Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበኤርትራ ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መራዘምና ለቀጣናው የሚኖረው የሰላም አንድምታ

በኤርትራ ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መራዘምና ለቀጣናው የሚኖረው የሰላም አንድምታ

ቀን:

በዮሐንስ ገበየሁ

እ.ኤ.አ. ሜይ 2009 የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በኤርትራ የጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ተከትሎ፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በዚያው ዓመት ዲሴምበር 23 ቀን በውሳኔ ቁጥር 1907 አማካይነት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በኤርትራ ላይ ጣለ። ማዕቀቡ ወደ ኤርትራ የሚገቡና ከኤርትራ የሚወጡ የጦር መሣሪያዎችንና ከጦር መሣሪያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁሳቁሶችን የሚያግድ ውሳኔ ነው። ውሳኔው በተመድ የሶማሊያ ጉዳይ ተቆጣጣሪ ቡድን ሪፖርት ግኝት መሠረት የኤርትር መንግሥት አልሸባብ ለተባለውና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ለሚነገርለት አክራሪ እስላማዊ ቡድን የፖለቲካ፣ የፋይናንስና የሎጂስቲክ ድጋፍ እያቀረበች መሆኑ በመረጋገጡ የተላለፈ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ኤርትራ ከጂቡቲ ጋር በነበራት የድንበር ግጭት አለመግባባት ምክንያት ድንበር አካባቢ ያሉ የጦር ሠራዊቷን ከድንበሩ አስወጥታ ለድርድር ዝግጁ አለመሆኗን ተከትሎ የተጣለም እንደሆነ ውሳኔው ያመላክታል። ማዕቀቡ እ.ኤ.አ. በ2009 ከተጣለ በኋላ እየታደሰ እስከ 2016 የቆየ ሲሆን፣ በ2016ም በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 2317(2016) አማካይነት ታድሷል።

- Advertisement -

የጦር መሣሪያ ማዕቀቡ አንድም ከኤርትራና ወደ ኤርትር የሚገባውንና የሚወጣውን የጦር መሣሪያና ከጦር መሣሪያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁሳቁሶችን ለመግታት፣ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ ለማድረግና የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ ታልሞ የተደረገ ነው። ስለሆነም ማዕቀቡን ለመከለስ፣ ለማሻሻል ወይም ለማንሳት የታለመለትን ግብ በተለይም በኤርትራ ያለውን የባህሪ ለውጥ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። በዚህ መሠረት የኤርትራ መንግሥት የባህሪ ለውጥ ባለማምጣቱ፣ የሶማሊያና የኤርትራ ተቆጣጣሪ ቡድን (ከዚህ በኋላ በጽሑፉ ውስጥ ተቆጣጣሪ ተብሎ ይጠቀሳል) ወደ ኤርትራ ገብቶ የኤርትራ መንግሥት አልሸባብንና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን እየረዳ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ እንዲችል አለመፍቀዱ የባህሪውን ግትርነት ማሳያ ነው፡፡ ተቆጣጣሪ ቡድኑ እንዲገባ ያልፈቀደው አሁንም ድረስ ለአሻባሪዎች ድጋፍ እያደረገ፣ ማዕቀቡን እየጣሰ፣ በኤርትራዊያን ላይ ብሔራዊ ባርነት ሊባል በሚችል ሁኔታ ጭቆናና ኢሰብዓዊ ዕርምጃ እየወሰደ በመሆኑ፣ የጂቡቲ የጦር ምርኮኞችን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃን አልሰጥም በማለት ጠብ አጫሪነቱን እየቀጠለ በመሆኑ፣ ቀጣናውን የብጥብጥና የሽብር ማዕከል ለማድረግ  የአካባቢውን ታጣቂ ቡድኖች አሁንም ድረስ እየረዳ መሆኑ በመረጋገጡ ማዕቀቡ ተራዝሟል። 

ተቆጣጣሪ ቡድኑ በኤርትራ የተጣለው ማዕቀብ በትክክል መተግበሩ አለመተግበሩን ወደ አገሪቱ ከሚገባውና ከሚወጣው የጦር መሣሪያ፣ የኤርትራ መንግሥት አካባቢውን የማተራመስ አጀንዳውን መተው አለመተውን በማረጋገጥ፣ በኤርትራ ያሉ የማዕድንና ሌሎች የሀብት ምንጮች የሚሰበሰበው ገንዘብ ታጣቂ ቡድኖችን ለመደገፍ መዋሉን በማረጋገጥ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ መቆሙንና መሻሻል አለማሳየቱን ከእነዚህ ጉዳዮች አንፃር ገምግሞ እንዲያቀርብ ነው የተዋቀረው። የቡድኑ አባላት አወቃቀርን ስንመለከት የጦር መሣሪያ ባለሙያ (Arms expert) ከኤርትራና ወደ ኤርትራ ያለውን የጦር መሣሪያ ፍሰትና ሁኔታ ለማወቅ፣ የቀጣናውና የታጣቂ ቡድኖች ባለሙያ (Regional Expert and Armed Groups Expert) ኤርትራ በቀጣናው የምታደርገውን የማተራመስ አጀንዳ ለመገምገም፣ የፋይናንስና የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያ (Finance Expert and Natural Resources Expert) በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ታጠቂዎችን ለመደገፍና የጦር መሣሪያ ለመግዛት ያለውን የፋይናንስ ምንጭ ለመተንተንና ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ማዕቀቡን ለመጣስ መጠቀም አለመጠቀሟን፣ የሰብዓዊነት ባለሙያ (humanitarian expert) የሰብዓዊ መብቶችን ሁኔታ ሪፖርት ለማጠናከር በሚያስችል ሁኔታ የተዋቀረ ነው።  

የማዕቀቡ መራዘም ለቀጣናው ያለው አንድምታ ምንድነው?

ማንኛውም ማዕቀብና በተለይም የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ውጤታማነት የሚለካው፣ ማዕቀቡ የተጣለበት አገር የባህሪ ለውጥ ማምጣት ሲችልና የተጣለው ማዕቀብ እውነትም ወደ አገሪቱ የጦር መሣሪያ መግባትን መከልከል ሲቻል ነው። ማዕቀቡ የኤርትራ መንግሥት ለዓለም ዓቀፍ ሰላም ፀር መሆኑን የሚያሳይ፣ ወደ ኤርትራ ወይም ከኤርትራ መንግሥት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ያለን የጦር መሣሪያ ሽያጭ፣ ወታደራዊ ሥልጠና፣ የሎጂስቲክ ድጋፍ፣ ወዘተ. የሚገታና አገሪቱ በተለይም በሥልጣን ላይ ያለው አስተዳደር ከዓለም ማኅበረሰብ መገለል እንዲደርስበት የሚያደርግ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያው ቀውስን በኢስያስ መንግሥት እንዲፈጥር የታለመና የፈጠረ መሆኑ በግልጽ ይታያል።

በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የኤርትራ መንግሥት የባህሪ ለውጥ ባለማምጣቱ ምክንያት ተራዘመ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ የኤርትራ መንግሥት በማዕቀቡ ምክንያት የደረሰበትን ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ቀውስ ግን ማየት ይቻላል። ኤርትራ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት በራሷ ሕዝብ ላይ የምታደርሰው በደል፣ ኢትዮጵያንና ጂቡቲን ለማተራመስ የምታደርገው ጥረት፣ የዓለም ማኅበረሰብን ከልክ ባለፈ ጥርጣሬ እየተመለከተች መምጣቷ የዚሁ ሥነ ልቦናዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ማሳያ ነው።

ይሁን እንጂ የማዕቀቡን ጥንካሬ ሊያዳክሙ የሚችሉ አንዳንድ ክስተቶችን ሁሉም አገሮች በንቃት መከታተል እንደሚገባቸው ማዕቀቡን የጣለው የፀጥታው ምክር ቤት በውሳኔው አመላክቷል። በዚህ ረገድ ከኤርትራ ወደ ጣሊያን በከፍተኛ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊዎች የተደረጉ ጉብኝቶች፣ በተለያዩ ሚዲያዎችና ለተመድ ተቆጣጣሪ ቡድን የደረሱት መረጃዎች ኤርትራ በእጅ አዙር ከዩክሬን የጦር መሣሪያ እየገዛች ስለመሆኑ የተገኙ መረጃዎች፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የየመን አማፂያንን ለመውጋት በሚል ሰበብ በኤርትራ የመሠረቱት የጦር ሠፈር፣ ኳታር ጂቡቲና ኤርትራን ለማስታረቅ በሚል ሰበብ የምታደርገው መውጣትና መግባት ማዕቀቡ በኤርትራ ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ ይህ ጤና የኤርትራን መንግሥት ባህሪን ከማሻሻል ይልቅ በእብሪት ልቡ እስኪፈነዳ ድረስ እንዲያብጥ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያመላክት መሆኑ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።

ማዕቀቡ በኤርትራ ለውጥ አለመኖሩን በደንብ ያሳየ ነው። በውሳኔው ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት የታላቋ ብሪታኒያና የአሜሪካ አምባሳደሮች ይህንኑ በደንብ አስቀምጠውታል፡፡ የእንግሊዝ አምባሳደር ማቲው ራይክሮፍት ስለኤርትራ ሲናገሩ፣ “We don’t welcome the progress because nothing has changed,” ብለዋል፡፡ የአሜሪካ አምባሳደር ኢዞቤል ኮልማን በበኩላቸው የተናገሩት የእንግሊዝ አምባሳደር ያሉትን ያጠናከረ ነበረ። ከላይ የተጠቀሱት የሁለቱ ኃያላን መንግሥታት እንዳስቀመጡት እውነተኛ ለውጥ በኤርትራ መጣ የሚባለው የኤርትራ መንግሥት ሽብርተኞችንና ታጣቂ ቡድኖችን ማገዝ ሲያቆም፣ በዚህም ለዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋት አደጋ መሆኑ ሲያበቃ ነው።   

በዚህ ረገድ ያለው ዋና ጉዳይ በኤርትራ ያለው አስተዳደር ባህሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀየራል ወይ የሚለውና የእውነተኛ ለውጥ ጥያቄ ከአስተዳደሩ መሪዎች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑ ነው። ኤርትራ የመሪዋ የኢሳያስ አፈወርቂና በዙሪያቸው ያሉ ባለሥልጣናት ርስት በመሆኗና አገሪቱን የሚያስተዳድራት ቡድን በከፍተኛ የተማከለ የውሳኔ ዘዴ የታሰረ ከመሆኑ አንፃር፣ አመራሮች ካልተለወጡ አስተዳደሩ ይለወጣል ማለት ዘበት ነው። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው የኢሳያስ ፍላጎትና ምኞት የሚገለጽበት ሲሆን፣ የኢሳያስ ምኞት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በነበረው ‹‹የነፃነት ጦርነት›› ቂም በቀል የተቀረፀና የአፍሪካ ቀንድን የማተራመስ ፍላጎትን እየገታች ያለችውን ኢትዮጵያን ማተራመስ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚንቀሳቀሰ የሥነ ልቦና ቀውስ ያለበት ነው።

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ነገሮችን ሁሉ በመሣሪያና በጦርነት እልባት ለመስጠት የሚፈልግ ነው። የፖሊሲው ዕይታም አመራሮች ለተቀረው ዓለም ባላቸው ቂም በቀል፣ የአፍሪካ ቀንድ ባለው አለመረጋጋትና በኤርትራ ውስጥ ጠንካራ መንግሥት ለመመሥረት ባሉት ተግዳሮቶች ፍራቻ የተከበበ ነው። በመከበብ ስሜት ውስጥ ያለ ፖሊሲ ደግሞ የከበበውን ዓለም ሁሉ በጠላትነት የሚፈርጅ ብቻ ሳይሆን፣ በአዕምሮው ውስጥ የፈጠረውን የመከበብ ስሜት ለማርገብ መሣሪያን የሚያነሳ፣ ጦርነትን የሚያውጅ፣ ጠብ አጫሪነትን ቋንቋውና መግባቢያው የሚያደርግ ይሆናል ማለት ነው። የኤርትራ መንግሥት ፖሊሲ መግለጫም እነዚህ ናቸው።

ኤርትራ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ ለሚሹ ታጣቂ ቡድኖች የምታደርገው ድጋፍ፣ የጂቡቲን የጦር ምርኮኞች ሁኔታ መረጃ አልሰጥም ማለቷ፣ ከማዕድን የምታገኘውን ገንዘብ ለጦር መሣሪያ ግዥ በማዋል ማዕቀቡን ለመተላለፍ የምታደርገው ጥረት፣ የተመድ ተቆጣጣሪ ቡድን በኤርትራ ገብቶ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አለመፈለጓ፣ የኤርትራ መንግሥት ባህሪውን ለመለወጥ አለመፈለጉን በደንብ ሊያሳዩ ከሚችሉ ጉዳዮች በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። የኤርትራ መንግሥት አልሸባብን ከኳታር በሚለቀቅ ገንዘብ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)፣ የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን)፣ የአርበኞች ግንቦት 7፣ የሕዝቦች ትብብር ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ለሚባሉ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖችንና በጂቡቲ የሚንቀሳቀሰውን ‹‹Pour la Restauration de L’unité et de la Démocratie›› (አንድነትና ዴሞክራሲ አስመላሽ ግንባር) በመደገፍ ቀጣናውን ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴና አጀንዳ እየቀጠለ መሆኑን ሪፖርቶች በግልጽ ያሳያሉ።

ከላይ የተጠቀሱትን ታጣቂ ቡድኖችን በፋይናንስ፣ በፖለቲካና በሎጂስቲክስ በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሠራ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በቅርቡ እንኳ 113 የሚሆኑ የግንቦት 7 አባላት በምዕራብ ትግራይ በኩል ሲገቡ መያዘቸውና 15 የሚሆኑት መገደላቸው፣ 73 የሚሆኑት መማረካቸው የኤርትራ መንግሥት ቀጣናውን የማተራመስ አጀንዳውን አለመተውን ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም በብርቱ እንደገፋበት የሚሳይ ይፋ ማስረጃ ነው። የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕከል ቀጣናውን ማተራመስ እንደሆነ ማሳያ ነው።

በዘርፉ ጥናት ያደረጉ አካላት ኤርትራ ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታርና መሰል አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት። ኤርትራ ውስጥ የጦር ሠፈር የገነቡት አገሮችና ከኤርትራ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው አገሮች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ኢትዮጵያን ‹‹የክርስቲያን ደሴት›› እንደሆነች የሚፈርጁ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን ለማስለምና ቀይ ባህርን የዓረብ እንዲሆን ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የምትገታ ደንቃራ አገር አድርገው የሚያምኑ መሆናቸው፣ ጉዳዩን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የሚያደርግ ነው።

በኤርትራ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ ያላቸውና በኤርትራ የጦር ሠፈር የመሠረቱ አገሮች ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን አልሸባብንና አይኤስ የተባሉ የሽብር ቡድኖችን መደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ ቡድኖቹ በአምሳላቸው የተቀረፁ መሆኑ የታወቀ ሀቅ ነው። እነዚህ አካላት ኳታር የምታደርገውን እስላማዊ አክራሪነትን የማስፋፋት ዓላማ የሚያራምዱና የሙስሊም ወንድማማቾችን ርዕዮተ ዓለም የሚወክሉ መሆናቸውን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልጻሉ። በዚህ ረገድ ጥናትና ትንታኔ ያደረጉት ሩሲያዊው የፖለቲካ ተንታኝና ታዋቂው ጋዜጠኛ አንድሪው ኮሪብኮ፣ የባህረ ሰላጤው አገሮች በኤርትራ ያላቸው የጦር ሠፈር በየመን አማፅያንን ለመዋጋት ካላቸው ፍላጎት እኩል የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ለመቀነስ፣ ብሎም አገሪቱን ለማዳከም ነው ማለት ማጋነን እንዳልሆነ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

እንደ አንድሪው ኮሪብኮ በኤርትራ ያለው የጦር ሠፈር ኢትዮጵያን ለማዳከምና በየመን አማፅያንን ለመዋጋት ያለመና በሁለቱም ወገን የተሳለ ጎራዴ ነው ይላሉ። ስለኳታር ሲተነትኑ የኳታር በኤርትራ መኖር በኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረና ሆን ተብሎ የታለመ (Orchestrated, Managed and Ideologically Induced Chaos) አመፅ በመቀስቀስ፣ የአፍሪካ ቀንድ የመጨረሻ የሰላም ዕድልን (Bastion of Peace, Security and Stability) የሆነችውን ኢትዮጵያ ለማተራመስ ያቀደ ነው ይላሉ።    

ይህን ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥበብ፣ በዕውቀትና በትንታኔ ላይ በተመሠረተ የብሔራዊ ጥቅም፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ እየመራው ስለመሆኑ የተለያዩ አመልካቾች አሉ። ኢትዮጵያ ለተመድ ተቆጣጣሪ ቡድን የምትሰጣቸው መረጃዎች፣ ከኃያላኑ አገሮች ጋር የምታደርገው የሠለጠነ ትብብር፣ የምሥራቅ አፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ የምታደርገው ያላሰለሰ ጥረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን አስመልክቶ ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ያለው የምንጊዜም ዝግጁነት፣ በኤርትራ የጦር ሠፈር ካላቸው አገሮች ጋር ኢትዮጵያ ያላት ጥበብ የተሞላበት እንቅስቃሴና ዲፕሎማሲ ለዚህ ማሳያ ነው።    

ኢትዮጵያ በኤርትራ እየሆነ ያለው ወሳኝ ብሔራዊ ጥቅሟን (Vital National Interest) የሚነካ መሆኑን በግልጽ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በኤርትራ ውስጥና ከኤርትራ ጋር ትብብር ላላቸው አገሮች ማሳሰብ እንደ ቀጠለች ነው። ድምፅን በድምፅ መሻር የሚችሉ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገሮች ኢትዮጵያ ስታነጥስ፣ ታላቁ የአፍሪካ ቀንድ ጉንፋን እንደሚይዘውና ለኢትዮጵያ አለመረጋጋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ ለዓለም አቀፍ ሰላም፣ መረጋጋትና ደኅንነት ያለውን አንድምታ መመልከት እንዳለበት የሚያሳይ ነው በኤርትራ ምድር ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታና የኤርትራው መንግሥት ባህሪ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያደርገው ዲፕሎማሲም ይህንኑ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳየት ከቀን ተሌት እየሠራ መሆኑ ይታወቃል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...