Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ማስጀመር አልተቻለም

በኦሮሚያ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ማስጀመር አልተቻለም

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም ትምህርት አለመጀመሩ ታወቀ፡፡ በክልሉ የሚገኙ የአምቦ፣ የመቱና የሃረማያ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መማር ማስተማር ሥራቸው አልገቡም፡፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ወርቅነህ ዓርብ ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከማክሰኞ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው የነበረው የመማር ማስተማር ሒደት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡

‹‹ተማሪዎችን አሳምኖ እንዲማሩ ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እየተማራችሁ ነው መጠየቅ የሚገባው ይባላሉ፡፡ ፍላጎታቸው ያን ያህል አይደለም፡፡ በአንድ ጉዳይ ሲያምኑ በሌላ ጉዳይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የሚመራው አካል እከሌ ነው የሚባል ስላልሆነ ለመለየት አስቸጋሪ ነው፤›› በማለት አቶ ተሰማ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከአገሪቱ ሁሉም ክልሎች የመጡ ተማሪዎች ከግቢ ባይወጡም ፈቃደኛ ሆነው ወደ ክፍል መግባት እንዳልፈለጉ አቶ ተሰማ አስረድተዋል፡፡ በጥያቄነት ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከልም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ስለሞቱና ስለተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ፣ እንዲሁም በ2011 ዓ.ም. ተግባራዊ ይሆናል ስለተባለው የመውጫ ፈተና እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከተማሪዎች ጋር በመሰብሰቢያ አዳራሽ መወያየት አስቸጋሪ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ከተማሪዎች ጋር አዳራሽ ገብተን ውይይት እናድርግ ሲባል ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ሻንጣቸውን ይዘው እንወጣለን ብለው ሰብሰብ ሲሉ ነው የምናነጋግራቸው፤›› ብለዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሒደቱ ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ሌላው መቱ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የዩኒቨርሲቲው አመራር ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ለበርካታ ቀናት ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭትና በ2011 ዓ.ም. ይሰጣል በተባለው የመውጫ ፈተና የተነሳ፣ ተማሪዎች ወደ ክፍል ገብተው መማር እንዳቆሙ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

መቱ ዩኒቨርሲቲ የ2010 ዓ.ም. የማስተማር ሥራውን ሲጀምር ተማሪዎች ባነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ ትምህርት ተቋርጦ እንደቆየ የሚታወስ ሲሆን፣ ተፈጥሮ በነበረው ግጭትም የትግራይ ብሔር ተወላጆች ከግቢ ወጥተው ቆይተዋል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን ቢጀምርም፣ አሁንም ተመልሶ መቋረጡን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ትምህርት ከተቋረጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ሌላው የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት አብዛኞቹ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንደሄዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለተቃውሟቸው ዋነኛ ምክንያቶችም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚነሱት ጥያቄዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

በጂማ ዩኒቨርሲቲ የነበረው የመማር ማስተማር ሒደት ከአንድ ሳምንት በላይ ተቋርጦ እንደቆየ መረጃዎች ቢያመለክቱም፣ ከሰኞ ኅዳር 25 ቀን እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በአብዛኛው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባት የማስተማር ሥራው በከፊል እንደተጀመረ ታውቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የውጭ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሲኒየር ዳይሬክተር ወ/ሮ ጨረር አክሊሉ ዓርብ ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአብዛኛው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባታቸው የማስተማር ሥራው ተጀምሯል፡፡

‹‹ከጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች በስተቀር ከሞላ ጎደል የማስተማር ሥራው ተጀምሯል፤›› ያሉት ወ/ሮ ጨረር፣ ‹‹ባለፈው ሁለት ሳምንት የትምህርት ፕሮግራም መቆራረጥ ነበር፡፡ ከሰኞ ጀምሮ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ተጀምሯል፤›› ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ትምህርታቸውን ያረጡበት ምክንያትም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ካነሷቸው ጥያቄዎች ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ከ2010 ዓ.ም. መግቢያ አካባቢ ጀምሮ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከተነሳው ግጭት ጋር ተያይዞ፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞ ሲሰማ ነበር፡፡

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የክልሉ ተወላጆች ጥለው እንዲወጡ ጥያቄ እንዳቀረቡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችን ጥያቄ ተቀብሎ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ ቢያደርግም አሁንም ተቃውሞዎች ቀጥለዋል፡፡

በወለጋ፣ በመቱ፣ በአምቦ፣ በጂማና በሃረማያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት፣ ስለሞቱትና ስለተፈናቀሉት ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም. ተግባራዊ አደርገዋለሁ ያለውን የመውጫ ፈተና ተማሪዎች እየተቃወሙት ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የመውጫ ፈተናው መሰጠቱ እንደማይቀር መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ ተማሪዎች ግን የመውጫ ፈተና መሰጠቱን እየተቃወሙ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ እንዲሰጥ ጥረት ቢደረግም፣ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ለብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል አፋር ክልል በመሄዳቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡ በስልክ አግኝቶ ለማረጋገጥ የተደረገው ሙከራም አልተሳካም፡፡

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...