Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንከኖች መላ ይፈለግላቸው!

  ሰባት ስድስት ያህል ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከ80 በላይ ቋንቋዎች፣ በጣም በርካታ ባህሎች፣ ልማዶች፣ ወጎች፣ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ የተለያዩ እምነቶችና አስተሳሰቦች ባሉባት በዚህች ታሪካዊት አገር ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ማሰብ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ መልክዓ ምድሮች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር፣ የመዳኘትና የጋራ ጥቅሞቻቸውን የሚያስከብሩበት ሕገ መንግሥትም ይኖራቸው ዘንድ የግድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ እኩልነታቸው የሚረጋገጥበት፣ የጋራ ጥቅሞቸው የሚከበሩበት፣ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ ዋስትና የሚያገኙበት፣ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደሩበትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚሰፍንበት፣ ወዘተ. ይሆናል ማለት ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥትም በኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተች ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት በማሰብ ከፀደቀ የ23 ዓመታት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ሰሞኑን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የተከበረው 12ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክብረ በዓልም ሆነ ከዚህ በፊት የተከበሩት በዓላት መነሻቸው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት ዓላማ የሰነቀው የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ ሰነድ የሆነው ሕገ መንግሥት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸውን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ከማካተቱም በላይ፣ የሕዝቡን ትስስርና የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታ አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡

  በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች በተለያዩ ወገኖች ቢነሱም፣ በሕገ መንግሥት ምሁራንም ሆነ ሕገ መንግሥቱን በጥልቀት በተረዱ ዘንድ አንድ የጋራ አቋም አለ፡፡ ይህም ሕገ መንግሥቱ በትክክል በሥራ ላይ ቢውል የብሔር ጥያቄዎችን ከመመለስ ጀምሮ፣ ለመብቶችና ለነፃነቶች የሰጠው ዋስትና ሚዛን ይደፋል የሚለው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንደየተደረሰበት የዕድገት ደረጃ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉት መቼም ቢሆን ወደ ጎን የማይባል ቢሆንም፣ አሁን ባለበት በደረጃ ደግሞ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ለሚባሉ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚችል መካድ አይቻልም፡፡ በርካቶች በተለያዩ ጊዜያት ለማስረዳት እንደሞከሩት፣ በአገሪቱ የሚከሰቱ ብዙዎቹ ችግሮች መንስዔአቸው ሕገ መንግሥቱ በትክክል በሥራ ላይ ባለመዋሉ ነው፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ተግባራዊነት ላይ አሉታዊ አስተያየቶች የሚደመጡትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱን ሕዝብ የኋላ ታሪኮች በመምዘዝ የተዛቡ ግንኙነቶች ታርመው በመላው ሕዝብ የጋራ ፍላጎቶች ላይ የተመሠረተች አገር እንድትፈጠር የሚረዱ ሐሳቦችን ቢያቀነቅንም፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ልዩነቶች ያለ ገደብ በመራገባቸው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን አደጋ ውስጥ ከተውታል፡፡ ልዩነቶች በአግባቡ ተስተናግደው በመከባበርና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ዕውን ማድረግ ሲቻል፣ አክራሪ ብሔርተኝነት ከመጠን በላይ አቆጥቁጦ አገሪቷን ሰንጎ ይዟታል፡፡

  የፌዴራል ሥርዓቱ የመላውን ሕዝብ ፍላጎት ማዕከል አድርጎ ኢትዮጵያን ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች አገር ማድረግ የሚያስችል ዕምቅ አቅም እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ይህ ዕምቅ አቅም በትክክል ሥራ ላይ መዋል የሚችለው ግን ሕገ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን ሲችል ብቻ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከክልሎች የተሰጠውን የውክልና ሥልጣን በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ ሲወጣ፣ ክልሎች ተጠናክረው ሕዝቡን በሥርዓት ሲያስተዳድሩ፣ በየደረጃው ያሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት ሲወጡ፣ ሦስቱ የመንግሥት ዓምዶች (ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው) እየተናበቡ ሲሠሩና እርስ በርሳቸው ቁጥጥር ሲያደርጉ፣ የሕግ የበላይነት የሥርዓቱ ዋልታና ማገር ሲሆን፣ መገናኛ ብዙኃን በነፃነት ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ ወዘተ. አግጥጠው የሚታዩ እንከኖች ይወገዳሉ፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ካለመሆኑም በላይ ተጠያቂነት እየጠፋ፣ በሥልጣን ለመባለግ የሚመቹ ድርጊቶች እየበዙ፣ ሕግ አውጪው አካል አስፈጻሚውን ለመቆጣጠር እያቃተው፣ ሕዝብ ቅሬታ ሲያቀርብ የሚያዳምጥ እየጠፋ፣ በሕግ የተደነገጉ መብቶች እየተጣሱ ነፃነትን የሚጋፉ ሕጎች እየወጡ እሪታ ሲበዛ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተዳፍኖ ዴሞክራሲ መቀለጃ ሲሆን፣ የእኩል ተጠቃሚነት መብት ሲደፈጠጥ፣ ወዘተ. በስፋት ታይቷል፡፡ በእነዚህ ችግሮች ሳቢያም የአገሪቱንና የሕዝቡን ዕጣ ፈንታ የሚፈታተኑ ሥጋቶች ተፈጥረዋል፡፡ ለበርካቶች ሕልፈትም ምክንያት ሆነዋል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ የሕዝብን አብሮነትና ዘመናት የተሻገረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚንዱ ቅስቀሳዎች ተሰምተዋል፡፡

  ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ አንድነት ምሰሶ በመሆን የሕዝቡን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በማጠናከር ረዥም ርቀት የሚያስኬዱ ዓላማዎችን ቢያነግብም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ችግሮች ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ተፈታትነዋል፡፡ ለበርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ምላሽ የሚሰጥ ሕገ መንግሥት ይዞ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት አለመቻል ተጠያቂነትን ማምጣት አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ የወረቀት ጌጥ ሳይሆን የሕጎች ሁሉ የበላይ ሰነድ መሆኑን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ፣ ለሕግ የበላይነት በመገዛት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ እንዲውል ቁርጠኛ በመሆን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች ሳይቀሩ በማስተዋል ማሰብ ያለባቸው፣ መጀመርያ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ሳይሸራረፉ ሥራ ላይ ይዋሉ የሚለውን ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በፌዴራል ሥርዓቱም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ ያሉት ሕገ መንግሥቱ በአግባቡ ተግባራዊ ባለመሆኑ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ በተጨባጭ የሚታዩት ለውጦች ዕውን እንዲሆኑ መሠረት ጥሏል፡፡ የሚታየውን ዕድገትም ለማስቀጠልና ዴሞክራሲ ለመጎናፀፍ ሁነኛ መሣሪያ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዘለቄታዊና አስተማማኝ ሰላም የሚገኘውም ሕገ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይህ በገቢር ሲታይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ የበለጠ ይጠብቃል፡፡

  የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ትስስሩ በጠንካራ መሠረት ላይ ይቆም ዘንድ፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው በመረጡት ሥፍራ የመኖር፣ የመዘዋወር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡ የገዛ ወገንን እንደ መጤ የማየትና የማግለል አጉል ባህሪ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ አይደለም፡፡ ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ ክልሎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬአቸው ሀብትና ንብረታቸውን ተቀምተው የተባረሩ ወገኖች ሰቆቃ አይረሳም፡፡ ከአስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ መገለጫ እሴቶቹ መካከል አንዱ፣ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያግደው የገዛ ወገኑን አቅፎና ደግፎ ማስተናገድ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ደግሞ ማንኛውም ዜጋ በአገሪቱ ውስጥ በፈለገው ሥፍራ መኖርና ሀብት ማፍራት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህንን መሠረታዊ መብት በመጋፋት የተፈጠረው እሮሮ ዛሬም ድረስ ያስተጋባል፡፡ ራሳቸውን ከጎጥና ከመንደር አስተሳሰብ ያላላቀቁ ኃይሎች በማንነት ስም የገዛ ወገናቸውን እንደ ባዕድ ሲያሳድዱ፣ ሲያፈናቅሉ፣ ሲገድሉ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ የብሔር ስም እየጠሩ ሲሳደቡ ሕገ መንግሥትን ከመናቅ በላይ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ አስተዋዩና ኩሩው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ሌላው ቀርቶ ፖለቲከኛ ነን ባዮች በጫሩት ጠብ ግጭት ሲፈጠር፣ እርስ በርሱ እየተደጋገፈና እየተሳሰበ የሰብዓዊነትን ጥግ አሳይቷል፡፡ ለዚህ ምስክሩ ደግሞ በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል የተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭትና መፈናቀል ነው፡፡ የሁለቱ ክልል ሕዝብ እርስ በርሱ ያደረገው መተሳሰብና ከለላ መሰጣጣት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትልቅ ተምሳሌት ነው፡፡

  የሕገ መንግሥት ምሁራን እንደሚሉት ሕገ መንግሥት ጥንካሬዎቹ የሚለኩበት የተለያዩ መሥፈርቶች አሉ፡፡ አንደኛው በአገር ውስጥ ለሚነሱ ጥያቄዎች በብቃት ምላሽ መስጠት መቻል፣ ችግሮች ሲፈጠሩ የሚፈቱበትን ሥልት ማመላከት፣ የወደፊት ተስፋና ሥጋቶችን በብቃት መተንተን፣ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር፣ የአገርን ዘለቄታዊ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ማዕከል ማድረግና የሕግ የበላይነት የሚያሰፍን ሥርዓት መፍጠር የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ በኩረ ሐሳቦች ጠንካራ ሕግ አውጪ (ፓርላማ)፣ አስፈጻሚ (መንግሥት) እና ሕግ ተርጓሚ (የዳኝነት አካል) እንዲኖር ግፊት ያደርጋሉ፡፡ በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚመች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መደላድል ለመፍጠርና የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ዓውድ ለማመቻቸት ይቻላል፡፡ ይህንን በማድረግ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደል፣ የሌብነት መስፋፋት፣ የተጠያቂነት አለመኖርና የመሳሰሉት ሕገወጥ ድርጊቶች ይከስማሉ፡፡ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ፣ መደራጀት፣ ለሁሉም እኩል የሆነ ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ ማግኘት፣ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ መሆን፣ ወዘተ. ቀላሉ ይሆናሉ፡፡ የሁሉም ነገር ማሰሪያ ልጡ የሕግ የበላይነት ብቻ ይሆናል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ደግሞ ይህቺ ታሪካዊት አገር ሞገሥ ታገኛለች፡፡ የሕዝቡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ይጠናከራል፡፡ ደሙ እየፈላ በስሜት በመነሳት ድንጋይ የሚወረውርና ንብረት የሚያወድም ሳይሆን ሥልጡን፣ ሞጋችና በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ትውልድ ይፈጠራል፡፡ ይህ መልካም ፀጋ ደግሞ ለአገር በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ግን አሁን እየታዩ ላሉ አሳሳቢ እንከኖች በሕገ መንግሥቱ መሠረት መላ መፈለግ የግድ ይሆናል!

   

   

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  በቴሌ ብር የማይሠሩ ማደያዎች ቀነ ገደብ ተቀመጠባቸው

  ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለመሥራት እየመከረ ነው በኢትዮጵያ...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...