Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የቆሸሸች አበባ

ስለአዲስ አበባ ከተማ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫነቷ፣ የአፍሪካ መዲናነቷ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ መናኸሪያነቷ አይካድም፡፡ ይሁንና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተለየ መጎናፀፍ የቻለችውን ያህል፣ ስሟን በሚመጥን ቁመና ላይ ነች ወይ? ተንከባክበናታል ወይ? ሌሎችም በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቢሯቸውን እዚህ እንዲከፍቱ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠርን ነው ወይ? ጠብቀናታል ወይ? የሚሉትን  ጥያቄዎች ብናነሳ የምናገኘው መልስ ልብ አይሞላም፡፡

ከተማዋን ከፅዳት እንክብካቤዋ አንፃር እንመዝን ከተባለ ስለአዲስ አበባ የዓለም አቀፍ መቀመጫነት ደፍረን ለመናገር አቅሙ አይኖረንም፡፡ የዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫ አንዱ መመዘኛ የከተማ ፅዳት ቢሆን ኖሮ፣ የአዲስ አበባን ውጤት ቀድመን አውቀን ተሸማቀን በተቀመጥን ነበር፡፡ የመዲናችንን የፈሳሽና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስለምናውቅ ውድድር አያሻንም ብለን ሹልክ እንላለን፡፡

ለማንኛውም አዲስ አበባ የምናወራላትን ያህል ወይም ስሟን የሚመጥን የፅዳት አጠባበቅ የሌላት ከተማ ብቻ ሳትሆን፣ ዓይነ ግቡ ሊያደርጋት የሚችል መልካም የሚባል የከተማ ፕላን የሌላት ነች ማለት ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በሚመጥን ደረጃ እየገነባናት አይደለም፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችን የሚመጥን አካሄድም አይታይም፡፡

 ከተማን ከተማ ከሚያሰኙ ማራኪ ግንባታዎች አኳያ አዲስ አበባ ደሃ ነች፡፡ ነፋሻማ አየር የሚገኝባቸው ንፁህና አረንጓዴ ሥፍራዎች የሌሏት፣ ይህንንም ለማምጣት ወኔ ያለው አስተዳደር ያላደላት ከተማ ነች፡፡ አስተዳደሩን የሚረከቡ ኃላፊዎች ሁሉ የአዲስ አበባን ፅዳት ጉዳይ በቅጡ አስበው አዲስ አበባን ንፁህ ማድረግ አልቻሉም፡፡

ወንዝዎቿም በስም ብቻ የሚኖሩ የቆሸሹ ናቸው፡፡ ጠጋ ሲሏቸውም ለአፍንጫችን ጠንቅ የሆኑና ለዕይታም የማይመቹ ናቸው፡፡ ከወንዞቻችን ግራና ቀኝ ለምለም ነገር ሳይሆን የፕላስቲክ ክምርና ቆሻሻ ማዘውተሪያ እንጂ ለውበትና ፅዳት ያልታደሉ ሆነዋል፡፡

የጋማ ከብቶች ከነዋሪዎችና ከተሽከርካሪዎች ጋር እየተጋፉ የሚጓዙባት አዲስ አበባ፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎቿ በፕላስቲክ ቆሻሻዎች የተደፈኑ፣ ከሚሠሩት የማይሠሩት የሚበዛባቸው እንደሆኑ ነዋሪዎቿ የምናውቀው ነው፡፡ ስለከተማችን ፅዳት ደንታ የሌለን ስለመሆናችም አይካድም፡፡ ቆሻሻ የማስወገድ ባህላችን ደካማ ነው፡፡ ከቤት ውጭ ላለው የከተማዋ ፅዳት ተቆርቁሮ አዲስ አበባን ከተጣለባት ቆሻሻ ለማላቀቅ የሚያስችል አሠራር የለንም፡፡ በቂ የቆሻሻ ማጠራቀሚያና ማስወገጃ ሥፍራም የለም፡፡

አካባቢን ለማፅዳት ምቹ ሁኔታዎች እያለ እንኳን አካባቢን በቋሚነት የማፅዳት ልምድ የለም፡፡ ብዙዎች ይህ ጉዳይ የራሳቸው ስለመሆኑም የመገንዘብ ችግር አለ፡፡

እኔ በምኖርበት አንድ ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ የተቋቋመ ኮሚቴ በሁለትና ሦስት ወር የፅዳት ፕሮግራም አለው፡፡ በፅዳቱ ቀን ሁላችንም ከቤታችን ደጃፍ ጀምሮ ግቢውን እናፀዳለን፡፡ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ግን በዚህ ፕሮግራም ላይ አንዳንዶች አይሳተፉም ደጃፋቸውንና ጓሯቸውን እያፀዳን ‹‹ምን አገባኝ›› ብለው በራቸውን ዘግተው ሲቀመጡ በተደጋጋሚ አስተውያለሁ፡፡ ይህ የእኛንም ችግር ያሳያል፡፡

ስለዚህ ዛሬ ለከተማችን ፅዳት ጉድለት ከተማዋን በኃላፊነት ተረክቦ የሚያስተዳድረው አካልና እኛም ነዋሪዎቹ ለአዲስ አበባ ፅዳት ግድፈት ተጠያቂዎች ነን፡፡ ለከተማችን ፅዳት አለመጨነቃችን ከተማችንን ምቹ መኖሪያ እንድትሆን እየፈረድንባት ነው፡፡ ሁላችንም የከተማ ፅዳት ጉድለት ላይ ደፍረን የምንናገረውን ያህል ለፅዳቱ ያበረከትነውን አስተዋጽኦ ብናይም፣ ለጉድለቱ አንዳችን በሌላኛው ላይ ጣት እየቀሰርን ቆይተናል፡፡ በእርግጥ ለከተማ ፅዳት መፍትሔ ለመስጠት አስተዳደሩ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በተግባር የሚታይ ዕቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለከተማዋ ፅዳት ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

የከተማ ፅዳት ጉድለት ጋር የሚፈጠሩ መሰናክሎች የከተማ ውበትን በመቀነስ ብቻ የሚወሰን አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በአብዛኛው የከተማው ጎዳናዎች ላይ ውኃ ተኝቶ ለትራፊክ እንቅስቃሴው እንቅፋት ለመሆኑ አንደኛው ምክንያት ውኃ ማስወገጃዎች በአግባቡ ባለመገንባታቸው ብቻ ሳይሆን የከተማችንን ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ነው፡፡ አገልግሎት መስጠት እየቻሉ ውኃ መቀበልና መሸኘት ያልቻሉ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ትልቁ ችግራቸው በቆሻሻ መደፈናቸው ነው፡፡ ቆሻሻውን ደግሞ ያመነጨነው እኛ ነን፡፡ ይህንኑ ለማረጋገጥ ባለፈው ዓመት የመንገዶች ባለሥልጣን የፍሳሽ ጉድጓዶችን ሲያፀዳ የወጣውን ቆሻሻ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ አካባቢን ለማፅዳት ምክንያት መደርደር አያሻም፡፡

ለማንኛውንም ሰሞኑን አስተዳደሩ ምን እንዳነሳሳው ባናውቅም አዲስ አበባን ለማፅዳት ቋሚ ፕሮግራም እንደ ቀረፀ ይፋ አድርጎ ይህንኑ ተከትሎ ተከታታይ ማንቂያ ማስታወቂያዎች ስንሰማ ቢዘገይም ዕቅዱ መልካም ስለመሆኑ አይጠረጠርም፡፡

ይህ እንዲሆን እኛም መተባበር አለብን፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ካፀዳን በኋላ ቆሻሻውን የምናኖርበት ቦታ ከሥር ከሥር በቶሎ የሚያነሳ ተሽከርካሪ በቂ የሆነ ዝግጅት ተደርጓል ወይ? ሌላው ነገሩ የአንድ ሰሞን እንዳይሆን ምን ይደረግ? ኃላፊነቱንስ እንዴት መውሰድ እንደሚቻል መታየት አለበት፡፡

የከተማው አስተዳደር ወርኃዊ ከተማን የማፅዳት ዕቅድ በትክልል ለማዋል ዝግጁ መሆን እንዳይስተጓጎል በቂ ዝግጅት መደረጉንም ማረጋገጥ ያሻል፡፡ ከተማን ለማፅዳት እያንዳንዱ ኃላፊነት ኖሮት እንዲሠራ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ጉዳይ በቅጡ ማሰብ ንፁህና አረንጓዴ ከተማ እንድትኖረን ከአስተዳደሩ ጥረት ጎን ለጎን ኃላፊነት የሚወስድ በየአካባቢውም የፅዳት አምባሳደሮች ኖሮን ሥራ ቢሠራ ለውጥ ይመጣል፡፡ ካልሆነ ነገሩ የአንድ ሰሞን ግርግር ይሆናልና በተደራጀና በተጠና መልኩ ከተማችን እንድትፀዳ ትሁን፡፡

ምናልባትም እንዲህ ያለውን ሥራ በበጎ ፈቃደኞች ጭምር በመደገፍ መሥራት ያሻል፡፡ አስተዳደሩ ምቹ የሆኑ ነገሮችን በማቅረብ ሥራው በየአካባቢው ነዋሪዎች የሚሠራ ሆኖ ከሥር ሥር ዘላቂ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ለዘለቄታው ግን ቆሻሻ ማንሳት ቢዝነስም ነውና ወደዚያ የሚገባበት መንገድ ሌሎች አማራጮችንም እየተቀበሉ ሥራ ላይ በማዋል ይሠራል፡፡

አስተዳደሩ ግን የበለጠ የሚመሠገነውና በእርግጥም ለከተማዋ ፅዳት መጨነቁን የምናውቀው ሰሞኑን በቋሚነት በየወሩ አስፈጽማለሁ ያለውን ሲከውንና ውጤቱንም ሲያሳይ ነው፡፡

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት