Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹በኃላፊነት የምንመደበው በዕውቀት ብቻ ቢሆን ኖሮ እኔ ጥሩ ወታደር ነኝ›› አፈ ጉባዔ...

‹‹በኃላፊነት የምንመደበው በዕውቀት ብቻ ቢሆን ኖሮ እኔ ጥሩ ወታደር ነኝ›› አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ

ቀን:

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የተጓደሉ ሊቀመንበሮችን ለመተካት ዕጩዎችን ያቀረቡት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ዕጩዎቹን የመለመሉበት መሥፈርት ዕውቀትን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን አስመልክቶ ለተነሳባቸው ጥያቄ፣ ዕውቀት ሁልጊዜ መሥፈርት ሊሆን እንደማይችል ይልቁንም የፖለቲካ ድርጅቶች በሚሰጡት ውሳኔ የአመራርነት ምደባ እንደሚካሄድ ገለጹ፡፡

አፈ ጉባዔው በምክር ቤቱ የአባልነት ሥነ ምግባርና ሥነ ሥርዓት ደንብ በሚሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ለምክር ቤቱ 18 ቋሚ ኮሚቴዎች ከመደቧቸው ዋና ምክትል ሊቀመናብርት መካከል፣ የተወሰኑት በተለያዩ ምክንያቶች በመጓደላቸው በምትክነት ያጯቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ለምደባ ሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. አቅርበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመናብርት ከተጓደሉባቸው ምክንያቶች አንዱ በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት መዋቅር ውስጥ በመመደባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ አፈ ጉባዔው ያቀረቡት አዲስ ምደባ በተጓደሉ አመራሮች ምትክ ብቻ ሳይሆን፣ ነባሮችንም ወደ ሌላ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚያሸጋሽግ ነው፡፡

- Advertisement -

ይህንን ያስተዋሉት የምክር ቤቱ አንድ አባል አፈ ጉባዔው ባቀረቡት አዲስ ምደባ ላይ በርከት ያሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ጥያቄዎቹን ያነሱት የምክር ቤት አባል አቶ ተክሌ ተሰማ የደኢሕዴን ተወካይ ሲሆኑ፣ በአዲሱ ምደባ ቀደም ሲል ከነበሩበት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበርነት ወደ ሌላ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበርነት እንዲዘዋወሩ፣ በአፈ ጉባዔው የውሳኔ ሐሳብ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ተካቷል፡፡

አቶ ተክሌ ባነሱት ጥያቄ ለምደባ የቀረቡት ዕጩዎች የትምህርት ምዘና የሚመደቡበት ቋሚ ኮሚቴ ከሚጠይቀው ዕውቀት ጋር የሚጣጣም አለመሆኑን፣ የዕጩ ተመዳቢዎች ይሁንታን አፈ ጉባዔው ለምን እንዳልጠየቁ በማንሳት ዕውቀትን መሠረት አድርጎ የማይከናወን የሥራ እንቅስቃሴ ውጤቱ መደናበር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴዎቹን በየዘርፋቸው የሚያማክር የባለሙያዎች አደረጃጀት በሌለበት ዕውቀትን መሠረት ያላደረገ ምደባ ተገቢ አለመሆኑን፣ እንዲሁም የተጓደሉት የቋሚ ኮሚቴ ሊቀመናብርት በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ሲወሰዱ የምክር ቤቱ ይሁንታ ስለመጠየቁ አንስተዋል፡፡

‹‹ቢያንስ የምክር ቤቱ አመራሮችን ሳያሳውቅ መንግሥት የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችን ወደ ራሱ ኃላፊነት የሚወስድ ከሆነ፣ ነገሩ ከኔትወርክ የፀዳ ነው የሚባል አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡ በማከልም በአንድ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ ከአንድ ፓርቲ ሁለት ሊቀመናብርትን መመደብም ትክክል እንዳልሆነና ስብጥር ሊኖር እንደሚገባ ለአፈ ጉባዔው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አቶ ተክሌ በብቸኝነት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የጀመሩት አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ ከአንድ ፓርቲ ሁለት ተወካዮችን በአመራርነት የመመደብን ተገቢነት አስመልክቶ የተነሳው ጥያቄ በተገቢው መድረክ (ከምክር ቤቱ ውጪ) ሊቀርብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ለቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበርነትና ምክትል ሊቀመንበርነት ያቀረቡት ምደባ ዋናው ዓላማው ሥራ እንጂ ለመጠቃቀም አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዕውቀት ደረጃን በመሥፈርትነት ስላለመጠቀማቸው ለተነሳው ጥያቄም ዕውቀት ሁልጊዜ መሥፈርት ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ሁላችንም በዕውቀታችን እየሠራን አይደለንም፡፡ በዕውቀት የምንመደብ ከሆነ እኔ ጥሩ ወታደር ነኝ፤›› ሲሉ በአፈ ጉባዔነት ሊሰየሙ እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡

በማከልም፣ ‹‹ድርጅታችን በመደበን ኃላፊነት ላይ ነው የምንሠራው፣›› ብለዋል፡፡ አፈ ጉባዔው በሰጡት በዚሁ ማብራሪያም ያቀረቡት ምደባ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ ፀድቋል፡፡

አቶ አባዱላ ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ በሜጄር ጀኔራል ማዕረግ የጦር ኃይሉ አባል እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በገዛ ፈቃዳቸው ከመንግሥት ኃላፊነታቸውና ከኦሕዴድ ሊቀመንበርነታቸው ሲለቁ፣ አቶ አባዱላ ከጦር ኃይሉ እንዲለቁ ተደርጎ በዶ/ር ነጋሶ ምትክ የፓርቲው ሊቀመንበር፣ እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ ከመከላከያ ሚኒስትርነታቸው በኋላ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት፣ በመቀጠልም አፈ ጉባዔ ሆነዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...