Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ኤርፖርት ማስፋፊያ 40 በመቶ ተጠናቀቀ

የአዲስ አበባ ኤርፖርት ማስፋፊያ 40 በመቶ ተጠናቀቀ

ቀን:

በ345 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ግንባታ 40 በመቶ ተጠናቀቀ፡፡

እያደገ የመጣውን የአየር ትራንስፖርት መንገደኞች ፍሰት ለማስተናገድ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን በጥር 2007 ዓ.ም. መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ ተርሚናል አንድና ሁለትን ማስፋፋት፣ አዲስ የቪአይፒ ተርሚናል ግንባታ፣ የተሽከርካሪዎች መተላለፊያ ድልድይና ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ አካቶ የያዘ ነው፡፡

አሁን ያለው ተርሚናል 30,000 ካሬ ሜትር ወለል ስፋት ያለው ሲሆን፣ አዲስ የሚገነባው ተርሚናል ወለል ስፋት 74,000 ካሬ ሜትር ነው፡፡ የተርሚናል ማስፋፊያ ግንባታው የሚካሄደው ከተርሚናል ሁለት ግራና ቀኝ ሲሆን፣ በስተቀኝ በኩል ከተርሚናል አንድ (አሮጌው ተርሚናል) ጋር ይገናኛል፡፡

የአዲሱ ተርሚናል ግንባታ ንድፍ ሲጂፒ በተባለ ታዋቂ የሲንጋፖር ኩባንያ የተሠራ ሲሆን፣ ግንባታውን የሚያካሂደው ሲሲሲሲ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ ግንባታውን የሚቆጣጠረው ኤዲፒአይ የተባለ የፈረንሣይ ኩባንያ ነው፡፡

በ1994 ዓ.ም. የተመረቀው ተርሚናል ሁለት ስድስት ሚሊዮን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባና በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ እንደነበረ የተነገረለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ጋርና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ እየናረ የመጣው የመንገደኞች ቁጥር ከተርሚናሉ አቅም በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ኤርፖርት በዓመት 8.5 ሚሊዮን መንገደኞች በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ምሽትና ማለዳ ላይ ተርሚናሉ በመንገደኞች ተጨናንቆ ይታያል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን በማጣደፍ ላይ ይገኛል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ኤርፖርቱ በዓመት 22 ሚሊዮን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኤርፖርት መንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዋና መሐንዲስ አቶ ኃይሉ ለሙ የማስፋፊያ ግንባታው 40 በመቶ መጠናቀቁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የኮንክሪት ሥራ 98 በመቶ፣ የብረታ ብረት ሥራ (Steel Structure) 40 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ በቀጣይ ዙሪያውን መስታወት ማልበስ፣ ጣሪያ ማልበስና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ እንደሚጀመር አክለዋል፡፡

የሻንጣ ማጓጓዣ መሣሪያ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የመተላለፊያ በሮች መቆጣጠሪያ፣ የመንገደኞች መሳፈሪያ ድልድዮችና የመሳሰሉት መሣሪያዎች በእንግሊዝና በቻይና እየተመረቱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የግንባታ ሥራው እንደተጠናቀቀ የተጠቀሱት መሣሪያዎች መጥተው የሚገጠሙ በመሆኑ፣ የፕሮጀክቱን ክንውን በአንድ ጊዜ ከፍ እንደሚያደርገው ታውቋል፡፡

አዲስ የሚገነባው ተርሚናል ሰፊ የመገበያያ ሥፍራዎች፣ በርካታ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች፣ የቀረጥ ነፃ ሱቆች፣ ልዩ ሳሎኖች፣ የቢዝነስ ክላስ ላውንጅና የአይቲ ማዕከል ይኖረዋል፡፡ ተርሚናሉ ገቢና ወጪ መንገደኞች የሚያስተናግዱ ሁለት ፎቆች፣ አራት አሳንሰሮችና ሁለት ኤስካሌተሮች የሚገጠሙለት ሲሆን፣ ከተርሚናሉ ፊት ለፊት የተሽከርካሪዎች መተላለፊያ ድልድይ ይገነባለታል፡፡ ግንባታው በጥር 2010 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እያንዳንዱ የሕንፃው ግንባታ ዓለም አቀፍ የኤርፖርት ግንባታ መርህ ደረጃዎች ተከትሎ እንደሚካሄድ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ገብረ አብ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ሕንፃው የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳት አደጋ እስከተወሰነ መጠን መቋቋም በሚያስችል የግንባታ ቴክኖሎጂ እየተገነባ እንደሆነ የገለጹት አቶ ፀጋዬ፣ እያንዳንዱ የግንባታ ቁሳቁስ ከፍተኛ የጥራት ቁጥጥር ፍተሻ እንደሚደረግለት ተናግረዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድም ተክሉ የመንገደኞች ፍሰት በየዓመቱ 22 በመቶ በማደግ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለአሥር ዓመት የመንገደኞች ፍሰትን በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ልዩና ዘመናዊ የሆነ የቪአይፒ ተርሚናል ራሱን ችሎ እንደሚገነባ ገልጸው፣ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት በአፍሪካ ቀዳሚ ኤርፖርቶች ተርታ የሚሠለፍ እንደሚሆን እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአሁኑ ወቅት በጂንካ፣ በሮቤ፣ በሐዋሳ፣ በደምቢ ዶሎ፣ በሽሬና በሰመራ ኤርፖርቶች ግንባታ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ የተወሰኑትን በቅርቡ ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...