Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ60 ሚሊዮን ዶላር የወረቀትና ፐልፕ ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ጥሬ ዕቃው በአብዛኛው የሸንኮራ አገዳ ገለባ ይሆናል ተብሏል

በኢትዮጵያና በቻይና ኩባንያዎች ሽርክና የተመሠረተው ፒውር ውድ የወረቀት፣ የፐልፕና የማሸጊያ ውጤቶች ማምረቻ ኩባንያ 60 ሚሊዮን ዶላር በሚገመት ካፒታል ተቋቁሞ፣ የፋብሪካ ግንባታ ሥራውን ለመጀመር ስምምነት መፈረሙ ታወቀ፡፡

እስማኤል ቱሬ ቢዝነስ የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ከቻይናው ኒዮ ግሎሪ ኩባንያ ጋር ባደረገው የእሽሙር ሽርክና ስምምነት መሠረት፣ በ68 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ የሚተከል ፋብሪካ ዕውን ለማድረግ በዱከም ከሚገኘው የቻይናው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ጋር በቅርቡ ስምምነት አድርጓል፡፡ የእስማኤል ቱሬ ቢዝነስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማሂር እስማኤል ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ለሚካሄደው የወረቀትና የፐልፕ ፋብሪካ ግንባታ 38 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ከኢንዱስትሪ ዞኑ ተረክቧል፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ የሚለው መሬት 15 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትም አቶ ማሂር አስታውቀዋል፡፡

ፋብሪካው በ11 ወራት ውስጥ ዕውን ሲደረግ 10 ሺሕ ቶን ናፕኪን፣ 15 ሺሕ ቶን ክራፍት ወረቀት፣ እንዲሁም 7,500 ቶን ካርቶን በዓመት የማምረት አቅም እንደሚኖረው ያስረዱት አቶ ማሂር፣ በአብዛኛው ያለቀላቸውን የወረቀት ምርቶች የሚያመሩት ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚጠሙባቸውን ጥቅል የወረቀትና የፐልፕ ምርቶች ለገበያ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱን ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ ከ35 እስከ 40 በመቶ ያህሉን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብም ተጠቅሷል፡፡

ፋብሪካው በግብዓትነት ከሚጠቀምባቸው መካከል የሸንኮራ አገዳ ገለባ ዋናው ሲሆን፣ በአገሪቱ ያሉትና የሚገነቡት የስኳር ፋብሪካዎች የግብዓት ምንጭ እንደሚሆኑም አቶ ማሂር አስረድተዋል፡፡ ከሸንኮራ አገዳ ገለባ በተጨማሪ መልሶ ጥቅም ላይ የሚውሉ ወረቀትና ፐልፕ እንደሚካተቱበትም ታውቋል፡፡ በጠቅላላው ለ700 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ የሚጠበቀው ፋብሪካ፣ ከወንጂ ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ ቀጥሎ በአገሪቱ ሁለተኛው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የእስማኤል ቱሬ እህት ኩባንያ ከሆኑት አንዱ የሆነው ኤኮቶፒያ ሪሳይክሊንግ ፋብሪካም አገልግሎታቸውን የጨረሱና የተወገዱ የመኪና ጎማዎችን፣ እንዲሁም የፕላስቲክ ውጤቶችን በመጠቀም የትልልቅ ማሞቂያ ማሽነሪዎች ማቀጣጠያ ነዳጅ፣ ሽቦ እንዲሁም ጋዝ ለማምረት የሚያችል ፋብሪካ በ180 ሚሊዮን ብር ኢንቨስመንት በገላን ከተማ እየገነባ እንደሚገኝ የገለጸው ኩባንያው፣ በአሁኑ ወቅት የዚህ ፋብሪካ ግንባታ ሥራ 95 በመቶ መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ የዚህ ፋብሪካ ሥራ መጀመር የአገሪቱን የነዳጅ ፍጆታ ሦስት በመቶ የመቀነስ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ግምቶች አሉ፡፡

በአሜሪካ ነዋሪ የነበሩት አቶ ማሂር የሚመሩት እስማኤል ቱሬ ኩባንያ የተመሠረተው ከ40 ዓመታት በፊት ነው፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች እስማኤል አህመድ ቱሬ እንዲሁም ሳራ እስማኤል አህመድ በተባሉ ኩባንያዎች ሥር ሲተዳደሩ ቆይተው፣ ከሦስት ዓመት በፊት ሁለቱም በእስማኤል ቱሬ ኩባንያ ጥላ ውስጥ ተዋህደው በመተዳደር ላይ እንደሚገኙ የኩባንያው ግለ ታሪክ ይጠቁማል፡፡ ፋንግዙ (ኤፍ ኤንድ ዜድ) ኢንዱስትሪስ በተባለው እህት ኩባንያው አማካይነት ናኖ እስክሪፕቶ በማምረት ላይ የሚገኝ ፋብሪካም የእስማኤል ቱሬ እህት ድርጅት ሲሆን፣ ከጠቅላላ አስመጪነትና ላኪነት እንዲሁም አከፋፋይነት ቀስ በቀስ ወደ አምራችነት እያመራ የሚገኝ ኩባንያ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

ኤክሰለንት፣ ያንግ ፋ፣ ሴፍዌል (እሳት የሚቋቋሙ ካዝናዎችንና ፋይል ካቢኔቶችን የሚያመርት) ዊፕሮ፣ ካማ የተባለውን የናፍጣ ጄኔሬተር አምራች ከሆነው የቻይና ኩባንያ በተጨማሪ፣ ለበርካታ የውጭ ድርጅቶች በብቸኛ ወኪልነት እየሠራ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች