Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዮድ አቢሲኒያ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል የሚል አቤቱታ ለመንግሥት አቀረበ

ዮድ አቢሲኒያ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል የሚል አቤቱታ ለመንግሥት አቀረበ

ቀን:

  • ጥርጣሬውን ወደ አቶ ሰይፉ ፋንታሁን ማድረጉን ሰነዶች ይጠቁማሉ

የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ታዋቂ በመሆን ‹‹የኢትዮጵያ የባህል አምባሳደር›› ተብሎ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተሰየመው ዮድ አቢሲኒያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ‹‹የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል›› በማለት አቤቱታ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ማቅረቡ ታወቀ፡፡

ዮድ አቢሲኒያ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቤቱታውን ማቅረቡን የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ ኮሬ ፊርማ የተሠራጨው የአቤቱታ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ድርጅቱ በተሸለመበት የንግድ ሥራ ያገኘውን መልካም ስምና ዝና ለማጉደፍ፣ ጤናማ የንግድ ውድድር ማድረግ ከተሳናቸው የዘርፉ ተሠላፊዎች ጥቃት ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡ በኤፍ ኤም 102.1 የ‹‹ታዲያስ አዲስ›› ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ ሰይፉ ፋንታሁን፣ ከስቱዲዮ በቀጥታ ወደ ዮድ አቢሲኒያ ስልክ በመደወል በአገሪቱ ባህል ያልተለመደ መረጃ አስተላልፎ እንደነበር በአቤቱታው ተገልጿል፡፡

አቶ ሰይፉ የድርጅቱን ሠራተኛ ለ20 የቻይና እንግዶች በ10,000 ዶላር የውሻ ጥብስ እንዲዘጋጅለት መጠየቁን የሚጠቁመው ሰነዱ፣ በወቅቱ ለስልኩ ምላሽ የሰጡት ሠራተኛ ‹‹ይኼንን ለአገራችን፣ ለባህላችንና ለእምነታችን አፀያፊ የሆነ ተግባር አንፈጽምም፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስታውሷል፡፡

ኅዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ደግሞ በማኅበራዊ በድረ ገጽ፣ ‹‹‹ቻይናዊው ዮድ አቢሲኒያ ውሻ ሊያስጠብስ ታዲያስ አዲስ ሽወዳ›› የሚል መረጃ መለቀቁንና በሌላ ቦታ ደግሞ ማንነታቸው የማይታወቅ አምስት ተመሳሳይ ቻይናውያንና የአቶ ሰይፉ ፋንታሁን የሚታይበት ፎቶ ለሕዝብ መሠራጨቱንም ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ድርጀቱ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያገኘውን ታዋቂነት እጅግ የሚያረክስ ዘመቻ እንደተከፈተበት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ገልጿል፡፡

በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተሠራጨው ሐሰተኛ መግለጫ ቀደም ብሎ በአቶ ሰይፉ ከተሠራጨው ጋር ተመሳሳይነት ስላለው፣ ድርጅቱ ጥርጣሬውን በአቶ ሰይፉ ፋንታሁን ላይ ማድረጉም የተሠራጨው የአቤቱታ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ ስለጉዳዩ ለማጣራት የዮድ አቢሲኒያ ኃላፊዎች አቶ ሰይፉ ምሥላቸው በድረ ገጽ ስለሚታይ፣ እሳቸው መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ወይም ከጥርጣሬ ለማውጣት፣ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ባለመስጠታቸው ጥርጣሬያቸውን ይበልጥ እንዳጠናከረው ለተቋማቱ በቀረበው ደብዳቤ ላይ ገልጸዋል፡፡

ዮድ አቢሲኒያ የውጭ አገር መንግሥታት ልዑካንን፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ድርጅቶች ተወካዮችንና በርካታ ቱሪስቶችን እያስተናገደ የሚገኝና የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ በማስገኘትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኝ ድርጅት በመሆኑ፣ መንግሥት የሕግ ጥበቃ ሊያደርግለት እንደሚገባ በአቤቱታው ማመልከቱንም ሰነዱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በድርጅቱ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 607 እና 608 የሚያስጠይቅ በመሆኑ አቤቱታ የቀረበላቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣  በማስረጃ ተደግፎ የቀረበላቸውን አቤቱታ መርምረውና አጣርተው ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስዱ ድርጅቱ መጠየቁ በአቤቱታው ተገልጿል፡፡

ዮድ አቢሲኒያ ጥርጣሬ ያሳደረበትን አቶ ሰይፉ ፋንታሁንን ሪፖርተር አነጋግሮ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ከስምንት ዓመታት በፊት ስልክ በመደወል ‹ፕራንክ› (ማሞኘት) አድርጓል፡፡ በወቅቱ የድርጀቱ ሠራተኛ እውነተኛና ድርጅቱ የሚሠራውን ባህልንና እምነት የጠበቀ ተግባር በማንፀባረቃቸው በድርጅቱ ባለቤት ጭምር መሸለማቸውን ገልጿል፡፡

በፌስቡክ ተለቀቀ ስለተባለው መግለጫ የሚያውቀውና የሰማው ነገር እንደሌለ የገለጸው አቶ ሰይፉ፣ ባለቤት በሌለው ፌስቡክ 20 እና 30 አድራሻዎች በአንድ ሰው እየተከፈቱ ሐሰተኛ መረጃ በሚቀርብበት በአሁኑ ጊዜ፣ ‹‹የአንተ ነው የእከሌ ነው፤›› ማለት እንደማይቻል ተናግሯል፡፡ ያናገረው ማንም የለም እንጂ ለሚያናግረው ማንኛውም አካል ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾ፣ ስለሚባለው ነገር ግን ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት አቶ ትዕዛዙ ኮሬን ሪፖርተር አነጋግሯቸው የድርጅታቸውን ስም የማጥፋት ዘመቻ መጀመሩን አረጋግጠው፣ በሕግ ሁሉንም ምላሽ እንደሚያገኙ እምነታቸው በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ሕግ ስለወሰዱት መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሕግ አማካሪና ጠበቃቸውን አቶ ተስፋዬ ዘውዴን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ በዮድ አቢሲኒያ ላይ እየተፈጸመ ያለው የስም ማጥፋት ወንጀል ከባድ መሆኑን ጠቁመው፣ ጉዳዩን ወደ ሕግ የወሰዱት በመሆኑ ለጊዜው ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...