Sunday, September 24, 2023

የመንግሥትን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የሚጠይቀው የውኃ አጠቃቀም ስትራቴጂ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከማስተማር በተጨማሪ የመመረቂያ ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ የነበሩ የኬሚስትሪ ተማሪዎች አማካሪ ሆነው ያጋጠማቸውን ልምድ አቶ አመሐ በቀለ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የመመረቂያ ጽሑፋቸውን እየሠሩ ከነበሩ ተማሪዎች ለአንዱ አማካሪ ሆኜ በማግዝበት ወቅት፣ ለጥናቱ ግብዓት ሲሰበሰብ ካገኛቸውና ካነጋገራቸው ግለሰቦች መካከል በአቃቂ አካባቢ ያነጋገረው ወጣት ታሪክ አስደንጋጭ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ከአዲስ አበባ በአቃቂ በኩል አድርጎ ወደ አባ ሳሙኤል በሚፈሰው ወንዝ ዳር በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ራሳቸውን ስለሚያስተዳድሩ አርሶ አደሮች የአንዱን ታሪክ ይገልጻሉ፡፡ ይህ የተመራቂው ተማሪ የጥናት አካል የሆነው ወጣት አርሶ አደር ውኃውን አትክልት ለማጠጣት ሲሞክር ሰውነቱን እንደሚያሳክከው፣ ሌላ ጊዜ በቆዳው ላይ መሰነጣጠቅ እያስከተለበት መሆኑን የጥናት ሥራውን በሚያማክሩበት ወቅት መታዘባቸውን ይገልጻሉ፡፡

አቶ አመሐ በቤተ ሙከራ አማካሪነት የሚያገለግሉ የኬሚስትሪ ባለሙያ ናቸው፡፡ ይህን ልምዳቸውን ያካፈሉት ከታኅሳስ 15 እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው የሁለት ቀናት የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ላይ ነበር፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ አመሐ፣ ኢትዮጵያ ያላት የውኃ ሀብት ከፍተኛ ቢሆንም ውኃው በቴክኖሎጂ በታገዘ የአጠቃቀም ዘዴ ካልተያዘ፣ ከሀብትነቱ ይልቅ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ታድላለች ተብሎ ከሚነሱ የተፈጥሮ ሀብቶች ውስጥ የውኃ ሀብት ይጠቀሳል፡፡ አንዳንዴም አገሪቱን ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ›› በማድረግም ስሟ ሲነሳ መስማት የተለመደ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በተለይ ከዓለም የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር በተያያዘና ከአካባቢ መራቆት ጋር በተገናኘ፣ የአገሪቱ የውኃ ሀብት መቀነሱንና አደጋ ላይ መውደቁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሲነገር ይሰማል፡፡

በቅርቡ የተሾሙት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ በአዳማው የምክክር ጉባዔ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ባደጉበት ወቅት የአገሪቱን ውኃ ሀብት በዝርዝር ገልጸው ነበር፡፡

‹‹አገራችን እንደሚታወቀው ሰፋፊ የተፈጥሮ ፀጋዎች ያላት ውብ አገር ናት፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በውኃ ዘርፍ ብቻ ያሏት የተፈጥሮ ፀጋዎች ማንኛውንም ዓይነት የኢኮኖሚ እመርታ ለማስመዝገብ፣ በዚያው መጠን የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል መሠረታዊ ዕድገት የሚፈጥሩ ስትራቴጂካዊ የተፈጥሮ ሀብት ናቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በየተፋሰሶቹ በተደረገ ጥናት የአገሪቱ አለኝታ የሆነው ውኃ 123 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ሜትር የሚደርስ ሲሆን፣ ከዝናብ የሚገኘው ውኃ ወደ አንድ ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሚደርስም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ከጠቀሷቸው ሁለቱ የውኃ መገኛዎች ውስጥ 12 በመቶ የሚሆነው በገጸ ምድር ላይ የሚገኘው እንደሆነ፣ በትክክል የማይታወቅ በማለት ሚኒስትሩ የገለጹት ወደ 36 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚገመት የከርሰ ምድር ውኃ አገሪቷ እንዳላት አክለዋል፡፡ እንዲሁም ቅሪተ አካል በሚገኝበት የመሬት ጥልቅ ክፍል ያለው የውኃ መጠንም በትክክል እንደማይታወቅ ጠቁመዋል፡፡

ይህ ሁሉ የሚገመተው በአንፃሩ በተፋሰሶች አማካይነት ወደ ሌላ አገር ከሚሄደው በተጨማሪ፣ አብዛኛው ውኃ በትነት መልክ እንደሚባክንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹በአገሪቱ ያለንን ሀብት በአግባቡ ይዘን ወደ ጠቃሚ ሀብት ልንለውጥ ይገባናል፤›› ያሉት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ፣ ‹‹ይህን ማድረግ ስላልቻልን የተለዋዋጭ የተፈጥሮ አደጋና ድርቅ ተጋልጠናል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም አለ የተባለውን ከፍተኛ የውኃ ሀብት ተጠቅሞ የሕዝቡን ኑሮ በአግባቡ መለወጥ እንዳይቻል ያደረጉ ምክንያቶችን ሚኒስትሩ የዘረዘሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ‹‹የውኃ ሀብታችንን እንዳንጠቀም የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ እንዳይኖረን ያደረጉን ያለፉት ሥርዓቶች፤›› ይገኙበታል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ወጥ የሆነ የውኃ አጠቃቀም ፖሊሲ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አለመኖሩ ሌላው ችግር እንደነበርም አክለው ገልጸዋል፡፡

የውኃ ሀብቱን በመጠቀም ረገድ መንግሥት አበረታች የልማት ሥራዎችን እየተገበረና መልካም ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ወቅት ያለው ሳይንሳዊ አጠቃቀምና በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል ውሱንነትን ጨምሮ የውኃ ሀብት መጠኑን ማስተካከል የሚችል የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን አለመቻሉ ትልቁ ተግዳሮት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የውኃ ዘርፍን በአግባቡ መጠቀምና ወደ ተሻለ የልማት ምንጭነት ለማሳደግ ከሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ተቋማት ዋነኛውን ኃላፊነት ወስዶ እንዲንቀሳቀስ በአዋጅ የተቋቋመው፣ የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ተቋሙ በኢንስቲትዩትነት በ2005 ዓ.ም. በአዋጅ ከመቋቋሙ በፊት በፕሮጀክት ደረጃ በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) ድጋፍ፣ ለ15 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ውኃ ምርምር ማዕከል በመሆን አገልግሏል፡፡

የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ጋረደው፣ ኢንስቲትዩቱ የውኃ ዘርፍን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ በሰው ኃይል ልማትና በምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ታስቦ በመንግሥት መቋቋሙን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በዋናነት በሰው ኃይል ልማትና በውኃ ሀብት ዙሪያ ችግር ፈቺ ምርምር ማካሄድ፣ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ፣ ማስተላለፍና  በሌሎችም ተያያዥ ዘርፎች ላይ የምርምር አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ችግር ሊፈቱና ጠቃሚ የፖሊሲ ሐሳቦች ለማመንጨት፣ የሥራ አፈጻጸምን ለመገምገምና የወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

አቶ ዘነበ ተቋማቸው ልዩ የቤተ ሙከራ አገልግሎት መስጠት አንዱ ተልዕኮው መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በአገር ውስጥ ያለ የከርሰ ምድርም ሆነ የገጸ ምድር ውኃ የተለያዩ ፍተሻዎች እንደሚደረግላቸውም ይጠቁማሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችና ኢንዱስትሪዎች እያደጉ እንደሚገኙ የሚጠቁሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሚለቅቁት ፍሳሽ ፍተሻ ሊደረግለት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ለመጠጥነት የሚውለው ውኃም ለጤና ተስማሚ ስለመሆኑ አስፈላጊው ፍተሻ ሊደረግለት ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ ይህንን ፍተሻ ለማከናወን የሚውሉ ቤተ ሙከራዎች በጣም ጥቂት እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡ ፍተሻውን በአገር ውስጥ በማከናወን የውጭ ምንዛሪን ማዳን ይገባልም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ልዩ ቤተ ሙከራውን ለማደራጀት ኢንስቲትዩቱ እየሠራ ነው፡፡ ‹‹ቤተ ሙከራውን ለማደራጀት ከፍተኛ በጀት ያስፈልጋል፡፡ የገንዘብ እጥረትም አለ፡፡ ችግሩን ለመፍታት መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ለቤተ ሙከራው አገልግሎት የሚውሉ ኬሚካሎችም በተመሳሳይ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ናቸው፤›› በማለት ከሚያበረክተው አገልግሎት አንፃር ተመዝኖ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ቤተ ሙከራውን ገንብቶ አስፈላጊዎቹን የመመርመሪያና የመፈተሻ መሣሪያዎች ለማሟላት፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የሚጠበቅ መሆኑን፣ የተቋሙ ኃላፊዎች አጠቃላይ የፋይናንስ ፍላጎቱን ለማጠናቀቅ የዳሰሳ ጥናት እያካሄዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ኃላፊዎቹ ቢያንስ አንድ የመፈተሻ መሣሪያ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

‹‹መሣሪያዎቹ ባላቸው የገበያ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ስንመለከት ውድና ከፍተኛ ፋይናንስ የሚፈልጉ ናቸው፤›› በማለት ለሪፖርተር ያስረዱት አቶ ዘነበ፣ ፋይናንሱ በመንግሥት ብቻ የሚሸፈን ነው ለማለት ስለሚያስቸግር አማራጭ የገቢ ምንጮች የሚገኙበትን መንገዶች መንግሥት ሊያስብበት እንደሚባ አክለዋል፡፡

የፋይናንስ አቅሙ አገርን የሚፈታተን መስሎ ቢታይም ውኃ ሕይወት በመሆኑ የግድ ቤተ ሙከራውን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ውኃ ማግኘት ሕይወት ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ሕይወት የሆነ ጉዳይ ላይ ደግሞ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ አገሮች ለምሳሌ ኬንያን ብንመለከት ውኃ ሰብዓዊ መብት ነው ብለው እየሠሩ ነው፡፡ እኛም አገር ለሕይወት ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ስለሌለ ንፁህና የተጣራ ውኃ ለማግኘት ደረጃውን የጠበቀ ቤተ ሙከራ የግድ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በቤተ ሙከራ አገልግሎት ዘርፍ የማማከር ሥራ የሚሠሩት የኬሚስትሪ ባለሙያው አቶ አመሐ በበኩላቸው የክህሎት ክፍተት፣ የባለሙያዎች  እጥረት፣  ፍተሻ የሚደረግባቸው መሣሪያዎችና ኬሚካሎች አለመሟላት ዘርፉን ፈተና ውስጥ  እንደከተተው ይጠቁማሉ። ቴክኖሎጂን በበቂ ሁኔታ አለመጠቀምም ጉድለት መሆኑን በመጥቀስም የሚኒስትሩን ሐሳብ ያጠናክራሉ። ለአብነት ኢንዱስትሪዎች የሚለቁት ፍሳሽ ተገቢውን የአሠራር ሥርዓት አልፎ አለመወገዱና ለውኃ መበከል ምክንያት መሆኑን በማውሳት፣ ከተፋሰሱ በታች ያሉ የኅብረሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙት በመሆኑ ለተለያዩ ጉዳቶች ሊዳርጋቸው እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ አመሐ ገለጻ፣ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎትም ለኅብረተሰቡ የሚያከፋፍለው ውኃ በአግባቡ ፍተሻ እየተደረገለት ስለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ተቋሙ ባደራጀው ቤተ ሙከራ ሥራውን በአግባቡ መምራት ፈታኝ ሆኖበታል። ይህ እጥረት እንደ አተት ላሉ የውኃ ወለድ በሽታዎች ምክንያት ነው፡፡ የታሸገ ውኃ የሚያቀርቡ የንግድ ተቋማት የአገሪቱን አስገዳጅ ደረጃ አሟልተው ስለማቅረባቸው ተገቢው ክትትል መደረግ አለበት። በሌላ በኩል ለሌሎች የልማት ዓይነቶች የኬሚካል ግብዓቶች በራሳችሁ በውኃ ሀብት ጤናማነት ላይ ችግር እየፈጠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም ያህል በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) የተከለከለው የዲዲቲ ምርት በስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ በወባ ማጥፊያነት ስለሚውል፣ የአገሪቱ የውኃ ሀብት ጥራት ጥያቄና ሥጋት ማስነሳቱ እንዳልቀረ አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለማቃለል በአቶ አመሐ የሚሰነዘሩ የመፍትሔ ሐሳቦች አሉ። የቤተ ሙከራ አደረጃጀትን በአግባቡ በመተግበር እየቀረበ ያለው ለጤና ተስማሚ ውኃ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይገባል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፉ የተሰማሩ አካላትም ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የቆሻሻ ፍሳሽ አወጋገዳቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል፡፡ ፍሳሻቸውን በአግባቡ ካላስወገዱ በውኃ ሀብት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 197/2000 መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተደንግጓል። በዚህ መሠረት የሚመለከተው አካል ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ መሥራት አለበት። የምክክሩ ተሳታፊዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የታሸገ ውኃ የሚያቀርቡ የንግድ ተቋማት የአገሪቱን አስገዳጅ ደረጃ ስለማሟላታቸው የጥራት ፍተሻ ለማድረግ፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ወደ ወንዝ የሚለቁት ፍሳሽ ጉዳት ያለው መሆኑን ለመፈተሽ በልዩ ሁኔታ የተደራጀ ቤተ ሙከራ መገንባት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ የባለሙያዎቹን ጥያቄ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሚኒስቴሩም ሆነ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ መቼ ምላሽ እንደሚሰጡ የገለጹት ነገር የለም፡፡ ሆኖም የኢንስቲትዩቱ ኃላፊዎች ቀደም ሲል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሥራችሁ የፈለገ አበረታች ቢሆን እንኳ ደረጃውን የጠበቀ ልዩ ቤተ ሙከራ መገንባት ካልቻላችሁ የትም አትደርሱም፤›› እንዳሏቸው በማስታወስ፣ ከመንግሥት በጎ ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል፡፡

የልዩ ቤተ ሙከራው መገንባት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን መጠነ ሰፊ የውኃ ሀብት ካጋጠመው መበከልና ሥጋት ሊያላቅቅ እንደሚችልም እያሳሰቡ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -