሁለቱ አገሮች በአሁኑ ወቅት እጅና ጓንት ናቸው፡፡ በሁለቱ አገሮች ውስጥ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን መንግሥት የሚቃወሙ ቡድኖች ይኖራሉ፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጊዜ እንደተባለው እነዚህ አገሮች ለእነዚህ ቡድኖች መሸሸጊያ ከመሆን አልፈው፣ አስፈላጊውን ወታደራዊ ሎጅስቲክስ በማሟላት ኪሳቸው የፈረጠመ እንዲሆን በገንዘብ እየረዷቸው ነው፡፡ የእነዚህ ቡድኖች በገንዘብ መፈርጠም ደግሞ  ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚፈጥረውን ሥጋት ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከግማሽ በላይ እያደረሰችው ያለውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ተከትሎ ለግብፆች የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ የሚረዱ ወገኖች እስካሉ ድረስ፣ ግብፅና ኤርትራ ወዳጅነታቸው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዳተባለውም በቀጣናው ኮማንድ ፖስት የማያቋቁሙበት ሁኔታ አይኖርም ብሎ አለመገመት ሞኝነት ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ውስጣዊ ችግር በቶሎ ፈትታ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ለአገሩ የሚቆምበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባት፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የህዳሴውን ግድብ የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጡ በኋላ ዓባይን ለመገንባት ኅብረተሰቡ ያሳየውን መነሳሳትና ቁርጠኝነት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አሻራውን ያሰረፈበት የህዳሴው ግድብ በዓይነ ቁራኛ ለሚያዩት አገሮችም ሰለባ መሆን የለበትም፡፡ ‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ› እንደሚባለው የአገሬ ሰው የውስጣችንን ችግር በራሳችን ፈትተን፣ ኤርትራ ከዓረብ አገሮች ጋር ያላትን ቁርኝት በተገቢው ሁኔታ ማጤን ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...