Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መጫንና ማውረድን ማን አንድ አደረገው?

እነሆ ጉዞ! እነሆ መንገድ! ከጀሞ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። የተሳፈርንበት ‘ሃይገር ባስ’ በመንገደኞች ታጭቋል። መስኮቶች ተከፋፍተዋል። በተከፈቱት መስኮቶች እየነፈሰ የሚገባው አየር ግን የተዘጋ ነው። እንዲያ ነው! ‹‹የቆጡን እናወርዳለን ብለው የብብታችንን አስጣሉን እኮ እናንተ!›› ይላል አንዱ። ደንዳና ሰውነቱ መተማማኛ ዛኒጋባ እንዳጣ ያስታውቅ ነበር። ‘እንዴት? እነማን  ናቸው እነሱ?’ መሰል ተመሳሳይ ጥያቄዎች የሚጠይቀው አጠገቡ የለም። ውለውም ሆነ አድረው ተጠያቂዎቹና ተተቺዎቹ ተመሳሳይ ናቸው። በምንመላለስበት ጎዳና ሁሉም የሰው ጉድፍ ጠቋሚ ነው። ራሱን የሚታዘበውና የሚተቸው ማን ነው? ወደ ውስጥ ከመተንፈስ ወደ ውጭ እየቀለለን፣ አንዳንዱ አተነፋፈሳችንን ግብዝነት እያጠቃው የመጣ ይመስላል። ከትናንት እስከ ዛሬ ምናልባት ነገም ይኼ ክፉ አመል መንገዱ የሚገባደድ አይመስልም። የተሳፈርንበት ሃይገር መንቀሳቀስ ጀምሯል።

ከጥግ እስከ ጥግ በዘርፍ በዘርፉ ወግ ይሰለቃል። ሐሜቱ፣ ብስጭቱ፣ ምሬቱና እንጉርጉሮው ልክ አልነበረውም። ልክ ያለው ነገር ጠፍቷል። እንቅስቃሴውና ሒደቱ ግን ያለማቋረጥ ቀጥሏል። በትናንቱ ጎዳና ላይ ዛሬም የሰለቹ ኮቴዎች ከእነእንጉርጉሯቸው አቧራ ማቡነኑን ገፍተውበታል። ትዝታ አዘሉ ሒደት በማድያት የተወረረ ነው። ትውልድ ሊያጠራው ያልቻለ ችኮነት አለበት። እንኳን ነዋሪው እንኳን ተወላጁ መንገዱም ይኼን ችኮነት ሳይሰለቸው አልቀረም። ከብላቴናው እስከ ነፍስ አዋቂው የዚህች ምድር ቋጠሮ ያላማረረው የለም። ግን ለመኖር ነገን መናፈቅ ግድ ነውና፡፡ ያልታየን መመኘት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነውና፡፡ ከመሞት መሰንበት ዛሬም የኃይል ሚዛኑን እንደተቆጣጠረ ነው። ‹‹ይህ ባይሆን ምን እንሆን ነበር?›› ይላል ከጎኔ የተቀመጠ ወጣት። አባባሉ ብቻ ከሐሳቤ ገጠመ እንጂ በምን ሰበብ እንዲያ እንዳለ አልተረዳሁትም። ይኼም አንድ ገጽታችን ነው። አለመደማመጥ!

ከፊታችን የተቀመጡ ወይዘሮዎች ወጋቸው በአካባቢያቸው ያለነውን ተሳፋሪዎች ቀልብ ስቧል። ሁለቱ ወይዘሮዎች እርስ በርሳቸው ‘አንቱ’ እየተባባሉ ነው የሚጨዋወቱት። ዘመናቸው ያስጠናቸው እንዲህ ያለውን መቀባበልና መከባበር ብቻ ይመስላል። ‹‹ልጅዎ እንዴት ነው? እየተማረ ነው?›› ይላሉ በመስኮቱ በኩል ጥግ የተቀመጡት። ‹‹ኤድያ ምኑን ይማረዋል? ያንዛርጠዋል እንጂ!›› ይላሉ መልስ የሚሰጡት ወይዘሮ። ‹‹የለም መምከርና መቆጣት ነው። ልጅ አይደል?›› ሲሉ በምናብ የሳልነውን ታዳጊ ልጅ ጉዳይ ያነሱት ወይዘሮ፣ ‹‹የዘንድሮ ልጅ ነው የሚመከረው? ጫትና ‘ቻት’ ያለዕድሜያቸው ይለምዱና አንድ ሲሏቸው አንድ ይላሉ። መቼ ያዳምጣሉ?›› አሉ የወዲህኛዋ። ‹‹ይኼንን ጫት ያላመረረና ያላማረረው የለም እ? ታዲያ ምን እንብላ? አንድ ሺሕ ብር በማትሞላ ደመወዛችን እንኳን ጤፍ ልንሸምት ከሱቅ እንጀራ ገዝቶ መብላት የሚቻል አልሆነም፤›› ሲል አንዱ ጣልቃ ገብቶ። ነገሩ እየተጋጋለ ሄደ።

‹‹መንግሥትስ እሱን ብሎ አይደል ወጣቱ ሲደነዝዝ በርቱ የሚል በሚያስመስል ዝምታ የተጀቦነው፤›› ብላ አንዲት ወጣት ዘው አለች። ‹‹ምን ብንለው ምን ስቅ ላይለው በከንቱ እኮ ነው ስሙን የምናነሳው፤›› አላት ከጎኗ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹እሱስ እውነትህን ነው፤›› ብላ ዝም ከማለቷ ሁለቱ እናቶች ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። ‘እሱ ፈጣሪ ይርዳቸው ማለት እንጂ ይኼን ዘመን ምን ዓይነት ምክር ያሳልፋቸዋል ብለው ነው?’ ይባባላሉ። ‹‹እውነት ነው! እውነት ነው!›› ሥጋትና ቅሬታ ልሳናቸው ውስጥ ለውስጥ ይሹለከለካሉ። ‘እህትማ ነበራት ያውም የእናት ልጅ፣ ተሟግቶ የሚረታ ወንድም አጣች እንጂ’ ሆኖባቸው ነገሩ ግራ ተጋብተዋል። ግጥሙን ሳይቀር ‘ኢትዮጵያ አገሬ ታጠቂ በገመድ ልጅሽን ሱስ ነው እንጂ አይቀብረውም ዘመድ’ ብለው ሳይቀይሩት አልቀሩም። ኅብረት ጉልበት አጥቶ ትውልድ ምግባር ላይ ሲያለምጥ እያዩ የሚያደርጉት ቢያጡም በሐሳብ መብሰልሰላቸው አልቀረም። ምንስ ቢሆን የወለደ መቼ ይችላል?

ወያላው ‹‹ሒሳብ…›› እያለ መዞር ጀምሯል። አንዳንድ ተሳፋሪዎች ወያላውን፣ ‹‹አሁንም ታሪፉ አልቀነሰም እንዲህ ሲሰፋችሁ እኮ የነዳጅ ፍጆታ ይቀንሳል፤›› ሲሉት፣ ‹‹ኧረ እንደውም በቫት አድርጉት እያሉን ነው፤›› እያላቸው  እየተሳሳቁ ጥቂት ሄድን። ከኋላ አራት ሆነን ከተቀመጥነው ተሳፋሪዎች አንድ ወጣት፣ ‹‹ይኼን የመሰለ መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ሲያዩት የአፍሪካ መሪዎች ምን ብለው ይሆን?›› ሲል ራሱንም ሌላውንም ይጠይቃል። በስተቀኙ ያለ ወጣት፣ ‹‹ሲያዩት እኮ ነው እነሱ፡፡ እዚህ የሚመጡት እኮ ወንድሜ አንድም ለእንቅልፍ አንድም ለማይረባ ወሬ ነው። መቼ ለአፍሪካ የሚሆናት በራሷ በአፍሪካ ልጆች የሚሞከር ነገር አሳይተውን ያውቃሉ? ያውም እንዲህ ያለውን መሠረተ ልማት አይተው? ልባቸው ሲደነግጥ ታየኝ እኮ!›› ብሎት ጥርሱን ነከሰ። ከእኔ አጠገብ ከጠያቂው በስተግራ በኩል የተቀመጡ የእምነት አባት፣ ‹‹ተው መሪን የሚሾመው እግዜር ነው። እንደሱ አይባልም…›› ብለው ሳይጨርሱ ለመናገር የሚቸኩለው ይኼው ወጣት፣ ‹‹ምነው እግዜር ታዲያ እየመረጠ ህልሙን ያልጨረሰውን ሾመብን አባት?›› ብሎ የድፍረትና የንቀት ጥያቄ ጠየቃቸው። ‹ቄሱም…› ዝም እንዳሉ ሊቀሩ ልጁም አጉል ትዝብት ውስጥ ወድቆ አረፈው። ልቦናችን የሚያውቀውን አፋችን ካልተናገረው ይበላናል ማለት ነው? ወይስ አንዱ የዴሞክራሲ ገጽታ ይህ ነው?! ፍርዱን ለእናንተው!

በተቀደደው ስፒከር በኩል ‘ወገኔ ያገር ልጅ ወገኔ’ የሚል ዜማ አትኮሮታችንን ሰርቆ ይሰማል። ‘እንሟገትላት እናንሳት እያሏት መቼም ያፈራችው አይጠላት አይጠላት’ የሚለው ስንኝ ተሳፋሪዎችን ከንፈር ያስመጥጣል። ‹‹ይገርማል እኮ እናንተ? አላችሁ በሚሉን ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠቅመን ከምንጮኸው ይልቅ በአምባሰልና ትዝታ ቅኝት የምንተነፍሰው ተሻለን እኮ?›› ይላል ከመሀል። ሌላው ደግሞ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በባዶ ሆድና በባዶ ጭንቅላት መብት ብሎ ነገር ነው የማይገባኝ!›› ይላል። ሰው የሚናገረው በገባውና በሚያውቀውን ልክ መሆኑን አስምረንበት እንደማመጣለን። ‹‹ታዲያ መብታችንን ለሆድና ለጥቅም አሳልፈን እየሰጠን ሙሰኛውና አምባገነኑ ቢፈነጭብን ምን ይገርማል?›› ትላለች ወጣቷ። ‹‹ንሺማ ጠይቂው?›› ይላል በወዲህኛው መደዳ ጋቢ የለበሰ የአገር ቤት ሰው። ‹‹ይኼ እኮ ነው የአገሬው ችግር። ሦስተኛው ዓለም  ውስጥ እንደምንኖር እንረሳዋለን። የዕውቀትና የምግብ ዋስትናችንን ሳናረጋግጥ የመብት ዋስትና ለማረጋገጥ የኋሊት እንራመዳለን። በዴሞክራሲ ስም ዲክታተር እንኮለኩላለን። በአብዮት ስም ትህትናን ጥለን ትዕቢት እንሸላለማለን፤›› እያለ ወጣቱ አባባሉን ለማስረዳት ተጣጣረ።

‹‹አቦ አትፈላሰፍ! ፍልስፍና እንኳን ለአንተ ለእነ  ማርክስና ሌኒንም አልጠቀመ፤›› ሲል ከወዲያ ማዶ አንዱ ቀጠን ባለ ድምፅ  ወዲህ ደግሞ፣ ‹‹አንዳንዱ ሰው እኮ ይገርማል! በቋሚነት ለማይኖር ሐውልትና ስም ኖሮ ለማለፍ ይፍጨረጨራል። ዘመኑ የዚህ (ብር እንደሚቆጥር አውራ ጣቱንና ጠቋሚ ጣቱን እያፋተገ) መሆኑ እየታወቀ ላም ባልዋለበት ኩበት ይለቅማል፤›› ይላል። ከጎኑ የተቀመጠ ጎልማሳ ልጁ ገንዘብ በገነነበት ዘመን ሐሳብ ለማንጠር በመፍጨርጨሩ በራሱ ሲበሳጭ ይታያል። የጭውውቱና የሚነሱት ሐሳቦች ጉራማይሌነት ሰው በትክክል የሚያስበውንና የሚፈልገውን ማወቅ እንደተሳነው ያሳብቁበታል። መንገድ ሀቅን ሁሉ ዘርግፎ ታዘቡት ይለናል። እንሄዳለን እኛ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሜክሲኮ የቀድሞ ገጽታዋ በባቡር መስመር ዝርጋታው ምክንያት ከተለዋወጠ ከራርሟል። የተሳፈርንበት ‘ሃይገር’ አውቶብስ ሾፌር ከሞገደኝነቱ ረገብ ብሏል። ‹‹አንዴ ፈጽመን ያሰብንበት ላንደርስ ዘለዓለም መጓዝ…›› ይላል አጠገቤ የተቀመጠው ልጅ። ስልቹነት ከዕድሜው በላይ ተጭኖት አያለሁ። ለነገሩ ማን ያልተጫነበት አለ? ‹‹ወራጅ›› ይላል አንዳንዱ። ቸኩሏል። ‹‹ቆይ ቦታ ይያዝ!›› ይላል ወያላው። ‹‹እሰይ ደርሳችው ሕግ አክባሪ ሆናችሁ ደግሞ?! ምነው ሲያሰኛችሁ መሀል መንገድ ገትራችሁ ትጭኑን የለም እንዴ?›› አለው አንድ ግልፍተኛ። ‹‹መጫንና ማውረድ ይለያያላ!›› አለ ወያላው እያፌዘ። ‹‹ለነገሩ እውነትህን ነው። መጫንና ማውረድ አንድ አልሆን ብሎ አይደል እንዴ ሕገወጡ የበዛው። ሙሰኛው እንደ አሸዋ፣ ፍትሕ የሚሻው እንደከዋክብት የበዛው? መጫንና ማውረድ አንድ አልሆን ብለው ነው!›› እያለ ብቻውን ማነብነቡን ቀጠለ ሰውዬው። የተሳፈርንበት ሃይገር አውቶቡስ ቦታ ከመያዙ ደግሞ ለመውረድ ግብግቡ አየለ። ‹‹ኧረ ጎበዝ ቀስ በሉ። ስንሳፈር ግብግብ ስንወርድ ግብግብ?›› ብሎ ጎልማሳው ተች። ለጎልማሳው ሒስ ጆሮ የሚሰጥ የለም። ግብግቡ ቀጠለ። ቅድሚያ መሰጣጣት፣ መከባበርና መደማመጥ ደበዘዘ። አጠገቤ ተቀምጦ የነበረው ልጅ ‹‹ምነው እንዲህ የሚያልቀው መንገድ ሁሉ ጠባሳ በጠባሳ ሆነ?›› አለኝ። መልስ አልነበረኝም። በዚህች ምድር የማውቀው ሲወርዱና ሲወጡ ግብግብ መሆኑን ነው። መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት