Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየ40/60 ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሦስት ቢሊዮን ብር የብረት ግዥ ውል ማራዘሙ ተቃውሞ...

የ40/60 ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሦስት ቢሊዮን ብር የብረት ግዥ ውል ማራዘሙ ተቃውሞ አስነሳ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ፣ ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል አርማታ ብረት እንዲያቀርቡለት ከአገር በቀል ፋብሪካዎች ጋር ውል ከገባና ፋብሪካዎቹ ብረቱን ካመረቱ በኋላ ውሉን ማራዘሙ ተቃውሞ አስነሳ፡፡

የ40/60 ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለፋብሪካዎቹ በሰጠው መሥፈርት (ስፔስፊኬሽን) መሠረት የተመረተውን ብረት እንደማይረከብ አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር  ለመንግሥት ተቃውሞ አቅርቧል፡፡ ኢንተርፕራይዙና አገር በቀል ፋብሪካዎቹ የተፈራረሙት ውል የግዥ ስምምነት የሚጠናቀቀው ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ነገር ግን የውል ማጠናቀቂያ ጊዜው 13 ቀናት ብቻ ሲቀረው፣ ኅዳር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሦስቱ ፋብሪካዎች ማለትም፣ ሲ ኤንድ ኢ ወንድማማቾች፣ ኢስት ስቲልና ስቲሊ አርኤምአይ በጻፈው ደብዳቤ ውሉ እንዲራዘም ጠይቋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ውሉ እንዲራዘም የፈለገበትን ምክንያት ሲገልጽ፣ በበጀት ዓመቱ ይጀመራሉ ተብለው የታሰቡ የ40/60 ቤቶች ግንባታዎች ያልተጀመሩ በመሆናቸው፣ የዕቅድ ለውጥ በመኖሩ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጀመረው አዲስ አሠራር ምክንያት የበጀት አጠቃቀም ለውጥ በመኖሩ፣ ለፋብሪካዎቹ ቅድመ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ባለመከፈሉ ምክንያት በውል ስምምነቱ በተጠሰው የጊዜ ሰሌዳ የአርማታ ብረቱን ማንሳት እንደማይችል አስረድቷል፡፡

- Advertisement -

በቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የግብዓት ዘርፍ ማስተባበሪያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክሉ ቤያሞ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ ያልተከፈሉ ክፍያዎችን በቀጣዩ በጀት ዓመት እንደሚከፈል ገልጿል፡፡ ‹‹በውል ስምምነቱ አንቀጽ አራት ተራ ቁጥር አንድ ላይ ውሉ ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ ለአምስት ወራት ፀንቶ የሚቆይ ሆኖ፣ ከግንባታ ግብዓት ፍጆታ አፈጻጸም በመነሳት ውሉ በስምምነት ሊራዘም እንደሚችል የሚገልጽ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በፊት የተደረገው የውል ስምምነት የሚያልቀው ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በመሆኑ ውሉ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም እንገልጻለን፤›› ሲል ኢንተርፕራይዙ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡

በ40/60 ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ውሳኔ ችግር ውስጥ የገቡት አገር በቀል ብረት ፋብሪካዎች በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ካቋቋሙት የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ጋር መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ከምክክሩ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝን ውሳኔ ተቃውሞ ለኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለሚመለከታቸው ስድስት መሥሪያ ቤቶች ደብዳቤ አስገብቷል፡፡

ማኅበሩ ታኅሳስ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ሲ ኤንድ ኢ ወንድማማቾች፣ ስቲሊ አርኤምኤይና ኢስት ስቲል የተባሉት የማኅበሩ አባላት 210 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆን፣ በገንዘብ ደግሞ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ልዩ ልዩ የአርማታ ብረቶች ለቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለማቅረብ ውል ተፈራርመው በማምረት ላይ እንደሚገኙ አስታውሷል፡፡

ሦስቱም ኢንዱስትሪዎች ከኢንተርፕራይዙ ጋር በፈጸሟቸው የሥራ ውሎች መነሻነት በድምሩ ለ210 ሺሕ ቶን አርማታ ብረት ማምረቻ የሚውል ጥሬ ዕቃ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት (L/C) በመክፈት ግዥ መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡ የአርማታ ብረቶቹን በየዓይነታው እያመረቱ ኢንተርፕራይዙ እንዲረከባቸው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ማኅበሩ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ በሥራ ትዕዛዘ መሠረት ምርቶቹን ያመረቱ ቢሆንም፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ኢንተርፕራይዙ ሊረከባቸው እንዳልቻለ፣ ከፍተኛ የባንክ ወለድ የሚያንቀሳቅሱ መጠነ ሰፊ ኢንዱስትሪዎች መሆናቸው ከግምት ውስጥ ባለመግባቱ አገር በቀል ፋብሪካዎቹ ለከፍተኛ አደጋ መጋለጣቸውን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ በኢንተርፕራይዙ የክፍያ መዘግየት ምክንያት የገጠማቸውን ፈተና በትዕግሥት ለመቋቋም ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ በጨረታ ተወዳድረውና ሕጋዊ የሥራ ውል ተፈራርመው ወደ ሥራ ቢገቡም ከስምምነት ውጭ ኢንተርፕራይዙ አጋጥሞኛል ባለው ችግር ሳቢያ የራሱን ውሳኔ በተናጠል መቀየሩ አግባብ አለመሆኑን ማኅበሩ ተቃውሟል፡፡

‹‹ይህ አሠራር በኢንዱስትሪዎቹ ህልውና እንዲሁም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ላይ፣ ብሎም በአጠቃላይ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤›› ሲል ማኅበሩ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡    

ኢንዱስትሪዎቹ በዚህ ችግር ምክንያት ለከፍተኛ የባንክ ዕዳ የሚዳረጉ መሆናቸው ከግምት ካለመግባቱ በተጨማሪ፣ ዕጣ ፈንታው ያልታወቀው ብረት ወደ ገበያ ወጥቶ ለሌላ ተጠቃሚ ይሸጥ ቢባል እንኳ በዓይነትና በስብጥር የኢንተርፕራይዙን ልዩ ፍላጎት መሠረት አድርጎ የተመረተ በመሆኑ፣ ገበያ የማግኘት ዕድሉ አናሳ መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል፡፡

‹‹በአሁን ወቅት የአገር ውስጥ የብረት አምራቾች በብረት አስመጭ ነጋዴዎች አማካይነት የተደራጀ ጥቃት ተከፍቶባቸው በከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ፤›› ያለው የማኅበሩ ደብዳቤ፣ ‹‹አገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ እየተሰነዘረባቸው ያለውን የአስመጪ ነጋዴዎች ጫና መንግሥት በቅርበት የሚያውቀው ነው፤›› ሲል ማኅበሩ የኢንተርፕራይዙ ውሳኔ እንዲቀለበስ ጠይቋል፡፡

የሥራ ትዕዛዝ የሰጠው አካል ግዥውን ከውጭ ድርጅት ጋር አድርጎት ቢሆን ኖሮ አስቀድሞ በውጭ ምንዛሪ ክፍያውን ይፈጽም ስለነበር፣ የዕቅድ ለውጥ አድርጌያለሁ በሚል ሰበብ ብቻ ትዕዛዝ ሊሽር እንደማይችል ማኅበሩ በደብዳቤው ገልጿል፡፡ ነገር ግን ኢንዱስትሪዎቹ በቅርብ ስለተገኙና አገር በቀል ስለሆኑ ብቻ ህልውናቸውን የሚያንኮታኩት እንዲህ ያለ ያልተጠበቀ ሁኔታ ማሳለፍ በእጅጉ ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑን ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረት ኢንጂነሪግን ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አሰግድ ማሞ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ጉዞውን የሚያዳናቅፉ እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን በአስቸኳይ በማረም ኃላፊነት የተሞላበት አሠራር እንዲሰፍን፣ መንግሥት ጉዳዩን በጽሞና ተመልክቶ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

‹‹ይህ ሁኔታ የማይስተካከል ከሆነ ግን የኢንዱስትሪዎቹ ህልውናና የአገሪቱ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሒደትን እጅግ አሳሳቢ ለሆነ ውድቀት ይዳርጋል፤›› ሲል ማኅበሩ ያለውን ሥጋት ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...