Saturday, December 9, 2023

ልማታዊ መንግሥትና የገጠመው የጥገኛ ገዥ መደብ ምሥረታ ጣጣ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ አኅጉርን እንዴት ከድህነት አዘቅጥ አውጥቶ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግርር ማረጋገጥ ይቻላል በሚል ንድፈ ሐሳብ ላይ ያተኮረ፣ የዶክትሬት ማሟያ ጥናታዊ ምርመራቸውን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እያሰናዱ እንደበር ይታወሳል፡፡

አቶ መለስ “African Development: Dead Ends and New Beginnings” የሚል ርዕስ የሰጡትን ጥናታዊ የምርምር ሥራቸውን መግቢያና የአሥር ምዕራፎችን የተጨመቀ ይዘት በ56 ገጾች ለውይይት ያቀረቡ ቢሆንም፣ ሙሉ የምርምር ሥራቸውን አጠናቀው ሳያሳትሙ በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አቶ መለስ “Dead Ends and New Beginnings” በተሰኘው ጥናታዊ ምርመራቸው ሁለት የኢኮኖሚ ሞዴሎችን በንፅፅር በመመልከት፣ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገትንና መዋቅራዊ ሽግግርን በፍጥነት ለማረጋገጥ የትኛው መንገድ ውጤታማና የተሻለ አማራጭ እንደሆነ በመፈተሽ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡

በዚህ ጥናታዊ የምርምር ሥራቸው “Dead Ends” የሚለውን ሐረግ የሚወክለው የካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ሥርዓትን ያረጋገጡት ምዕራባዊያን አገሮች የተከሉት የኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ሞዴል አማራጭ፣ በአፍሪካ ሕይወቱን ጨርሶ ወደ መቃብሩ እየባ ስለመሆኑና “New Beginnings” በሚለው ሐረግ ሥር ደግሞ ዴሞክራሲያዊ የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሞዴል ትግበራ ጅማሮ ብቻ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንና መዋቅራዊ ሽግግርን በአፍሪካ ማረጋገጥ እንደሚቻል ይሞግታሉ፡፡ ሁለቱም የኢኮኖሚ ሞዴሎች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣት የቴክኖሎጂ አቅም ክምችት (Technology Accumulation) ጠቀሜታ መሠረታዊነት ላይ ይስማማሉ፡፡

የሁለቱ የኢኮኖሚ ሞዴሎች አስተምህሮ የልዩነት ሐተታ ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የሆነው ቴክኖሎጂ የመፍጠርና የማከማቸት ሒደትን ማን ቢመራው ውጤታማ ይሆናል በሚለው ነጥብ ላይ ነው፡፡

የኒዮ ሊበራል ዘውግ አስተምህሮ መንግሥት በገበያ ጣልቃ ሳይገባ ነገር ግን የአመቻችነትን ሚና ብቻ እየተወጣ በነፃ የገበያ ውድድር የተክኖሎጂ አቅም የማከማቸት (Technology Accumulation) የማያቋርጥ የቴክኖሎጂ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል፣ በገበያ ውድድርም የሀብት ክፍፍልን ማዳረስ እንደሚቻል ይሞግታል፡፡ የመንግሥት ሚና መሆን ያለበትም ሥርዓቱን የመጠበቅ ማለትም የንብረት መብት ጥበቃንና የአዕምሮ ፈጠራ ውጤቶችን መብት ማረጋገጥ፣ የሰው ኃይል ልማትና ጥናትና ምርምሮችንና የመሳሰሉትን የመደገፍ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ መሆኑን ያምናል፡፡

አቶ መለስ ግን በጥናታዊ ምርመራቸው የኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ሞዴል አመክንዮ የሆነውን የውድድር ገበያ መርህ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ፋይዳ እንደማይኖረው ተከራክረዋል፡፡ የኢኮኖሚ ተመራማሪና መምህር አቶ ሀብታሙ አለባቸው በአቶ መለስ ጥናታዊ ምርምር ላይ ባደረጉት የግምገማ ምልከታ፣ አቶ መለስ የኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ሞዴል በአፍሪካ እንደማይሠራ ለማሳየት የተጠቀሙበት የጥናታቸው አንጓ በአፍሪካ የሚታየው የገበያ ጉድለት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የውድድር ገበያ የሚወሰነው በአገር ውስጥ ባለው የገበያ መጠንና ስፋት፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ባለው የማምረት አቅም መሆኑን በማውሳት፣ ጥልቅ የገበያ ጉድለት ባለበት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ያለ መንግሥት ጉልህ የአኮኖሚ ጣልቃ ገብነት ፈጣን ዕድገትንም ሆነ መዋቅራዊ ሽግግር እንደማይታሰብ በጥናታቸው መደምደማቸውን አቶ ሀብታሙ ያስረዳሉ፡፡

ገበያው በሌለበት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለ መንግሥት እጅና እግሩን አጣምሮ የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ፍላጎት ገበያው ራሱ እንዲመልሰው የሚሰበከው የኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ሞዴል፣ እርስ በርሱ የሚጣረስ መሆኑን አቶ መለስ በመከራከሪያነት እንደሚያነሱ ይጠቁማሉ፡፡

አማራጩ መንገድም መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነትና የመሪነት ሚና የሚይዝበትን የኢኮኖሚ ሞዴል ዕውን ማድረግ መሆኑን፣ የአቶ መለስ ጥናታዊ ምርምር ድምዳሜ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮን በማጣቀስ ይከራከራል፡፡

የአፍሪካ መንግሥታት ያላቸውን ውስን ሀብት ራሳቸው እያንቀሳቀሱ የቴክኖሎጂ አቅምን የማከማቸትና የተጠና የሀብት ክፍፍል ማስፈን እንደሚቻል፣ የልማት ወኪል የሆኑ ከመንግሥት ፍላጎት ጋር ለሚስማሙ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ኪራይን በመደልደል (Rent Allocation) ማለትም ከታክስ ነፃ ዕድሎችን፣ የመሬት አቅርቦትና የመሳሰሉትን በውጤታማነት መርህ በመፍቀድ ቀጣይነት ያለው የቴክኖሎጂ ፈጠራን (Innovation)፣ የሀብት ድልድልና የዕድገት ምንጭ እንደሚሆን ይደመድማሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪና መምህር አቶ ናሁሰናይ በላይም የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ሞዴል ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተስማሚ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

የኢኮኖሚ ሞዴሉ ገዥው ፓርቲ ከሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ርዕዮት ጋር የተጣጣመ እንደሆነ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመቀየር ተፈጥሯዊ ሒደትን መጠበቅ እንደማይቻል በማመን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የለውጥ አካላትን በአብዮታዊነት መርህ ማሳተፍን የመረጠ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡ አብዮትን (Revolution) መጠቀም ያስፈለገው ፈጣን ለውጥ ስለሚፈለግ እንደሆነ ያብራሩት አቶ ናሁሰናይ፣ የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ አስተምህሮ ዓላማም የገበያ ውድድር የሚወስደውን ረዥም ጊዜና መማቀቅ ማሳጠር ትልሙ እንዲሆነ ገልጸዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በዚህ መንገድም ሆነ በሌላ የካፒታሊዝም ኢኮኖሚን መገንባት እንደሆነ፣ ነገር ግን የካፒታሊዝም ሥርዓትን በተፈጥሯዊ መንገድ ለመገንባት የሚያስፈልገው የከበርቴ መደብ እስኪመሠረት መጠበቅ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደማይፈቅድ በማመን፣ የሚመራው መንግሥት የአገሪቱ ሀብትን በሞግዚትነት ወይም ተፈጥሯዊ ባለቤት ሳይሆን የካፒታሊዝም ሥርዓት ግንባታን ለማካሄድ የመረጠው መንገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ መንገድ በሌሎች አገሮች ለአብነትም በጃፓንና በኮሪያ ተሞክሮ የተረጋገጠ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ሞዴል በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረበት ጊዜ  አንስቶ በመንግሥት መሪነት በርካታ የኃይል ማመንጫ፣ ከፍተኛ ክልል አቋራጭ የትራንስፖርት መንገዶች፣ የባቡር መሠረተ ልማቶች፣ የኢንዱስትሪ ዞኖችና በመንግሥት ዋና መሪነት ላለፉት 15 ዓመትና በላይ ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ የገዥው ፓርቲ ዓላማና መስመርን እንዲያራምዱ የተመሠረቱ የፓርቲ ኢንዶውመንት ኩባንያዎችም ያካበቱትን የኢንቨስትመንት ካፒታል ጥቅም ላይ በማዋል ሲንቀሳቀሱ መንግሥት በታክስ ዕፎይታና በመሬት አቅርቦትና በመሳሰሉት የሚያከፋፍለውን ኪራይ የሚጠቀሙ የግሉ ዘርፍ የአኮኖሚ ተዋናዮች ላለፉት በርካታ ዓመታት ትርጉም ያለው ሚና እየተጫወቱ መቆየትቸው ይነገራል፡፡ በመንግሥት አደራጅነት የመከላከያ የልማት ተቋማትን ሀብት አሰባስቦ በ2002 ዓ.ም. የተመሠረተው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንም፣ አገራዊ የኢንዱስትሪ አቅም እንዲገነባ የተጣለበትን ኃላፊነት ይዞ ብዙም ባይሳካለትም እየዳኸ ይገኛል፡፡

የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሥርዓትን አንስተው ከመሞገት ባለፈ ተግባራዊ የሙከራ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡት አቶ መለስ ዜናዊ በሕልፈት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ፣ የባለ ሁለት አኃዝ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ፍሬን ለማየት የበቁ ሲሆን፣ ይህ ፈጣን ዕድገት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

የኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ሞዴል አቀንቃኞች በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሞዴል ላይ የሚሰነዝሩት ዋነኛው ትችት፣ በመንግሥት መሪነት የሚደለደል ኪራይ ለብክነት ወይም ለምዝበራ ይዳረጋል የሚል ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊም በዚህ ትችት ይስማማሉ፡፡ የሰው ልጅ የራሱን ጥቅም የማስቀደም ተፈጥሯዊ ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ በፓርቲና በመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ብዝበዛ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ያምኑ ነበር፡፡ ለዚህ የሚሰጡት መፍትሔ ጠንካራ ዲሲፕሊን ያለው ፓርቲ በየጊዜው ራሱን የሚታገልና የሚለውጥ፣ ከቆመለት ዓላማ የማይዛነፍ መሆን እንዳለበት በጽሑፋቸው አትተዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀርና የሚፈጠረውን ኪራይ የማባከንና የመበዝበዝ አዝማሚያ በመንግሥትና በፓርቲው ኃይሎች ቢንሰራፉ አገርና መንግሥትን የመበተን አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሞዴል ላለፉት 13 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን በማስመዝገብ የኢኮኖሚ ሞዴሉ ይህ ቀውስ ጎልቶ ያልታየበት የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲና የኢሕአዴግ መሥራች የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ቋሚ ኮሚቴ፣ 35 ቀናት የፈጀ ጥልቅ ውይይትና ግምገማ አካሂዶ የፓርቲው አናት ብልሽት እንደገጠመው ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹አመራሩ የሐሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቲክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙርያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሠረተ አመራር የማይሰጥ፣ ሕዝብንና ዓላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል፤›› ሲል የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ያትታል፡፡

በማከልም ‹‹ለሕዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከአገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ እየቆጠረ፣ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬትማ የሕዝብ ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ፣ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዥ መደብ የማሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን…›› የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ይገልጻል፡፡

በጥቅሉ ለፓርቲው የተበላሹ አባላት የሰጠው ስያሜ እንደ ቀድሞ ‘ኪራይ ሰብሳቢዎች’ ወይም ሌቦች የመሳሰሉት ሳይሆን፣ ‹‹ጥገኛ ገዥ መደብ የመመሥረት›› ፍላጎት ያላቸው እንደሆነ ነው፡፡ ለመሆኑ ጥገኛ ገዥ መደብ ማለት ምን ማለት ነው?

ጥገኛ ገዥ መደብ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ ናሁሰናይ በላይ፣ ስለጥገኛ መደብ የሕወሓት ማኅበራዊ መደብ በማብራራት ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ አንድ ፓርቲ ሲመሠረት የሚቆምለትን ወይም የሚታገልለትን ማኅበራዊ መደብ ወይም ማኅበራዊ መሠረት የግድ ይኖረዋል፡፡ የሕወሓት ማኅበራዊ መደብም አርሶ አደሩ፣ ሰፊው የከተማ ነዋሪና አብዮታዊ ልሂቅ የሆነውን አካልም እንደሚያካትት ያወሳሉ፡፡ ስለዚህ ሕወሓት የቆመለትን መደብ ጥቅም የማስከበር ፖለቲካዊ ትግል እንደሚያደርግ ይጠቁማሉ፡፡ የየትኛውም ፓርቲ አመራር የቆመለትን የማኅበረሰብ መደብ ዘንግቶ ያገኘውን ሥልጣን ለራሱ ጥቅም መበልፀጊያ ሲጠቀምበት፣ ጥገኛ (ፓራሳይት) ሆኗል ወይም የመደብ ራስን ማጥፋት (Suicide) ፈጽሟል እንደሚባል ያስረዳሉ፡፡

በቅርቡ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚት አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ማኅበራዊ መሠረቱ ተማሮ እያለ የሚረካ አመራር ካለ እሱ ማኅበራዊ መሠረቱን የካደ ነው፤›› ሲሉ ሰሞኑን ከዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ ጋር በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጡ ተናግረዋል፡፡

በትግራይ የመስኖ አገልግሎት ይህንን ያህል ደርሷል እያለ የሕወሓት የትግራይ አመራር ሪፖርት ቢያቀርብም፣ ኅብረተሰቡ ዘንድ የደረሰ ነገር እንደሌለና ሕወሓት ማኅበራዊ መደቡን ሲያማርር እንደከረመ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ማኅበራዊ መደቡ እያለቀሰ አመራሩ ልሾም ልሸለም እያለ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የጥገኛ መደብ አደጋና አገራዊ ይዘት

የጥገኛ መደብ መመሥረት የሚፈጥረው አደጋ በትንሹ ይጀምርና አገር እስከ ማፍረስ እንደሚደርስ አቶ ናሁሰናይ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ዜጎች በስማቸው በሚነግድ አካል እየተዳደሩ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ሕገ መንግሥት ይጥሳል፤›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ስለመሆናቸው እንደሚደነግግ የሚያስታውሱት አቶ ናሁሰናይ፣ በዚህ ሒደት ግን የሥልጣን ባለቤትነታቸው ይነጠቃል፣ ይህ ሲሸረሸር ደግሞ በራሳቸው ጉዳይ የመወሰንና ራሳቸውን የማስተዳደር መብታቸውን ያጣሉ ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ጥቅማቸውም እንደማይከበር ይገልጻሉ፡፡

‹‹ስለዚህ አደጋው ጥገኛ መደብ የመንግሥትን መዋቅር ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ከትንሹ አለመረጋጋት አንስቶ እስከ የመንግሥት መፍረስ ይደርሳል፡፡ በእኔ አረዳድ በሶማሊያ የዚያድ ባሬ መንግሥት የፈረሰው በጥገኛ መደብ መንሰራፋት ቁጥጥር ውስጥ ወድቆ ነው፤›› ይላሉ፡፡

አገራዊ አንድምታውን ሲያነሱም ሕወሓት የጥገኛ ገዥ መደብ የመመሥረት አዝማሚያ ታይቷል ብሎ በፖለቲካ ቋንቋ ከነደረጃው ተናገረው እንጂ፣ የሁሉም የኢሕአዴግ ፓርቲዎች ችግር ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

ኦሕዴድም ቀደም ብሎ ሲገመግም አመራሩን ተጠያቂ አድርጎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ናሁሰናይ፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ በሁሉም የኢሕአዴግ ፓርቲዎች ውስጥ ያለ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ የችግሩን አገራዊ ባህሪ በመረዳት ለኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች መልዕክት ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ ‹‹በሕወሓት የተፈጠረው የአመራሩ ቀውስ በእህትና በአጋር ድርጅቶች መካከል ለበርካታ አሥርት ዓመታት የነበውን በመርህና በትግል ላይ የተመሠረተ ውህደት፣ ለዙሪያ መለስ ስኬት ያበቃን የአመለካከትና የተግባር አንድነት በየጊዜው እየሸረሸረ እንደመጣና በጋራ ዓላማ ዙሪያ በአንድ ልብ መንፈስ ከመንቀሳቀስ ይልቅ፣ በንትርክና በጥርጣሬ መተያየት እንዲሆን በማድረግ በኩል የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳደረገ በትክክል አስቀምጧል፤›› በማለት ይገልጻል፡፡

አቶ ናሁሰናይ እንደሚሉት ደግሞ ጥገኛ ገዥ መደብ መደበቂያው ብሔር ወይም የማኅበረሰቡን ስስ ድክመቶችን ዋሻው አድርጎ በመሆኑ፣ አገራዊ ይዘት የሚሆንበት ዕድል እንደሚኖረው ይገልጻሉ፡፡

መፍትሔው

የተገለጸው ጥገኛ ገዥ ወይም ሥልጣን ላይ የቆየ የፖለቲካ ጉልበት ያለው፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ጥቅምን ሲመጠምጥ የነበረ በመሆኑ በአመለካከት ለውጥ በቀላሉ ይወገዳል ብለው የማያምኑ አስተያየት ሰጪዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ሕወሓት በበኩሉ በአመለካከት ደረጃ ችግሩን እንደፈታ ይገልጻል፡፡ ‹‹ማንም ሰው በጥገኝነት የማይከብርበትን ሥርዓት ለመፍጠር ልንሠራ ይገባል፡፡ ሕወሓት ከዚህ አንፃር የራሱን ሥራ ሠርቷል፡፡ አስተካክሎ መጥቷል፡፡ ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋርና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን የሚያዋጋው አቅም ሰንቋል፤›› ይላል፡፡

አቶ ናሁሰናይ ሕወሓትም ሆነ የኢሕአዴግ አመራሮች ችግሩን ከእነ መጠኑና ጥልቀቱ የተረዱት በመሆኑ እንደሚፈቱት ያምናሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በፍጥነት እንዲከተላቸው ከተፈለገ በተለይ ሕወሓት በፍጥነት የለውጥ ምልክቶችን ማሳየት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ የሽግግር ጊዜ ዕቅዶችን በየዘርፉ ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፡፡ ሌሎች ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች አቶ ናሁሰናይ ካነሱት ሐሳብ ጋር የሚስማሙ ሲሆን፣ አቶ ለማ መገርሳ ወደ ኦሕዴድ ሊቀመንበርነትና የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው እንደመጡ በሕገወጥ መንገድ በተያዙ መሬቶች፣ በማዕድን ዘርፍ ላይ በተሰማሩ እሴት በማይጨምሩ ባለሀብቶች ላይ  ዕርምጃ በመውሰድና በሌሎች ተመሳሳይ ዕርምጃዎች የለውጥ ምልክት በማሳየታቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኦሮሞን ማኅበረሰብ ለማንቀሳቀስ መቻላቸውን በማሳያነት ያነሳሉ፡፡ 

የሕወሓት የቀድሞ ከፍተኛ አመራርና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት፣ እንዲሁም የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ገብሩ አሥራት ግን በሕወሓት ተስፋ የላቸውም፡፡ ሕወሓት የወደቀ መንግሥት መሆኑንና ከእሱ የሚጠብቁት ተስፋ እንደሌለ ገልጸው፣ መፍትሔ መሆን የሚችለው የፖሊሲ ለውጥ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የችግሩ ምንጭ የፖለቲካ ኢኮኖሚው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩ በአንዴ የሚፈታ ሳይሆን ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት ከፓርቲው ጋር አብሮ የሚኖር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ መፍትሔው በየጊዜው እየደፈቁና እየቀነሱ መሄድ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ዘመኑ ተናኘ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡                                                                                                                                                                                                   

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -