Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ የተካተቱት የኬኬ ድርጅት ባለቤት የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተው...

በአቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ የተካተቱት የኬኬ ድርጅት ባለቤት የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተው አጠናቀቁ

ቀን:

‹‹ተከላከሉ የተባልነው ባልተመሰከረብን ክስ ነው››

የአቶ ከተማ ከበደ ጠበቆች

ከግንቦት ወር መጀመርያ ጀምሮ በቁጥጥር ሥር በዋሉትና በመዝገብ ቁጥር 141356 ነሐሴ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ የተካተቱት፣ የሙስና ተግባር ወንጀል ክስ የተመሠረተበት የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ከበደ፣ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተው አጠናቀቁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ ከተማ ክስ የተመሠረተባቸው በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት ኬኬ ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ያስመጣቸውን የተለያዩ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎች፣ ከሚሌ ቅርንጫፍ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ጀምሮ እስከ መዳረሻ አዲስ አበባ ላጋር አቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ድረስ ባሉ የፍተሻ ጣቢያዎች መፈጸም ያለባቸውን የጉምሩክ ሥነ ሥርዓቶች አልፈጸሙም ተብለው ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ጋር በጥቅም በመተሳሰር፣ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በሚሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ተመርጠው ሳይፈተሹ ‹‹ተፈትሸዋል›› የሚል ማረጋገጫ እየሰጣቸው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረጋቸው፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሎ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ ካሰማ በኋላ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን በመስጠቱ፣ አቶ ከተማ ወይም ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በመከላከያነት ከቆጠራቸው ሦስት ምስክሮች ውስጥ ሁለቱን አሰምቷል፡፡

የድርጅቱ ጠበቆች ባስያዙት ጭብጥ፣ ኬኬ ከሚሌ እስከ መዳረሻ ወይም አዲስ አበባ ላጋር ጉምሩክ ድረስ ባሉ የጉምሩክ ፍተሻ ጣቢያዎች የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት መፈጸሙን የሚያረጋግጡ ዲክለራሲዮኖች እንዳሉት፣ በመንግሥትም ላይ ሆነ በሕዝብ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የሚያስረዱላቸው የመጀመርያ ተከላካይ ምስክር ያቀረቡት በወቅቱ የሚሌ ቅርንጫፍ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን አቶ እሸቱ ግረፍን ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ ተመርጠው ያለ ፍተሻ እንዲያልፉ የተደረጉት በአቶ መላኩ ቀጥታ ትዕዛዝ ሳይሆን በሥጋት ሥራ አመራር ኮሚቴ መሆኑን ጨምረው እንደሚያስረዱም ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ ጭብጥ አስይዘዋል፡፡

የመጀመርያ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡ አቶ እሸቱ ግረፍ ማንነታቸውን ለፍርድ ቤቱ ከገለጹ በኋላ፣ ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዱት የሙያ ምስክርነት መሆኑን ገልጸው አስረድተዋል፡፡ ከኅዳር ወር 2003 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ድረስ የሚሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እንደነበሩ ገልጸው ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ በመከላከያ ምስክርነት የቀረቡት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሌሎችና በኬኬ ድርጅቶች ላይ በማስረጃነት ያቀረባቸው የቁጥር ዝርዝር ብቻ በያዙ 52 ገጾች ማስረጃዎች ምን ማለት እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የመጀመርያዎቹ ስድስት ገጾች የአስመጪዎች ስም ዝርዝር የተጻፈባቸው መሆኑን የገለጹት አቶ እሸቱ፣ ሌሎቹ ገጾች ደግሞ የተሽከርካሪ ሰሌዳ፣ የኮንቴይነር ቁጥርና የዲክለራሲዮን መረጣ የተካሄደባቸው ሲሆኑ፣ በእነዚህ ማስረጃዎች ውስጥ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን የሚመለከት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

በኬኬ ተመዝግበው የተገኙ ዘጠኝ ዲክላራሲያኖች ሲሆኑ፣ እነሱም የተገኙት አሲኩዳ (አስመጭ ያዘዘውን ዝርዝር የዕቃ ዓይነት፣ መጠኑንና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት በአግባቡ መፈጸሙ የሚረጋገጥበት ሲስተም) ውስጥ መሆኑን፣ ኬኬ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ያስገባቸው የተለያዩ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎች ተገቢው የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት እንደተፈጸመባቸው የሚያሳዩ መሆኑን ምስክሩ አረጋግጠዋል፡፡

እያንዳንዱ ዲክላራሲዮን (ከዘጠኙ ስምንቱ ዲክላራሲዮኖች) የሚያረጋግጠው ከሚሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ እስከ መዳረሻ አዲስ አበባ ላጋር ፍተሻ ጣቢያ ድረስ ባሉት የፍተሻ ጣቢያዎች ተገቢው ቁጥጥር የተደረገባቸውና ተገቢው ታክስና ቀረጥ የተከፈለባቸው መሆኑን የሚያስረዱ መሆኑን፣ አቶ እሸቱ የሙያ ምስክርነታቸውን ሰነዶቹን እያመሳከሩ ሰጥተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ዲክላራሲዮኖቹን እንደ ማስርጃ አድርጎ ያቀረባቸው የኬኬ ድርጅት ተሽከርካሪዎች በሚሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ እንዳይፈተሹ ተደርገው እንዳለፉ እንደሚያስረዱለት ቢሆንም፣ በሰሌዳ ቁጥርና በኮንቴይነር ቁጥር እንደማይገናኙ ነገር ግን በዲክላራሲዮን ተመሳሳይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ተመሳሳይ የዲክላራሲዮን ቁጥሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማከል የሚለዩት ግን በመዳረሻ ጣቢያ በሚሰጥ ኮድ (መለያ) በመሆኑ፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ማስረጃዎችና የኬኬ ድርጅት ዲክላራሲዮኖች እንደማይገናኙ አስረድተዋል፡፡ አንድ ዲክለራሲዮን ከቀረጥ ነፃ (አቶ ስንታየሁ ተክሌ የተባሉ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ) የገባ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኬኬ ድርጅት ዲክላራሲዮኖች ከአሲኩዳ ሲስተም የተወሰዱና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓቶች የተፈጸሙባቸው ሕጋዊ ሰነዶች መሆናቸውንም ደጋግመው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በዓቃቤ ሕግ በኩል የቀረበው ጥያቄ አግባብ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የኬኬ ድርጅት ተሽከርካሪዎች ሚሌ ላይ እንዳይፈተሹ ተደርገው በመረጣ እንዳለፉ የገለጸ ቢሆንም፣ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም የተጠቀሰባቸው ዘጠኝ ዲክላራሲዮኖች ግን በሚሌ መቆጣጠርያ፣ ጋላፊና ሌሎችም የፍተሻ ጣቢያዎች ተገቢው ፍተሻ ተደርጎባቸው እስከ መጨረሻው መዳረሻ ፍተሻ ጣቢያ ድረስ ሙሉ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት የተፈጸመባቸው መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ሕጋዊ ሰነዶች መሆናቸውን አቶ እሸቱ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

ኬኬ ስለሚያስመጣቸው ማናቸውም ጥሬ ዕቃዎችም ሆነ ጭነቶች በሚመለከት፣ እንኳን ከዋና ዳይሬክተሩ ከቅርብ ኃላፊዎችም የተሰጠም ሆነ የሚሰጥ ትዕዛዝ እንዳልነበረ አቶ እሸቱ አክለዋል፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በወቅቱ አቶ መላኩ የነበሩ ቢሆንም፣ ሥልጣናቸው ስላልሆነ የሚሰጡት ትዕዛዝ እንዳልነበርም ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በመረጣ ያልተስተናገደ ድርጅት መሆኑንና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓትን ፈጽሞ የሚሠራ ድርጅት መሆኑን ጠበቆቹ በየተራ ላቀረቡላቸው ጥያቄ አቶ እሸቱ የሙያ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በመስቀለኛ ጥያቄው ኬኬን የሚመለከቱትን ዘጠኙን ዲክላራሲዮኖች በተግባር ማየታቸውን፣ ሰነዶቹ ከኬኬ ጽሕፈት ቤት ስለመገኘታቸው፣ ዕቃዎች ሁሉ በሚሌ በኩል ብቻ የሚያልፉ ስለመሆናቸው እንዲያረጋግጡ አቶ ለእሸቱ ጥያቄ አቅርቦላቸው፣ ዲክላራሲዮኖቹ መዳረሻ ጣቢያ ሲደርሱ ለሁሉም ጣቢያዎችና ለባንክ ጭምር የሚበተኑ ሰነዶችን በማየት ማረጋገጣቸውን፣ ከተከሳሽ ጽሕፈት ቤትም ማየታቸውን፣ ሁሉም ጭነቶች በሚሌ መቆጣጠሪያ እንደሚያልፉና ለሌሎችም ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጠበቆች ላቀረቡላቸው ድጋሚ ጥያቄና ፍርድ ቤቱ ላቀረበላቸው የማጣሪያ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው፣ የመከላከያ የሙያ ምስክርነታቸውን አብቅተዋል፡፡ የክርክር ማቆሚያቸውን ሁለቱም ወገኖች በጽሕፈት ቤት በኩል እንዳቀረቡ የፍርድ ቀጠሮ እንደሚሰጥ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...