በመስከረም ወር በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተቀሰቀሰ ግጭት ለተፈናቀሉ ከ660 ሺሕ በላይ ዜጎች፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረግና ግጭቱ ዕልባት እንዲያገኝ እገዛ ለማድረግ ፍላጎቱ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት አስታወቀ፡፡
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊና በኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በአራት አገሮች የሚያደርጉት ጉብኝት አስመልክቶ ዓርብ ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
በአሜሪካ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር መፈለጓን፣ እንዲሁም አዲስ አጋርነት በመመሥረት ላይ መሆኗንና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት የአሁኑ የትራምፕ አስተዳደር ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለው፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አሜሪካ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋሮች ጋር በመላው ዓለም አሳሳቢ ለሆነው የስደተኞች ፍልሰት በግንባር ቀደምትነት እገዛ እያደረገች መሆኗን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያም የውስጥ መፈናቀል የደረሰባቸውን ዜጎች በዓለም አቀፍ ስደተኞች እገዛ ውስጥ እንደምታካትታቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹በመላው ዓለም ከ60 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስደተኞች ሆነዋል፡፡ በአፍሪካም እንዲሁ ችግሩ እየሰፋ ነው፡፡ ለአብነት ኢትዮጵያ እንኳን በርካታ ስደተኞችን ከጎረቤት አገሮች ተቀብላ እያስተናገደች ነው፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ ከ660 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ተፈናቅለዋል፡፡ እነዚህን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አንድ ላይ በማካተት ማገዝ የምንችልበትን ሁኔታ እያየን ነው፤›› በማለት ያማማቶ አስረድተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አገሮች ጋር ለመቀናጀትና ለተፈናቃዮችም ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረግ፣ እንደገና እንዲቋቋሙና የተቀሰቀሰው ግጭትም እንዲፈታ አሜሪካ ጉዳዩን እየተከታተለች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ጋር የጀመራቸውን የትብብር መስኮች የማጠናከር ፍላጎትን በተመለከተ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ወር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋሽንግተን 37 የአፍሪካ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን መጋበዙን አስታውሰው፣ አሜሪካ ከአኅጉሪቱ ጋር በኢኮኖሚ ልማት፣ በፀጥታና ደኅንነት፣ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ግንኙነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ አምባሳደር ያማማቶ በጉብኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋርም ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ የአሜሪካ ቁልፍ አጋር መሆኗንና ለአካባቢው ሰላም ለምታደርገው ድጋፍ የአሜሪካ አድናቆት እንደሚቸራት መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡ የአፍሪካን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት አሜሪካ ኢትዮጵያን ማዕከል አድርጋ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡