Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናደም አፋሳሽ ግጭቶች የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤት አለመሆናቸውን ለመተንተን ውይይት ተጀመረ

ደም አፋሳሽ ግጭቶች የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤት አለመሆናቸውን ለመተንተን ውይይት ተጀመረ

ቀን:

በተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ‹‹የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤቶች ናቸው›› ለሚሉ አካላት ምላሽ ለመስጠት፣ መንግሥት የፖለቲካ አመራሩንና ሠራተኞችን ማወያየት ጀመረ፡፡

በፌዴራል መንግሥት ደረጃ 80 ገጾች ያሉትና በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለአወያይ አመራሮች ተበትኗል፡፡

በዚህ መሠረት ሐሙስ ኅዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አመራርና ሠራተኞች፣ ‹‹የዴሞክራሲ አንድነት ግንባታ ሒደትና የወደፊት አቅጣጫዎች›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው በዚህ ሰነድ ላይ የግማሽ ቀን ውይይት አካሂደዋል፡፡

የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አመራሮች በአገሪቱ እየተነሱ ያሉት ግጭቶች የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤቶች ሳይሆኑ፣ የትምክህተኞችና የጠባቦች ሥራ ናቸው የሚሉ ሐሳቦችን አራምደዋል፡፡

በማዕከል ደረጃ የተዘጋጀውን ሰነድ ያቀረቡት የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ገብረ አምላክ እንዳሉት፣ ተፈቃቅሮ የኖረውን ሕዝብ የማጋጨትና ሕይወት የማጥፋት ነገር እየታየ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በእርግጥ ለግጭቶች ምንጭ ነው ወይ? ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊነት እየተገነባ ነው፤›› ያሉት አቶ አባተ፣ ‹‹በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የተደቀኑ ሥጋቶች፣ አደጋዎችንና ፈተናዎችን መመከት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሠራተኞች አሳስበዋል፡፡

ነገር ግን የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሠራተኞች ከተነሳው ርዕሰ ጉዳይ በላይ በጥልቀት የተለያዩ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡

የሚበዙት አስተያየቶች ያጠነጠኑት ሕገ መንግሥቱ ወይም የፌዴራል ሥርዓቱ ለደም አፋሳሽ ግጭት መንስኤዎች ባይሆኑም፣ ነገር ግን ኅብረተሰቡ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ከፈለገ መንግሥት ለማሻሻል መነሳት አለበት በሚለው ላይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይነቀፍ፣ መንግሥት ከሕዝብና ከምሁራን ጋር በጉዳዩ ላይ መነጋገር አለበት ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን እየተነሱ ያሉ ችግሮችን መንግሥት ሁልጊዜ ከጠባብነትና ከትምክህተኝነት ጋር ማገናኘት እንደሌለበት፣ እነዚህ የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰቦች የሉም ባይባልም የግዙፎቹ ችግሮች መነሻዎች አይደሉም የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

በተለይ በአገሪቱ የሰፈነው የሀብት ክፍፍል የሎሌና የጌታ ያህል መራራቁ፣ አገሪቱ ከምታመነጨው ሀብት የሚበዛው ኅብረተሰብ ተቋዳሽ አለመሆኑ፣ በአገሪቱ ሀብት የማፍራት መብት የተደነገገ ቢሆንም፣ ሰዎች ተዘዋውረው መሥራትና ሀብት ማፍራት አለመቻላቸው፣ በኑሮ የሚቸገር ሕዝብ በርካታ በመሆኑ፣ ሙስና (ኪራይ ሰብሳቢነት) መንሰራፋቱ፣ ሥራ አጥነት፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር፣ የፍትሕ መታጣት ተጠቃሽ የግጭት መንስዔዎች ሆነው በሠራተኞች ተወስተዋል፡፡

‹‹ከዚህ በተጨማሪ አንድ ግጭት የሚፈነዳው ወዲያውኑ አይደለም፡፡ ውሎ አድሮ በስሎ ነው፡፡ በዚህ ሒደት መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ ባለመሆኑ ግጭቶች እየፈነዱ ዕልቂት እየተፈጠረ ነው፤›› የሚል አስተያየት በአንድ ተሳታፊ ቀርቧል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ችግር ከመፈጠሩ በፊት መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ቡድን ልኮ ነበር፡፡ ቡድኑ ችግሮችን ፈትቶ ተመለሰ ወይ? ችግሩ ተፈታ ከተባለ በኋላ ያ ሁሉ ዕልቂት ለምን ደረሰ? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ልጆቻችን ዩኒቨርሲቲ በተለይም ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም መማር አልቻሉም፡፡ መንግሥት ተማሪዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች በየደረጃው እንደሚፈቱ በመግለጽ ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ ጥሪ ያቀርባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት ትጀምሩና የሚል ኃይል አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ ልጆቻችን አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ የትምህርት ዘመኑስ እንዴት ሊሆን ነው?›› የሚል ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሠራተኞች መንግሥት ላለፉት 26 ዓመታት የፌዴራል ሥርዓቱን እንዴት ሲመራ ቆየ? የሚል ጥያቄም አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት ሌላ ዘዴ የለም ወይ? የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ የሠራተኞቹን ጥያቄ የተቀበሉት የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ምክትል ሥራ አስኪያጆች አቶ መኮንን አምባዬና አቶ ዘብረህ ያይኖም ናቸው፡፡ ሁለቱ ኃላፊዎች ለሠራተኞቹ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጡም፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ብዙ ጥቅሞች እንዳመጣና ሠራተኞችም የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የሚቃጣ አደጋን እንዲመክቱ በመዘርዘር አስረድተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱም ሆነ የፌዴራል ሥርዓቱ ሰላምን በማስፈን፣ የሕዝቡን ተሳትፎ በመጨመር፣ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ማስቻሉን ከጠቀሷቸው መካከል ይገኛሉ፡፡ በዚህ በተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ ላይ በሁሉም የመንግሥት መዋቅሮች በስፋት ውይይት እንደሚካሄድ የታወቀ ሲሆን፣ ይህ ውይይት በተለያዩ ተቋማት መካሄድ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ