Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዝክረ ሌፍተናት ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ ጎን እንዲቆሙ እንጠይቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዝክረ ሌፍተናት ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ ጎን እንዲቆሙ እንጠይቃለን

ቀን:

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ዛሬ በነፃነት የምንኖርባት አገራችን ኢትዮጵያ፣ በበርካታ አባቶቻችንና እናቶቻችን ጀግንነትና ከብረት የጠነከረ ወኔ፣ ቆራጥነትና ብርቱ መስዋዕትነት በክብርና በኩራት የተረከብናት ነች፡፡

ከቅርብ የታሪካችን ዘመን ብንነሳ እንኳን የቋራው አንበሳ አፄ ቴዎድሮስ ከደባርቅ እስከ መቅደላ ከግብፃውያንና ከእንግሊዝ ጦር ጋር ተፋልመው፣ አፄ ዮሐንስ ከጉራዕ እስከ ጉንደትና መተማ ዘልቀው ከደርቡሾችና ከግብፃውያን ጋር ተናንቀውና አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተው፣ ‹‹አፍሪካዊው የጦር ጄኔራልና ጀግና›› የሚል ክብርን የተጎናጸፉት አሉላ አባ ነጋ በዶጋሊ ግንባር ከወራሪው ጣሊያን ሠራዊት ጋር ተፋልመው፣ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም ከአምባላጌ፣ መቐለ እስከ ዓድዋ ግንባር ድረስ ከበርካታ ውድ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ልጆቿ ጋር ያደረጉት ተጋድሎና ያስመዘገቡት አንፀባራቂ ድል፣ አገራችንን ኢትዮጵያን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ቀንዲልና ፋና እንድትሆን አድርገዋታል፡፡

እንዲሁም የዓድዋውን ሽንፈት ለመበቀል ከአርባ ዓመታት በኋላ አገራችንን የወረረውን ፋሺስት ጣሊያንን ‹በአምስቱ ዓመታት› የመከራ ዘመንም አባትና እናት አርበኞች በበረሃና በዱሩ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ነፃነት ባደረጉት ታላቅ ተጋድሎ ወራሪውን የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በታላቅ ኃፍረትና ውርደት ሽንፈቱን ተከናንቦ ወደመጣበት እንዲመለስ በማድረግ በዓለም መድረክ ነፃነቷ፣ ታሪኳና ክብሯ የተጠበቀች ሉዓላዊ፣ ታላቅ ባለ ታሪክ አገርን አስረክበውናል፡፡

ይህ አኩሪ የኢትዮጵያውያን ታሪክና ጀግንነት በጦር ግንባር ብቻ ሳይሆን፣ በዲፕሎማሲው መስክም ሆነ ከአፍሪካ እስከ ኮሪያ ልሳነ ምድር ድረስ በዘለቀው በኢትዮጵያውያን ጀግኖቻችን የሰላም ማስከበር የተሳካ ዘመቻ፣ አሁንም ድረስ አገራችን በሉዓላዊነቷና በልጆቿ አኩሪ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ያለና የላቀ ስም ያላት አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ክቡርነትዎ ላለፉት ሃያ ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጀግኖቻችን በአኅጉራችን በአፍሪካ በሶማሊያ፣ በላይቤሪያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሩዋንዳ በሰላም አስከባሪነት የጀግንነት ገድል በመፈጸም የአባቶቻችንና የእናቶቻችንን አኩሪ የጀግንነት ታሪክ በመድገም አገራችን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ ስሟና ዝናዋ ከፍ እንዲል አድርገዋታል፡፡ ይኼንን አኩሪ የጀግንነት ታሪክና ቅርስ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረክ በኩራት አንገታችንን ቀና አድርገን የምንተርከውና የምንናገረው ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዓለማችን ሰላም እንዲሰፍን ከባለ ቃል ኪዳን አገሮች ማኅበር /League of Nations እስከ ተባበሩት መንግሥታት /United Nations መመስረት ድረስ ብቸኛ፣ አፍሪካዊትና የጥቁር ሕዝቦች ተወካይ በመሆን ደማቅ የሆነ አሻራዋን ያኖረች፣ የአፍሪካ ሕዝቦች ነፃነት፣ አንድነትና የወንድማማችነት መንፈስ መስፈን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን፣ የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረትን በማቋቋም ግንባር ቀደሙንና ትልቁን ሚና ያተጫወተች የአፍሪካውያን ባለውለታ አገር ናት፡፡

ለአብነትም ለመጥቀስ ያህል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማስፈን ያደረጉትን ጀግንነት፣ ትልቅ አስተዋፅኦና አሁንም ድረስ እያደረጉት ያለውን ጥረት በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድረ ገጽ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፡-

Besides being a seat to various International Nongovernment Organizations (NGOs) and diplomatic seats, Ethiopia is the political capital city of African. This ancient state has been wholeheartedly and constructively contributing to world peace and stability in line with the principles and missions of UN so that the world could enjoy peaceful coexistence. Evidently, it is number one in Africa and fourth largest peace keeping force producer in the world.

ክቡርነትዎ ለዚህ ታላቅ ክብርና ኩራት ካበቁን ባለውለታዎቻችንና ጀግኖቻችን መካከል ደግሞ ባለፈው ዓመት በሞት የተለዩን ‹‹የበጋው መብረቅ›› በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ጀግና፣ አርበኛው ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ናቸው፡፡ እኚህ ታላቅ አርበኛ፣ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በአርበኝነት፣ በውትድርና፣ በጦር አዛዥነትና አዋጊነት፣ በአስተዳዳሪነትና በተለያዩ በርካታ የሙያ ዘርፎች አገራቸውን በቅንነት ያገለገሉ ታላቅ ጀግና ናቸው፡፡

አርበኛው ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦችም ኩራት የሆኑ፣ ታሪክ ሁሌም ስማቸውንና ገድላቸውን በክብር የሚዘክረው፣ የሚያስታውሳቸው ሰው ናቸው፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም፤ ከስምንት ዓመት በፊት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተካሔደበት 70ኛ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በታሰበበት ወቅት የእንግሊዙ የቢቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ የአፍሪካ ጉዳዮች አናሊስት የሆነው Martin Plaut እውቁን ኢትዮጵያዊ ጀግና፣ አርበኛና የጦር መሪ ጀኔራል በተመለከተ ‹‹African Forgotten Soldiers in WWII›› ሲል የፋሽስትንና የናዚን ወራሪ ኃይል በታላቅ ጀግንነት ስለተፋለሙት ኢትዮጵያዊ ጀግና፣ ስለ አርበኛው ሌ/ጀኔራል ጃጋማ ኬሎና ሌሎች አፍሪካውያን የጦር ጀግኖች የጦር ሜዳ ውሎ የሚዳስስ ሰፋ ያለ ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡

በተመሳሳይም ከአራት ዓመት በፊት የዚሁ የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባልደረባ የሆነችው Elizabeth Blunt የተባለች ሴት ጋዜጠኛ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት፣ በሌፍተናት ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ መኖሪያ ቤት ተገኝታ የእኚህን ኢትዮጵያዊ ታላቅ ጀግና ቃለመጠይቅ በማድረግ ‹‹Ethiopian General Who Fought Fascism›› በሚል በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያንን ያስደነቀና ያስደሰተ ሰፊ ዘገባን አስነብባ ነበር፡፡

ባለፈው ዓመት ሕያውና አኩሪ ታሪካቸው ትተውልን በ96 ዓመታቸው በክብር ያለፉትን ኢትዮጵያዊውንና አፍሪካዊውን ጀግና፣ አርበኛ ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎን አኩሪ የተጋድሎ ታሪክ ለመዘከርና ውርሳቸውን ሌጋሲያቸውን ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በማሰብም የአገራችን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የበላይ ጠባቂነት፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት በሆኑት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ሊቀመበርነትና በብርጋዴር ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ዋና አስተባባሪነት የሚመራ አሥር ሰዎች የተካተቱበት የዝክረ ሌፍተናት ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ጊዜያዊ ኮሚቴ አቋቁመን እኚህን ጀግና ለመዘከር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

እኚህን ለኢትዮጵያውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆኑ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ የጦር መሪ፣ ጀግና፣ አርበኛ ለመዘከር የምናደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተም ክቡርነትዎ ለማነጋገር በጽሕፈት ቤትዎ በኩል ደብዳቤ አስገብተን ቀጠሮ ተይዞልን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ክቡርነትዎ ካለብዎት እጅግ የተደራራበ የሥራ ኃላፊነትና የጊዜ መጣበብ የተነሳ የተያዘልን ቀጠሮ መራዘሙንና በቅርብ ክቡርነትዎን ማነጋገር እንድንችል ሌላ ቀጠሮ እንደሚያዝልን በጽሕፈት ቤትዎ በኩል የስልክ መልዕክት ደርሶን ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ክቡርነትዎን ለማግኘትና ስለ ሥራችን እንቅስቃሴ ለመወያየት ተስፋ ያደርግነው ቀጠሮ ከጠበቅነው በላይ በመራዘሙ ምክንያት እኚህ ታላቅ ጀግና ለመዘከር የምናደርገው እንቅስቃሴ ያሰብነውን ያህል መራመድ አልቻለም፡፡ እኚህ ኢትዮጵያዊ፣ ጀግና የጦር መሪ በሞት ከተለዩን መንፈቅ ቢያልፋቸውም ሌላው ቀርቶ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚገኘው መካነ መቃብራቸው እንኳ እስካሁን ድረስ የመታሰቢያ ሐውልት አልቆመላቸውም፡፡ እኚህ ታላቅ ጀግና በመንግሥትም ሆነ በሕዝብ ዘንድ ታላቅ ታሪካቸውና አኩሪ የጀግንነት ሥራቸው እየተዘነጋ የመጣ ይመስላል፡፡

የዝክረ ሌፍተናት ጀኔራል ጃጋማ ጊዜያዊ ኮሚቴ ምንም እንኳ ,ባሳለፈነው ዓመት በ96 ዓመታቸው በሞት የተለዩንን ጀግናውን ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ አርበኛ፣ ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎን አኩሪ ታሪክና ውርስ ለመዘከርና ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በማሰብ የተቋቋመ ጊዜያዊ ኮሚቴ ቢሆንም፣ ኮሚቴያችን በተመሳሳይም ለአገራቸው በተለያዩ የሙያ መስኮች በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ የጀግንነት ሥራ ሠርተው ያለፉና በመሥራት ላይ የሚገኙ የአገርና የሕዝብ ባለውለታ የሆኑ፣ ታሪካቸውና ሥራቸው የተዘነጋ ጀግኖቻችን ተገቢውን ክብርና ሥፍራ እንዲያገኙና ትውልድ እንዲዘክራቸው የበኩሉን እንቅስቃሴ ለማድረግ እየሞከረም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ጀግኖችና አርበኞች ትናንትና ብቻ አይደለም ዛሬና አሁንም ድረስ በርካታ ጀግኖች፣ አርበኞች በተለያዩ ሙያ ዘርፎች ተፈጥረዋል፣ እየተፈጠሩም ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ ዛሬና ወደፊትም ጀግኖችን ለመፍጠርና ለማብዛት ደግሞ የቀደሙ የጀግኖቻችን ሕያው ሥራቸውን፣ አኩሪ ታሪካቸውን ማክበርና ማወደስ፣ መታሰቢያና መታወሻ እንዲኖራቸው ማድረግም የሚገባ ነው እንላለን፡፡ 

ስለሆነም መንግሥት እኚህን በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራቸውን በክብር ካስጠሩ ጀግኖቻችን መካከል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት የሚነሳውን፣ ኢትዮጵያዊውን አርበኛና ጀግና፣ የጦር ጄኔራልና መሪ የሆኑት ሌፍተናት ጃጋማ ኬሎ ተገቢውን ክብርን እንዲያገኙ፣ መታሰቢያ እንዲኖራቸው በማሰብ፣ ሕያው ታሪካቸውን ለመዘከር የምናደርገውን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ክቡርነትዎን ማግኘት እንድንችል በጽሕፈት ቤትዎ በኩል የተያዘልን ቀጠሮ ተግባራዊ እንዲሆንልን፤ መንግሥታችንና ለጀግኖቹና ለባለ ውለታዎቹ ፍቅርና ክብር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብም የእኚህን ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ታላቅ ጀግና፣ አርበኛ ሌፍተናት ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ ታሪካቸውን ውርሳቸው ሌጋሲያቸውን ለትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የምናደርገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ከጎናችን እንድትቆሙ ስንል በኢትዮጵያዊነት አክብሮትና ትሕትና እንጠይቃለን!!

(የዝክረ ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ጊዜያዊ ኮሚቴ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...