Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ብዙ ወላጆች ሳያውቁ ያጠፉ ይመስለኛል›› ወ/ሮ ናርዶስ ማሞ ደስታ፣ ሳይኮቴራፒስት

ወ/ሮ ናርዶስ ማሞ ደስታ ትባላለች፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሶሻል ወርክ በአሜሪካ ካንሳስ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪዋንም የአእምሮ ጤና ላይ በማተኮር በሶሻል ወርክ ሠርታለች፡፡ ከዚያም በሳይኮ ቴራፒስትነት ዕውቅና አግኝታ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ በአሁኑ ወቅት በቡድንና በግለሰብ ደረጃ አእምሮ ጤና ላይ የምክር አገልግሎት በሚሰጠው ማይንድሴት (mindset) ክሊኒካል ዳይሬክተር ሆና በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ በተቋሙ ከምክር አገልግሎት ጋር የሚያያዙ ሥራዎችን ትመራለች እንደ ባለሙያነቷም የምክር አገልግሎት ትሰጣለች፡፡ ከአእምሮ ጤና ችግር ጋር በተያያዘ የተገልጋዮች የአእምሮ ችግሮችን በመረዳት የምክር አገልግሎት መሻትን በሚመለከት የሚስተዋሉ እውነታዎችን እንዲሁም በተቋሙ የምክር አገልግሎት ምን እንደሚመስል ምሕረት አስቻለው ከወ/ሮ ናርዶስ ማሞ ደስታ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የምክር አገልግሎት የምትሰጡት ለማን ነው?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- የአእምሮ ጤና መዛባት ችግር ላለባቸው ብቻም ሳይሆን ለቤተሰብ እንዲሁም የአእምሮ ችግር ያለባቸውን ለሚንከባከቡ ነው፡፡ ተቋሙ በዚህ መልኩ የምክር አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከሞላ ጎደል አንድ ዓመት ሊሆን ነው፡፡ የምናየው በተለያየ መንገድ የአእምሮ መዛባትና የሥነ ልቦና ችግር ያጋጠማቸውን ነው፡፡ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ሱስና ሌሎችም ችግሮችን እናያለን፡፡ ከዕድሜ አንፃር ደግሞ ከሕፃናት እስከ አዋቂዎች እንመለከታለን፡፡ እኔበተለይ ሕፃናት ላይ እሠራለሁኝ፡፡ እስካሁን ከአምስት ከስድስት ዓመት ሕፃናት ጀምሮ እስከ ስልሳ ዓመት ዕድሜ ያላቸውን አይቻለሁኝ፡፡ ወጣቶችና ታዳጊ ወጣቶች ላይ በተይም ከሱስ ጋር በተያያዘ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- በኅብረተሰቡ ዘንድ የአእምሮ ችግሮችን የማወቅና የመረዳት ችግር አለ፡፡ በሌላ በኩል መፍትሔ ለመፈለግ የሚኬድበት አቅጣጫም የተሳሳተ ሲሆን፣ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በዚህና በመሰል ሁኔታዎች ውስጥ ወደ እናንተ አገልግሎት ሽቶ የመምጣት ነገር እንዴት ይታያል?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ያጋጠመኝ ነገር ችግሩ በንግግር ይድናል ብሎ አለማሰብና አለማመን ነው፡፡ እዚህ ቢሮ ገብቼ የአእምሮ ጤና ላይ ከሥነ ልቦና አንፃር መሥራት እችላለሁ ማለት አልቻልኩም ነበር፡፡ የተለያዩ ሰዎችና ተቋማትን አናግሬአለሁኝ የነበረው ነገር ከተማ ተመሥርቶ መንገድ የሌለው ያህል ነበር፡፡ ችግር ያለባቸው ሔዱ ከተባለ የሚሔዱት የሥነ አእምሮ (Psychatrist) ባለሙያ ጋር እንጂ ከእሱ ቀጥሎ የሥነ ልቦና ባለሙያ ማማከርን አያስቡትም፡፡ አገልግሎት የጀመርኩት ሌላ ቦታ ነበር፡፡ ለማማከር የሚመጣ ሰው አልነበረም፡፡ ከመጣሁኝ ሦስት ዓመት ሆኖኛል ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት እዚህ አገር ያሉ ኢትዮጵያዊ ሳይኮ ቴራፒስቶችን መፈለግ ጀመርኩ ሳልመጣ አጠያይቄ አንድ ሰው መኖሩን አውቄ ነበር እዚህ ስመጣ ደግሞ ሁለት ሦስት ብቻ እንደነበሩ ተረዳሁኝ፡፡   

ሪፖርተር፡- ታዲያ እንዴት ወደ ሥራ ልትገቢ ቻልሽ?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- አንድ የግል ክሊኒክ ውስጥ ራሴ ሜዲካል ዳይሬክተሩን አናግሬ የሕክምና ክፍሉ እንዲከፈት አደረግን፡፡ በመጀመሪያዎቹ ጊዜ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብዬ አንድ ሁለት ሰው ብቻ ነበር የማናግረው፡፡ ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎችም ተገልጋዩም አገልግሎቱ መኖሩን ሲያውቁና ጥቅሙን ሲረዱ ነገሮች እየተለወጡ ይመጣሉ፡፡ አሁን በጣም ጊዜ የለኝም ማለት እችላለሁኝ፡፡ አገልግሎቱ መኖሩን አለማወቅ እንጂ አገልግሎቱ መኖሩን ካወቀ ኅብረተሰቡ ፍገለጎት እንዳለው የሚያሳዩ ነገሮች አሉ፡፡ አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ገቢያቸው ጥሩ የሆነ ያልሆነም ናቸው፡፡ በፊት ከነበረው አንፃር ብዙ ለውጦችና መሻሻል አለ፡፡   

ሪፖርተር፡- ዛሬ በቂ መረዳት ወይም ግንዛቤ አለ ማለት እንችላለን?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- ይህን ማለት እንኳ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ለሳይኮ ቴራፒስት አገልግሎት የሚከፍሉት ለሳይካትሪስትና ለማንኛውም ዓይነት ሀኪም ከሚፈፍሉት በንፅፅር ከፍ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሳይኮ ቴራፒስቱ ጋር የሚያጠፉት ጊዜም በአሥር እጥፍ የሚጨምር ነውና፡፡ ከዚህና ከሌሎችም ነገሮች አንፃር ዋጋው ለምን ከፍ አለ የሚሉ አሉ፡፡ ቢሆንም ግን ብዙዎች ተጠቅመውበት ሲመለከቱ ያምናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዋጋው ባሻገር የግንዛቤ ችግሮችስ?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- በቂ ነው ባልልም ግንዛቤውም ከድሮው የተሻለ ነው፡፡ በመጀመሪያ ይህ ነገር የአእምሮ ጤና መዛባት እንዳይሆን ብሎ ነገሮችን የመከታተልና የማየት ነገር የለም፡፡ የአእምሮ ጤና ችግርን በአንድ የመጠቅለል ነገር ነው ያለው፡፡ ድብርት ነው ወይስ ጭንቀት ብሎ የመለየት ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል የአእምሮ ጤና መዛባትን ከሀይማኖትና ከባህል ጋር የማያያዝ ነገር አለ፡፡ ችግሩ ሀኪም ማማከር ያስፈልገዋል ወይ? ችግሩ ያጋጠመውን ሀኪም ጋር ልውሰደው አልውሰደው የሚለውን ለማማከር ወደ እኛ ከሚመጣው የማይመጣው ይበልጣል፡፡ በጊዜ መታከም ሲችል ረዥም ጊዜ የወሰደበት ሰውም ብዙ ነው፡፡ ሱስ የአእምሮ ጤና ችግር መካከል እንደሆነ አለማወቅም ሌላው ነገር ነው፡፡ ቢሆንም እያየን ያለነው ለውጥ አበረታች ነው፡፡ በእምነት አባቶች ከፀበል ወደ ሀኪም የተላኩ መኖራቸውን ማየት ተስፋ አለን ያሰኛል፡፡   

ሪፖርተር፡- ለውጦች ቢኖሩም በማኅበረሰቡ ከአእምሮ ጤና ጋር የተያያዘው ችግር ሰፊ ነው፡፡ የተሻለ ግንዛቤ እንዴት መፍጠር ይቻላል?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- ከተለያዩ ሰዎች ጋር ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ እሠራለሁኝ፡፡ ሥራው ከታች መጀመር አለበት እላለሁኝ፡፡ ብዙዎቹ የአእምሮ ጤና መጓደሎች በሀያዎቹ መጀመሪያ ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቤተሰብ ውስጥ፣ ትምህርት ቤት ሥራውን መጀመር ይገባል፡፡ ልጆች ያለባቸው የጤና ችግር የእነሱ ጥፋት እንዳልሆነ፤ መፍትሔም እንዳለው ሊነገራቸው ይገባል፡፡ የአእምሮ ጤና መጓደል በቀላሉ በመድሃኒት ወይም በመመካከር ሊታከሙ እንደሚችሉ ለተማሪዎች፣ ወጣቶችና ወላጆች መንገር ትልቅ ነገር ነው እላለሁኝ፡፡ ስለዚህ ውይይቱ ከታች መጀመር አለበት በዚህ ብዙዎች መረዳት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም እዚህ ላይ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአእምሮ ጤና መጓደልን በፊልሞች የማንፀባረቅ ሙከራዎች በተለያዩ የአገራችን ፊልሞች ታይተዋል፡፡ እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለሽ?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- የአእምሮ ጤና ችግሮችን በአንድ ጠቅልለው ያስቀምጣሉ፡፡ በተሳሳተ መልኩ መጓደሎቹን የማስቀመጥ ነገርም ጭምር አለ፡፡ ብዙ ሰው የሚማረው ከፊልም፣ ከድራማ ከመሆኑ አንፃር በመገናኛ ብዙኃን በድራማና በፊልም የአእምሮ ጤና መጓደሎች የተለያዩ መሆናቸው እያንዳንዳቸውም በትክክል መሳል ሲችሉ ግንዛቤ መፍጠር ይቻላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ውጤቱ በተቃራኒው ይሆናል፡፡ ለዚህ ከባለሙያ ጋር መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበረሰቡ ኑሮ ሩጫ የበዛበት በመሆኑ የአኗኗር ዘዬ ግለኝነት እያመዘነበት አንዱ ለአንዱ ድጋፍ መሆን የማይችልበት ጊዜ ነው፡፡ በሌላ በኩል የኑሮ ሸክም ከባድ በመሆኑ ሰዎች ሁለት ሦስት ሥራ በመሥራት ውጥረት ውስጥ የገቡበት ወቅትም ነው፡፡ ከዚህ ከዚህ አንፃር ወደ እናንተ ብዙ የሚመጡ ኬዞች እንዴት ያሉ ናቸው?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- ማይንድ ሴት የምክር አገልግሎት ማዕከል እንደመሆኑ የከፋ የአእምሮ ችግር፣ ተኝተው መታከም ያለባቸው መድሃኒት የሚያስፈልጋቸውም ወደ እኛ አይመጡም፡፡ ስለዚህ እኛ ጋር የሚመጡት የሥነ ልቦና ሳይኮ ቴራፒ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ እነዚህ መድሃኒት እየወሰዱ ጎን ለጎን ሳይኮ ቴራፒ የሚያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ድብርት፣ ጭንቀት፣ ሱስ ችግር ያለባቸው በብዛት ይመጣሉ፡፡ እውነት ነው በፊት ለዕርዳታ ይዘረጉ የነበሩ እጆች ሰሚ ጆሮዎች ዛሬ የሉም፡፡ ስለዚህ ሰዎች ጠንካራ ስሜቶችን ከእኛ ጋር መጥተው ያወጣሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የታዳጊ ወጣቶች በሱስ መጠመድ የብዙ ወላጆች እራስ ምታት ሆኗል፡፡ ልጆቻቸውን ትልልቅ ትምህርት ቤት፤ የሕዝብም የላኩ ወላጆች ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ አንዳንድ ልጆች ያሉበት ሁኔታ ወላጆቹ ልጆቻችንን አናውቃቸውም እስከማለትና አለማመን ይደርሳል፡፡ በዚህ መልኩ አንቺ ጋር የመጡ ስንቶች ናቸው?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- በጣም ብዙ፡፡ የምረዳቸው ብዙ ተማሪዎችና ወጣቶች አሉ፡፡ የሚታየው ነገር አገራችን ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ያሳያል ምክንያቱም ሱስ ሆ ተብሎ የተጀመረ ነገር ሆኗል፡፡ በጣም ጥሩ፣ መንፈሳዊ የሚባለው የትኛውም ትምህርት ቤት ከዚህ ችግር ውጭ አይደለም፡፡ የሚያስፈራ ነገር ነው፡፡ ይህ ችግር በአንድ ለአንድ ምክክር የሚፈታ ሳይሆን ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር የሚጠይቅ ነው፡፡ ልጆች መመራት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ከአስተማሪዎችና ከትምህርት ቤቶች ጋር ትልቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በተለያየ መንገድ ሮጠው እየለፉ ልጆቻቸው የጠየቁትን ሁሉ የሚያሟሉ ነገር ግን የልጆቻቸውን ትክክለኛ ባህሪና አዋዋል ለመረዳት ጊዜ የሌላቸው ወላጆች ብዙ ናቸው?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- ብዙ ወላጆች ሳያውቁ ያጠፉ ይመስለኛል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማያውቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከውጭ አገር ባህል ስንወስድ ጥሩ ጥሩውን የልጅ አስተዳደግ አልወሰድንም የተማሩ ወላጆች የኑሮ ዘዬ ፊልም ላይ እንደምናየው አይደለም፡፡ የድሮ ወላጆች መግረፍ ልጅ የሚለውን መስማት አለመፈለግ ትክክል አልነበረም እኔ እንደ እናት አባቴ አላሳድግም ያለ ወላጅ በተለያየ አጋጣሚ ውጭ ሲሔድ ፊልም ላይ ይቃርምና ያን ይከተላል፡፡ በእርግጥ ባለሙያም ቢሆን ልጅ ሲያሳድግ ሁሉን አያውቅም እየሞከረ እያየ ነው፡፡ ነገር ግን ወላጆች ማድረግ ያለባቸው ቆም ብለው የአስተዳደጋቸውን ተፅዕኖ መገምገም ነው፡፡ ለዚህ ብዙ መጽሐፍ ማንበብ ይቻላል ከኢንተርኔትም ብዙ ይገኛል የዚህን ዓመት ሕፃን እንዴት ሥነ ሥርዓት ማስተማር እችላለሁ በሚለው ቢፈለግ ብዙ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ቆም ብለን አናይም፡፡ የሥነ ልቦና ባለሙያም ልጄ እንዲህ እንዲህ እየሆነ ነው ምን ልጠርጥር ምን ልፍራ ብሎ ማማከርም ይቻላል፡፡ ልጆችን ማዳመጥ፣ ለልጆች ትኩረት መስጠት፣ አስጠኚ መቅጠር ጥሩ ትምህርት ቤት መምረጥ ወላጆች ላይ የሚታይ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በተቃራኒው ልጆችን እንደፈለጋችሁ ሁኑ ማለት የፈለጉትን ሁሉ መስጠት ትክክል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለልጆች የፈለጉትን ሁሉ መስጠት ምን ማለት ነው?

ወ/ሮ ናርዶስ፡- ለልጆች የፈለጉትንና የጠየቁትን ሁሉ መስጠት ደስታቸውን መንፈግ ነው፡፡ አንድ መጫወቻ የተገዛለትና አሥር የተገዛለት እኩል በመጫወቻዎቹ አይደሰቱም፡፡ አንድ የተሰጠው ያን አንድ ያከብረዋል፣ ለረዥም ጊዜ ይጫወትበታል አያያዙም ጥሩ ይሆናል፡፡ በጣም ብዙ ያለው ግን ይሰለቸዋል፡፡ ሌላም ሌላም ይፈልጋል፡፡ ልጆች ሥሥትን ይወቁ ባይባልም የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ዋጋ ሳይከፍሉበት ማግኘት ለእውነተኛው ዓለምም አያዘጋጃቸውም፡፡ ምክንያቱም ከፈለግክ ታገኛለህ ነው እንጂ ከፈለግክ ትሠራለህ ታገኛለህን አይደለም የሚያውቁት፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...