Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊስምን መልአክ ያወጣዋል?

ስምን መልአክ ያወጣዋል?

ቀን:

ደንገዝገዝ እያለ ስለሆነ መኪናቸውን የሚነዱበትን ፍጥነት ጨመሩ፡፡ በጣም ከመምሸቱ በፊት አዲስ አበባ መግባት ፈልገው ነበረና፡፡ የፋሲካ ሰሞን በመሆኑ ብዙዎች ዘመድ አዝማድ ለመጠየቅ ከከተማ ይወጣሉ፡፡ እሳቸውም ሦስት ልጆቻቸውና ነፍሰ ጡር ባለቤታቸውን ይዘው እናታቸውን ለመጠየቅ ወደ ክፍለ ሀገር ሄደው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው፡፡

ሦስተኛ ልጃቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን ደገፍ ብሎ ተኝቷል፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሲመለሱ ስለሚጠብቃቸው ፈተና ያወራሉ፡፡ በድንገት መኪናቸው መንገድ ስቶና ድልድይ ሰብሮ መጠነኛ ወራጅ ወንዝ ውስጥ ገቡ፡፡ በቅጽበቱ የተከሰተውን በውል ባያስታውሱም ለቅሶና ጩኸት፣ የሰዎችና የመኪና ጋጋታ እንዳዩ ይገምታሉ፡፡

ከሰዓታት በኋላ ሆስፒታል ውስጥ ሲነቁ መኪና አደጋ እንደደረሰባቸውና ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ሕክምና እየተሰጣቸው እንደሆነ ይነገራቸዋል፡፡ ራሳቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ ሆስፒታሉን በኡኡታ አናጉት፡፡ ሐኪሞቹ አረጋግተዋቸው በማንም ላይ የከፋ አደጋ እንዳልደረሰ ይነግሯቸዋል፡፡ ስለወቅቱ ሲናገሩ እንባ እየተናነቃቸው ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ዳግመኛ የሚያዩ አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ስድስተኛ ወሯን የያዘችው ባለቤታቸው በማህጸኗ የያዘችው ልጅ ይተርፋል ብሎ የገመተም አልነበረም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሁለተኛና ሦስተኛ ልጃቸው ከወራት በኋላ ቢያገግሙም የመጀመሪያ ልጃቸው ከመኪና አደጋው ድንጋጤ በቀላሉ ልትላቀቅ አልቻለችም፡፡ አእምሮዋ በመረበሹ የሕክምና ክትትል ታደርግ ጀመር፡፡ ባለቤታቸው ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሆኗት አራተኛ ልጃቸውን እስክትገላገል ቤተሰቡ እንዳይሆን መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በስተመጨረሻ ልጁ ተወለደ፡፡ ‹‹የልጁ መወለድ መልካም ነገር ይዞ ነበር የመጣልን፡፡ የመጀመሪያ ልጄ ለውጥ አሳየች፡፡ ቤተሰባችን በትንሹም ወደ ቀድሞው ተመለሰ፤›› ይላሉ፡፡ በቤተሰባቸው ለልጆች ስም የሚወጣው ልጆቹ በተወለዱበት ጊዜ ቤተሰቡ ያለበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ አራተኛ ልጃቸው ቤተሰቡ በተመሰቃቀለበት ወቅት መልካም ነገር ይዞ በመምጣቱ፣ ብዙ ስም በዘመድ አዝማድ ወጣለት፡፡ ሊያረካቸው ግን አልቻለም፡፡ በመጨረሻ የእህታቸው ልጅ፣ ‹‹ቤተሰባችሁ ላይ የመጣው አደጋ እንደ ጥፋት ውኃ ነበር፡፡ ፈጣሪ ላልተወለደው ልጅ ሲል አድኗችኋል፡፡ መዳኛችሁ ሆኗልና ኖህ በሉት፤›› አለች፡፡ ስሙም ጸና፡፡     

‹‹ስምን መልአክ ያወጣዋል›› ይባላል በአገራችን፡፡ ልጆች ከማንነታቸው ጋር የተጣጣመ ስም እንደሚሰጣቸው ይታመናል፡፡ መጠሪያ በማንነት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል የሚል አመለካከትም አለ፡፡ ስም ሰዎች በሕይወት ሳሉና ካለፉም በኋላ ይኖራል፡፡ በዚህ ምድር የአንድ ዘመን ነዋሪነት አሻራ ነው፡፡ ሰዎች ሲተዋወቁ፣ ስለእነሱ ሲወሳ፣ የእነሱ የሆኑ ነገሮች ሲገለጹም መጠሪያቸው ቦታ አለው፡፡ መለዮ ነው፡፡

ስም የሚወጣባቸው መንገዶችና ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡ በአገራችን ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጐረቤት፣ አንዳንዴ ባዕድም ስም ይሰጣሉ፡፡ ልጅ ሳይጸነስ፣ በእርግዝና ወቅትና ከተወለደ በኋላም፣ መጠሪያ ይሆኑታል ተብለው ከተሰጡት ስሞች መካከል የተሻለው ይመረጣል፡፡ ጥንዶች ትዳር ሳይመሠርቱ አንዳንዴም ሳይተዋወቁ በየግላቸው የልጆቻቸውን ስም የሚያወጡበት እንዲሁም ልጅ ከእናቱ ማህጸን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ መጠሪያው አነጋጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡

ስም አሰጣጥ ከአንድ ልጅና ቤተሰቡ ባሻገር የብዙ አገሮች የዘመናት አጀንዳ ሆኗል፡፡ የስም አወጣጥ፣ ስምና ማንነት፣ የልጆች ስያሜዎች አንድን አካባቢ ወይም አገር የሚወክሉበት ሁኔታ የብዙዎችን ትኩረት ሲስብም ይስተዋላል፡፡ መጠሪያ ልጆች የተወለዱበትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ድባብ የሚያንፀባርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ባህል፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት አልያም ሌሎች ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች የስም መነሻ ይሆናሉ፡፡

ልጆች ወደዚህ ዓለም ከመጡበት ወቅት አንፃር መስከረም፣ ፀደይ ሲባሉ አልያም ቤተሰብ ከነበረበት ሁኔታ አንፃር ካሳሁን፣ በፍቃዱና ስጦታን የመሰሉ ስሞች ይደመጣሉ፡፡ ጥንዶች ካሉበት ሁኔታ በመነሳት እነትዕግስትና ፍቅርን ያሉ መጠሪያዎች ይሰጣሉ፡፡ መጠሪያ እንደተለያዩ አካባቢዎች ባህልና ቋንቋም ይወሰናል፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንግዶች ስለሚከበሩ፣ በአንድ ቦታ እንግዶች ሳሉ የሚወለዱ ልጆች በእንግዶቹ ስም ይጠራሉ፡፡

ልጆች በሚወለዱበት ወቅት ቤተሰቦች ያሉበት የጤና ሁኔታና ቤተሰቦች ከልጆቻቸው የሚጠብቁት ነገርም በመጠሪያቸው ይታተማል፡፡ በወሊድ ወቅት ባለቤታቸውን ያጡ አባት ልጃቸውን ‹‹ጎዳኸኝ›› ብለዋል፡፡ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ስኬታማ እንዲሆኑ በሚጠቁሙ ቃላት ወይም በስኬታማ ሰዎች ይጠሯቸዋል፡፡ ልጆች የተወለዱበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ በማገናዘብ የሚወጡ ስሞችም ይጠቀሳሉ፡፡ ሃይማኖት ሌላው የስያሜ መነሻ ሲሆን፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች ያሉ ቅዱሳን፣ ነቢያትና ሌሎችም የእምነቱ መነሻዎች ለልጆች ስያሜ ይሆናሉ፡፡ ጂብሪል፣ መሪየም፣ ዮሐንስና ሐናን ማንሳት ይቻላል፡፡ ቤተሰቦች ለዓለም ወይም ለሰዎች ያላቸውን አስተያየት እንደ ዘመኑና ሰውበቃኝ ባሉ ስሞች ማየት ይቻላል፡፡ እነኃየሎምና ደምመላሽ በጉልበታማነት ረገድ ይጠቀሳሉ፡፡

በአንድ አገር፣ በአጐራባች አገሮች ወይም ዓለም ላይ ያለ ፖለቲካዊ ሁኔታ የልጆች መጠሪያ መነሻ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ልጆች ለባለሥልጣኖች በሚሰጥ የክብር ስያሜም ይጠራሉ፡፡ በተወለዱበት ወቅት የነበረውን ፖለቲካዊ ድባብ የሚገልጽ መጠሪያ ያላቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ለምሳሌ አብዮቱ ሲፈነዳ የተወለዱ ልጆች እንደ አብዮት፣ ሠራዊትና ሻምበል ባሉ ስሞች ይጠራሉ፡፡ በተለያየ ወቅት የተካሄዱ ጦርነቶችም መነሻ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል በተደረገው ጦርነት ወቅት ዘመቻና ሚሊሺያ የተለመዱ መጠሪያዎች ሆነው ነበር፡፡ በታህሳስ 1953 ግርግር የተወለደው ደግሞ ችብሩ ተብሏል፡፡ የዓድዋ ጀግኖችና የኮርያ ዘማቾች በልጆቸቸው ስሞች ታሪካቸውን ያስነብባሉ፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ እንደ ህዳሴ ዓባይ ያሉ ስሞች ተሰምተዋል፡፡ ዓባይ ከመገደቡ በፊት ይገደብ ዓባይ የሚል ስም ያለው ሰው እንደሰሙ የነገሩን አባት አሉ፡፡  

የታዋቂ ፖለቲከኞች፣ የሰብአዊ መብት አቀንቃኞች፣ መሪዎች፣ ድምፃውያንና ደራስያን መጠሪያ ተመርኩዘው ጉቬራ፣ ኦባማ፣ ቡሽ፣ ቦብ፣ ኬኔዲ፣ ኤልሳቤጥ የተባሉ ሰዎችም ገጥመውናል፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች ያሉ ቃላትን በማገጣጠም ለልጆች የሚሰጡ ስሞች ይደመጣሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ አገሮች የሚዘወተሩ ስሞችና ቦታዎችም መጠሪያ እየሆኑ ነው፡፡ ፍራኦል (በኦሮምኛ ከዘመድ በላይ)፣ ኑስካኔ (በኦሮምኛ እኛም ተነሳን)፣ ካቤናት፣ ማርኮን፣ ቬሮኒካና ቪክቶሪያን የመሰሉ ስሞች እንደ ምሳሌ ይወሰዳሉ፡፡

ያልተለመዱ ስሞችን ለልጆቹ መስጠት ከማግባቱና ልጆች ከማፍራቱም በፊት ምኞቱ እንደነበረ የሚናገረው አቶ በላይ ነው፡፡ ልጆቹን እርስ በርስ የሚያስተሳስር ስም ነው ብሎ ያሰበው ልጆቹን አንድ፣ ሁለት፣ ሦስትና አራት ብሎ መሰየምን ነው፡፡ ‹‹የልጆቼ መጠሪያ ልዩ ስለሆነና አንዳቸው ሌላቸውን ተከትለው መምጣታቸውን የሚያሳይ በመሆኑ በጣም እወደዋለሁ፤›› ይላል፡፡ ሁለት ሴትና ሁለት ወንድ ልጆች ያሉት ሲሆን፣ መጠሪያቸው በሚኖርበት ጅማ ከተማ ባሉ ጓደኞቹና በልጆቹ ትምህርት ቤትም መነጋገሪያ መሆኑን ያስረዳል፡፡

የመጀመሪያና ሁለተኛ ልጆቹ ትልልቆች ስለሆኑ ሰዎች ስለስማቸው የሚሰጧቸውን አስተያየትና ጥያቄ ይነግሩታል፡፡ በላይ አንድ ቤተሰብ ከሚያምንበት ነገር በመነሳት ለልጆች የሚሰጠው ስያሜ ቅርስ ነው ይላል፡፡ ‹‹ስም እንደ ቅርስ ነው፡፡ ቤተሰብ ከአንድ ነገር ተነስቶ የሚሰጠው ስም በልጆች ማንነት ላይም ተጽእኖ ያሳድራል፤›› ይላል፡፡ ስያሜ ከሰው ባህሪና አንድ ሰው በሰዎች ዘንድ ከሚሰጠው ቦታ ጋር መያያዝ እንደሚችል ያምናል፡፡ በቀጣይ የሚወለዱ ልጆቹ እንደ አመጣጣቸው በቁጥር እንደሚሰይማቸውም ገልጾልናል፡፡

ወ/ሮ ምሥራቅ የማነ እሷና ባለቤቷ ለልጆቻቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚገልጽ ስም እንዳወጡላቸው ትናገራለች፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ማክዳ፣ ሁለተኛው ኢዛና ይባላሉ፡፡ ‹‹ልጆቼ ስለአገራቸው ታሪክ እንዲያውቁና ስማቸው ለሌሎችም ስለኢትዮጵያ የሚያሳውቅ እንዲሆን እፈልጋለሁ፤›› ትላለች፡፡ መጠሪያቸው ኢትዮጵያዊነትን ከማሳየት ባሻገር የተሰየሙባቸው ነገሥታት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አስታዋሽ እንደሆነ ታክላለች፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስትናን በተቀበለው ንጉሥ ኢዛናና ብልህ በነበረችው ማክዳ ከተሰየሙት ልጆቿ በመቀጠል የሚወለዱ ልጆቻቸው ሳይዛናና ሳባ ቢባሉም ደስተኛ ናት፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ስም አንድ ሰው ማንነቱን ሲጠየቅ በቅድሚያ ከሚመጡ መገለጫዎች አንዱ በመሆኑ በተቻለው መጠን ሰውየውን የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ ትርጉም ያላቸው ስሞች በልጆች ሥነ ልቦና ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ታምናለች፡፡ ሁለቱም ልጆቿ በተወለዱበት ወቅት ዘመዶቿ፣ ጓደኞቿና የሥራ ባልደረቦቿ በርካታ የስም ጥቆማ ያደረጉበት ጊዜ አስደሳች እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ምንም እንኳን እሷና ባለቤቷ የልጆቻቸውን ስም አስቀድመው ቢያወጡም፣ ሰዎች ካላቸው ፍቅር በመነሳት ለልጆቿ ያወጧቸውን ስሞች አትዘነጋቸውም፡፡ አንድ አባት ልጃቸው ከተወለደች በኋላ፣ ቤታቸው የሄዱ ሰዎች ለልጃቸው የሰጧትን ወደ 50 የሚጠጉ ስሞች ዝርዝር ጽፈው አስቀምጠዋል፡፡ በስተመጨረሻ እሳቸው ያወጡላትን ስም ቢያጸኑትም፣ ዝርዝሩን ለዓመታት ይዘውት ቆይተዋል፡፡

ስም አንድ ሰው ያደገበትን ባህል ማንፀባረቅ እንዳለበት የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ ልጆች የሚያድጉበት ማኅበረሰብ ቦታ የሚሰጣቸው ሁነቶች ለእነሱም ትርጉም ስላላቸው ስማቸው እውነታን የሚያንፀባርቅ እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ ሲፈን ታዬ ቤተሰቦቿ ስትወለድ ከነበሩበት ሁኔታ በመነሳት ‹‹ላንቺ ብዬ›› የሚል ትርጉም ያለው ስም እንደሰጧት ትናገራለች፡፡ ያደገችበትን የኦሮሞ ባህል እንደሚገልጽም ታስረዳለች፡፡

እናቷ እሷን ያረገዙት ባልተጠበቀ ወቅት ነበር፡፡ እሳቸውም ባለቤታቸውም በኢኮኖሚ ዝግጁ አልነበሩም፡፡ ሁለቱም በሥራ ቦታቸው ፈታኝ ሁኔታ የተፈጠረበት ጊዜ በመሆኑ ለልጃቸው ሲሉ ብዙ መስዋእትነት መክፈላቸውን ትናገራለች፡፡ ከእሷ በኋላ የተወለደችው እህቷ ሌሊሴ (ለምለም) የተባለችው ደግሞ የነበሩበት ሁኔታ ተቀይሮ መልካም ሕይወት መምራት በመጀመራቸው ነው፡፡ ‹‹ስሜ ቤተሰቤ ለእኔ ያደረጉትንና ያደረግኩበትን ባህልም ያሳያል፤›› ትላለች ሲፈን፡፡ ለእሷ መጠሪያ የማንነት ጥያቄን በተወሰነ መልኩ ይመልሳል፡፡ ሰዎች ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከሚገልጹበት መንገድ አንዱም ስም ነው፡፡

ስም አወጣጥ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮችም የራሱ አካሄድ አለው፡፡ በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ስም እንዲሁ አይሰጥም፡፡ ቤተሰብ፣ ዘመዶችና የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ ይሳተፋሉ፡፡ ለምሳሌ ናይጄሪያ ውስጥ የልጆች አያቶች በስም አወጣጥ ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሚሰጡ ስሞች መካከል ፀረ አፓርታይድ ትግልን የሚያሳዩ ይጠቀሳሉ፡፡ ለልጆች ስም የመስጠት ደማቅ ክብረ በዓል የሚካሄድባቸው አገሮችም አሉ፡፡ ልጅ በሚጣልበት ተስፋ፣ ከቤተሰቡ በሞት በተለዩ ሰዎች፣ በአወላለድ ሁኔታ (ሲዘገይ ወይም ቶሎ ሲመጣ)፣ መነሻ ስም ይሰጣል፡፡ ከአማልክት ጋር የተያያዙ መጠሪያዎች፣ ቤተሰቡ በማኅበረሰቡ የሚሰጠውን ቦታ የሚያሳዩ ስሞችም አሉ፡፡ የአፍሪካውያን ስም አሰጣጥ የልጆችን ማንነት፣ ባህል፣ የቤተሰብ ዕጣ ፈንታ፣ እምነትና ተስፋ እንደሚመረኮዝ የማኅበረሰብ ጥናትና የቋንቋ ተመራማሪዎች ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

አቶ ሥዩም በቀለ ለልጆቻቸው ስም በማውጣት ሒደት አልተሳተፉም፡፡ ባለቤታቸው የምትወዳቸውን ስሞችና በሕይወቷ ካላት ተሞክሮ በመነሳት ስም ታወጣለች፡፡ እሳቸው ይቀበላሉ፡፡ ‹‹ዘጠኝ ወር አርግዤ የምወልደው እኔ ስለሆንኩ ለልጆቹ ስም መስጠት የእኔ ድርሻ ነው ብላኝ ተቀብያታለሁ፤›› ይላሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ ለልጆች የሚሰጥ ስም ከትርጉሙ ይልቅ ወደ ውበቱ እንዳዘነበለ ይናገራሉ፡፡ ስም ቀላልና ማራኪ ከመሆን ባሻገር በልጆች ሕይወት ያለው ቦታም ቢታሰብበት መልካም እንደሆነ ያምናሉ፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ስሞች ጊዜ አልፎባቸዋል ተብሎ ስለሚታመን ለልጆች አይሰጡም፤ ቢሰጡም አንዳንዶች ከተወሰነ ዓመት በኋላ ይቀይራሉ፡፡ ስማቸውን ባለመውደድ በቅጽል ስም ወይም በስማቸው መነሻ ፊደል ብቻ እንዲጠሩ የሚያደርጉም አሉ፡፡ ብዙዎች ከዘመኑ ጋር ይሄዳል የሚባል ስም ቢኖራቸው የሚመርጡትም ለዚሁ ነው፡፡

አንድ አስተያየት ሰጪ ልጇን ሔርመን (ስጦታ) ብላ የሰየመቻት የሬዲዮ መርሐ ግብር ላይ ስልክ የደወለች ሴት ስምን ሰምታ ነበር፡፡ ወንድ ልጇ ከሴት ልጇ ጋር በፊደል ተቀራራቢ ስም እንዲኖረው ሔኖስ (ሰው) የሚል ስም እንድትሰጠው የነገራት ደግሞ የሥራ ባልደረባዋ ነበር፡፡ ‹‹የመጀመሪያ ልጄ የተጸነሰችው በልደቴ ቀን ስለነበር ለልደቴ ባሌ የሰጠኝ ስጦታ በመሆኗ ስሙ ይገልጻታል፤›› ትላለች፡፡

ልጃቸውን ወደዚህ ዓለም ያመጡት በሁሉም ሰው ዘንድ እንዲታይላቸው እንደሆነ የሚናገሩት ጥንዶች ደግሞ ናታይ ብለውታል፡፡ ባል ዝቅተኛ ገቢ ካለው ሚስት ደግሞ ከሀብታም ቤተሰብ በመወለዳቸው ጋብቻቸው ተቃዋሚው ብዙ ነበር፡፡ በልጃቸው ስም ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምድር ላይ ለሕይወቱ መቃናት ከፍተኛ ድርሻ የምትወስደው እናቱን እንደ አንደኛ ባለውለታው፣ ባለቤቱን ደግሞ እንደ ሁለተኛ የሚያየው ሰለሞን ደግሞ፣ ልጁን ሦስተኛ ትልቅ ቦታ የምሰጥሽ ሴት ነሽ በማለት ሣልሳዊት ብሏታል፡፡ ሁለተኛ ልጁ በዚህ ምድር ላይ ስኬታማ ትሆን ዘንድ ሆናልያት ሲል ሰይሟታል፡፡ ሰለሞን አገርኛ መሠረት የሌላቸው ስሞችን አጥበቆ ይቃወማል፡፡ በተለይ አሁን አሁን እየተበራከቱ የመጡት የዕብራይስጥ ስሞች ኢትዮጵያዊ ልጅን አይወክሉም ይላል፡፡

የልጆችን ስም ከአባቸውና ከአያታቸው ጋር አያይዞ ትርጉም እንዲሰጥ ማድረግም የተለመደ ነው፡፡ በዘመነ ደርግ ታዋቂ የነበሩ አንድ ግለሰብ ልጆቻቸውን በአጠቃላይ ተውላጠ ስም ሰጥተዋል፡፡ ልጆቻቸው አንተነህ፣ አንቺነሽ፣ እኔ ነኝና እኛ ነን ይባላሉ፡፡ የልጆችን ስም እናትና አባት በየተራ የማውጣት ልማድ ያላቸው ቤተሰቦች እንዲሁም የልጆችን ስም መነሻ ፊደል ተመሳሳይ ማድረግም ይስተዋላል፡፡ ሜላት፣ መዋዒና መለይ በሚል የተሰየሙ ልጆች ይጠቀሳሉ፡፡

አንዳንድ አገሮች ልጆች የሚሰጣቸው ስም ‹‹አሳፋሪ›› ወይም ‹‹አስቀያሚ›› እንዳይሆን መመርያ አውጥተዋል፡፡ ለምሳሌ እንደ ዴንማርክ፣ ጀርመንና ሀንጋሪ ያሉ አገሮች፣ ለልጆች መውጣት የሚችሉ ስሞች ዝርዝር ያወጡ ሲሆን፣ ከዛ ውጪ መሰየም የተከለከለ ነው፡፡ በአገራችን ለልጆች መጠሪያ ስሞች የሚጠቁሙ መጻሕፍትና ድረ ገጾች አሉ፡፡ 8142 ላይ በመደወል የልጆች ስም ጥቆማ ማግኘትም ተጀምሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...