Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተፈናቃይ አርሶ አደሮች ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎቻቸው ኪሳራ ተሰልቶ ካሳ እንዲከፈላቸው ጠየቁ

ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎቻቸው ኪሳራ ተሰልቶ ካሳ እንዲከፈላቸው ጠየቁ

ቀን:

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ የማስፋፊያ ቦታዎች ሲፈናቀሉ የቆዩ አርሶ አደሮች፣ ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካይነት ለከንቲባ ድሪባ ኩማ ባቀረቡት አቤቱታ፣ እነሱ የተፈናቀሉባቸው አብዛኛዎቹ ቦታዎች ለዓመታት ታጥረው ያለሥራ የተቀመጡ በመሆናቸው ኪሳራው ተሰልቶ እንዲከፈላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡

አርሶ አደሮቹ ታኅሳስ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለከንቲባ ድሪባ በጻፉት አቤቱታ፣ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ከቀያቸው በመፈናቀላቸው ሀብትና ንብረት አልባ ሆነው ሲቀመጡ የተባለው የሕዝብ ጥቅም ሳይከበር፣ የታለመው ልማትም ሳይመጣ መሬቱ ታጥሮ ያለ ሥራ መቀመጡ እንዳስቆጫቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ላይ የነበሩ አርሶ አደሮች እስካሁን ድረስ ቢያለሙ ሊያገኙ የሚችሉትን ሀብት፣ መንግሥት በቅጣት መልክ መሬቱን ከወሰዱ አካላት ተቀብሎ እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እስከ ዛሬ ከመሬታቸው ባይፈናቀሉ፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በልማት ምክንያት ቢነሱ ሊከፈላቸው የሚችለውን የካሳ ክፍያ አርሶ አደሮቹ አስልተው ለከንቲባው አቅርበዋል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ፣ በቦሌ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በየካ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ አርሶ አደሮች ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ በኮሚቴ አባላት አቶ ተስፋ ረጋሳ፣ አቶ ተሾመ ፈይሳ፣ አቶ ሰቦቃ ለታና አቶ መገርሳ ሚደቅሳ ፊርማ ለከንቲባ ድሪባ የቀረበው አቤቱታ እንደሚገልጸው፣ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም የተያዘው ዕቅድ ከዚህ ጋር የተቆራኘ መሆኑ መልካም ነው፡፡

የአርሶ አደሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋ ረጋሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ሊመረት የሚችለውን ሰብል፣ የእንስሳት ተዋፅኦና በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ በልማት ቢነሳ የሚከፈለውን የወቅቱ የገበያ ዋጋ አስልቶ፣ መሬቱን ሆን ብለው በመያዝ ወደ ልማት ያልገቡ አካላትንም በሕጉ መሠረት በመቅጣት ከቦታው ላይ ለተፈናቀሉና በችግር ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች መክፈል ይኖርበታል፡፡

ኮሚቴው ባቀረበው አቤቱታ ለአብነት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በ1998 ዓ.ም. የተሰጠ 60 ሔክታር መሬት፣ ከሪቬራ ሆቴል ፊት ለፊት ለአፍሪካ ኅብረት የተሰጠ 20 ሔክታር፣ ለቤቶች ልማት የተሰጠ 888.62 ሔክታር መሬት፣ ኮዬ አካባቢ ለተለያዩ በርካታ ልማቶች የተሰጡ መሬቶች ታጥረው ይገኛሉ ብሏል፡፡

ቦሌ ክፍለ ከተማ ለውኃና ፍሳሽ የተሰጠ 105 ሔክታር፣ ለአይሲቲ ፓርክ የተሰጠ 40 ሔክታር፣ ለአየር መንገድ ማስፋፊያ የተሰጠ 40 ሔክታር መሬት፣ ከ13 እስከ 23 ዓመታት ታጥረው ያለ ሥራ መቀመጣቸው ተጠቁሟል፡፡

የአርሶ አደሮቹ ኮሚቴ ለአብነት ለካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠው 60 ሔክታር መሬት በሔክታር 10 ኩንታል ቢመረትበት አንዱ ኩንታል በ1,800 ብር ቢሸጥ ጠቅላላ ዋጋው 28,800 ብር እንደሚሆን፣ ይህም በ11 ዓመታት ሲባዛ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ሊገኝ እንደሚችል በማስላት ኪሳራው ለተፈናቃይ አርሶ አደሮች ሊከፈል እንደሚገባ አበክሮ ጠይቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል አንድ ካሬ ሜትር መሬት የሚከፈለው 29.31 ብር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በተደረገው መጠነ ሰፊ ውትወታ አስተዳደሩ የአንድ ካሬ ሜትር መሬት ካሳ በካሬ 54 ብር አሳድጓል፡፡

ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት ቢነሱ ሊያገኙ የሚችሉትን ገንዘብ በከንቱ ማጣታቸውን በመጥቀስ፣ የከተማው አስተዳደር ጉዳዩን በድጋሚ ሊያጤን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በአጠቃላይ የአርሶ አደሮቹ ኮሚቴ በልማት ስም ከአርሶ አደሩ የተወሰዱ የእርሻ መሬቶች ወደ ልማት እስኪገቡ ድረስ ገበሬው እንዳያርስ መከልከል አግባብ አለመሆኑን፣ መሬቱን በልማት ሽፋን አጥረው ለበለጠ ትርፍ ያቆዩ አካላት የተፈጠረውን የካሳ ክፍያ ልዩነት እንዳኪፍሉ መደረግ አለበት ይላል፡፡

‹‹ይህ አሠራር የሕግ ማስከበር አካል እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ነው፤›› ሲሉ አቶ ተስፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በዚህ ዓመት 20 ሺሕ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም የ881 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

እስካሁን በተሰበሰበው መረጃ በአዲስ አበባ 134 ሺሕ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህንም በአምስት ዓመታት ውስጥ በድጋሚ ለማቋቋም ዕቅድ መያዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...