Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየእርሻ ኢንቨስተሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀውን ጥናት ተቹ

  የእርሻ ኢንቨስተሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀውን ጥናት ተቹ

  ቀን:

  በአገር አቀፍ ደረጃ በግብርና ኢንቨስትመንት መስክ የተፈጠሩ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት በተጠራው ስብሰባ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ተጠንቶ ለውይይት የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ በእርሻ ኢንቨስተሮች ተተቸ፡፡

  ቅዳሜ ታኅሳስ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል በተካሄደው ስብሰባ፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ዶ/ር እያሱ አብረሃና የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተገኝተዋል፡፡

  በስብሰባው ላይ የተገኙ ባለሀብቶች እንደተናገሩት የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ባለሀብቱን ያላሳተፈ፣ ከእውነታው የራቀ፣ ባለሀብቶች ከባንኮች ጋር የተናጠል ውል ገብተው ብድር የወሰዱ ቢሆንም የሥራ አፈጻጸማቸውን በጅምላ የተቸ ነው፡፡

  ያላለማውንና የወሰደውን ብድር ለሌላ ያዋለ፣ የቀረጥ ነፃ መብቱን ላልተገባ ያዋለ ካለ ተለይቶ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል እንጂ፣ ሁሉንም ባለሀብት በአንድ ላይ ደካማ ብሎ መፈረጅ አግባብ አይደለም ሲሉ ባለሀብቶች ተናግረዋል፡፡

  ባለሀብቶቹ በስብሰባው ላይ እንደገለጹት በእርሻ ኢንቨስትመንት ሁሉም ኩባንያዎች አንድ ጊዜ አልገቡም፡፡ ኢንቨስተሮቹ በተለያዩ ጊዜያት የገቡ እንደመሆናቸው መጠን፣ የተለያየ የሥራ አፈጻጸም ስላላቸው በጥናቱ ላይ እንደቀረበው በጅምላ መተቸት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡

  ባለሀብቶቹ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በተለይ በጋምቤላ ክልል መሬት ተደራርቧል በሚል በደፈናው ብድር እንዲቆም መደረጉ፣ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሠራር መንሰራፋት፣ ሙስናና የኔትወርክ አሠራር መበርታት፣ የፀጥታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ የሕግ የበላይነትን አለማስከበር፣ የፍትሕ አካላት አድሎአዊ አሠራር፣ እንዲሁም የገበያ ችግርን ለዘርፉ መዳከም ዋነኛ ምክንያት ናቸው ብለዋል፡፡

  ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ባሉበት ወቅት የሥራ አፈጻጸም ደካማነት ጎልቶ ሊወጣ አይገባም በማለት ባለሀብቶቹ ተችተዋል፡፡

  በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ 215 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 15,680 ለሚሆኑ መካከለኛና ከፍተኛ ባለሀብቶች መተላለፉን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ ልማት የተሸጋገረው ከ30 እስከ 35 በመቶ ብቻ መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል፡፡

  ለባለሀብቶች ከተላለፈው መሬት ውስጥ በፌዴራል መንግሥት በኩል ለ134 ባለሀብቶች 500 ሺሕ ሔክታር መሬት፣ የተቀረው ደግሞ በክልል መንግሥታቱ በኩል ለባለሀብቶች መተላለፉን ጥናቱ አመልክቷል፡፡

  በጥናቱ እንደተለገጸው 623 ባለሀብቶች 630,518 ሔክታር መሬት ተረክበዋል፡፡ ከተረከቡት መሬት ውስጥ ሥራ የጀመሩበት 405,572.84 ሔክታር ሲሆን፣ የለማው ግን 64,010.62 ሔክታር (15.8 በመቶ) ብቻ ነው፡፡ 369 ባለሀብቶች ማልማት ያልጀመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 140 ምንጣሮ የጀመሩ ናቸው፡፡ ወደ ልማት ከገቡት 254 ባለሀብቶች 216 በውላቸው መሠረት፣ የተቀሩት 38 ባለሀብቶች ደግሞ ከውላቸው ውጪ ልማት ያካሄዱ ናቸው፡፡ 152 ባለሀብቶች ደግሞ 39,697.96 ሔክታር መሬት ከይዞታቸው ውጪ ማልማታቸው በጥናቱ ተገልጿል፡፡

  የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጋምቤላ ክልል ያካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የ381 ባለሀብቶች 45,531.11 ሔክታር መሬት ተደራርቦ ተገኝቷል፡፡ አቶ ጋትሉዋክ በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት፣ የሚታየውን የመሬት መደራረብ ችግር ክልሉ ለማስተካከል ይሠራል፡፡ በነበረ ይዞታ ላይ ሌላ ባለሀብት ማስተናገድ አይገባም ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹የራሳችን ችግር ነው፤›› ያሉት አቶ ጋትሉዋክ፣ ችግሩን ለመፍታት እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡

  በጋምቤላ ክልል ለእርሻ ኢንቨስትመንት እንቅፋት ፈጥሯል የተባለው የብድር አሰጣጥ ነው፡፡ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ኢንቨስተሮች መካከል ለ200 ባለሀብቶች ብድር ተሰጥቷል፡፡ በጥናቱ እንደተብራራው 12 ተበዳሪዎች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ 188 ባለሀብቶች ደግሞ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር አግኝተዋል፡፡

  ለተበዳሪዎቹ 4.96 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ሲሆን፣ 4.3 ቢሊዮን ብር መለቀቁን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ነገር ግን በቦታ መደራረብና በሌሎች ምክንያቶች በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ ብድር እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ብድር እንዲቆም በመደረጉ ሳቢያ በርካታ ባለሀብቶች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ መደረጉንና በዚህም አገሪቱ ለከፋ ችግር እንደተዳረገች የዘርፉ ተዋናዮች ይገልጻሉ፡፡

  የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ያቆመበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ‹‹መሬት ተደራርቦ ተሰጥቷል፡፡ የቱ መሬት ከየቱ ጋር መደራርቡን ባላወቅንበት ሁኔታ እንዴት ብድር እንሰጣለን?›› ብለዋል፡፡ የመሬት መደራረብ የዘርፉ ችግር መሆኑ ተጠንቶ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ባንኩ ብድር መስጠት ማቆሙንና በቅርቡ (በመጋቢት ወር) ግን በድጋሚ ብድር መልቀቅ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...