Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ አራት መቶ ሺሕ ብር የሚጠጋ የሰብል መድን ካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ለሰብልና ለእንስሳት ካሳ እስካሁን ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን ገልጿል

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በአገሪቱ ለሚገኙ ዋና ዋና አምራች አካባቢዎች ከሰባት ዓመት ወዲህ የሰብል መድን ሽፋን መስጠት መጀመሩን አስታውሶ፣ በዚህ ዓመት በዝናብ እጥረት ምክንያት የሰብል ምርታቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ገበሬዎች 380 ሺሕ ብር የሚጠጋ የመድን ካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ፡፡

የመድን ድርጅቱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ በአዳሚ ቱሉ እና በጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪ ለሆኑ 400 ገበሬዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት የመድን ካሳ ክፍያ ተፈጽሞላቸዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ብቻ ከ4400 በላይ የሰብል አረቦን የሸጠው ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ የመድን ሽፋኑን የገዙት በአብዛኛው ጤፍ፣ በቆሎና ስንዴ አምራቾች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት በኤልኒኖ ምክንያት በተከሰተው ድርቅ ሰብሎቻቸውን ላጡ ገበሬዎች አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካሳ መክፈሉን አስታውቋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰብሎች መድን መስጠት ከተጀመረ ጀምሮ፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ)ን ጨምሮ በርካታ የረድዔት ድርጅቶች በሚሰጡት ድጋፍ አማካይነት የሰብል ምርትና የእንስሳት ሀብት የመድን ሽፋን መስጠት እየተዘወተረ መምጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡

በ48 የኦሮሚያ ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሰብል መድን ሸፋን እየሰጠ የሚገኘው ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ ከአንድ መቶ ብር ጀምሮ አምራቾች እስከቻሉት ድረስ መግዛት የሚችሉበትን የሰብል የመድን አረቦን እንደሚሸጥ አስታውቋል፡፡ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለሰጠው የሰብል መድን ሽፋን፣ የአራት ሚሊዮን ብር ካሳ ክፍያ መፈጸሙን መድን ኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች