Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የወልዲያ ዘመናዊ ስታዲየም

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የወልዲያ ዘመናዊ ስታዲየም

ቀን:

አንድ ለእናቱ የነበረው የአዲስ አበባ ዓለም  አቀፍ ስታዲየም ከዓመታት ብቸኝነት ተላቆ በርካታ መሰሎቹን ለማየትና እርጅናውን የሚያሳብቁ ዘመናዊ ስታዲየሞችን ለመታዘብ በቅቷል፡፡

የወልዲያ፣ የባህር ዳርና የሐዋሳ ከተሞች በኢትዮጵያ አስገራሚ የተባሉ ስታዲየሞችን ገንብተው ዕውን አድርገዋል፡፡ ከእነዚህና በመገንባት ላይ ከሚገኙት ሌሎች የአገሪቱ ስታዲየሞች፣ በኢትዮጵያውያን ዕውቀትና የገንዘብ አቅም ግንባታው ተጠናቆ ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ የሚመረቀው የወልዲያ ስታዲየም አንዱና የመጀመሪያው ያደርገዋል፡፡

ከዕድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ስታዲየም ባሻገር ቦሌ አካባቢ የሚገነባው በአደይ አበባ ምስል የሚያሸበርቀው ብሔራዊ ስታዲየም፣ የወደፊት የእግር ኳሱ ድባብ ማራኪነት እንዲላበስ የሚያስችሉ ውጫዊ ገጽታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከአዲስ አበባ በ520 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የሰሜናዊቷ ወልዲያ ከተማ የተገነባው የሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም እስካሁን በአገሪቱ ከተገነቡት ለየት ያለ ዘመናዊ ይዘቶችን ያስተዋወቀ የስፖርት ማዕከል ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የስታዲየሙን የምረቃ ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ ታኅሣሥ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሆነ፣ ማዕከሉ ያረፈበት ቅጥር ግቢ በጠቅላላ የቆዳ ስፋቱ 177,000 ሜትር ካሬ ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) መሥፈርቶችን አሟልቶ ግንባታው የተጠናቀቀው ስታዲየም 25,155 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ነው፡፡ ሙሉ የፀሐይ መጠለያና ዘመናዊ ልዩ መብራቶች (ፓውዛዎች) የተገጠሙለት ከመሆኑ ጎን ለጎን፣ በሜዳው ዙሪያ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የሚጠይቀውን መመዘኛዎች የሚያሟላ በአንድ ጊዜ ስምንት ተወዳዳሪዎችን ማስተናገድ የሚችል የመሮጫ መም (ትራክ) ያለው ነው፡፡

በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ከስታዲየሙ በተጓዳኝ የኦሊምፒክ መመዘኛዎችን ያሟሉ ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ ማለትም የእጅ ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ሜዳ ቴኒስና ሌሎችንም ከእንግዳ ማረፊያ ጋር አጣምሮ የያዘ ከመሆኑ ባሻገር የኦሊምፒክ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል የመዋኛ ገንዳ ስፋቱ 25 X 50 ሜትር፣ ጥልቀቱ ደግሞ ከሁለት እስከ አምስት ሜትር የሚሸፍን እንደሆነ ጭምር የግንባታው የበላይ ተቆጣጣሪ ዶ/ር አረጋ ይርዳው አስረድተዋል፡፡

የስታዲየሙ ክብር ትሪቡን ሕንፃ ባለ ሦስት ፎቅ ሆኖ፣ በውስጡ አራት ቡድኖች በአንድ ጊዜ ሊያስተናግዱ የሚችሉ የልብስ መቀያየሪያ ክፍሎች፣ ሻወር፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የሕክምናና ሌሎችንም ተያያዥ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች የተሟሉለት ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ሕንፃው የክብር እንግዶች ማረፊያና ማስተናገጃ፣ እንዲሁም ጨዋታዎችን በሬዲዮ ወይም በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ስምንት ቻናሎችና የድምፅ መከላከያ ጭምር የተገጠመላቸው ስለመሆኑም በመግለጫው ተገልጿል፡፡

ስታዲየሙና ማዕከሉ ተወዳዳሪዎችን ከአደጋ ሊከላከል የሚችል ዘመናዊ አጥሮች ሲኖሩት፣ በተጨማሪም ስታዲየሙ ካሉት አሥር በሮች ሰባቱ በአደጋ ጊዜ አምቡላንሶችን ወደ ሜዳ ማስገባት የሚችሉ እንደሆኑም ተነግሯል፡፡

ሌላው ስለዚሁ የወልዲያ ዘመናዊ ስታዲየሞች የተነገረው በቅጥር ግቢው 308 የአውቶሞቢል፣ 14 የአውቶቡስና 16 የብስክሌት ማቆሚያ ቦታ ከተሟላ የትራፊክ ምልክቶች ጋር የተዘጋጀለት ከመሆኑ ጎን ለጎን፣ በስታዲየሙ ዙሪያ የተገጠሙ 156 ፓውዛዎች፣ የመብረቅ አደጋ መከላከያ፣ በዝናብ ጊዜ መጫወት እንዲያስችልና የሰረገን ውኃን ወደ ውጭ በመምጠጥ የሚያስተላልፍ ደረጃውን የጠበቀ የተፋሰስ ቦይ (ቱቦ) እንዲሁም የድምፅ ማጉያ፣ የውድድር ውጤት ማሳያ ኤሌክትሮኒክስ ማሳያዎች (ስኮር ቦርድ) እና የቴሌፎንና ኢንተርኔት አገልግሎት ሲስተም የተገጠመለት ስለመሆኑ ጭምር ዶ/ር አረጋ ገልጸዋል፡፡

የስታዲየሙና የማዕከሉ ግንባታዎች በአብዛኛው በአገር ውስጥ ምርቶችና በአገር በቀል ባለሙያዎች የተከናወነ መሆኑን ያከሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ግንባታው የወሰደው ጊዜ አራት ዓመት ተኩል ነው፡፡ የግንባታውን ሙሉ ወጭ የሸፈኑት ሼህ መሐመድ በአጠቃላይ 567,890,000 ወጪ ማድረጋቸው ተናግረዋል፡፡

የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት የሆነችውና በሰሜን ወሎ በየጁ የምትገኘው ወልዲያ፣ ከባህር ወለል 2,000 ጫማ ላይ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም በፕሪሚየር ሊጉ እየተጫወተ የሚገኝ አንድ የእግር ኳስ ክለብ ባለቤት ነች፡፡ ኅብረተሰቡም ከፍተኛ የእግር ኳስ ፍቅር ያለው ስለመሆኑም ይነገርለታል፡፡

በመጨረሻም የስታዲየሙ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ከሆነ በኋላ በባለቤትነት የሚያስተዳድረውን አካል አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር አረጋ፣ ንብረትነቱ የሼህ መሐመድ የሆነው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኃላፊነት ግንባታውን ካጠናቀቀ በኋላ እንደማይመለከተው ገልጸው፣ ንብረትነቱም የወልዲያ አስተዳደርና የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስታዲየሙ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ ይችል ዘንድ ከተቋማቱ ዕውቅና የሚያገኘው የአየር ንብረቱ ጭምር ግምት ውስጥ ገብቶ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፣ ሼህ መሐመድ የዚህን ስታዲየም ሙሉ ወጭ እንደሚሸፍኑ ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ የፊፋና የካፍን መስፈርት ግምት ውስጥ በማስገባት ሦስት ጊዜ የዲዛይን ማሻሻያ ሥራ ተደርጎለታል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የኢትዮጵያ አየር እንደ ፋብሪካ ውጤቶች ታሽጎ (ፓክ) ተደርጎ የሚሸጥ ቢሆን ከየትኛውም አገር በተሻለ ተጠቃሚ ባደረገን ነበር ሲሉ የወልዲያን የአየር ንብረት ተስማሚነት አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ የወልዲያውን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ አስፈላጊነቱን አስመልክቶ ዶ/ር አረጋ፣ ‹‹መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር ገና ተጀመረ እንጂ በቂ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ አክለውም ከግማሽ በላይ የወጣት በሆነበት አገር ማዘውተሪያዎችን እንደየደረጃው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አስፋፍቶ ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጭምር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...