Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአሜሪካ ኩባንያ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጠረ

የአሜሪካ ኩባንያ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጠረ

ቀን:

ሌጀንደሪ ሜጋ ኮርፕ የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ከኢትዮጵያ መከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅትና የመከላከያ የግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ የአሥር ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ተስማማ፡፡

ድርጅቶቹ ዓርብ ታኅሳስ 14 ቀን ከቀትር በኋላ በሸራተን አዲስ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ሌጀንደሪ መከላከያ ምርቶች አክሲዮን ማኅበር የተሰኘ አዲስ ኩባንያ በኅብረት መመሥረታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አዲስ የተመሠረተው አክሲዮን ማኅበር 51 በመቶ በአሜሪካውያን ሲያዝ፣ ቀሪው 49 በመቶ በመከላከያ ኮንስትራክሽንና በመከላከያ የግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅቶች የተያዘ ነው፡፡ አዲሱ ኩባንያ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጊዜና ወጪን የሚቆጥቡ የግንባታ ግብዓቶችን እያመረተ፣ ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እንደሚያቀርብ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

የሌጀንደሪ ሜጋ ኮርፕ መሥራችና ሊቀመንበር ሄክቶር ሬይስ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የወሰነው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች አገር በመሆኗ ነው ብለዋል፡፡ ኩባንያቸው ባካሄደው ጥናት የመከላከያ ኮንስትራክሽንና የመከላከያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅቶች ትክክለኛ አጋር መሆናቸውን ማረጋገጡን አክለዋል፡፡

አዲስ የተመሠረተው ኩባንያ የሚያቀርባቸው ዘመናዊ የግንባታ ግብዓቶች የፕሮጀክት ወጪን ከ20 እስከ 30 በመቶ፣ የግንባታን ጊዜ ደግሞ በ40 በመቶ እንደሚቀንሱ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ምርቶቹን ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ እንደሚያቀርብ ገልጸው፣ በአዲስ አበባ ለሚካሄዱ የኮንዶሚኒየምና የሌሎች ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልዳይ በርሄና የመከላከያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻምበል መብራቱ ለምለም፣ ድርጅቶቻቸው ከሌጀንደሪ ሜጋ ኮርፕ ጋር አብረው በመሥራታቸው በቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሌጀንደሪ ሜጋ ኮርፕ በመሠረተ ልማት ዘርፍ የተሰማራ የአሜሪካ ኩባንያ ሲሆን በአፍሪካ በካሜሩን፣ ደቡብ አፍሪካና ጋቦን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅትና የመከላከያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት እ.ኤ.አ. 2010 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በ1.3 ቢሊዮን ብር ካፒታል በአዲስ መልክ የተቋቋሙ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 777,634,298 ብር በገንዘብና በዓይነት የተከፈለ ካፒታል ነው፡፡ የሁለቱ ድርጅቶች ዓመታዊ ገቢ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

የመከላከያ ኮንስትራክሽን በርካታ የመከላከያ ሕንፃዎችን የሚገነባ ሲሆን፣ እጅግ አስቸጋሪ የተባሉ መንገዶችን በአፋር በረሃ ዳሎል አካባቢ በመገንባት ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...