Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዝጋሚው የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ ጉዞ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በታሪክ ከማይዘነጉና በርካቶችን እንደ ቅጠል ካረገፉ ወረርሽኞች መካከል ኤችአይቪ ዋነኛው ነው፡፡ ከተከሰተ አምስት አሥርታት ያለፉ ቢሆንም እስካሁን ለበሽታው ፈውስ ማግኘት የማይፈታ ህልም ሆኗል፡፡ ለዓለም እፎይታ የሆነው የፀረ ኤድስ መድኃኒት እስኪገኝ ድረስም በርካቶችን የአልጋ ቁራኛ አድርጎ ነበር፡፡ በሽታው ከተከሰተ እስካሁን ከ70 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ 35 ሚሊዮን የሚሆኑን ደግሞ ለሞት ዳርጓል፡፡

 የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ከሆነባቸው አኅጉሮች መካከል አፍሪካ በአገር ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ በኢትዮጵያ ስለበሽታው የነበረው ግንዛቤ ዝቅተኛ በነበረበት በዚያ ወቅት ወረርሽኙ በየቤቱ ገብቶ በርካቶችን ለሞት ዳርጎ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በየመንደሩ ለሚጣለው የሐዘን ድንኳንም ዋነኛ ምክንያቱ ኤችአይቪ እስኪሆን ድረስ አስከፊነቱ ከብዶ ነበር፡፡ የበሽታው ሥርጭት ጣሪያ በነካበት እ.ኤ.አ. በ1996 ወቅት ስርጭቱ በአዲስ አበባ 15.6 በመቶ፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ 12.7 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ እ.ኤ.አ. በ2000 በአገሪቱ ውስጥ ከኤችአይቪ ጋር ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ቁጥር በከተማ 660,000 በገጠር ደግሞ 490,000 ነበር፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ይህ ቁጥር ወደ 720,000 እና 750,000 አሻቅቦ ነበር፡፡ የሥርጭት መጠኑ ከፍተኛ በነበረበት እ.ኤ.አ. በ2000 186,000 አዲስ የኤችአይቪ ኬዝ ተመዝግቦ ነበር፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮችን የሞት ቀጣና አድርጎ ለነበረው የኤችአይቪ ወረርሽኝ መድኃኒት ለማግኘት በርካታ ተመራማሪዎችና የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች በየፊናቸው ደፋ ቀና ማለት የጀመሩት ከዚያ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡

የዜጎቻቸውን ህልውና አደጋ ውስጥ ለወደቀባቸው አገሮች፣ ሰብዓዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተስፋ መስጠት የቻለ ውጤት ማግኘት የተቻለው ግን ቆይቶ ነበር፡፡ ሒደቱ ምርምሩን ለሚመሩ ትልልቅ የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች የዜጎችን ሕይወት ከማትረፍ ባሻገር ሊሳካም ላይሳካም የሚችል ትልቅ ኢንቨስትመንት ነበር፡፡

አንድ መድኃኒት ለማግኘት የሚወስደው የምርምር ጊዜና የሚያስፈልገው ወጪ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የምርምር ሒደቱ በትንሹ ከ25 እስከ 30 ዓመታት ይፈጃል፣ እስከ 2.6 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪም ይጠይቃል፡፡ ይህንን ያህል መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው ለአገልግሎት የሚበቁ የተለያዩ መድኃኒቶች ለገበያ የሚቀርቡት ኩባንያው መድኃኒቱን ለማምረት ያወጣውን አጠቃላይ ወጪ ሸፍኖ ሊያተርፈው በሚችል ዋጋ ይሆናል፡፡ ከዚህም ባሻገርም የኩባንያውን የባለቤትነት ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የፓተንት ከለላ ይደረግለታል፡፡

የአንድ መድኃኒት የፓተንት ከለላ እንደየአገሩና እንደየመድኃኒት ዓይነቱ የተለያየ ነው፡፡ በአሜሪካ ይህ የጥበቃ ጊዜ እስከ 20 ዓመታት ከዚያም በላይ ይዘልቃል፡፡ ገበያውን የሚቀላቀሉ አዳዲስ መድኃኒቶች ‹‹ብራንድ ኔም ድራግ›› ሲባሉ፣ የጥበቃ ጊዜያቸው ካበቃ በኋላ በሌሎች ኩባንያዎች ሲመረቱ ደግሞ ‹‹ጀነሪክ ድራግ›› የሚል ስያሜ ያገኛሉ፡፡ የፓተንት ጊዜው እስኪያበቃ ድረስም መድኃኒቱን የማምረት፣ የማከፋፈልና ከሽያጩ ትርፍ የመሰብሰብ መብት ያለው መድኃኒቱን ያገኘው ኩባንያ ብቻ ይሆናል፡፡ የፓተንት ጥበቃው ያላበቃለትን መድኃኒት አንድ ሌላ አካል አምርቶ ቢገኝ በድርጊቱ በሕግ ይጠየቅበታል፡፡

ይህ የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪው ለዘመናት ሲተዳደርበት የቆየ አሠራር ነው፡፡ ይህንን ለኩባንያዎቹ ፍፁም የሆነ መብት የሚሰጠውን መተዳደሪያ ሕግ ታዳጊ አገሮችን ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችል ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲገዛ ሆኗል፡፡ ይህ ስምነት የአንድ መድኃኒት የፓተንት ጥበቃ ጊዜው ሳይጠናቀቅ ሌላ ኩባንያ ማምረት እንዲችል የሚፈቅድ ነው፡፡ በዓለም የንግድ ድርጅት አባል አገሮች የተፈረመው ይህ የትሪፕስ ስምምነት በማደግ ላይ ያሉ አገሮች አንድን በፓተንት ጥበቃ ሥር የሚገኝን መድኃኒት እንዲያመርቱ ያፈቅዳል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት በታዳጊ አገሮች ላይ ያለው የበሽታ ጫና እና በፓተንት ጥበቃ ሥር የሚገኙ ውድ መድኃኒቶችን ገዝቶ ለዜጎቻቸው ላማቅረብ አገሮቹ ያለባቸው የአቅም ውስንነት ጉዳይ ነው፡፡ ስምምነቱ እነዚህ አገሮች የሚያመርቷቸውን መድኃኒቶች ለአገር ውስጥ ጥቅም ከማዋል ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዳይችሉ ገደብ ያስቀምጥባቸዋል፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ታዳጊ አገሮች መካከል የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት በራሳቸው ለማምረት አቅሙ የሌላቸው አገሮች ከሌሎች አቅሙ ካላቸውና እያመረቱ ከሚገኙ ታዳጊ አገሮች ገዝተው እንዲጠቀሙ ይፈቅዳል፡፡

ይህም በተዘዋዋሪ መንገድ ኤክስፖርትን የሚፈቅድ ይምሰል እንጂ ግብይቱ መካሄድ ያለበት በሁለት ታዳጊ አገሮች ስለሆነ የሚኖረው የንግድ ልውውጥ የአገሮቹን መሠረታዊ የመድኃኒት አቅርቦት ከማርካት ያለፈ አይሆንም፡፡ በዚህ ረገድ የህንድን ልምድ በምሳሌነት ማንሳት  ይቻላል፡፡ ይህ በዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል ለሆኑ አገሮች ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ የድርጅቱ አባል ላልሆኑ አገሮችም በጊዜ ገድብ እንዲጠቀሙበት ይፈቅዳል፡፡

ስምምነቱ የሰጣቸውን የተለየ ጥቅም በአግባቡ እየተጠቀሙበት ነው ወይ የሚለው ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ ስምምነቱ እ.ኤ.አ ከ1995 ጀምሮ ተፈጻሚነት ያገኘ ቢሆንም፣ ከአንዳንድ አገሮች በስተቀር በተለይም አብዛኞቹ አፍሪካዊ አገሮች ስምምነቱ በሚሰጣቸው መብት መጠቀም እንዳልቻሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በየአገሩ ያላው የመድኃኒት ተደራሽነትም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

እ.ኤ.አ በ1999 የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው 90 በመቶ የሚሆነውን በዓለም ላይ የሚመረቱ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙት 15 በመቶ የሚሆኑ ባደጉት አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2000 በዓለም ላይ ካለው አጠቃላይ የመድኃኒት ድርሻ 52 በመቶ የሚሆነው ለአሜሪካውያን የሚቀርብ ነው፡፡ ከፍተኛ የበሽታ ስርጭት ባለባቸው ታዳጊ አገሮች የመድኃኒት አቅርቦት ድርሻ ግን አሥር በመቶ እንኳን አይሞላም፡፡ ለዚህም በመድኃኒት ተደራሽነት ችግር ምክንያት መዳን እየቻሉ የሚሞቱ ሚሊዮኖችን ማንሳት በቂ ነው፡፡

በአገሮቹ ከፍተኛ ስርጭት የሚታይባቸው የበሽታ ዓይነቶች በዋናነት ኤችአይቪ፣ ወባ፣ ካንሰር፣ ስኳር፣ ቲቢና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለእነዚህ በሽታዎች የሚሆኑ መድኃኒቶች ደግሞ በፓተንት ጥበቃ ሥር የሚገኙ ናቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ችግሩን ለመቅረፍ እ.ኤ.አ ከ1977 ጀምሮ የተለያዩ ወሳኝ የሚባሉ መድኃኒቶችን ለይቶ በማውጣት መሠረታዊ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ያለባቸውን አገሮች መድኃኒት በቅናሽ ዋጋና በዕርዳታ የሚያገኙበትን አሠራር ዘርግቷል፡፡ ሥርዓቱ ሲዘረጋ የተለይተው የወጡ መድኃኒቶች ዝርዝር 208 የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 340 መድረሳቸውን የድርጅቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡ የወባ፣ የኤችአይቪ፣ የቲቢ፣ የተዋልዶ ጤና፣ የካንሰር፣ የስኳር መድኃኒቶች በዝርዝር ከተካተቱ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ነች፡፡

 ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ከታችኛው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ምድብ ለመግባት ስትራቴጂ ቀርፃ ወደ ሥራ ከገባች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ተለይተው ከወጡ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከልም ፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪውን ማጎልበት በግንባር ቀደምትነት ይገለጻል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፋርማሱቲካልና ሜዲካል ኢኪውፕመንትና የሕክምና መሣሪያዎች ዳይሬክቶሬት ክፍል ኃላፊው አቶ ሶፊያን አብዱረሂም የአገር ውስጥ የመድኃኒትን ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት የመሸፈን ስትራቴጂ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ በምርምር ረገድም የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተጋገዝ የሚሠራቸው የተለያዩ ምርምሮች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡

50 በመቶ የሚሆነውን የአገር ውስጥ መድኃኒት አቅርቦት በአገር ውስጥ ለመሸፈን፣ ሲያልፍም ወደ ጎረቤት አገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆኑ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ይሁንና በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በጀት ዓመት የተያዘው ዕቅድ ከወረቀት ባለፈ ሊሳካ አለመቻሉ ታይቷል፡፡ ‹‹አገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች የአገሪቱን የመድኃኒት አቅርቦት አሥር በመቶ ያህል ቢሸፍኑ ነው፡፡ እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ከውጭ የሚገባ ነው፤›› በማለት አቶ ሶፊያን ዕቅዱ ከወረቀት ባለፈ ውጤታማነቱ ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንቱ አቶ ዮናስ ገብረፃዲቅ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ 15 መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ስምንቱ መድኃኒት አምራቾች ናቸው፡፡ አጠቃላይ የገበያ ድርሻቸውም አሥር በመቶ ብቻ የመሆነውም በኢንዱስትሪው ላይ ማነቆ የሆኑ ትልልቅ ችግሮች በመኖራቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ማነቆዎች 50 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲሆን፣ ከባለፈው 2009ዓ.ም የካቲት ወር ጀምሮም ኩባንያዎቹ ምንም ዓይነት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻሉም፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው ጥሬ ዕቃ የሚገባው ከውጭ አገሮች መሆኑ ደግሞ የምንዛሪው እጥረት የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ከባድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህም አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች የሚያመርቱት የምርት መጠን እንዲቀንስ ሆኗል፡፡ ሠራተኞች የቀነሱም አሉ፡፡

ይህም አገሪቱ ከስምንት ዓመታት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታልመው ምን ያህል ዝግጁ ሆና ነው? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ በታዳጊ አገር ስም የምታገኛቸው የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ሲቀሩባት ያለውን የመድኃኒት ፍላጎት ከምን ልታደርገው ይሆን የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ከሚሠሩ ድርጅቶች መካከል ሲዲቲ (Center for Innovative Drug Development and Therapeutic Trials for Africa) አንዱ ነው፡፡

ሲዲቲ  በአፍሪካ ውስጥ የመድኃኒት፣ የክትባት፣ የላቦራቶሪ ዲያግኖስቲክ፣ የመድኃኒት ምርምርና ሌሎችም በሕክምናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን በትምህርትና በሌሎች የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለመሙላት የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ የዓለም ባንክ ድጋፍ ያደርግለታል፡፡ በሲዲቲ አፍሪካ የሳይንስ ዘርፍ አስተባባሪው ዶ/ር ፀጋሁን ማንያዘዋል ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ያላደገው የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪው ዕርምጃዋን ወደኋላ እንደሚጎትተው ይናገራሉ፡፡

በዕርዳታ ይገኙ የነበሩ እንደ የቲቢና የኤችአይቪ ያሉ ውድ መድኃኒቶችን በራሷ በጀት መግዛት አልያም ማምረት ይኖርባታል፡፡ ይህ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ‹‹ያ ጊዜ ከመድረሱ በፊት ካሁኑ ዝግጅት ማድረግ መድኃኒት ማምረት ይኖርባታል፡፡ ሲዲቲም በዚህ ረገድ የተሻለ ነገር ማበርከት የሚችሉ ወጣት የምርመር ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ ይሠራል፤›› ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ አገሪቱ በባህላዊ መድኃኒት ዘርፍ ያላትን አቅም መጠቀም እንደምትችል ይናገራሉ፡፡

በመድኃኒት ምርምር ሒደት የፕሪ-ክሊኒካል ምርምር ሒደት ጨርሰው በተለያዩ ችግሮች ምርምራቸው የተቋረጠ ባህላዊ መድኃኒቶችን እንደ መነሻ በማድረግ ሰፊ የምርምር ሥራ መሥራትና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ ሲዲቲ በበኩሉ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከባህላዊ መድኃኒቶች ቢያንስ አምስት ዓይነት አዳዲስ መድኃኒቶች ለማውጣት እንደሚሠራ ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ በገዳይነታቸው በሚታወቁ በሽታዎች ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፓተንት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የአገር ውስጥ የመድኃኒት ፍላጎት የግል ድርጅቶችና የመንግሥት አካል በሆነው በመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ አማካይነት ይፈጸማል፡፡ ኤጀንሲው ከየጤና ተቋማቱ በሚቀርብለት የመድኃኒት ፍላጎት መሠረት ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ካሉ የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች በጨረታ ይገዛል፡፡ ከመንግሥት የጤና ተቋማት የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች በየክልሉ በሚገኙ 19 ቅርንጫፎቹ አማካይነት ይቀበላል፣ ያከፋፍላል፡፡ የመድኃኒት ፍላጎቱና ስርጭቱ በየዓመቱ ከ20 እስከ 25 በመቶ ዕድገት እያሳየ እንደሚሄድ የሚናገሩት በኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አድና በሬ ናቸው፡፡

የእነዚን መድኃኒቶች ግዥ የሚፈጸመው በፕሮግራምና በተገላባጭ ፈንድ ነው፡፡ በተገላባጭ ፈንድ የሚገዙ መድኃኒቶች በጤና ተቋማት በጀት የሚገዛ ሲሆን፣ ተቋማቱ አስቀድመው የሚፈልጉትን የመድኃኒት ዓይነትና መጠን ይገልጻሉ፡፡ ክፍያውን የሚፈጽሙት ኤጀንሲው የጠየቁትን መድኃኒት ገዝቶ ሲያስረክባቸው ነው፡፡ የፕሮግራም መድኃኒቶች የሚባሉት ደግሞ በዕርዳታ የሚገቡ ናቸው፡፡ እነዚህ በዕርዳታ የሚገቡ መድኃኒቶች ሲሆኑ፣ አንዳንዴ በዓይነት፣ አንዳንዴ ደግሞ በጀቱን ለኤጀንሲው በማስተላለፍ በኤጀንሲው በኩል ግዥው እንዲፈጸም ይደረጋል፡፡

እንደ ወይዘሮ አድና ገለጻ፣ በፕሮግራም የሚገዙ መድኃኒቶች የወባ፣ የቲቢ፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የክትባት መድኃኒቶችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች ከሌሎቹ በተለየ በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው ሲሆን፣ ዋጋቸውም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በየዓመቱ ከሚገዛው አብዛኛው የመድኃኒት አቅርቦት የሚሸፈነውም በዕርዳታ ድርጅቶች ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ በፕሮግራም የቀረበው መድኃኒት ካለው ፍላጎት አንፃር የሚያጥርበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር፣ ስለዚህም የእርዳታ መድኃኒቶችን በተገላባጭ ፈንድ የሚገዙበት አጋጣሚዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

በ2007 ዓ.ም 12.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒት በየጤና ተቋማቱ ኤጀንሲው አሰራጭቷል፡፡ በ2008 ዓ.ም እንዲሁ 12.8 ቢሊዮን ብር፣ በ2009 ዓ.ም. 13.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒት በኤጀንሲው ማሰራጨት ተችሏል፡፡ በ2010 ዓ.ም ደግሞ 15.3 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ መድኃኒት በየጤና ተቋማቱ ለማሰራጨት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በዚህ የመድኃኒት አቅርቦት ውስጥ የአገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ ከአጠቃላይ ገበያው ሲታይ ውስን ሆኖ ይታያል፡፡

ለምሳሌ በ2009ዓ.ም በኤጀንሲው የተፈጸመው የመድኃኒት ግዥ 13.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ አምራቾች 1.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒት ለመግዛት ዕቅድ ተይዞ ማግኘት የተቻለው ከ900 ሚሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒት ብቻ ነበር፡፡

ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት፣ በግዥ ሒደት ላይ በሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ ችግሮች መድኃኒቶች ወቅታቸውን ጠብቀው ኅብረተሰቡ ጋር የማይደርሱበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሶፊያን፣ ለዚህ ዋናው መፍትሔ በአገር ውስጥ ማምረት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ የአገር ውስጥ አምራቾች እየተመረቱ ያሉ መድኃኒት ዓይነቶች ውስን ከመሆናቸው ባሻገር የኩባንያዎቹ አቅም ውስን መሆን ሌላው ፈተና ነው፡፡

‹‹የአገር ውስጥ አምራቾች የሚያመርቱት አሞክሳሲሊን፣ አምፒሲሊን የመሳሰሉትን ምትክ የሌላቸው መሠረታዊ መድኃኒቶችን ነው፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ በዓለም አቀፍ ጨረታ ላይ ለሚሳተፉ የአገር ውስጥ አምራቾች ኤጀንሲው ከለላ የሚሰጥ ቢሆንም፣ ጨረታውን አሸንፈው የተባለውን ምርት መጠን ማቅረብ ላይ ችግር መኖሩን ይናገራሉ፡፡

በዓለም አቀፍ ጨረታው ሲሳተፉ ኤጀንሲው 25 በመቶ ከለላ ይሰጣቸዋል፡፡ በጨረታው ማሸነፍ ከቻሉ ደግሞ 30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም 70 በመቶ የባንክ ብድር የሚያገኙበት ዕድል ይመቻቻል፡፡ እንዲህም ሆኖ ድጋፉ አንሷል የሚሉ የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች መኖራቸውን፣ ባለፈው ዓመት መድኃኒት ለማቅረብ ከተስማሙ ኩባንያዎች መካከልም ምንም ማቅረብ ያልቻሉ ኩባንያዎች መኖራቸውን፣ ከአንዳንዶቹ በስተቀር አብዛኞቹም እናቀርባለን ብለው ቃል የገቡትን ሙሉ በሙሉ ማቅረብ አለመቻላቸውን ወ/ሮ አድና ተናግረዋል፡፡

 

በሌላ በኩልም 90 በመቶ የሚሆነው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ከውጭ አገር መግባቱ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አምራቾች ጋር እኩል ተወዳዳሪ መሆን እንዳይችሉ ማድረጉን ፕሬዚዳንቱ አቶ ዮናስ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አብዛኛዎቹ አገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች ከህንድና ከቻይና ነው የሚገቡት፡፡ ውድድሩ ጥሬ ዕቃና ዋናውን ምርት ከሚያመርቱ ድርጅቶቸ ጋር ነው የሚሆነው፤›› ሲሉ ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር ቀርቶ የሚጠበቅበትን የአገር ውስጥ የአቅርቦት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንኳ እንደሚቸገር አቶ ዮናስ ይናገራሉ፡፡

አዝጋሚ የለውጥ ጉዞ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ ራሱን ችሎ መቆም የተሳነው ይመስላል፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 የዓለም የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ አጠቃላይ ገቢ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁ ድርሻ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የፋርማሱቲካ ኩባንያዎች ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከልም በኒውዮርክ ከተማ የሚገኘው ፒፋይዘር አንዱ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ የ2016 ከመድኃኒት ሽያጭ 52.8 ቢሊዮን ዶላር መሰብሰብ ችሎ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪው እንደ አሜሪካ ላሉ ግዙፍ ኢኮኖሚ ላላቸው አገሮች ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙትም በፓተንት ከተያዙ መድኃኒቶች ሽያጭ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 ከፍተኛ ገቢ ካስገኙ መድኃኒቶች አንዱ የካንሰር መድኃኒቶች ሽያጭ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ 79 ቢሊዮን ዶላር ተሽጦ ነበር፡፡ እንደ ካንሰር መድኃኒት ያሉ በውድነታቸው ከሚታወቁ መድኃኒቶች መካከል ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት አንዱ፡፡ በሽታው በኢትዮጵያ እያገረሸ ስለመሆኑ ሪፖርተርን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘገብ መክረሙ የሚታወስ ነው፡፡ አገሪቱ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት የምትገነባው ኢኮኖሚ እንዲህ ያሉ ወጪዎችን በራሷ ለመሸፈን የሚያስችላት ይሆን የሚለው ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው፡፡

 

የትሪፕስ ስምምነት በሚሰጣት ልዩ ጥቅምስ ምን ያህል ለመጠቀም ዝግጁ ነች የሚለው ጉዳይም ሌላ ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ የአገር ውስጥ አምራቾች ትኩረት አድርገው የሚሠሩት የፓተንት ጉዳይ የሌለባቸውን ጀነሪክ መድኃኒቶችን ነው፡፡ እነዚህ ጀነሪክ መድኃኒቶች በዓለም ጤና ድርጅት መሠረታዊ መድኃኒቶች ተብለው የተለዩና በታዳጊ አገሮች ያላቸው የበሽታ ስርጭት ከፍተኛ የሆነ ነው፡፡ የትሪፕስ ስምምነት በታዳጊ አገሮች የሚገኙ የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች የፓተንት ጉዳይ ሳያሰጋቸው መድኃኒቶችን እንዲያመርቱ የሚፈቅድላቸው ቢሆንም፣ ኩባንያዎቹ እነዚህን መድኃኒቶች ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ የተለዩ መስፈርቶችን ማሟላት ግድ ግድ እንደሚላቸው አቶ ዮናስ ይናገራሉ፡፡

በፓተንት ጥበቃ ሥር የሚገኙት መድኃኒቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በግሎባል ፈንድ እርዳታ ነው፡፡ እነዚህን በእርዳታ የሚገቡ መድኃኒቶች በአገር ውስጥ የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች አመረቱ ማለት በዕርዳታ ከሚገባው ጋር ገበያ ለመወዳደር ይገደዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለእነሱ አዋጭ አለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ስለዚህም የፓተንት ጥበቃ ጊዜያቸው ያበቃላቸውን ጀነሪክ መድኃኒቶችን ብቻ ለማምረት እንደሚገደዱ አቶ ዮናስ ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ ግን በፓተንት ከተያዙ መካከል የካንሰር፣ የልብ፣ የደም ግፊት መድኃኒት የመሳሰሉትን ለማምረት ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

የትሪፕስ ስምምነት ለታዳጊ አገሮች የሚሰጠው ልዩ ጥቅም በጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስምምነቱ ተጠቃሚ ለመሆን የተጀመረው እንቅስቃሴ ከረፈደ መሆኑ ምን ተይዞ ጉዞ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ‹‹እሱ ምንም ችግር የለውም ሎቢ በማድረግ ለተጨማሪ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ ይቻላል፤›› የሚሉት አቶ ዮናስ አገሪቱ ስምምነቱ የሰጣትን ልዩ ጥቅም ሳትጠቀምበት ብትቆይም ለመቶ እርምጃ መነሻው አንድ ነውና ጅምሩ አበረታች መሆኑን ይናገራሉ፡፡

 

‹‹አንድ መድኃኒት ለማምረት ረጅም ጊዜ ይፈጃል፡፡ አንዱ ለአንዱ እያቀባበለ በተቋም ደረጃ የሚሠራ እንጂ አንድ ግለሰብ ሲለው የሚሠራው ሲለው ደግሞ የሚተወው መሆን የለበትም፤›› የሚሉት ዶ/ር ፀጋሁን አገሪቱ በመድኃኒት ራሷን እንድትችል እዚህም እዚያም የሚሠሩ ምርምሮችንና ተመራማሪዎችን አንድ ላይ ማምጣት እንዲሁም መንግሥት ከሚያወጣቸው ጤና አቅጣጫዎች ጋር እያናበቡ ክፍተቶችን መሙላት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች