Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የግብፅ የፓርላማ አባላት ፊርማ ማሰባሰብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ላይ አንዳችም ለውጥ አያመጣም››...

‹‹የግብፅ የፓርላማ አባላት ፊርማ ማሰባሰብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ላይ አንዳችም ለውጥ አያመጣም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ቀን:

የግብፅ የፓርላማ አባላት ፊርማ ማሰባሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የግብፅ ጉብኝት ላይ አንዳችም ለውጥ እንደማያመጣ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በግብፅ ፓርላማ ተገኝተው ለአገሪቱ ሕዝብና ለፓርላማ አባላት ንግግር እንዲያደርጉ የተያዘውን ፕሮግራም ለማስቆም፣ የግብፅ ፓርላማ ተወካዮች የተቃውሞ ፊርማ እያሰባሰቡ እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ኅዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ ‹‹የግብፅ የፓርላማ አባላት ፊርማ ማሰባሰብ በጉብኝቱ ላይ የሚያመጣው አንዳችም ለውጥ የለም፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. በግብፅ ፓርላማ ተገኝተው፣ ለአገሪቱ ሕዝብና ለፓርላማ አባላት ንግግር እንደሚያደርጉ ሲገለጽ ነበር፡፡ አቶ መለስ፣ ‹‹እነዚህ የፓርላማ አባላት ጉዳዮችን በማዛባትና አቅጣጫ በማስለወጥ የሚታወቁ ናቸው፤›› ብለው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብፅ ጉብኝት አሁንም በፕሮግራም የተያዘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሊቢያ ውስጥ እየተፈጸመ ነው የሚባለውን የባሪያ ንግድ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት ቃል አቀባዩ፣ በኮቲዲቯር አቢጃን በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት እንደተደረገና ውሳኔ እንደተላለፈ ገልጸዋል፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ ዋናው መደምደሚያም የሊቢያ መንግሥት ድርጊቱን ለማስቆም አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስድ የሚል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የውሳኔ ሐሳቡ አስፈላጊው ዕርምጃ የማይወሰድ ከሆነ አገሮች በተናጠልም ሆነ በጋራ ዕርምጃ ለመውሰድ ይገደዳሉ ይላል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በግብፅ ካይሮ በሚገኘው ኤምባሲ አማካይነት በሊቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የተመለከተ መረጃ ማፈላለጉን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ወደ ሊቢያ እንደገቡ የጠቆሙት አቶ መለስ፣ ምን ያህልና እነማን እንደሆኑ መለየት እንደማይቻል ግን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ዜጎችን የማውጣት ሥራ ይከናወናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በእንደዚህ ዓይነቱ የዜጎቻችን ስቃይና መከራ የከበሩ የራሳችን ዜጎች በዚህ የሕገወጥ ዝውውር ሰንሰለት ውስጥ አሉ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በሊቢያ በተደረገው የባሪያ ንግድ ላይ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምን ያህል መረጃ አለው? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞቹ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ ‹‹አለን›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ያሉበት ቦታ ከተለየ የት አካባቢ እንደሆነ ቢገለጽ? የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው፣ ‹‹ቦታዎች ተለይተዋል፡፡ ግን ለዜጎቻችን ደኅንነት ስንል አንገልጻቸውም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

ከሳምንት በፊት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ስደተኞች በሊቢያ ተይዘው ከፍተኛ የሆነ ድብደባና እንግልት ሲደርስባቸው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ከተለቀቀ ወዲህ፣ በሊቢያ ያለው ሁኔታ አስፊሪ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አሰቃቂው ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከተለቀቀ በኋላ፣ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከሊቢያ ለማስወጣት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት ዜጎችን ከሊቢያ በማስወጣት ቀዳሚ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በኮትዲቯር በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ በሊቢያ እየተፈጸመ ያለውን የባርነት ንግድ አውግዘው መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሊቢያ መሽጎ በሚገኘው አይኤስ በሚባለው አሸባሪ ቡድን፣ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው አይዘነጋም፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...