የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2010 በጀት ዓመት ከ870 በላይ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን 13 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ለማስጀመር የሚያስችለውን የጨረታ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ፡፡
ከባለሥልጣንኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በበጀት ዓመቱ ግንባታቸው እንደሚጀመር ከሚጠበቁትና በአሁኑ ወቅት የጨረታ ሒደታቸው በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኙት 13 መንገዶች ውስጥ፣ ስድስቱ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ሰባት መንገዶች ደግሞ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በሱማሌ ክልሎች የሚገነቡ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ሆኖም ባለሥልጣኑ የበጀት ዓመቱ እስኪጋመስ ድረስ ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ ምንም የግንባታ ውል አለመፈጸሙ አዲስ ነገር ሆኗል፡፡ ምክንያቱም በቀደሙት ዓመታት ባለሥልጣኑ እስከ በጀት ዓመት አጋማሽ ድረስ የመንገድ ግንባታ ውላቸው ይፈጸማል ካላቸው ፕሮጀክቶች ቢያንስ አንድ ሦስተኛውን ይፈጽም ስለነበር ነው፡፡
በጨረታ ሒደት ላይ ከሚገኙትና በኦሮሚያ ክልል ከሚገነቡት ስድስት መንገዶች ውስጥ የሐረር-ኮምቦልቻ-ኤጀርሳ ጎሮ-ፋኛን ቢራ 97.2 ኪሎ ሜትር መንገድ አንዱ ነው፡፡ የኢተያ-ሮቤ-ሴሩ (ሎት ሁለት)፣ ሮቤ-ሴሩ 68.3 ኪሎ ሜትር መንገድና ከመልካ ጀብዱ-ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ድረስ ያለው መንገድም በቅርቡ የግንባታ ኮንትራት ስምምነታቸው ይፈጸማል ከተባሉት መንገዶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ በአማራ ክልል ደግሞ የደበርቅ-ዛሪማና የጅሁር-ደነባ-ለሚ መገንጠያ፣ ጉፍ ጉፍቱ-ወረ ኢሉ-ደጎሎ (ሎት ሁለት) መንገድ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡ በሶማሌ ክልል ውስጥ በበጀት ዓመቱ ለመገንባት የታቀደውና አሁን በጨረታ ሒደት ላይ መሆኑ የተነገረለት የመንገድ ፕሮጀክት ከጨረቲ-ጎሮቢክሳ- ጉርደምሌ ድረስ የሚዘልቀው የ102 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ነው፡፡
እነዚህ መንገዶች በቅርቡ የጨረታ ውጤታቸው ታውቆ ግንባታ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡ ባለሥልጣኑ በ2010 በጀት ዓመት ግንባታቸውን ለማስጀመር በዕቅድ ከያዛቸው 69 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ እስካሁን ምንም ዓይነት የኮንትራት ስምምነት ያላደረገ ሲሆን፣ ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ ምንም ዓይነት የግንባታ ውል አለመፈጸሙ ለባለሥልጣኑ አዲስ ነገር መሆኑ ታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ የበጀት ዓመቱ እስኪጋመስ ድረስ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ የግንባታ ስምምነት ያልፈጸሙበት ምክንያት ከገንዘብ እጥረት ጋር እንደሚያያዝ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች መንግሥት ግንባታዎችን ለማቀዛቀዝ ካለው ፍላጎት አንፃር ሊታጠፉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ነው ይላሉ፡፡ ሆኖም ባለሥልጣኑ ባለፈው በጀት ዓመት ውላቸው ሳይፈጸም የቀሩ ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ግን መፈራረሙን አስታውቋል፡፡ እነዚህ ዘጠኝ መንገዶች በጥቅሉ 441.82 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ሲሆን፣ መንገዶቹን ከሚገነቡ ኮንትራክተሮች ጋር ስምምነት ያደረገበት ዋጋም 8.58 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከዘጠኙ መንገዶች ውስጥ አራቱን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በጨረታ አሸናፊ ሆነው ተረክበዋል የተባሉት አራት የቻይና ሥራ ተቋራጮች ናቸው፡፡ ሲሲሲሲ፣ ቻይና ጌዙባ ግሩፕ ሊትድ፣ ቻይና ቴሲዱ ሲቪል ኢንጂነሪንግና ሁናን ሁዳ የተባሉት ሥራ ተቋራጮች ናቸው፡፡ ከባለሥልጣኑ ጋር ውል የፈጸሙባቸው መንገዶች ደግሞ ሐዋሳ አየር ማረፊያ – ጥቁር ውኃ (ቢሻን ጉራቻ)፣ ቴፒ-ሚዛን፣ የመቐሌ ኢንዱስትሪ መዳረሻ መንገድና የቱሉ ቦሎ-ኬላ መንገዶች መሆናቸውን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
የቻይና ኮንትራክተሮች ከወሰዱዋቸው አራት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ፣ ቀሪዎቹን ያሸነፉት ተክለ ብርሃን አምባዬ፣ ማርኮን ትሬዲንግና ሱር የተባሉት አገር በቀል ኮንትራክተሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ1.8 ቢሊዮን ብር የሁለት መንገድ ፕሮጀክቶች ሲረከብ፣ ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ደግሞ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሁለት መንገድ ፕሮጀክቶችን ሥራ መረከቡ ተገልጿል፡፡ ማርኮን ትሬዲንግ ደግሞ በ554.4 ሚሊዮን ብር መንገድ ለመገንባት ከባለሥልጣኑ ጋር መዋዋሉን የባለሥልጣኑ መረጃ ይሳያል፡፡
እነዚህን መንገዶች ለማጠናቀቅ ከ11 ወራት እስከ ሰባት ዓመታት ይወስዳል ተብሏል፡፡ አራቱ በትግራይ፣ አንዱ በደቡብ፣ ሁለቱ በኦሮሚያ፣ አንድ በአማራ ክልሎች ውስጥ የሚገነቡ መሆናቸውን አንዱ ፕሮጀክት ደግሞ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች የሚያገናኝ መንገድ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡