በዓለም ዙሪያ ስለግሎባላይዜሽን የተባሉ ነገሮች በሙሉ ፉርሽ እየሆኑ ነው፡፡ ዓለምን አንድ የማድረግ ዓላማ ሰንቆ ላለፉ ሁለት አሠርት ዓመታት ብዙ የተባለለት ግሎባላይዜሽን፣ በአሜሪካና በአውሮፓ በዚህ ዘመን እየተከሰቱ ባሉ አዳዲስ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰቦች እየተለወጠ ነው፡፡ ዓለምን አንድ መንደር የማድረግ ሐሳብ የነበረው የሊበራል አስተሳሰብ፣ በምዕራብ አገሮች ውስጥ እየታዩ ባሉ ብሔርተኞች እየመከነ ነው፡፡ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሳይታሰቡ ምርጫ ያሸነፉበት፣ በምዕራብ አውሮፓ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት የወጣጭበት ሕዝበ ውሳኔ፣ በተለያዩ አገሮች ውስጥ ፅንፈኛ የቀኝ ክንፍ ፓርቲዎች እየገነኑ መውጣት፣ ስደተኞችን ከመጥላትና ከመሳሰሉት አንፃር ዓለማችን በመለወጥ ላይ ናት፡፡ ከዚህ ለውጥ ጋር የሚጣጣሙ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መቀየስ ብልህነት ነው፡፡ ቀደም ሲል በተያዙ አመለካከቶችና እምነቶች ላይ ድርቅ ማለት ለዘመኑ አይመጥንም፡፡
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማትን፣ የዴሞክራሲ ግንባታንና ሰላምን ማረጋገጥ በከፍተኛ ደረጃ ኋላቀርና የድህነት አዘቅት ውስጥ ለምትገኘው አገር የህልውና ጉዳይ መሆኑ አጠያያቂ እንዳልሆነ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለአገሪቱና ለሕዝቡ ህልውና ቁልፍ ለሆኑት ጉዳዮች ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት አለበት ይላል፡፡ መንግሥት የሚከተለው አጠቃላይ አገራዊ የፖሊሲ አቅጣጫም ይህንን መሠረታዊ እውነታ በሚገባ ያገናዘበ ካልሆነ በስተቀር፣ አገራዊ ህልውናና ደኅንነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መውደቁ እንደማይቀር ያብራራል፡፡ አሁን ካለው የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለአገር ህልውና አሥጊ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን በሚገባ አውቆ መዘጋጀት ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ይበጃል፡፡ ከአገሮች ጋር ከሚኖር የሁለትዮሽ ግንኙነት ጀምሮ በበርካታ ውስብስብ ግንኙነቶች የሚስተዋሉ አስቸጋሪ አዳዲስ ክስተቶች ለለውጥ የሚያነሳሱ ናቸው፡፡
በምዕራቡ ዓለም እየተለወጠ ካለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በተጨማሪ፣ ከጎረቤት አገሮች ጀምሮ ኢትዮጵያ ያለችበት የጂኦ ፖለቲካ ቀጣና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ በጎረቤት ደቡብ ሱዳን ግጭትን አስወግዶ ሰላም ለማስፈን የሚደረገው እንቅስቃሴ በርካታ እጆች እየገቡበት መቋጫ ማግኘት አልቻለም፡፡ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት አሁንም አስተማማኝ አይደለም፡፡ በየመን በሚካሄደው ጦርነት ሳቢያ የባህረ ሰላጤው አገሮች በአካባቢው የሚያደርጉት ጤናማ ያልሆነ ማንዣበብና የኤርትራ መንግሥት አንገቱን ቀና ማድረግ መጀመር ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ አደጋ የሆነው የሽብርተኝነት መስፋፋት ራሱን የቻለ ደንቃራ ነው፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶችና ጦርነቶች በመቻቻልና በሰላም አብሮ ለመኖር የማይቻልበት ጊዜ ላይ ለመደረሱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በዚህ እሳቤ አገርን ከአደጋ ሊከላከሉ የሚችሉ የቤት ሥራዎችን ማከናወን ካልተቻለ ለጥቃት ያጋልጣል፡፡ ሁሉንም እንደ አመጣጡ ማስተናገድ የሚቻለው በቂ ዝግጅት ሲደረግ ብቻ ነው፡፡
በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ፣ በእስያም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካም ሆነ በላቲን አሜሪካ ሕዝብና መንግሥታት እየተጣጣሙ ላለመሆናቸው ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ መንግሥታት ለሕዝብ የገቡትን ቃል ባለማክበራቸው ምክንያት የተለመደውን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ዘይቤዎች የሚጋፉ አዳዲስ አስተሳሰቦች እየተቀነቀኑ ነው፡፡ ስደተኞችን ከአገር ማባረር ጀምሮ እስከ የነጭ የበላይነትን ማስታጋባትና በማኅበረሰቦች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት ማሻከር እየተለመደ ነው፡፡ መንግሥታት እየተለወጠ ካለው የዓለም ዘይቤ ጋር እኩል መራመድ እያቃታቸው መጪውን ዘመን ሊያከብዱ የሚችሉ ሥጋቶች እየታዩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለአገር የሚጠቅሙ አስተሳሰቦችን ያራምዳሉ የሚባሉ ፓርቲዎች እየተገፉ፣ አክራሪዎችና ፅንፈኞች የሚመሩዋቸው እየጎለበቱ ነው፡፡ የሕዝብን ዘለቄታዊ ጥቅም በመወከል ስም በምርጫ ሥልጣን ላይ ሲወጡ እየታዩ ነው፡፡ ይህ ወዴት ያመራል? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡
በሕዝብና በመንግሥት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ በአገራችን ባለፈው አንድ ዓመት ምን እንዳጋጠመ ይታወቃል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮች መነሻቸው በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተፈጠረ ቅራኔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ያለፈበት፣ የብዙዎች አካል የጎደለበትና ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት የወደመበት አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ይህም ችግር አሁን ላለንበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዳርጎናል፡፡ ካለፈው ስህተት በመማር አንድም የሰው ሕይወት የማይጠፋበት አሠራር እየተዘረጋ ነው ወይ? የዴሞክራሲ ምኅዳሩ አሳታፊነት ላይ ምን እየተሠራ ነው? በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ የሚታየው ብሶት የተላበሰ ቅሬታ መልስ እያገኘ ነው ወይ? በዓለም ዙሪያ ሕዝብ በመንግሥታት ላይ እያሰማ ካለው እሮሮ አንፃር የአገራችን አጠቃላይ ሁኔታስ ምን ይመስላል? በአገሪቱ ውስጥ ከተከሰተው ችግርም ሆነ በዓለም ዙሪያ እየታየ ካለው ክስተት ምን ያህል ትምህርት ተገኝቷል? አደገኛ ክስተቶች እንደ ጊዜያዊና ኃላፊ ነው የሚታዩት? ወይስ ዳግም እንዳይከሰቱ በቂ ዝግጅት ይደረግባቸዋል? ወዘተ የመሳሰሉት በሚገባ ካልተጤኑ መጪው ጊዜ ፈጽሞ ልክ አይሆንም፡፡ ለአገርም ለሕዝብም ህልውና ጠንቅ ስለሆነ፡፡
የአገሪቱ የውጭና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፣ የፖሊሲው የትኩረት አቅጣጫ በውጭ በሚካሄድ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ከሆነ ትርጉም ያለው ፋይዳ አይኖርም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ወሳኝ የሆኑን ውስጣዊ ችግሮች በበቂ ሁኔታ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ውስጣዊውንና ውጫዊውን ሁኔታ ማጣጣም ተገቢ ነው፡፡ ለልማቱ የሚደረገውን ርብርብ ያህል ለዴሞክራሲውም መደረግ አለበት፡፡ ልማቱን አስቀድሞ ዴሞክራሲን መዘንጋት ወይም ችላ ማለት ለአገር ህልውና ጠንቅ መሆኑ ከሚገባው በላይ ታይቷል፡፡ ለሁሉም ዜጋ እኩል የሆነችና ማኅበራዊ ፍትሕ የነገሠባት አገር እንድትኖር ደግሞ የአጠቃላይ ሕዝቡ ሁለገብ ተሳትፎ የግድ ነው፡፡ ሕዝቡ በአገሩ የጋራ ጉዳይ ወሳኝ ተሳትፎ እንዲኖረው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት የሚሳተፉበት ለሁሉም የተመቻቸ ምኅዳር እንዲፈጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት የሚያግዙ መድረኮች በስፋት እንዲያብቡ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ጨምሮ በርካታ መሠረታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት በተግባር እንዲረጋገጥ፣ ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲኖር ተገቢው ጥረት መደረግ አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ የተቃኙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲቀረፁ፣ የአገሪቱን ውስጣዊ ሁኔታ በሚገባ ያገናዘበ የውጭና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አስተማማኝ ይሆናል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ህልውና ሲባል ከልማዳዊ አሠራሮችና ከኋላቀር ድርጊቶች በመላቀቅ፣ ለአጠቃላይ ሕዝቧ የምትመች አገር ግንባታ መሠረት መጣል ተገቢ ነው፡፡ የአገርና የሕዝብ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው እየተለወጠ ካለው ዓለም ጋር መጣጣም የሚያስፈልገው!