Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢትዮጵያ የለውጥ አብሪዎችን ለምን አጣች?

ኢትዮጵያ የለውጥ አብሪዎችን ለምን አጣች?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

          ኢትዮጵያችን የለውጥ ጥማት ማነስ የለባትም፡፡ ይኼ የዛሬው ጉዳያችን በተለይና በዋነኝነት ምናልባትም በብቸኝነት የሚመለከተው ከገዢው ፓርቲ ውጪ ያሉትን ነው እንጂ፣ የገዢውም ፓርቲ የወቅቱ ‹‹እንደገና በጥልቀት የመታደስ›› ንቅናቄ አንዱ ባህርይ ለውጥ ነው ይላል፡፡ ችግሩ ግን የለውጥ ጥማት ማነስ አይደለም፡፡ ካለፉት ውድቀቶች፣ ጥፋቶች፣ ስህተቶች፣ ተምሮ ዝግጅትን በማሟላት ረገድ ግን የፖለቲከኞቻችን ነገር ዛሬም ‹‹ምኑ ተይዞ›› ነው፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ የአገሪቷንና የሕዝቦቿን ተቀዳሚ ጉዳዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ አንጥሮ እየተነተነ፣ ለየወቅቱ ማትኮሪያ የሆኑ መፍትሔዎችንና ተግባሮችን አሳጥሮና አቅሎ ወደ ሕዝብ በማሸጋገር በተከታታይ ለመምራት የቻለም ሆነ የሞከረ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡

መጀመርያ ነገር በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አመለካከከቶች፣ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ላይ ያተኮረ መሳሳብ ባለመኖሩ ለአያሌ ቅንጥብጣቢ ፓርቲዎች መፈጠር ተዳርገናል፡፡ ስንጥረጥር አስተሳሰቦችና ቡድኖች በዓላማ እየተሳሳቡ፣ ንጠቱና በየፈርጁ መዘርዝሩ፣ መሰል ከመሰል መፈላለጉ ቀጥሎ በየጠበላቸው መሰባሰብ ችለው ወደ ጥቂት ጠንካራ ፓርቲ የሚያድጉበት ሒደት ገና እንደተጀመረ ደንግጦ ተቋርጧል፡፡

ብሔረተኛና ኅብረ ብሔራዊ ልዩ ልዩ ቡድኖች ወደ መሰባሰብ ሲመጡ፣ ከብሔረተኛ ጋር መጎዳኘት አንድነትን ወይም አገርን መክዳት የሚመስላቸው፣ የብሔረተኛ ግቢን አልፎ ኅብረ ብሔራዊ የዕይታና የአስተሳሰብ ግቢ ውስጥ መግባት ብሔርን መካድ የሚመስላቸው፣ በፓርቲ ውስጥ ከመሪነት በመለስ ያለ መዋቅር ውስጥ ገብቶ መታዘዝና ለውሳኔ መገዛት ክብረ ነክ ወይም ከጭቆና ቁጥር የሚሆንባቸው፣ ሲንጫጩና ሲያፈነግጡ ደጋግመን አይተናል፡፡ ወደ ፊትም አይታይም የሚባል የተገላገልነው ችግር አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ግን መታየቱ ሳይሆን የእነዚህን ዓይነት ወደፊት ሊራመዱ ያልቻሉ ወገኖችን ዳርቻ ላይ ሊያወጣ የሚችል የመስመር ጥራትና ጥምረት ሊፈጠር አለመቻሉ ነው፡፡ የዚህም ምክንያት ለመሰባሰብ የሚሞክሩት ቡድኖች የሚይዙት አቋም፣ በጥናትና በሐሳብ ልውውጥ የሚያድግና የሚጠራ አለመሆኑና ጥምረታቸውም፣ ጥረታቸውም መሠረቱን የሚገነባው በአገሪቷና በሕዝቦቿ ዋና ጉዳዮች ላይ ስላልሆነ ነው፡፡ የተቃውሞው ኃይል አንደኛው ችግር ይኼ ነው፡፡

የጠላትነት ፖለቲካው በዚህም ወገን አለ፡፡ በግልጽም ሆነ በድብቅ ሕወሓት ኢሕአዴግን የኢትዮጵያ ፀር አድርጎ ማየት በተቃዋሚዎች አካባቢ ከተዘወተረ ቢያንስ የኢሕአዴግን የሥልጣን ዘመን ያህል ዕድሜው የገፋ ነው፡፡ ከተራው እስከ የከፋው ድረስ ያለውን ሰበብና ምክንያት እንይ፡፡ ለአንዳንዶቹ ኢሕአዴግን ‹‹ጠላት›› እያሉ መጮህና መስበክ ቶሎ ዕድሜውን አሳጥሮ ሥልጣን ለመያዝ የሚጠቅም ዘዴ ነው፡፡ የጠላትነት ፖለቲካ አይበጅም እያሉ ሲያስተምሩን ለነበሩ አንዳንዶችም፣ የኢሕአዴግ በደልና ግፍ እነሱ ስለደረሰባቸውና ሊበቀሉት ስለፈለጉ ኢሕአዴግን በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ ጠላት አድርገውታል፡፡ በርከት ላሉት ኢሕአዴግን የአገር ጠላት አድርጎ ለማየት መሠረት የሆናቸው አገርን የጎዱ ፖለቲካዊና መንግሥታዊ ጥፋቶቹ ናቸው፡፡ የአገርን ጥቅም የመጉዳት ጥፋቶች በአፄ ኃይለ ሥላሴም ላይም ሆነ በደርግ ላይ መደርደር ይቻላል፡፡ የዚምባብዌው ሙጋቤም በአገርና በሕዝብ ላይ ታሪካዊ የሚባል ጉዳት አድርሷል፡፡ ግን ሙጋቤም ‹‹ፀረ ዚምባብዌ›› ደርግም ‹‹ፀረ ኢትዮጵያ›› አልተባሉም፡፡ ታዲያ ሕወሓት ኢሕአዴግ (ያውም ከነሱ የሚሻል የልማት ጥረት እያለው) በአገር የተነሳ ጠላት የሚደረግበት ፀረ ኢትዮጵያ የሚባልበት ልዩ ምክንያት ምንድነው? ኢሕአዴግ ለአንድ ወይም ለሌላ ብሔረሰብ የቆመ መንግሥት ለሚመስላቸው ሌላ አንድ እውነት ልንገራቸው፡፡ የሕወሓት ኢሕአዴግ መንግሥት በጥፋቶቹ ጉዳት ያደረሰውና እያደረሰ ያለው በትግራዮችም ብሔረሰባዊ ተዛምዶና ዘላቂ ጥቅም ላይ ነው፡፡ የትግራይ ልጆች እንደ አማራና ጉራጌ ከአንድ አካባቢ ያለፈና ተመልሶ ሊለቀም የማይችል ሥርጭት ያላቸው መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም የጥላቻ ተሸካሚና አዛማች በመሆን ወይም ከጥላቻ የሚያላቅቅ ትግል ባለማበጀት ምን ጉዳት አደረስን ብለው ቢጠይቁ የራሳቸውን ድርሻ ያገኙታል፡፡

የሚያደርሱትም ጉዳት በሌሎች ላይ ብቻ ሳይሆን ቀጥታ በራሳቸውም ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ አሕአዴግን በዘዴ መያዝ ለዴሞክራሲ የሚሰጠውን ጥቅም ማየት ቢያቅት ገዢው ቡድን የፈለገውን ፓርቲ ለይቶ በማጤስና አንጃ በአንጃ በማድረግ መሸኘት እንደሚቻለው፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ልምድ ትምህርት ወስዶ የሚያዋጣ የጥቃት መከላከያ ያበጀ አላየንም፡፡ የስለላና የመረጃ ሥራ ከሰውም በላይ በተራቀቁ ደቂቅ መሣሪያዎች የሚካሄድና ተከታትሎ መጨረስ የማይቻል እንደሆነ፣ ሠርጎ ገብ ሰላይ ከተግባሩና ከንግግሩ ሊታወቅ እንደማይችል፣ እንዲያውም በድርጅታዊ ፍቅሩ ሌሎችን የማስናቅና ከወላዋይ ይልቅ መራር ተቃዋሚ የመሆን ፀባይ የሚሳይ ሊሆን እንደሚችል፣ የስለላ ዋና ዒላማ የሚሆነውና ጥርስ ውስጥ የሚያስገባው በድርጅታዊ መደበኛ ስብሰባ ውስጥ ከሚባለው ይልቅ ጓዳ ጓዳውን የሚባለው እንደሆነ በመረዳት፣ ጠላትነትንና ጥላቻን የሚታገል በመንታ አቋም ያልተተበተበ በውስጥ ዴሞክራሲና በማስረጃ የሚሠራ ድርጅታዊ ሕይወት መቀዳጀት፣ በዚህም የአሉባልታንና የእርስ በርስ ጥርጣሬን አጥቂነት እያመከኑ በጥንካሬ መጓዝ ዛሬም ገና ህልም ነው፡፡

በተቃዋሚዎች የእስካሁን የትብብር ጥረት ውስጥ በዋናነት ያትረከርካቸው የነበረው ጥቅም ከኢሕአዴግ ሥልጣን ለመንጠቅ የሚያስችል አቅም መፍጠር ጉዳይ ሆኖ መቆየቱ ሊደበቅ የማይችል ሀቅ ነው፡፡ ትብብራቸው ኢሕአዴግን ከመጣል የላቀ ዓላማ ቢኖርበት ኖሮ (ለምሳሌ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አብሮ መኖር የምርጫ ጉዳይ ነው? ወይስ ከውኃ፣ ከድንበር፣ ከማኅበራዊ ሥርጭትና ከመሳሰሉት ጣጣዎች ጋር የተያያዘው ውስጣዊና ክፍለ አኅጉራዊ ህልውናቸውና የብልፅግና ፍላጎታቸው አለመነጣጠልን የግዴታ አድርጎባቸዋል? የመሀሉ ይቅርና እንደ ኦጋዴን ባለው የዳርቻ አካባቢ የሚደረግ የመነጠል ትግል ሰላምና ዕድገትን የሚያስገኝ ወይም የሶማሊያ ዓይነቱ ሕግ አልባነት እኔም አይቀርብኝ የማለት እብደት ነው? ለሚሉ ዓይነት ጥያቄዎች ሐቀኛ ምላሽ በመስጠት ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ) የመገንጠል መብትን ወይም አንቀጽ 39ን መቀበል አለመቀበል ለ22 ዓመታት ያህል መራኮቻና መፋረሻ ባልሆነ ነበር፡፡

የሕዝቦች የግልና የቡድን መብቶች መረጋገጥ ዴሞክራሲን በማምጣትና በመገንባት እንጂ በቡድኖች ስምምነትም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ በማጻፍ ብቻ የትም አገር ተረጋግጦ እንደማያውቅ፣ በሌላ በኩልም የተባሉት መብቶች የሚታጡት አንቀጽ ባለመቀመጡ ሳይሆን በዴሞክራሲ መጥፋት መሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አሁንም ገና የታወቀ አይመስልም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት መብቶችን የሚጥሰው ወርቅ የመሳሰሉ የመብት አንቀጾች በሕገ መንግሥቱ ተቀምጠው እያሉ የመሆኑ ልምድ እንኳን፣ በአንቀጹ ላይ ከመወዛገብ አላቆ ዴሞክራሲን እንዲያጠብቁ አላበቃቸውም፡፡

ከዚህም የባሰ የሚያስገርም የፖለቲካ ፋይዳ የለሽነት እናገኛለን፡፡ ‹‹ኦሮሞ ግንድ ነው፣ ግንድ እንዴት ይገነጠላል?›› የሚለው ሥዕላዊ አባባል እንደሚያሳየው የኦሮሞ የመነጠል ጥያቄ ትርጉመ ቢስ መሆኑ ዛሬ ይበልጥ እየተጤነ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ይሁን ወይም ብልጠት ተብሎ በኦሮሞ ብሔረተኝነት አካባቢ ‹‹የመገንጠል ጥያቄን የጠየቀም ያነሳም የለም፣ የምንለው የኦሮሞ ሕዝብ አብሮ በመኖርም ሆነ ባለመኖር ላይ የመወሰን መብቱ ይረጋገጥ ነው›› የሚል ፈሊጥ ተደጋግሞ ይሰማል፡፡ ልብ በሉ! ይኼን ባዮቹ ሰዎች የኦሮሞ ሕዝብ ከመሬት ተነስቶ ማለትም የመነጠል ጥያቄ ‹‹በሌለበት›› አብሮ ከመኖርና ከመለየት የቱ ይሻለኛል ብሎ ይወስን እያሉ መሆናቸውን መረዳትና የአቋማቸውን ተቃርኖ መታዘብ አልቻሉም፡፡

ተቃዋሚዎችን ከገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚዎችም መካከል የትብብር፣ የኅብረት፣ የግንባር ጉዳይ ሲመጣ የሚነሳውና የሚያወዛግበው ሌላው ነገር የአሰብ ወደብ ነው፡፡ የአሰብ ወደብ ዛሬም በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እናስመልሳለን የሚባልባት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ ለዚህ የቆሙት ቡድኖች ገና ሥልጣን ሲይዙ ‹‹የሚተገብሩት›› ይኼ አቋማቸው ከኤርትራ ጋር ተቀራርቦ ሰላምን ከማምጣት ይልቅ የጠብ አቋም ስላለመሆኑ ማሳመኛ የላቸውም፡፡ ሥልጣን ሲይዙ ክስ አቅርበው ለኢትዮጵያ ሊያስፈርዱ ቢችሉ ብለን ብናስብ እንኳን፣ ወደቡን ያለ ጦርነት እንዴት ከኤርትራ መንግሥት እንደሚረከቡና ይዘው እንደሚቆዩ አይነግሩንም፡፡ ወይስ አሁን ቢነገር የኢትዮጵን የወደፊት ጥቅም የሚጎዳ ሚስጥር ሆኖ ይሆን? የቅዠትና የዕብደት ጊዜ አልፎ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዕድገትና ህልውና ከወደብ ያለፈ መያያዝን የሚጠይቅ መሆኑ በተግባር በተረጋገጠበት በዛሬው ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ውስጥ የዴሞክራሲ የፈጣን ኢንዱስትሪያዊ ዕድገትና የመረጋጋት ፈርጥ ለመሆን እስከቻለች ድረስ፣ ከስኬቷ ጋር የመጎዳኘት ፍላጎት ከአንድ የበለጠ የወደብ ጥቅምን ሊያመጣ እንደሚችል ማስተዋል ስለምን ፖለቲከኞቻችንን ገደዳቸው? ከዚህ አቅጣጫ የተሻለ (ማለትም የወደብ ጥያቄን በሰላምና በልማት መንገድ የሚፈታ) ሌላ አማራጭ አለኝ የሚል ካለ ለምን አደባባይ ወጥቶ አያሳምነንም?  

ሌላው የተቃውሞው ጎራ ክፉና አደገኛ ገጽታ በልማትና በለውጥ ላይ ማኩረፍን የሚያካትተው የትግል ሥልት ነው፡፡ መፍትሔ የተነፈገው ፖለቲካዊ ብሶተኝነትና ኢሕአዴግን ወድቆ የማየት ፍላጎት ህሊና ከማሳጣቱ የተነሳ በግብርና ምርትና በወጪ ንግድ መታየት የጀመረውን የቅርብ ጊዜ ዕድገት አንዳች ነገር ወይም ድርቅ መትቶ ድራሹን ቢያጠፋው እሰከ መመኘት የደረሰ ‹‹ንቅናቄም›› እናያለን፡፡ የባሰም አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይለያይም፣ መንግሥት በሌለበትም ጊዜ ተሳባስቦ ይኖራል የሚል መከራከሪያ ላይ ቆም የሆነና የፈለገውን ዓይነት ቀውስ መትቶ ድብልቅልቁ ቢወጣ ብሎ የሚመኝና ኢሕአዴግን በዚህ ዓይነቱ መንገድም ለመገላገል የሚመኝ ‹‹ፖለቲካ›› ማጋጠሙ አልቀረም፡፡

መንግሥትን ይጥልልናል ተብሎ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል፣ ዕርዳታ እንዳይሰጥ፣ ብድር እንዲከለከል መለመንና ተፅዕኖ ማድረግ፣ ምልክቱና ዓርማው ተለወጠበት ብለው የተቃውሞ ምክንያት አድርገው የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን አንሳፈር (ቦይኮት) እናድርግ ማለት፣ በህዳሴው ግድብ ላይ መዝመት የፖለቲካ ሥልት ሆኗል፡፡ እንዲህ ያለ ነገር መንግሥትን ብቻ ነጥሎ የሚያደቅቅ ከመሰላቸው ፖለቲካ ደህና ሰንብች ቢሉ ይሻላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በአገር ልማት ዙሪያ ኩርፊያ የለም የሚለው ቅስቃሳ ኢሕአዴግም ለአገርና ለልማት ብሎ ተቃዋሚዎችን ያቅርብ የሚለውን ማካተትና በተቃዋሚ ዙሪያ ያለውን ኩርፊያ ማምከን ያስችላልና ከኢሕአዴግም ብዙ ይጠበቃል፡፡

ዓላማንና ፖለቲካን ወደ ሕዝብ ዘንድ እያደረሱ ድጋፍን ማግኘትም የትኛውም ፓርቲ የሚያተኩርበት ተግባር ነው፡፡ የእኛ አገር ተቃዋሚዎች ከሞላ ጎደል ከሕዝብ ጋር መገናኛ ጋዜጣ የላቸውም፡፡ የግል ጋዜጦችንም የሚቻለውን ያህል ቃለ መጠይቅና ትንታኔ በመስጠት አይጠቀሙባቸውም፡፡ አቋማቸውን ማወቅ የፈለገ ሰውም እንዲህ ናቸው (አደረጉ) ተብሎ የሚወራውንና ካለፍ ገደም የሚሰጡትን መግለጫ ወይም መጠይቃዊ ምላሽ ከማገናዘብ የተሻለ አማራጭ የለውም፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባም የዓውደ ዓመት ያህል በስንት ጊዜ ብልጭ የሚል ነው፡፡ የሕዝብ ድጋፍ እንዴት ነው ለመቀዳጀት የሚችሉት? ሕዝብንስ በፓርቲ ስብሰባ መገኘትን መልመድን መድፈርን እንዴት አድርገው ያስተምራሉ? ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡

የአባሎቻቸውም ፖለቲካዊ ባህርይ አባል ካልሆኑ የተቃዋሚ ረድፎች እጅግም የተለየ አለመሆኑ፣ ውስጣቸውን ከጭፍንና ከአፍራሽ ዕምነቶች እያፀዱ ግንዛቤንና አስተሳሰብን የማንሳት ሥራ አላቸው ወይ? አለ ወይ? ያሰኛል፡፡ ‹‹ወቅታዊ ጉዳዮችን ለማስገንዘብ››፣ ‹‹ንቅናቄ ለመፍጠር››፣ ‹‹ሥራን ለማቀላጠፍ››፣ ወዘተ እያለ ስብሰባዊ የአጠባ ጎርፍ በየጊዜው ለሚለቀው ኢሕአዴግ ግን የፓርቲ ጋዜጣ ትርፍ ነገር ነው፡፡ እንደ ስብሰባው ጎርፍነት የአባላት ምልመላውም ጎርፍ ሆኗል፡፡ ትምህርት ቀመሱን የመንግሥት ሠራተኛና ተመራቂውን ሁሉ በአባልነት መዋጥ ፓርቲንና መንግሥትን ያሰከረ የአገር ግዳጅ ሆኗል፡፡ ውጦሹ ውስጡ ሰብዕናን ከፍ የማድረግ ውጤት ቢኖረው ኖሮ ምንኛ መታደል በሆነ ነበር፡፡ በብዙ ቦታ የምናየው ክህነት ግን ‹‹የማይናቅ ሥራ ተሠርቷል፣ ፍሬያማ ውጤት ተገኝቷል፣ ይህ ማለት ግን ችግር የለም አጥጋቢ ነው ማለት አይደለም በቀጣይ…›› እያሉ በትንሽ ስኬት ሰፊ ገመናን መሸፈን፣ ስለመልካም አስተዳደርና ሙስናን ስለመዋጋት እያወሩ የጥቅም ድርሻን ማሳደድና ‹‹ማንም የማሰጠውና የማይከለክለው በሕግ/በሕገ መንግሥት የተረጋገጠ መብት ነው….›› እያሉ ውስጥ ውስጡን ሕግና መብት መጣስ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ‹‹ሥልጠና›› አንዱ ዋና ትምህርት ቤት ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፀር ተደርገው የሚታዩትን ተቃዋሚዎችን እያሹ የማዳከም ትግል ነው፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው መታወጅ በፊት ስብሰባዎች ይረበሻሉ፡፡ በአንድ ወቅት አዳማ ላይ በኦሮሞ ቋንቋና ባህል ያሳበበ፣ የአንድነት ፓርቲ ስብሰባ አረባበሽ አንድ ቀላል ምሳሌ ነው፡፡ በኢሕአዴግ የሚመራው የአዳማ አስተዳደር የሰጠውም ‹‹የራሱ ደጋፊዎች ናቸው የረበሹት›› ባዩ መግለጫው ሕዝበ ገብ ስብሰባዎችን ከየትኛውም ወገን ረብሻ የመጠበቅ ኃላፊነቱን የዘነጋ ነበር፡፡ ይኼ ዓይነቱ ችግር አዲስም በዚያም ያቆመ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ የአደባባይ ስብሰባ/ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ጥያቄ ሲመጣ (ፀጥታን የማስከበር ኃላፊነቱም ሆነ አደፍራሽነትን የመቆጣጠርና የማስወገድ አቅሙ ያለው መንግሥት ዘንድ ሆኖ ሳለ) ጠያቂው አካል ገና ለገና ሊነሳ ለሚችል ረብሻ ሁሉ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ይጠየቅ ነበር፡፡ እንዲህ መሰሉ የማይጣጣም የፊት ለፊትና ሥውር ሴራ እስከደራ ድረስ ሙስና የሚጠፋውና መልካም አስተደደር የሚሰፍነው እግዜር ተዓምር ካደረገ ብቻ ነው፡፡

ሌሎችም ችግሮች አሉ፡፡ አሜሪካን የነፃነትና የዕድገት ዘሪ አድርጎ ማመንና መተማመን ገና ደርግ ከመውደቁ በፊት ጀምሮ ስደተኛ ተቃዋሚዎችን የጨመደደ ችግር ነበር፡፡ እስከ ዛሬም ወደ አሜሪካ ማንጋጠጥ የራስን ነፃ ሚና ሲያስረሳ ቆይቷል፡፡ በትግል ዘዴም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ልክ የዛሬ ስምንት ዓመት ኢሕአዴግን ይቀጣል ተብሎ የተጓጓለት ኦባማ ሲመጣና ዋናው ጉዳይ የራስ ትግል/ጥረት መሆኑን ሲናገር፣ ተስፋቸው የበነነባቸው ‹‹ክህደት ፈጸመብን›› የሚል ብሽቀት ያቃጠላቸውም አልታጡም ነበር፡፡

‹‹ኳሷ በኢሕአዴግ ሜዳ ውስጥ ነች . . . ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት በማሻሻልና በእርቅ በኩል ብዙ የሚጠበቀው ከእሱ ነው›› የሚል ዓይነት የውስጥ አንጋጣጭነትም ሌላ ችግር ነው፡፡ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ፊርጣማነት (በሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ ትግል ውስጥ) ፈጥኖ የማይፌዝበት ተፅዕኖ ለማሳረፍ እስካልተጣረ የአቅመ ቢስ ልመና የትም አያደርስም፡፡

ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግሥት፣ የብሔር ብሔረሰብ መብት፣ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ስላለ፣ የመንግሥትን ሚና ስላጠበቀ፣ ሶሻሊስት ብለው የሚከሱትም ተቃዋሚዎች የመንደርደርያቸውን ፉርሽነት አሁንም ገና አልተረዱትም፡፡ የሶሸሊዝም ርዕዮተ ዓለምም ሆነ በዚያ የሚቀረፅ ሶስዮ ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ፣ የኢሕደዴግ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ››ም ለሕዝብ በመቆም ስም የብቻ ሥልጣን ማዝለቂያ መሣሪያ መሆኑን ፈልቅቆ ማሳየት አሁንም ገና ከባድ እንደሆነ ነው፡፡

የመንግሥት ልማታዊነት (ኢሕአዴግ ስላለውም ይሁን ወይ ከዚህ መፈክር ጋር የሚያውቁት አምባገነኖችን ስለሆነ) ፋይዳው ሳይብላላ፣ ‹‹ነፃ ገበያን የሚፃረር የአምባገነኖች ዘይቤ›› እየተባለ ጥቂት በማይባሉ ተቃዋሚ ቦትላኪዎች ዘንድ ይኮነናል፡፡ የየትኛውም ታላቅ አገር ዕድገት ያለመንግሥት ንቁ ተሳትፎ የመጣ አለመሆኑ፣ ዛሬም ፖለቲከኞች አልገባቸውም፡፡ የቅርብ ጊዜው የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስና መንግሥታት የተጫወቱት ሚና በየትም ቦታ ኢኮኖሚውንና ንግዱን እንዳለ ነፃ የሚተው አገር እንደሌለ ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱም፣ በእኛ አገር ውስጥ በ‹‹ነፃ ገበያ›› እና በ‹‹መንግሥት ልማታዊነት›› ጉዳይ ላይ ግንዛቤን ለማስማማት አላበቃም፡፡

የተጠቀሱትና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ ያሉ ችግሮች ሁሉ ዞሮ ዞሮ ወደ ኢትዮጵያ ምሁራን ይመሩናል፡፡ የሚተችና የሚሸረድድ እንደ ሞላ ሁሉ ፖለቲካችንን የሚያጣሩና አሠላለፍን የሚስተካክሉ ትንታኔዎችንና ክርክሮችን የሚጠበቅባቸውን ያህል እያቀረቡ፣ ፓርቲዎችንና የሕዝብ አዕምሮን መግራት ምነው አልችል አሉ? ምሁር የሚባሉት እንደ ፖለቲከኞቻችን በተካረሩ አቋሞች ጥላቻዎችና ኩርፊያዎች ውስጥ መጠመድ፣ አዲስ ዕውቀት መፈለግና በተቆርቋሪነት ከመትጋት መቦዘንና አሮጌ ዕውቀት/ወሬ እያኘኩ መዋብ፣ ያሉትን ፓርቲዎች ዋጋ ቢስ እያሉ ማናናቅን ማጥበቅ፣ ከዚያም ሆነ ከዚህ የፖለቲካ ቡድን ጋር ለመወገን ምሁርነታችን አይፈቅድልንም የሚሉ እብለትን፣ ከኃላፊነት ለመሸሽና አንገት ደፍቶ የግል ኑሮን ለማሞቅ ዘዴዬ ብሎ መጠቀም ሁሉ በምክንያትነት ሊደረደሩ ይችላሉ፡፡

ነገር ግን የሚፈይድ ነገር ሊያበረክቱ የሚችሉትና የሚጣጣሩት ጥቂቶችም አንኳን፣ ከገዢዎችም ሆነ ከተቃዋሚዎቹ ገንታራ ቡትለካዎች ራሳቸውን የለዩበትና የቦታ ርቀት ሳይገድባቸው ሊገናኙና በሁሉም ወገን ሊነበቡ የሚችሉበትን አንድ የድረ ገጽ መድረክ እንኳን በመክፈት ሚናቸውን ለመወጣት ለምን አቃታቸው? ይህስ ምን ሰበብ ይሰጥበታል? ከኅብረተሰባቸው ብዙ ልቀው ሊያበሩ የሚችሉ የእነ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ዘመን ዓይነት ጥቂት የለውጥ ከዋክብት ዛሬ (ብዙ የተማረ ሰው አለ በሚባልበት ጊዜ) መቸገራችን መልሶ በራሳችን ላይ የሚሳለቅ ነው፡፡

የውስጥ ቅራኔዎች፣ የፖለቲካ ጠቦች፣ የሕዝብ ጥያቄዎችና ብሶቶች ከቁጥጥር ሳይወጡና ሳይቀጣጠሉ፣ ከድንበር ዘለል ውኃዎች ጋር በተያያዙ የጥቅም ግጭቶችና ደባዎች ሳይጠቁ፣ በድንበር ነክ ፀቦችና ድንበር በማያቆማቸው የጎረቤት እሳቶች ሳይጋዩ፣ የመኖርና ደኅንነትን የማሸነፍ ፍላጎትና ትግላችን እንኳንስ ተነጣጥለን ተገነጣጥለንና ተበጣጥሰን የፖለቲካ ሰላም በጠፋባት አንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያንና የአካባቢዋን ሁኔታ ገምግሞ ይኼንኑ ሀቅ በመጨበጥ እጅግም አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ችግር የሆነው ከትንንሽ ቡድናዊ ጉዳዮች ይበልጥ ይኼንን ትልቅ የሕዝብ የጋራ ጥቅም ቀዳሚ ያደረገ መግባባት በፖለቲከኞቻችን አካባቢ አለመጎልበቱ ነው፡፡

የፖለቲካ ቡድኖች በዚህ ረገድ ዕርምጃ ማሳየታቸው፣ በተለይም የኢትዮጵያ ዋና አካል ለሆነው ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ‹‹መፍትሔ ሊሰጥ›› ሲባዝን የኖረውን አመለካከት ጥለው ማለፋቸው፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲና የፀረ ደህነት ትግል ወሳኝ መጠምዘዣ (አዲስ የተሻለ የመፍትሔ አቅጣጫ መያዣ “Turning Point”) ነው፡፡ እዚህ መጠምዘዣ ላይ ከተገባ ከግዛት ሒሳብ በቀር የብሔር መብት የማይገባው ትምክህታዊ ድንቁርና ይሰናበታል፡፡ ያለጎጥና ብሔር ትልቁን ዓለም ማየት የተሳነው ጠባብነትም ቦታ ያጣል፡፡ ሁለቱም ሕዝቦችን ከማመስ ይባረራሉ፡፡ የብሔር ጥያቄ የአገር መፍረሻ ሆኖ የመታየቱ ውዥንብር ይገፈፋል፡፡ ዴሞክራቶች ከመቼውም የተሻለ ምቹ ሁኔታ ያገኛሉ፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታና የብዙ ችግሮች መፍትሔ የማይቀርና የማያጠራጥር ሒደት ውስጥ ይገባል፡፡

ይኼንን የመጨረሻ ነጥብ ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው፡፡ ህልውናንና ዕድገትን የሚወስኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዓብይ የጋራ ጥቅሞች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለቡድኖች የመያያዣ ምሰሶ መሆኑ፣ ብሎም በነፃና ሚዛናዊ ምርጫ በርካታ ፓርቲዎችና መላ የአገሪቱ ሕዝቦች የደገፉት መንግሥት መደራጀት በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎችን (ችግሮችንና ተግባሮችን) ለመተኮስ የሚያስችል መሣሪያ ነው፡፡

ሊተኮሱ የሚችሉትንም ወፎች እንዘርዝር፡፡

በሁሉም ደረጃ ያለ የመንግሥት አውታርን የፀጥታና የመለከላከያ ኃይልን ከየትኛውም ቡድን ወገናዊነት የፀዳ ህልውና እንዲኖረው አድርጎ ማደራጀት፣

የአስፈፃሚው አካል እንቅስቃሴ በሕጋዊነት ውስጥ እንዲወሰን፣ የዳኝነት አካሉ የአስፈጻሚውን አድራጎት ሕጋዊነት መርምሮ እስከ መፍረድ የነፃነት አቅም እንዲያገኝ፣ ሕግ አውጪውም አስፈጻሚው ከሚያቀርብለት የሕግ ረቂቅ ባሻገር የአገሪቱን ሁኔታና የአስፈጻሚ አካሉን አያያዝ እየገመገመና እያስጠና የአስፈጻሚውን አካሄድ የሚያርቁ ሕጎችን ጭምር እንዲያፈልቅ አድርጎ ማስተካከል፣  

ለአንድ ውስን አካባቢ/ብሔር ቆሜያለሁ የሚል ቡድን የፌዴራል ሥልጣንን ሊቆጣጠርና አገራዊና ጎጣዊ ዓላማን ሊያሳክር የሚችልበትን ዕድል የሚደፍን፣ አልፎም ንዑሳን ማኅበረሰቦች በፌዴራልም ሆነ በአካባቢ ደረጃ እንዳይዘነጉም ሆነ በጎሰኛ አድልኦ እንዳይጠቁ በተግባር የሚሠራ ሥርዓት ማበጀት፣

የዕምነት መብቶች፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ በነፃ የመደራጀትና ቅዋሜን የመስማት መብቶችን (የመብቶች መጣስ እንዳይደርስ ከሚጠብቁ ገደቦች በቀር) በሕግ፣ በደንብና በመመርያ መልክም ሆነ በዘፈቀደ ድርጊት ከሚደርስ አፈና ነፃ ማውጣት፣

በብዙኃን ማኅበራት ውስጥ ወኪል/መዋቅር ተክሎ የመቆጣጠር መንግሥታዊ ሥራ እንዲቋረጥና ነፃነትን የሚተነፍሱ፣ የመንግሥት እንቅስቃሴን ተከታትለው እየተቹ እንዲታረም የሚጫኑና ልማትን የሚያበጁ ሁለገብ እንቅስቃሴዎች እንዲፈሉ በር መክፈት፣

ሃይማኖቶች መንግሥትን መታከክ ሳያስፈልጋቸው በሌላ በማንኛውም ወገን ሳይደፈሩና የሌላውንም ሳይደፍሩ ዕምነታቸውን የማራመድ፣ በዓላቸውን የማክበርና እንደ እምነቶቻቸው ክምችት ቤተ አምልኮ የማቋቋም እኩል መብታቸው በተግባር እንዲረጋገጥ ማድረግ፣

ከዚሁ ጋር በቀላሉ የማፋለስ የእምነቶችና የሕዝቦች መካባበርንና በእርስ በርስ መስተጋብር ችግሮችን የሚያቃልል ቅርርብ ማዳበር፣

ፖለቲካ አመጣሽ ውስጣዊ የኃይል ተግባራትን (ወደፊት የመከሰት ዕድላቸውን ጭምር) በዴሞክራሲና በሰላም መንገዶች ማምከን፣ መንግሥትንም ሴራን፣ ሁከትን አመፅን በመሰለል፣ በመቆጣጠር፣ በመግታትና የውደዱኝ ቱልቱላ በመንፋት ላይ ብዙ ኃይል ከማሰማራትና ሀብት ከማፍሰስ ነፃ ማውጣት፣

ከኢትዮጵያ ጋር ከተሸካከሩ ጎረቤቶች ጋር በአዲስ መንፈስ ሰላማዊ ግንኙነት ለማዳበር ከልብ መሥራት፣

መረጃና ዕውቀት የመፈለግ፣ የመመርመር የማወቅና የማሳወቅ ነፃነት የሞላበት እንዲሆን አድርጎ የአገሪቱን ትምህርት ማቃናት፣

የትምህርትና የሥራ ዕድል፣ መልካም አስተዳደራዊ አገልግሎትና የልማት እገዛ የማግኘት መብት የገዢ ፓርቲን ፖለቲካ በመደገፍና ባለመደገፍ የሚገኝና የሚታጣ የሚሆንበትን አሠራር መቅጨት፣

ዕድገት የሁሉም አካባቢዎች እኩል መብት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ፣ መንግሥታዊ ፖለቲካን ከመደገፍና ካለመደገፍ ጋር የሚያያዝ የሥራ ከፋች (ኢንቨስተር) አቀባበልን ማቋረጥ፣ ሥራ ከፋቾች በመንግሥታዊ ቢሮክራሲ ሹሞችና የበታቾቻቸው የሚመጠመጡበትንና መንግሥታዊ ሥልጣን የአክሲዮን ድርሻ መግዣ የሚሆንበትን ብልሹ አሠራር መበጠስ፣ እንዲሁም ሁሉም አካባቢዎች ለሥራ ከፋቾች ምቹና ሳቢ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማዳበርና ከአንድ አካባቢ ሀብት አፍርቶ ወደ ሌላ የማሸሽ ጠባብነትን የሚያሟሽሽ የአስተሳሰብ ለውጥና ድባብ ማምጣት፣

ታዳጊ ተማሪዎችን ቅልውጥና ናፋቂ እስከ ማድረግ ድረስ አገሪቱን ያላሸቀው ከሴሚናሮች፣ ከስብሰባዎችና ከሚታሰቡ ቀናት ጋር የተያያዘ የድግስ ብክነትን፣ ለድግስ፣ ለውሎ አበልና ለፖለቲካ አጠባ ሲባል በሚጎርፍ ስብሰባ የመንግሥትን ገንዘብ ማንከትን፣ እንዲሁም የመኖሪያ አድራሻ ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ሙያተኞች/ሠራተኞች በነፃ የክህሎት ማሻሻያ ለሚያገኙበት ሥልጠና የኪስ ገንዘብ/ውሎ አበል መክፈልን ቅዋሜ ሳይፈሩ ማስቀረት፣ በአጠቃላይ ነፍሳችንን ሊያወጣ የደረሰውን ሙስናን በየዓይነቱ መሸሸጊያ አሳጥቶ የመበጣጠስ ሒደትን መጀመር፣

በተለይ የአገራችን ሙስና ዋና ጎሬ የሆኑትን የመንግሥት ሕዝባዊ ፍቅር ማጣትን፣ ሙስና የማያሳፍር የኑሮ ዘዴ የሆነበትን እውነታ፣ የብቃትና የሥራ ገበታ አለመገኘትን፣ ሥራዬን ብበድል፣ ባዳላ፣ ብመዘብር አይታወቅብኝም/አልነካም ለማለት የሚያደፋፍሩ ነገሮችን (ዝርክርክ ድብስብስና ወገናዊ አሠራሮችን፣ የተጠያቂነትን መጥፋትን፣ ሰሚ የለሽነትንና ደንታ ቢስነትን) በለውጥ ማዕበል መጠራረግ፣

የሥልጣን አያያዝ ከሕዝብ እውነተኛ ድምፅ ጋር ባለመገናኘቱ ምክንያት፣ ጊዜያዊ ድጋፍ ለመሸመት ሲባል በወጉ ባልታሰበባቸው አዳጋሚ ሥራዎች ላይ ገዢ ቡድኖች ሀብት ሊያባክኑ የሚችሉበትን ዕድል ማጥበብ፣ በተጠያቂነትም ማገድ፣

ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጥ ዕርዳታና ብድር እንዲቋረጥ ማዕቀብ እንዲጣል የሚካሄድ ትግል ፋይሉ ተዘግቶ፣ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃና ስፋት ሕዝቦች፣ መንግሥት፣ በውስጥና በውጭ ያሉ ፖለቲከኞችና ምሁራን በተጣጣሙበት ሁኔታ ልማትን ማቀጣጠልና በእመርታ ማራመድ፣

አብሮም የአገር ውስጥን አምራችና ሸማች እየጎዳ ያለውን የብልሹና የሐሰተኛ ሸቀጦች ወረርሽኝን የሕዝብ ንቁ ተሳታፊነት በሚንቆረቆርበት ቁጥጥር መዋጋት፣ ንቅል ትርፍ በማግኘት ፍላጎት ብላሽ ሸቀጦችን የሚያስገቡ የአገር ውስጥ አስመጪዎችን በጥብቅ ዕርምጃ መቅጣት፣ አልፎም ወደ ተሻሉ የገበያ አማራጮች በመዞርና አዋጪ በሆኑ ዘርፎች የአገር ውስጥ አምራቾች በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪነት ልቀው የሚወጡበትን የዕድገት ዕድል መክፈትና የውስጥ ገበያን ከአታላይ ንግድ መጠበቅ፣

የአገር መልካም ምሥል ግንባታ ጥረት ገመና ከመሸፋፈንና ላይ ላዩን ከማሰማመር ወጥቶ የገቢ ዕድገትን ከቁጠባ ጋራ ባገናኘና በረሃማነትን በሚቀንስ የኑሮ ለውጥ የረሃብ ታሪክን በመዝጋት፣ መብቶችን በማክበርና በማስከበር ስኬት ላይ የሚመሠረትበት ምዕራፍ ውስጥ መግባት፣

ከኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ከግሽበት ፀባይ፣ ከሠራተኛ ሁኔታና ከመሳሰሉት በሻገር በቅዋሜ ያልተጠመደ መንግሥትና መልካም አስተዳደር መኖሩን፣ በፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት ጠበኛ መሆን አለመሆኑን፣ የመንግሥት ለውጥ ከትርምስ ጋር የተዛመደ መሆን አለመሆኑን፣ የመንግሥት ለውጥ ሕግን የተከተለ ቢሆንም በዋናዎቹ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት አሥጊ የፖሊሲ ለውጥ የሚያስከትል መሆን አለመሆኑን ሁሉ ሚዛን ውስጥ በሚያስገባው የውጭ ኢንቨስትመንት ዘንድ ተስማሚ የዓይን ማረፊያ መሆን፣    

ለዚህ ሁሉ በአገራዊ መግባባት ውስጥ አማራጭ የሚሆን ብስለትን፣ ብልህነትንና ድርጅታዊ ጥንካሬን ያዳበረ የተቃዋሚ ፓርቲ መፈጠርንና ሥልጣን ያለ ግርግና በምርጫ ሲተላለፍ ማየትን እንጓጓለን፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በጠላትነት መተያየትና እርስ በርስ መሰላለል የተረሳበት፣ ሥልጣን ላይ የወጣ ወገን ተቃዋሚውን በመንግሥታዊ የደኅንነት ኃይል ለማዋከብ የማያስብበትና የማይደፍርበት፣ የሕግ የበላይነት ከአፈናና ከተውኔት ይልቅ በተግባር የሚከበርበት፣ ተቃዋሚ፣ የመገናኛ ብዙኃን ችግር አጋጠመን የማይሉበት፣ ሕዝብ ስለአገሩ ለማወቅ ወደ ውጭ የዜና ማሠራጫዎችና ወደ ሹክሹክታ የማይሮጥበትና ከውጭ በበለጠ የአገሩን ማሠራጫና መንግሥቱን የሚያምንበት ጊዜ እንዲመጣ እንመኛለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...