Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየቦብ ማርሌ አደባባይና ምሥለ ቅርፅ ዕጣ ፈንታ ላይ ሊመከር ነው

  የቦብ ማርሌ አደባባይና ምሥለ ቅርፅ ዕጣ ፈንታ ላይ ሊመከር ነው

  ቀን:

  ለአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ፍሰት እንቅፋት በመሆናቸው መፍረስ አለባቸው ተብለው ከተለዩት አደባባዮች መካከል አንዱ የሆነው፣ የሬጌው ሙዚቃ ንጉሥ ቦብ ማርሌ ምሥለ ቅርፅ ያረፈበትና በስሙ የሚጠራው አደባባይ ዕጣ ፈንታ ላይ ሊመከር ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማን የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለል ይፈርሳሉ ተብለው ከተለዩና በቀለበት መንገዱ ከሚገኙ አደባባዮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ አደባባይ ከመፍረሱ በፊት፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚነጋገርበት ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

  በቀድሞ በኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ከአራት አቅጣጫዎች ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግደውን አደባባይ ለማንሳት ግን፣ ከሦስተኛ ወገን ጋር መምከር ግድ በመሆኑ ይህንን ምክክር ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ተሽከርካሪዎችን በትራፊክ መብራት ለማስተናገድ እንዲቻል ሐውልቱን እንዴት ማንሳት እንደሚገባና ከተነሳም እንዴት ተለዋጭ ቦታ ይሰጠው በሚለው ጉዳይ ላይ ባለሥልጣኑ የሚመክረው ከቦብ ማርሌ ቤተሰቦች፣ ሐውልቱን ከሠራው አርቲስት፣ ከሌሎች አካላትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ነው፡፡  

  ከምክክሩ የሚገኘው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ባለሥልጣኑ እያፈረሳቸው እንዳሉት ሌሎች አደባባዮች ይህንን አደባባይ ሳያፈርስ ይቆያል ተብሏል፡፡

  የቦብ ማርሌን ምስልን በማስቀረፅ በአደባባዩ እንዲቆም በማድረግ በዋና አስተባባሪነት የሚጠቀሰው ድምፃዊ ዘለቀ ገሠሠ፣ የሐውልቱን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ከባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊ ጋር መነጋገሩን፣ ነገር ግን እንዴት ይሁን? በሚለው ጉዳይ ላይ በጋራ ለመምከር እንደተስማሙ ገልጿል፡፡

  ‹‹ለትራፊክ ፍሰቱ ተብሎ የሚነሳ ከሆነ እንዴት የሚለው ጉዳይ ያሳስበናል፤›› ያለው ዘለቀ፣ ሐውልቱን ለማንሳት ባለሥልጣኑ ወደ ዕርምጃ ከመገባቱ በፊት በጋራ ለመነጋገር ስምምነት ላይ መድረሱን በበጎ ጎኑ አይቶታል፡፡ ‹‹ከአስተዳደሩ ጋር በሐውልቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የቦብ ቤተሰቦች እንዲያውቁት መልዕክት ልከናል፤›› ያለው ዘለቀ፣ ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነም ገልጿል፡፡  ‹‹የምሥለ ቅርፁ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እኛንም በቀጥታ የሚያገባን በመሆኑ ሐሳባችንን ለሚመለከተው ሁሉ እናቀርባለን፤›› ብሏል፡፡

  ቦብ ማርሌ ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ አደባባዩ በስሙ የተሰየመ ሲሆን፣ ከአደባባዩ ስያሜ በኋላ ሐውልቱ ተቀርጾ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ እንደ ዘለቀ ገለጻ፣ ‹‹ሐውልቱን ለመሥራት፣ አደባባዩን ለማስዋብና ለክትትል ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ ወጥቷል፡፡ ይህንንም ወጪ  እኔና አዋድ መሐመድ በጋራ ያወጣነው ነው፤›› ብሏል፡፡

  ባለሥልጣኑ ሊፈርሱ ይገባል ብሎ ከለያቸው አደባባዮች መካከል እስካሁን ሦስቱን በማፍረስ፣ የትራፊክ ፍሰቱ በመብራት እንዲስተናገድ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የተጎዱ መንገዶችን እየጠገነ ያለው ባለሥልጣኑ፣ በተለያዩ ምዕራፎች ከፋፍሎ እያከናወነ ያለው ሥራ ከተጠናቀቀ የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ ያስታግሳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ለጥገና ሥራውም ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የያዘ ሲሆን፣ አሁን አደባባዮቹን በማፍረስ መብራት በመትከል እያከናወነ ካለው ሥራው በተጨማሪ፣ በቀጣዩ ዓመት በተመረጡ አደባባዮች ላይ ከላይ መተላለፊያ መንገዶችን ለመገንባት የዲዛይን ሥራ በማናወን ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img