Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከ280 በላይ ተጠርጣሪዎችን በታክስና በንግድ ማጭበርበር መያዙን ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጥቅምት 1 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኙ 12 የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች አማካይነት በተካሄደ ኦፕሬሽን፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ አራት ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ጨምሮ 281 ተጠርጣሪዎች በፍትሐ ብሔርና በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርጓቸውን የታክስና የንግድ ማጭበርበር ተግባር ሲፈጽሙ መያዙን አስታወቀ፡፡ 

የባለሥልጣኑ የትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በታክስና በንግድ ማጭበርበር ተግባራት፣ በኮንትሮባንድና በመሳሰሉት ወንጀሎች ውስጥ የተሰማሩ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ከሕዝብ በሚደርሰው ጥቆማ መሠረት እየተከታተለ ለሕግ ያቀርባል፡፡ በመስከረምና በጥቅምት ወራት በተካሄዱ ኦፕሬሽኖች በርካታ የወንጀል ተግባርትን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የኦፕሬሽን ዘመቻ ከተደረገባቸው 136 ድርጅቶች ውስጥ 120ዎቹ በንግድና በታክስ ወንጀሎች ተጠርጣሪ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በዚህ መሰል ድርጊት የተሳተፉ 181 ግለሰብ ተጠርጣሪዎችም መያዛቸውንና ጉዳያቸው ወደ ወንጀል ምርመራ መላኩን አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡ ከሸቀጣ ሸቀጥ እስከ ሕንፃ መሣሪዎች ንግድ፣ ከመጠጥ እስከ ጌጣጌጥ ንግድ ባለው ሥራ መስክ የሚንቀሳቀሱ 59 ድርጅቶች ደረሰኝ ሳይቆርጡ ሲሠሩ መገኘታቸውን፣ በዚሁ ተግባር የተሳተፉ 99 ተጠርጣሪ ግለሰቦችም በወንጀል እንዲጠየቁ የሚያበቃ ማስረጃ ተገኝቶባቸው ጉዳያቸውን ለሚያጣራው ክፍል መተላለፋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ደረሰኝ አለመቁረጥ በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል ሲሆን፣ በግብር አዋጁ መሠረት ባልተቆረጠው እያንዳንዱ ደረሰኝ ከ25 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል፡፡ በመሆኑም 99 ተጠርጣሪዎች የ50 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸው፣ ለወንጀል ምርመራ ክፍል መተላለፋቸውን አቶ ኤፍሬም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዛፒ ጃንግዥ ዞንግሚ፣ ስሪኤም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ቦክራ ኮንስትራክሽን፣ ሳርፈ ቢዝነስ የተባሉትን ከፍተኛ ግብር ከፋይ ድርጅቶች ጨምሮ ሰላም ሳህሌ የተባለ በሥጋ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ድርጅት የተጭበረበረ ደረሰኝ ሲጠቀሙ ተደርሶባቸዋል ተብለው በጥርጣሬ የተያዙ ናቸው፡፡ የተጭበረበረ ደረሰኝ ያሳተመ፣ ያዘጋጀ፣ ያተመና ያሰራጨ የ100 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት የተደነገገ ሲሆን፣ ከሰባት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ የወንጀል ተግባር ስለመሆኑም በሕጉ ተቀምጧል፡፡

በተለይ ደረሰኙ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያለው ከሆነም ደረሰኙ ላይ ባለው ዋጋ መሠረት የገንዘብ ቅጣቱ የሚጣል ሲሆን፣ ከአሥር እስከ 15 ዓመታት የሚያስቀጣ ድንጋጌም እንደሰፈረ ተብራርቷል፡፡ በመሆኑም አምስቱ ድርጅቶች ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ አቶ ኤፍሬም ጠቁመው፣ በዚህ ሳቢያ ያደረሱትን ጉዳት ለማወቅ የኦዲት ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች