ኢሊያስ ሙሳ ደዋሌህ፣ የጂቡቲ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሚኒስትር
ጂቡቲ ነፃነቷን ካገኘች 40ኛ ዓመቷ ላይ ትገኛለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ጂቡቲ እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ አምስት አዳዲስ ወደቦችን ገንብታለች፡፡ የባቡር መስመር ለመዘርጋት እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር አውጥታለች፡፡ እነዚህን ኢንቨስትመቶች የማካሄዷ መሠረታዊ መነሻው በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የገቢና የወጪ ንግድ ፍሰት እንደሆነ፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ደዋሌህ፣ በጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት ጋባዥነት ወደ ጂቡቲ ላቀኑት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በጽሕፈት ቤታቸው በተካሄደ ቃለ ምልልስ ወቅት ሚኒስትር ኢሊያስ እንዳሉት በሁለቱ አገሮች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ፣ መንግሥት ለመንግሥት ያለው ግንኙነት ሁለቱን አገሮች የቀጣናው ተምሳሌት ያደርጋቸዋል፡፡ ጂቡቲ ኢንቨስት ባደረገችው መጠን አብዛኛውን የኢትዮጵያን የወጪና የገቢ ንግድ ዕቃዎች ለማስናገድ የአንበሳውን ድርሻ መያዝ እንደሚገባት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች ወደቦች የመጠቀም ፍላጎቷን መንግሥታቸው እንደሚያከብረውም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ዕቃዎች ብቻ ተማምነን ወደቦቻችንን አልገነባንም፤›› የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ይህም ሆኖ እስከ 70 በመቶ የአገሪቱን ዕቃዎች ለማስተናገድ ያላትን አቅም አብራርተዋል፡፡ በቀጣናው ሥጋት ብለው ከሚጠቅሷቸው ችግሮች ውስጥ የፀጥታ ችግር ዋናው እንደሆነና ኢትዮጵያ አማራጮቿን ለማስፋት ሌሎች ወደቦችን እንደምትቃኘው ሁሉ፣ ጂቡቲም የኃያል አገሮች ወታደራዊ ሠፈሮች መኖሪያ ለመሆኗ የምትገኝበት ስትራቴጂካዊ የጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ እንደጠቀማት ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዕድልና በሌሎችም የአገልግሎት መሠረተ ልማቶቿ ስለምትሰጣቸው አገልግሎቶች ከኢትዮጵያ ጋር ስላላት ግንኙነት፣ ወደፊት በሁለቱ አገሮች የንግድ ማኅበረሰቦች መካከል መፈጠር ስለሚገባው ግንኙነት ከጋዜጠኞች ተጠይቀው የሰጡትን ማብራሪያ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- የጂቡቲ መንግሥት በመሠረተ ልማት መስክ ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት እያደረገ ነው፡፡ እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ለወደብ ግንባታና ለሌላም ማዋሉ ይነገራል፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ የወጣበት ኢንቨስትመንት ምላሹን ላያስገኝ ይችላል የሚል ሥጋት አለዎት?
ኢሊያስ ሙሳ፡- የእኔ ትልቁ ሥጋት ይህን ያህል ገንዘብ ያወጣንበትን ኢንቨስትመንት ከማጣጣም የሚያግዱን ድህነት፣ ለችግሮች ያለብን ተጋላጭነትና ምናልባትም የፀጥታ ችግሮችና ቀውሶች ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ሥጋት አለመረጋጋት ነው፡፡ በምንገኝበት የአፍሪካ ክፍል፣ ከኢኮኖሚና ከልማት አኳያ ሲታይ በጥሩ አቅጣጫ እየተጓዝን እንደምንገኝ እንገነዘባለን፡፡ አብሮ ለመኖር መሥራት ይኖርብናል፡፡ ይህ ለእኛ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ይህ ወቅት ድህነትንና አለመረጋጋትን ተሸክመን የምንጓዝበት ጊዜ ላይ አይደለም፡፡ ይህ በእጅጉ የማይቻል እየሆነ ነው፡፡ የምንኖርበት አካባቢ በፀጥታ ችግሮች የታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ የበለጠ የሚያሳስበኝ ነገር አይኖርም፡፡ መልካም ሊባሉ የሚችሉ ውሳኔዎችን አሳልፈናል፡፡ ጠንካራ የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታ እንዳለን እናውቃለን፡፡ ይህንን ስል ስለኢትዮጵያና ስለጂቡቲ ማለቴ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ርቀው በመሄድ ሌሎቹንም ጎረቤት አገሮች ወደ ራሳቸው በማምጣት ከመጥፎው ይልቅ ከጥሩው ማዕድ እንዲቋደሱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በፎረሙ ወቅት ችግር ሆኖ የሚያሳስብዎ ጉዳይ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በቀጣናውና በዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ስለሚታዩ ችግሮች ሲጠቅሱም፣ አገርዎ ከተወዳዳሪነት ይልቅ የጎደለውን በሙላት ላይ የተመሠረተ የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ አካሄድን እንደምትመርጥ ገልጸዋል፡፡ በወደብ ልማት መስክ በሱዳን፣ በሶማሌላንድ፣ በኬንያ ብሎም በኤርትራ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ግርታ እንደሚፈጥሩም ጠቁመዋል፡፡ ይህ እርስዎ ያደረብዎ ግርታ ምን እንደሆነ ቢገልጹልኝ?
ኢሊያስ ሙሳ፡- በዓለም ላይ ምን እየተካሄደ እንዳለ በሚገባ እንደምትገነዘቡት፣ ኃያላን አገሮች ሳይቀሩ እኮ በየግል ፍላጎታቸው እየታጠሩ ነው፡፡ የግሎባላይዜሽን አጀንዳን ወደ ጎን እያሉት ነው፡፡ አገሮች ስለከለላ በግልጽ ሲናገሩ እየሰማን ነው፡፡ በራሳቸው አካባቢና ክልል ተወስነው መቀጥን እየመረጡ ነው፡፡ ጂቡቲያውን ግን የወደፊት ዕጣ ፈንታችን በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በኤርትራ ወይም በየመን እንደሚሆን፣ እንደሚገናኝና በዚያም እንደሚወሰን እናምናለን፡፡ የትኛውም ዓይነት ችግር በጎረቤት አገሮች ውስጥ ከተከሰተ በቀጥታ ተፅዕኖ ሊያሳርፍብን ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ነገሩን የመቀር አቅሙና ጥበቡም ስላለን በችግሩ ላይ ከማተኮር ይልቅ በመፍትሔው ላይ ማተኮሩን እንፈልጋለን፡፡ ጂቡቲ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ለውጥ አስተዋጽኦ ባደረገች ቁጥር ጥቅሙ መልሶ ለራሷ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ነበር አንዱ የንግግሬ ነጥብ፡፡ ሀብታችንን በጋራ መፍጠር አለብን፡፡ ጂቡቲ ትንሽ አገር ተደርጋ ልትታይ ትችላለች፡፡ ሆኖም ግን ለኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚዋ ነች፡፡ ለዓለም ኃያላን አገሮችም በጣም ወሳኝ አገር ነች፡፡ ሁሉም ኃያላን አገሮች በጂቡቲ የተገኙት ስለወደዱን አይደለም፡፡ ወደ እኛ የመጡት በዓለም የጂኦፖለቲካል ስትራቴጂ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ላይ ስለምንገኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በነበራት ጦርነት ምክንያት የገባችበትን ቀውስ የምታስታውሱ ይመስለኛል፡፡ ከቀውሱ በፊት በጂቡቲ ወደብ የሚስተናገዱት የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች መጠን ከአሥር በመቶ በታች ነበር፡፡ ይሁንና በድንገት የዕቃዎች ፍሰት ሙሉ በሙሉ ወደ እኛ መጣ፡፡ የሚተላለፉት ዕቃዎች ወደ እኛ እንዲዞሩ ተደረገ፡፡ በዚህ ወቅት ግን ያለ ምንም ችግር አንዲት የውኃ ጠርሙስ ሳትጠፋ ነበር ዕቃዎቹን ያስተላለፍነው፡፡ ዕድሉ ባመጣልን አጋጣሚ ለመጠቀምና ብዙ ትርፍ ለማጋበስ ብለን የአገሪቱ ዕቃ በሙሉ ወደ እኛ ወደብ መምጣት አለበት አላልንም፡፡ ይልቁንም በተቃራኒው የወደብ ታሪፍ ቅናሽ ነበር ያደረግነው፡፡ በወቅቱ የጂቡቲ ወደብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበርኩ፡፡ 24 ሰዓት በመሥራት ምንም ችግር ሳይፈጠር የዕቃዎች ጭነትና ፍሰት እንዲካሄድ አስችለናል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ውድቀት የሚያስከትል ሥጋት ሳይፈጠር ለማለፍ ተችሏል፡፡ አገሪቱ ጠንካራ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ አሁንም በዚሁ አካሄድ ቀጥላለች፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ጠንካራ ዕድገት ጂቡቲንም ተጠቃሚ አድርጓታል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ ብዙ ሀብት ለማፍራትና ይህንንም ለመጋራት እየሠራን የምንገኘው፡፡
ጂቡቲ በሯን ክፍት በማድረግ ፖሊሲ ለምን እንደምታምን ስንነጋገር፣ ነገ በሆነ አጋጣሚ ኤርትራ ጭምር ወደ መድረኩ መምጣቷ እንደማይቀር እናምናለን፡፡ ወደፊት ኤርትራ የቀጣናው ረባሽ ከመሆን ይልቅ፣ ሀብት እንዲፈጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋጽኦ የምታደርግበት ጊዜ እንደሚመጣ እናምናለን፡፡ ይህ በጊዜ ሒደት ውስጥ እንደሚፈጠር እናምናለን፡፡ በዚያች አገር ውስጥ አዲስ አመራርና አዲስ ፖሊሲ በጊዜ ሒደት መምጣቱ አይቀርም፡፡ ይህ በሚሆንበት ወቅት ግን ልንቀበላቸው ይገባል፡፡ በዚህ ወቅት የምንግባባው በመሠረተ ልማት፣ በንግድ እንዲሁም በድንበሮች አከባቢ በሚታይ የተረጋጋ ሁኔታ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ወደቦችን በተመለከተ የትኛውም የቀጣናውን አገሮች እንደ ተወዳዳሪያችን ወይም ለጂቡቲ ሥጋትን እንደሚደቅኑ አድርገን አንመለከታቸውም፡፡ ኢትዮጵያን ብቻም ሳይሆን መላውን ቀጣና ለማገልገል የሚያስችል የሎጂስቲክስ ማዕከል ለመገንባት ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ጭነቶች ወደ ጂቡቲ መምጣት አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ይህ ትርጉም አይኖረውም፡፡
ከፖሊሲው አኳያ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎቱን በማጤን ፍላጎቱን ሊያሟሉለት የሚችሉ አማራጮችን ማየት ይኖርበታል፡፡ አብረን ባደግን ቁጥር ቀልጣፋ የወደብ አገልግሎት ማስፈለጉ የማይቀር ነው፡፡ ጂቡቲ ብቻዋን ሁሉም አገልግሎት ልታቀርብ አትችልም፡፡ መቶ በመቶ የኢትዮጵያ ጭነት ወደ እኔ ወደብ እንዲመጣ አልጠብቅም፡፡ እኔም አማራጮቼን ማየት ይኖርብኛል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉት ላይ ወይም በሎጂስቲክስ አቅርቦት ረገድ ብዙ የገበያ ዕድሎችን ለማቅረብ የሚያችሉ አማራጭ ተወዳዳሪ ተጠቃሚነትን የሚያስገኙ መስኮችን መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ትንሽ ትኩረት ለመስጠት ያህል ከጂቡቲና በቀጣናው ካሉ አገሮች አኳያ ኢትዮጵያ በንፅፅር የራሷን ተጠቃሚነት የያዘችባቸው ዘርፎች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በኢንዱስትሪ ዘርፍ በመወዳደር ተወዳዳሪ ልሆን አልችልም፡፡ ይህ ለእኔ ብዙም ትርጉም አይኖረውም፡፡ ገንዘብና ጊዜን መፍጀት ብቻ ይሆናል፡፡ የምፈልገው ተወዳዳሪ በሆንኩባቸውና ከኢትዮጵያም ከተቀረውም ይልቅ በንፅፅር የተሻለ ተጠቃሚነትን በማገኝባቸው መስኮች ላይ ማተኮርን ነው፡፡
ጥያቄ፡- ጂቡቲ የምትኖረው በወደቦቿ አገልግሎት እንደመሆኑ መጠን፣ እንዴት ነው የሌሎች ወደቦች በአማራጭነት መምጣት ሥጋት የማይሆንባችሁ?
ኢሊያስ ሙሳ፡- አዎን፡፡ ግን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ታሪክ ከተነሳው ጥያቄ አኳያ ስንመለከተው፣ በእኔ ቀደምት ተሞክሮ አኳያም ኢትዮጵያ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት በአገር ውስጥ ብዙ ገንዘብ እያፈሰሰች ትገኛለች፡፡ አገሪቱ በዚህ ሒደት ተጠቃሚ ስትሆን፣ በጂቡቲ የሚኖረውም የወደብ እንቅስቃሴ ተጠቃሚነት ያገኛል፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮች መንሰራፋት የገበያ ዕድሎችን ያስፋፋል፡፡ የግብርናው ዘርፍ መጎልበትና ብዙ ምርት ማስገኘት ብዙ የጭነት ፍሰት ወደ ጂቡቲ እንዲጓጓዝ ያደርጋል፡፡ ከአቅምና ከመልካም ዕድሎች አኳያ ወደፊት መልካም ጊዜያት ከፊታችን እንዳሉ እናምናለን፡፡ ይህንን ለማስረዳት ጥቂት ነጥቦችን በምሳሌ ላሳያችሁ፡፡ ከወደብ ባለሙያዎች ትንታኔ መረዳት እንደሚቻለው፣ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር በምትሆንበት ወቅት ለአንድ ሰው በዓመት አንድ ቶን የፍጆታ ምግብና ሌላውም ያስፈልገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 100 ሚሊዮን እንደሆነ ብናስብ፣ 100 ሚሊዮን ቶን የምግብና የሌላውም ፍጆታ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶው ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታል፣ የተቀረው ከውጭ እንደሚመጣ እናስብ፡፡ በአገር ውስጥ ከተመረተው ምናልባት የተወሰነው ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብም ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ካለን ተጨማሪ አቅም አኳያም ቢሆን በአሁኑ ወቅት ልናስተናግድ የምንችለው የዕቃ መጠን በዓመት ከ20 ሚሊዮን ቶን ብዙ አይዘልም፡፡ የእኔ ግብ ምናልባት በሦስት ወይም አራት ዓመት ውስጥ 50 ሚሊዮን ቶን ማስተናገድ የምችልበት አቅም ላይ ለመድረስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምታስገባቸውና የምታስወጣቸውን ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ብቻችንን የማስተናገድ አቅም ላይ አልደረስንም፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ግን ገበያችንን በማስፋት እንደ ቻይና ካሉ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ ከሚገኙ አጋሮቻችን ጋር በመሥራት የጂኦፖለቲካዊ መገኛችን በፈጠረልን ዕድል መጠቀም ይኖርብናል፡፡ የኢትዮጵያ ከ60 እስከ 70 በመቶ ዓለም አቀፍ የንግድ ዕቃዎች ትራፊክ ማስተናገድ ከቻልን የወደቦቻችንን አቅም በሚገባ ለመጠቀም ያስችለናል፡፡ የተቀረው መጠን ወደ በቀጣናው ወደሚገኙ ወደቦች መሄድ ይችላል፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮቼን የገነባሁት ለኢትዮጵያ ትልቁ የወደብ አገልግሎት አቅራቢ እንደሆንኩ በመገንዘብ ነው፡፡ አብረን ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ የባቡር መስመር የገነባነውም ለዚሁ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌና አብረናቸው ያለነው መሪዎች፣ ቀደም ብሎ 500 ሚሊዮን ዶላር ለባቡር ፕሮጀክት ኢንቨስት የማድረግ ሐሳብ አልነበረንም፡፡ ከባቡር ይልቅ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር የሚያደርሱ ዋና ዋና መንገዶችን ብገንባበት እመርጣለሁ፡፡ ነገር ግን በጋራ የወደፊት ዕጣችን ስለምናምን ኢንቨስትመንቱን ለማካሄድና አደጋውን ለመጋፈጥ ወስነናል፡፡ የባቡር መስመር ዝርጋታው የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ያሳድገዋል፡፡ ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ረገድ ተወዳዳሪ ለመሆን ገና ይቀራታል፡፡ በወጪና በገቢ ንግድ ኮሪደሮች በኩል የሚታየው የጊዜና የገንዘብ ወጪ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ዝቅተኛ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ከጂቡቲ ወደ መቐለና አዲስ አበባ ዕቃ ለማጓጓዝ ሁለትና ሦስት ቀናት ይፈጅ የነበረው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በባቡሩ ምክንያት ከአሥር ሰዓት በታች ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ እንድትሆን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህን ማድረግ የእኔን አገር መልሶ ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡ ሰጥቶ የመቀበል ወይም እኛም እናንተም የምትጠቀሙበት ፍልስፍና ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በመነጋገር ያፀኑትን ይህንን የጠበቀ ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እያስቀጠሉት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጂቡቲ በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ ኢንቨስት ማድረጓ የታወቀ ነው፡፡ በፓይፕ መስመሮች ግንባታ ላይ በሁለቱ አገሮች መካከል ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ይኖራል?
ኢሊያስ ሙሳ፡- አዎን በርካታ የፓይፕ ፕሮጀክቶች ላይ የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶች ይኖሩናል፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን የመንግሥት ፋይናንስ እንቅስቃሴን በተመለከተ የሚፈቀድልን የወጪ ወይም የብድር ጣሪያ ላይ ደርሰናል፡፡ ለአገራዊና ለቀጣናዊ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶቻችን የመንግሥትን ኢንቨስትመንት በብቸኝነት መጠቀም አንችልም፡፡ ሌሎች ዕድሎች አሉ፡፡ ካፒታል በተትረፈረፈበት ዓለም ውስጥ ፋይናንስ የችግር መንስዔ ሊሆን አይችልም፡፡ ብዙ የካፒታል ምንጭ አለ፡፡ ሆኖም ውጤታማ ፖሊሲን መተግበር መቻሉ ላይ ነው ጥያቄ የሚኖረው፡፡ የሕግ ማዕቀፍ መፍጠር እምነትና ተስፋ የሚጣልባቸው ተቋማትን መፍጠር ለቀጥታ ኢንቨስቱ የሚቀመጥ መሥፈርት ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብና የመንግሥት የትብብር የሕግ ማዕቀፍ ሕግ አውጥተናል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ሕግ ለማውጣት እየተዘጋጀች እንደምትገኝ እናውቃለን፡፡ የቢዝነስ ከባቢው ሁኔታ በሚገባ ሲስተካከል ኢንቨስትመንቱ እንደሚጭምር ይታመናል፡፡ የሕግና የተቋማዊ ማዕቀፍ መፈጠሩ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ለመዋቅራዊ ለውጥ የግሉ ዘርፍ ሚና በጣም መሠረታዊ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የአንድ አገር መረጋጋት ነው ለሁሉ ነገር ትልቁን ድርሻ የሚይዘው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ቢሊዮንና ትሪሊዮን ዶላሮችን ኢንቨስት ማድረጉ ዋጋ ቢስ ነው፡፡ ባልተረጋጋ ቤት ውስጥ እየኖርን ድህነትና ለችግሮች ያለነንን ተጋላጭነት መዋጋት አይቻለንም፡፡ በኢትዮጵያ የምትከሰት ትንሿ ችግር ለጂቡቲም ከባድ ልትሆን ትችላለች፡፡ ይህም በሥነ ሕዝብና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ምክንያት ካለው የሁለቱ አገሮች ትስስር ነው፡፡ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምንጫወተውን ሚና እንመልከት፡፡ በየቤታችን አጣዳፊና ቅድሚያ የሚፈልግ ጉዳይ ሳይኖርብን ቀርቶ እኮ አይደለም በዚያች አገር ውስጥ ለሰላም የምንታገለው፡፡ የሶማሊያን ወታደሮች ለማጠናከር የምናወጣው ገንዘብ ለሶማሊያ መረጋጋት አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ የዚያች አገር መረጋጋት ለቀጣናው አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ አንድ አዕምሮ የነሳው የአልሸባብ አሸባሪ እስካሁን በስንት ጣር ተለፍቶ የተገነባውን ሁሉ ሊያፈነዳው ይችላልና ነው፡፡ በመሆኑም መረጋጋትና የቡድን ሥራ እንዲሁም ለወጣቶቻችን የምንሰጣቸው ተስፋ ዋጋ አለው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ሌሎች ወደቦችን በአማራጭነት ወይም በተጨማሪነት ለመጠቀም እየሠራች ነው፡፡ በመንግሥት ስትራቴጂ መሠረት መንግሥት በሱዳን፣ በሶማሌላንድና በሌሎችም አገሮች ውስጥ ወደብ በጋራ የመገንባት ፍላጎት አለው፡፡ የጂቡቲ መንግሥት ለኢትዮጵያ የወደብ መገንቢያ ቦታ ብትጠየቅ ታቀርባለች?
ኢሊያስ ሙሳ፡- እኛ ቢሊዮን ዶላሮችን አውጥተን ወደቦችን በገነባንበት ወቅት ኢትዮጵያ አዲስ ወደብ ለመገንባት ኢንቨስት ማድረጓ የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው? ያካሄድነው ኢንቨስትመንት እኮ ለጂቡቲ ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለቀጣናው አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ተጨማሪ አማራጭ ወደብ ለማልማት መፈለግ ምክንያታዊ ነው፡፡ እኔ የኢትዮጵያ መሪ ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣን ብሆን ኑሮ እነሱ አሁን እያደረጉት እንዳለው ሁሉ እኔም አማራጭ ወደብ ፍለጋ ውስጥ መግባቴ አይቀርም ነበር፡፡ ይህ በመደረጉ ግን አንዳችን ሌላችንን አንፈልግም ወይም አንዳችን ሌላችንን በክፉ እናያለን ማለት አይደለም፡፡ አንድ መሪ ለአገሩ የሚጠቅሙ አማራጮችን ማፈላለጉ የተለመደ ነገር ነው፡፡ በዚሁ አግባብ እኔም ወደቦቼን ያለማሁት መቶ በመቶ የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ዕቃዎች ፍሰት ብቻ ለማስተናገድ አይደለም፡፡ ሌሎች አማራጮቼን ማየት ያስፈልገኛል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት ንፅፅራዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚያስገኝልኝ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ከመገንባት አላቅማማም ነበር፡፡ በአንዱ አገር ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ስለማይታወቅ አማራጭ መኖሩ ግድ ነው፡፡ ‹ሁሉንም እንቁላሎችህን በአንድ ቅርጫት አታስቀምጥ› እንደሚባለው ሁሉ፣ እኛም ስለአማራጭ ወደብ አስፈላጊነት የጠራ ግንዛቤ አለን፡፡ ይኽም ቢባል ግን ኢትዮጵያን ቢያንስ ለመጪዎቹ 20 ዓመታት ለማገለገል የሚያስችል የአንበሳው ድርሻ እንደሚኖረን ግንዛቤው አለን፡፡ በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጋር ከነበራቸው የጠበቀ ወዳጅነት በመነሳት ሁሌም ለፕሬዚዳንታችን የሚነግሯቸው ነገር ነበር፡፡ ‹‹አስፈላጊ ፖሊሲዎችንና መሠረተ ልማቶችን በተገቢው መንገድ በመገንባት ከኋላችን የሚመጡት ትልውዶች እንዳይቸገሩ እናድርግ፤›› ይሏቸው ነበር፡፡ አብረን ከመስጠም ይልቅ አብረን መዘመር ይኖርብናል፡፡
ጥያቄ፡- የውጭ ኢንቨስትመትን ከመሳብና የሁለቱን አገሮች ትስስር ከማዳበር አኳያ፣ በጂቡቲ ስለተሰናዳው የንግድ ዓውደ ርዕይና ፎረም ምን ሊነግሩን ይችላሉ?
ኢሊያስ ሙሳ፡- የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና የቀጣናው ትስስር ላይ ያተኮረውን ፎረም ማዘጋጀታችን ለእኛ በጣም ጥሩ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ሆኖም ለጂቡቲና ለኢትዮጵያ ትስስር መጠናከር የተለየና ለሁለቱ አገሮች ብቻ የሚሆን የጋራ ቋሚ ፎረም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ጠንካራ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነትና ትስስር አለን፡፡ እንደ መሪ በሁለቱ አገሮች ውስጥ እየገነባነው ስላለው ነገር በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም አለን፡፡ እኔ ድሬዳዋ ነው የተወለድኩት፡፡ ነገር ግን ጂቡቲያዊ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልጄ ኢትዮጵያን የሚያገልገል የጂቡቲ ባለሥልጣን በመሆኔም ኩራት ይሰማኛል፡፡ ይኸው ነው፡፡ ይህንን መቀየር አይቻልም፡፡ ዘመዶቼ አሁንም ድረስ በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ኤርትራውያን ዘመዶቻችንም በኢትዮጵያ ይኖራሉ፡፡ ሁሉም አንድ ሕዝብ ነው፡፡ እኛ እንደ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርና እንደ ፕሬዚዳንት ራሳችንን ማስቀመጥ የሚገባን ይህንን አንድ ሕዝብ የምናገለግል ኃላፊዎች አድርገን ነው፡፡ ሁለቱ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው፡፡ ምናልባት ስያሜያችንና ሰንደቅ ዓላማችን ሁለት ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ግን አንድ ነን፡፡ ስለዚህ ፖሊሲዎቻችን ይህንን አንድ ሕዝብ በማርካት ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተቀረፁት ፖሊሲዎች ለኢትዮጵያውያን ዘመዶቼ ውጤት ማስገኘት ከቻሉ እኔንም በጂቡቲ የምኖረውን በአዎንታዊነት እንደሚነኩኝ አውቃለሁ፡፡ የእኛም እንደዚያው ነው፡፡
በዚህ ሒደት ውስጥ መሀል ላይ የቀረው የንግድ ማኅበረሰቡ ግንኙነት ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ስለችግሮቻቸውና ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎች መነጋገር አለባቸው፡፡ በየአገሮቻቸው ውስጥ የተቀረፁ ፖሊሲዎች የሚልጉትን ውጤት ስለማስገኘታቸው መነጋገር አለባቸው፡፡ የንግድ ሰዎቻችንን አስተሳሰብ ለአገሮቻችን ጠቀሜታ በሚያስገኝ መንገድ መሥራት አለብን፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ባለቤት አቶ ታዲዮስ በጂቡቲ ደሴቶች ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ ነው፡፡ በመሆኑም የእሳቸው ደንበኞች በኢትዮጵያ ቱሪዝም መዳረሻዎች ውስጥ የሚጎድለውን ፓኬጅ ከእኛ ለማቅረብ እየሠሩ ነው፡፡ የባህር ጨዋማ ሐይቅ አንዱ ፓኬጅ ነው፡፡ የጂቡቲ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን በመጋበዝ በሁለቱ አገሮች መካከል ንግድ እንዲያስፋፉ ይፈልጋል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግም ለአቶ ታዲዮስ ካለምንም ክፍያ መሬት አቅርበንላቸዋል፡፡ ኢንቨስትመንታቸው በእኛ ደሴቶች ውስጥ ዕውን እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡
እንዳለመታደል ግን ባለሀብቱ የፕሮጀክታቸውን አሥር በመቶ ፋይናንስ ወደ ጂቡቲ ማስተላለፍ አልቻሉም፡፡ ይህም አንድ ሚሊዮን ዶላር ያህል ነው፡፡ ይህ ገንዘብ የጂቡቲ ባንኮች አገልግሎት መስጠት እንዲያስችላቸው የሚፈለግ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ያለው ሕግ ግን ለኢንቨስትመንት በሚል አንዲትም ዶላር ከአገር ውስጥ እንዲወጣ የማይፈቅድ በመሆኑ ገንዘቡን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ የጂቡቲ መንግሥት ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስባል? ለአቶ ታዲዮስ አስፈላጊውን በማድረግ ኢንቨስትመንታቸው እንዲሳካ ከጂቡቲ ባንኮች ገንዘብ እንዲያገኙ ማገዝ እችላለሁ? ምናልባት ለሚያስፈልጋቸው ፋይናንስ ማስያዣ ንብረት እጠይቃቸዋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ያላቸው ንብረት እንደ ብድር ማስያዣ ሊታሰብ የሚችልበትና ፋይናንሱን ግን ከጂቡቲ ባንኮች የሚያገኙበት፣ ከኢትዮጵያ እንዲሁ የሚደረግበት አማራጭ ሐሳብ አለ፡፡ እንደህ ዓይነቱን ሐሳብ ከሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ግንኙነት ውስጥ ልናገኘው የምንችለው በመሆኑ፣ የሁለቱን አገሮችን የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ግንኙነት ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ ሁለቱ መንግሥታት በዚህ ጉዳይ ላይ አበክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡