Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ለመቅጠር ፍላጎት አሳየች

ሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ለመቅጠር ፍላጎት አሳየች

ቀን:

– የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት በቅርቡ ይጀመራል

ሳዑዲ ዓረቢያ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን በፀጥታ ኃይሎች ዘመቻ ካባረረች ከሦስት ዓመት በኋላ፣ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችን በኦፊሴላዊ መንገድ ለመቅጠር ፍላጎት ማሳየቷ ተሰማ፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ በመገኘት የአገሪቱን የሥራ ሥምሪት ሥርዓት ኢትዮጵያ በቅርቡ ካፀደቀችው የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ጋር ለማጣጣም እየሠራ መሆኑን፣ የሠራተኛና የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላዚዝ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው፣ ከምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው፡፡

አዲሱን የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚጠይቁ ጉዳዮች አንዱ፣ የኢትዮጵያውያን መዳረሻ ከሆኑ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ የሥራ ሥምሪት ስምምነት መፈራረም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በእስካሁኑ ጥረት ከኩዌት፣ ከኳታርና ከዮርዳኖስ ጋር ስምምነቶቹ መፈረማቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ለኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ትልቅ ገበያ የሆኑት ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወደ ስምምነት ለመግባት ይሁንታ ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት የሥራ ሥምሪት ስምምነቱን ለመፈራረም የሚያስችለው ድርድር ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን አክለዋል፡፡

ለድርድር አስቸጋሪ የነበረው ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን 1,200 ሪያል ዝቅተኛ ወርኃዊ የደመወዝ መጠን ሳዑዲ ዓረቢያ ለመቀበል ማንገራገሯ አንዱ ሲሆን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ ዓረቢያ የተባረሩ ዜጎቹን ደግሞ እንዳይልክ ኃላፊነት ይውሰድ የሚለው ነጥብ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሁለቱም የልዩነት ነጥቦች ኢትዮጵያን በሚጠቅም ሁኔታ መፈታታቸውንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ሕገወጥ ስደተኞችን በማደን ወደየአገሮቻቸው በኃይል በመለሰችበት ወቅት፣ ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከያሉበት ታድነው መባረራቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሥራ ፍለጋ በሚል ምክንያት የሚደረግ ጉዞ ላይ ዕገዳ የጣለ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ አልተነሳም፡፡

በ2008 ዓ.ም. የውጭ አገር የሥራ ሥምሪትን መስመር የሚያስይዝ ጥብቅ አዋጅ መፅደቁ አይዘነጋም፡፡ ይህ አዋጅ ከሚያስቀምጣቸው ግዴታዎች መካከል ቢያንስ 8ኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቅና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመሄድ የሚያስችል የሙያ ሥልጠና ሰርተፊኬት መያዝን ያስገድዳል፡፡

ይህንን አስመልክቶ የተጠየቁት ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ፣ ለጉዞ ብቁ የሚያደርጉ ሥልጠናዎችን በመላ አገሪቱ ለመስጠት ከፌዴራልና ከክልል የቴክኒክና የሙያ ሥልጠና ተቋማት ጋር ስምምነት መደረሱን አስረድተዋል፡፡ የቤት አያያዝና ሌሎች ሙያችን የተመለከተ የአገሮቹን ደረጃ የማውጣትና ካሪኩለም የመቅረፅ ሥራ መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም አዋጁ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ብለዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...