Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​ኢ-ባንኪንግ ሲቃኝ

​ኢ-ባንኪንግ ሲቃኝ

ቀን:

በአገሪቱ የመጀመርያው ባንክ የተቋቋመው በ1897 ዓ.ም. ነበር፡፡ የራስ መኰንን ይዞታ በነበረው በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተቋቋመው ይህ ባንክ ‹‹ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ›› ይባላል፡፡ ይተዳደር የነበረው የእንግሊዛውያን ንብረት በነበረው የግብፅ ብሔራዊ ባንክ ነበር፡፡ አፄ ምኒልክና ራስ መኰንን የመጀመርያዎቹ ሕጋዊ የባንክ ደብተር ያላቸው ደንበኞቹ ነበሩ፡፡ ቀስ በቀስ ሌሎችም ይከተሏቸው ጀመር፡፡

 ዘመናዊ የባንክ ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት የባንክን ሚና ተክተው ይሠሩ የነበሩ አራጣ አበዳሪዎች ነበሩ፡፡ በአሁንም ቢሆን አራጣ ሙሉ በሙሉ ቀርቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡  አሠራሩ ሕገወጥና ገንዘብ አበድረው የሚቀበሉት የወለድ መጠንም ከዝርፊያ የሚቆጠር ነበር፡፡ የባንኩ መቋቋም፣ መበደር፣ ገንዘባቸውን ማስቀመጥ ለሚፈልጉ ዜጎች ዕፎይታ ሆነ፡፡

ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ እስከ 1923 ዓ.ም. ድረስ አገልግሎት ሲሠጥ ከቆየ በኋላ በሚያዝያ 23 ቀን 1924 ዓ.ም. ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባንኩን ከእንግሊዝ ማኅበር ላይ በስምምነት ገዝተው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ተብሎ እንዲጠራ አደረጉ፡፡ በአፍሪካውያን ንብረትነት በአፍሪካ ውስጥ የተመሠረተ የመጀመርያው ባንክ ለመሆንም በቃ፡፡ ከሁለት አስርት በላይ በዚህ መልኩ ሲሠራ ቆይቶ በታኅሣሥ 1956 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተብሎ ለሁለት መከፈሉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዚህ የተጀመረው የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ጉዞ በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የአገልግሎት ዓይነቶችን አካትቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሁለት የነበረው የባንኮቹ ቁጥርም በአሁኑ ወቅት ወደ 20 ደርሷል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች በመክፈት ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ተሞክሯል፡፡ የሚሰጧቸው የአገልግሎት ዓይነቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣት የደንበኞቻቸውን ቁጥር ከፍ እንዲል እያደረገው ይገኛል፡፡

ከጥቂት ከዓመታት በፊት የቪዛ ካርድ አገልግሎት መጀመር በየባንክ ቤቱ የነበረውን ወረፋ እንዲቀንስ ረድቷል፡፡ ከቁጠባ ሒሳባቸው ላይ በቀላሉ ገንዘብ ማውጣት መቻሉም ብዙዎች የባንክ የሒሳብ ደብተር እንዲያወጡ አበረታቷል፡፡ አጠቃቀሙ ቀላል በመሆኑ የኤቲኤም ማሽኖችን የኪሳቸው ያህል የሚጠቀሙባቸውም ያጋጥማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ገንዘብ ሳይዙ ከቤታቸው የሚወጡና የሚያስፈልጋቸውን ከማሽኖቹ የሚወስዱ ሰዎችን ማየትም ተለምዷል፡፡

አንዳንድ የንግድ ማዕከላትና ሌሎችም የግብይት ተቋማት በኤቲኤም ካርድ የሚሠራውን የ‹‹ፖስ›› ማሽን በመጠቀም የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን ጥረት ሲያደርጉ ይታያል፡፡ የፖስ ማሽን ተጠቅመው ምርትና አገልግሎት ለሚገዙ ደንበኞች መጠነኛ ቅናሽ አድርገው የሚሸጡ የገበያ ማዕከላት መኖርም ማኅበረሰቡ ማሽኖቹን በተለየ እንዲጠቀማቸው የሚያበረታቱ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው ቁጥር Fis/0112012 መመሪያ መሠረት አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ እና ኤጀንት ባንኪንግ የአገሪቱን የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ያራመዱ ናቸው፡፡

ኤጀንት ባንኪንግ የሚባለው አንድ ባንክ ለሌላ ድርጅት በሚሰጠው የውክልና መብት ባንኩን ወክሎ የሚሠራበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ የባንክ አገልግሎት ባልተደረሰባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የተለመደ ነው፡፡ ሞባይል ባንኪንግ የሚባለው ደግሞ አንድ የባንክ ደንበኛ ስልኩን በመጠቀም በሒሳብ ደብተሩ ላይ ያለውን የተቀማጭ ገንዘብ መጠን፣ ያደረጋቸውን የገቢና የወጪ መጠን የሚመለከትበትና የተለያዩ ክፍያዎችን የሚፈጽምበት የአገልግሎት ዓይነት ነው፡፡ ኢንተርኔት ባንኪንግ የሚባለውም እንደዚሁ የሞባይል ስልክን አልያም ኮምፒውተርን በመጠቀም የሚሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አገልግሎቱን ለማግኘት የግድ ኢንተርኔት መኖር አለበት፡፡ በሞባይል ባንኪንግ ማግኘት ከሚቻለው የአገልግሎት ዓይነት በተጨማሪ ቼክ ማዘዝም ያስችላል፡፡

በቪዛ ካርድ በቀን ማንቀሳቀስ የሚቻለው በአንዴ 4,000 ብር፣ በቀን ደግሞ 6,000 ብር ብቻ ነው፡፡ ለ ኢ ባንኪንግ ደግሞ የተቀመጠ የገንዘብ ገደብ የለም፡፡ ባሉበት ሆነው እንደልብ ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዲችሉ እድል የሚሰጥ በመሆኑም በአንዴ በርካታ ደንበኞችን ለመሳብ ችሏል፡፡

አቶ ዳግማዊ ጌታሁን (ስም ተቀይሯል) የንግድ ባንክ ደንበኛ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ደንበኝነታቸው ከሌላ ባንክ  ጋር እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ የንግድ ባንክ ደንበኛ የሆኑት በአጋጣሚ የሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ደመወዝ በባንኩ በኩል መክፈል ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ እንዲህ ባለ አጋጣሚ የተጀመረው ደንበኝነታቸው ለዓመታት ሲገለገሉበት የነበረውን ባንክ ትተው የንግድ ባንክ ደንበኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በባንኩ ሌላ ሁለተኛ የተቀማጭ የሒሳብ ደብተር ካወጡም ሰነባብተዋል፡፡

ወደ አንደኛው የባንኩ ቅርንጫፍ ጎራ ብለው ለሳምንት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ከቁጠባ ሂሳባቸው ወጪ ያደርጋሉ፡፡ እንደ መጠባበቂያ የሚያስቡት የቪዛ ካርዳቸው ከኪሳቸው አይጠፋም፡፡ በአገልግሎቱ ከፍተኛ ዕምነት ከማሳደራቸው የተነሳ ኪሴ ባዶ ሆነ ብለው አይጨናነቁም፡፡ ታክሲ ይዘው ወደ አንዱ ቅርንጫፍ ጎራ ቢሉ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያገኙ ዕምነት አላቸው፡፡

 አብዛኛውን ወጪና ገቢያቸውን  ለማየት እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዮች የሚፈጸሙ ክፍያዎችን የሚያከናውኑት የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን በመጠቀም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የቤት ኪራይ የሚከፍሉት፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ገንዘብ የሚበዳደሩት፤ ሞባይል ባንኪንግን በመጠቀም ነው፡፡

ሺሕ እና ከዚያ በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ሲገዙ ክፍያውን ሞባይል ባንኪንግ በመጠቀም መፈጸም ይመርጣሉ፡፡ ለመኖሪያ ቤታቸው የሚያስፈልጉ እንደ አልጋ፣ ሶፋና የመሳሰሉትን ያሟሉት በካሽ እየከፈሉ ሳይሆን ሞባይል ባንኪንግን ተጠቅመው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ደመወዝ መግባት አለመግባቱን፣ ያላቸው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ምን ያህል መድረሱን ለማየት ብቻ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት የሚጠቀሙም ያጋጥማሉ፡፡ ዳዊት እንዳለ (ስም ተቀይሯል) የአንደኛው ባንክ ደንበኛ ነው፡፡ ሞባይል ባንኪንግ መጠቀም ከጀመረ ዓመት አልፎታል፡፡

‹‹ሞባይል ባንኪንግ በሂሳቤ ላይ ያለውን የወጪና ገቢ ሁኔታ መቆጣጠር ያስችለኛል፡፡ በዋናነት የምጠቀመውም ለዚህ ነው፤›› ይላል፡፡ የሞባይል ካርድ ለመሙላት፣ በአፋጣኝ ገንዘብ ማግኘት ቢያስፈልገው ኤም ብርን መጠቀም ይመርጣል፡፡ ያለፈው ዓመት ክረምት ላይ ነበር በኤም ብር የሒሳብ ደብተር ያወጣው፡፡ ለአገልግሎቱ አዲስ በመሆኑ በመጀመርያ ተቀማጭ ያደረገው የገንዘብ መጠን 600 ብር ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አከታትሎ ወደ ሂሳብ ደብተሩ ገንዘብ በማስገባት ቋሚ ደንበኛቸው እንደሆነ ይናገራል፡፡‹‹ሌሊት ካርድ መሙላት ሲያስፈልገኝ አለምንም ችግር ካርድ ለመሙላት አስችሎኛል፡፡ ዕቃ ለመግዛትም አልቸገርም፡፡ ኤም ብርን ተጠቅሜ የምፈልገውን እገዛለሁ›› ሲል ሞባይል ባንኪንግ ምን ያህል እያገለገለው እንደሚገኝ ይገልፃል፡፡

ገንዘብ ለማውጣት አልያም ለሌላ ሰው ለመላክ የሚጠቀመው ቪዛ ካርዱን ነው፡፡ ቪዛ ካርድን ተጠቅሞ ከሒሳቡ ላይ ብር ወጪ ለማድረግ ሲል አልፎ አልፎ ችግሮች ያጋጥሙታል፡፡ ብር ለማውጣት ትዕዛዝ አስተላልፎ ገንዘቡን ሳያገኝ የቀረባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ወጪ ሆነው ነገር ግን ሳይደርሱት የሚቀሩ ገንዘቦችን ለማስመለስ የሒሳብ ደብተር ወዳወጣበት የባንክ ቅርንጫፍ መሄድ እንደሚሰለቸው ይናገራል፡፡

አጋጣሚው በኦን ላይን ግብይት እየተሳተፉ ላሉ ድርጅቶችም ተስፋ ሰጪ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ኦን ላይን ማርኬቲንግ  ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ ይሁንና ኅበረተሰቡ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን የመጠቀም ባህሉ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ምርቶቻቸውን በድረ ገጾች የሚያስተዋውቁና የሚሸጡ ድርጀቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን አሠራሩ አዲስ እንደመሆኑ አንዳንድ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል የኦን ላይን የክፍያ አሠራር ሥርዓት ባለመኖሩ ክፍያውን ለመፈጸም ደንበኞችና ሻጮች የግድ መገናኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ከኦንላይን ግብይት ፅንሰ ሐሳብ ጋር ከመቃረኑ ባሻገር ትክክለኛ ገዥና የሚቀልዱትን ለመለየት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት መጀመሩ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀንሰው በዘርፉ የተሰማሩ ይናገራሉ፡፡

የተለያዩ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስና ኮስሞቲክሶችን ማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ በማስተዋወቅ በኦንላይን እየሸጠ የሚገኘው ዘላማይ አንዱ ነው፡፡ የድርጅቱ ባለቤት አቶ አመሐ ንጋቱ እንደሚሉት፣ ሌላው ዓለም በኦንላይን ግብይት የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ ነገሮች የሚቀሩ ቢሆንም ጥሩ የሚባሉ መሻሻሎች አሉ፡፡ በአገሪቱ በዘርፉ የተሰማሩትንም በገበያው እንዲቆዩ የሚያበረታታም ነው፡ ባለው ነገር የተሻለ መሥራት እንዲቻል ደግሞ የኢንተርኔት መቆራረጥ ሊስተካከል ይገባል፡፡

በኢንተርኔት መቆራረጥና በሌሎችም አጋጣሚዎች በሚከሰቱ ችግሮች አገልግሎቱ የሚዛባባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አገልግሎቱ የሚቋረጥበት፣ ከተባለው የገንዘብ መጠን በላይ ከአንዱ የሒሳብ ደብተር ወደ ሌላው የሚገባበት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ሥርዓቱን ብቻ ተማምነው በሚቀሳቀሱ እንደ አቶ ዳግማዊ ባሉ ሰዎች የየዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አያጠያይቅም፡፡ በቅርቡ ካጋጠሟቸው መካከል አቶ ዳግማዊ አንዱን  እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡

ከወራት በፊት የተፈጠረ ነው፡፡ ብዙም ከማይግቧቧት አንዲት ሴት በ1000 ብር ጫማ ይገዛሉ፡፡ በቂ ገንዘብ አልያዙም ነበርና ክፍያውን በሞባይ ባንኪንግ ለመፈጸም ፈለጉ፡፡ የሴትየዋን የባንክ ሒሳብ ቁጥርም ተቀብለው ብሩን መላክ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን የሚቆራረጠው ኢንተርኔት የክፍያውን ሒደት ያደናቅፍባቸው ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ተሳክቶላቸው የጫማውን ዋጋ ከፍለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ከዚያ ግን በተደጋጋሚ ጊዜ 1000 ብር ከሒሳባቸው ላይ ማውጣታቸውን የሚገልጽ የስልክ መልዕክት ደረሳቸው፡፡  

በመጀመሪያ የመሰላቸው መልዕክቱ በስህተት ተደጋግሞ እንደተላከላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን መለስ ብለው ተቀማጭ ሒሳባቸውን በስልካቸው ሲመለከቱ ስህተት አለመሆኑ ገባቸው፡፡ ከሒሳባቸው ላይ 1000 ብር በተደጋጋሚ ጊዜ ተላልፎ ኖሯል፡፡ ‹‹እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች በደንብ ከምተዋወቃቸው ሰዎች ጋር ሲሆን ለማስመለስ ይቀላል፡፡ ነገር ግን ከሩቅ ሰው ጋር ሲሆን መልስልኝ ማለት ትንሽ ይከብዳል›› ይላሉ፡፡ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ለመክፈል ብለው በአንዴ የሦስትና የአራት ወር ሂሳብ ከፍለው አከራያቸውን ለማስረዳት ተቸግረውም ያውቃሉ፡፡

ይህ በሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ላይ ብቻ ሳይሆን የቪዛ ካርድ በሚጠቀሙ ሰዎች ላይም የሚያጋጥም ነው፡፡ ዮዲት አረፋይኔ (ስሟ ተቀይሯል) አዲስ ቪው ሆቴል አካባቢ ከሚገኘው የንግድ ባንክ የኤቲኤም ማሽን በካርዷ ብር ለማውጣት ሞክራ ነበር፡፡ ነገር ግን ሊሠራላት ባለመቻሉ ከጎኑ ካለው ከዘመን ባንክ ኤቲኤም ማሽን ለመውሰድም ሙከራ አድርጋ ነበር፡፡ በሁለቱም ግን አልሠሩላትም፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ባንኮች 1000 ብር እንደ ወሰደች ተመዝግቧል፡፡ ከተቀማጭ ሂሳቧ ላይም ተቀንሷል፡፡

‹‹በንግድ ባንክ በኩል ያለው ብዙም ሳልቆይ ተሰጠኝ፡፡ በዘመን ባንክ በኩል ወጣ የተባለው ግን መጣራት አለበት ተብሎ አልተመለሰልኝም፡፡ ይኼ ከተፈጠረ አምስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ደውዬ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ በሆነ ሥልክ እንድደውል ቁጥር ሰጥተውኝ ነበር፡፡ በሱ ደጋግሜ ብደውልም ስልኩ አይነሳም›› ስትል እስከአሁን ድረስ ገንዘቧ አለመመለሱን ትገልጻለች፡፡

የዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች በሥራ ላይ መዋላቸውን ተከትሎ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ ደንበኞቹ የባንክ ሒሳባቸውን ቤታቸው ሆነው ማንቀሳቀስ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያቀደው እ.ኤ.አ. በ1980 ዎቹ አካባቢ ነበር፡፡ በ1983 ደግሞ ውጥኑን ዕውን አደረገ፡፡ ደንበኞቹም ቤታቸው ሆነው ከጠዋት 12 ሰዓት እስከ ሌሊት ስድስት ሰዓት ድረስ የባንክ ሒሳባቸውን በኮምፒውተር እንዲያንቀሳቅሱ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡

በዚህ የተጀመረው የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት የሞባይል የስልክ አገልግሎት ከተጀመረ በኋለ የአገልግሎት አድማሱ የበለጠ ሰፍቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞባይል፣ የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ሁለት ቢሊዮን እንደሚደርስ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

አገልግሎቱ በአገሪቱ መሰጠት የተጀመረው በቅርቡ ቢሆንም፣ በርካቶችን  ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድረ ገጽ ላይ በተገኘ መረጃ መሠረት ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት (እ.ኤ.አ. በ2015 እና 16) የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1.1 ሚሊዮን፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 137000 ደርሧል፡፡ በበጀት ዓመቱ ላስመዘገበው አመርቂ ውጤት የኢንተርኔት፣ የሞባይል፣ የኤሌክትሮኒክ ኤቲኤም ባንክ አገልግሎት ትልቁን ድርሻ እንዳበረከቱ ተመልክቷል፡፡

ይኼ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በዘርፉ ያሉ የተለያዩ ችግሮች ዕድገቱን ወደ ኋላ እየጎተቱት እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቻሌንጅ ኤንድ ፕሮስፔክት ኦፍ ኢ ባንኪንግ ኢን ኢትዮጵያ በሚል በ2008 ዓ.ም በወጣ አንድ ጽሑፉ ላይ፣ በዘርፉ ያሉ የተለያዩ ችግሮች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ አገልግሎቱን ለማስኬድ የሚችል የተማረ የሰው ኃይል ዕጥረት፣ የተመቸ የሕግ አሠራርና ቁጥጥር አለመኖር፣ የኢንተርኔት መቆራረጥና የዋጋ ውድነት፣ ማኅበረሰቡ ስለ ባንክ ጥቅም ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ የተመቸ የመሠረተ ልማት አለመኖር ዕድገቱን ወደ ኋላ እያስቀሩ ተመልክቷል፡፡  

በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በባንክ አገልግሎት ውስጥ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን የኢ ባንኪንግ አገልግሎቶች መስጠት ጀምረዋል፡፡ እርስ በርስ ያለው ፉክክርና ደንበኞችን ለመሳብ በሚደረገው ጥረት ጥቂት የማይባሉ በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች አገልግሎት አሰጣጣቸውን በፍጥነት እያሻሻሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ደንበኞች ተገቢውን አገልግሎት እንደማያገኙ ቅሬታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የህዝብ ግብኙነት ባለሙያ አስተያየት እንዲሠጡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...